የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር "ዕጣው አልደረሳችሁም" ተብለው ከዕጩነት ውጭ ሆነዋል ተባለ

Logo - Blue Semayawi party - Ethiopia

በግንቦት ወር በሚካሄደው 5ኛ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ

ሰማያዊ ፓርቲ ለማወዳደር ያዘጋጃቸው አንዳንድ ዕጩዎች ዕጣ ስላልደረሳችው በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ፓርቲው ገለፀ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በዌብ ሳይቱ እና በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው ዘገባ ስሞታውን እንደሚከተለው አሰምቷል፡፡

———

አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል›› በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን ‹‹የሚያልፉት በዕጣ ነው›› የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ‹‹ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡›› ተብሏል፡፡

ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡›› ብለዋል

ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

———

በአዲስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ሰማያዊ ፓርቲን ወክላ ለተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት ቀርባ የነበረችው ወይንሸት ሞላን ጨምሮ ሌሎችም አዲስ አበባ ውስጥ ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት የቀረቡ ዕጩዎች ‹‹ዕጣው ስላልደረሳችሁ አትወዳደሩም›› መባላቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ከወይንሸት ሞላ በተጨማሪ ብሌን መስፍንና አማኑኤል አዱኛ የተባሉ የሰማያዊ ዕጩዎች ‹‹ዕጣው አልደረሳችሁም›› ተብለው ከዕጩነት ውጭ ሆነዋል፡፡

ወይንሸት ሞላ ‹‹ዕጣው አልደረሰሽም›› በተባለችበት የምርጫ ጣቢያ የክልል ፓርቲዎችን የወከሉ ዕጩዎች አልፈዋል የተባሉ ሲሆን ወይንሸት ‹‹የክልል ፓርቲዎች ድምጽ ያሰባሰቡት በየክልሉ እንጅ አዲስ አበባ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ ሐገራዊ ፓርቲ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ መራጭ የሌላቸው ፓርቲው በዕጣ አለፉ ተብሎ ሐገራዊ ፓርቲ የሆነው ሰማያዊ ወድቋል መባሉ ያለንበትን ስርዓት በድንብ የሚያጋልጥ ነው፡፡›› ስትል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡

በወረዳ 7 17 ፓርቲዎችን የወከሉ ዕጩዎች የቀረቡ ሲሆን 12 ያለፉ ሲሆን ሰማያዊን ጨምሮ ሌሎች አምስት ፓርቲዎች ‹‹ዕጣው አልደረሳችሁም›› ተብለዋል፡፡ በወቅቱ ወይንሸት ሞላ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ‹‹12 ፓርቲዎችን በዕጣ አልፋችኋል ለማለት ለ80 ፓርቲ ፈቃድ መስጠት ለምን አስፈለገ?›› የሚል ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን የምርጫ አስፈጻሚዎችም ‹‹ይህ ከምርጫ ቦርድ የመጣ ትዕዛዝ ነው፡፡ መዝግቡ የተባልነውን ነው የመዘገብነው›› የሚል መልስ እንደተሰጣት ገልጻለች፡፡

**********

ተዛማጅ፡- ከገደብ በላይ ዕጩዎች ሲመዘገቡ – ባለፈው ምርጫና በዕጣ መሠረት ይለያሉ፡- የምርጫ ቦርድ ኃላፊ

Daniel Berhane

more recommended stories