ከገደብ በላይ ዕጩዎች ሲመዘገቡ – ባለፈው ምርጫና በዕጣ መሠረት ይለያሉ፡- የምርጫ ቦርድ ኃላፊ

(ምህረት ሞገስ)

በመጪው ግንቦት 2007 ዓ.ም በሚካሄደው አምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በአዲስ አበባ ብቻ 25 የፖለቲካ ፓርቲዎች 328 ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አስመዝግበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)፣ መላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት)፣ የኢትዮጵያ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) እና ሰማያዊ ፓርቲ ለአዲስ አበባ የምርጫ ክልል ለተዘጋጁ 23 ወንበሮች እያንዳንዳቸው 23 ዕጩዎችን አቅርበዋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ሃምሳ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከስድስት ሺ በላይ ዕጩዎችን አስመዝግበዋል፡፡

ይሀ ሁኔታ ካለፉት ምርጫዎች አንጻር ሲታይ እንግዳ ነገር ነው።

በተሻሻለው የምርጫ ህግ መሰረት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ መወዳደር የሚችሉት ዕጩዎች ቁጥር 12 ብቻ ናቸው። በተጨባጭ ግን በአሁኑ ወቅት በአንድ የምርጫ ክልል እስከ 19 የሚደርሱ ዕጩዎች መመዝገባቸውን የምርጫ ቦርድ አስታውቋል። ይህ እውነታ ከምርጫ ህጉ አንጻር እንዴት ይታያል? መፍትሄውስ ምን ይሆን? የተመዘገቡት ሁሉ በምርጫው ይወዳደራሉ? ወይንስ ሌላ አማራጭ ይኖራል? በማለት በምርጫ ቦርድ የአገልግሎቶችና ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ዋና ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላን አነጋግረን ቀጣዩን መረጃ ይዘን ቀርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮ በሚካሄደው በአምስተኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩ ምዝገባ ላይ የተለየ ነገር መከሰቱ ተሰምቷል። ጉዳዩን ቢያስረዱኝ?

አቶ ወንድሙ፡- በዘንድሮው ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩ ማስመዝገብ ላይ የተከሰተውና ለየት ያለው ነግር በምርጫ ክልሎች ዘንድ የዕጩዎች ቁጥር መብዛቱ ነው፡፡ በ1999 ተሻሽሎ በወጣው የምርጫ ሕግ መሠረት በአንድ የምርጫ ክልል መወዳደር የሚችሉት ዕጩዎች ቁጥር 12 መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ይህ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንድ የምርጫ ክልል መወዳደር የሚችሉ ዕጩዎች የመጨረሻው ቁጥር ነው፡፡ አሁን ግን በአዲስ አበባ የተለያዩ የምርጫ ክልሎች እስከ አስራ ዘጠኝ የሚደርሱና የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች ተመዝግበዋል፡፡ ይህ ማለት ሕጉ ከሚፈቅደው በላይ ዕጩ ተመዝግቧል ማለት ነው፤ በሕጉ መሠረትም እልባት ይሰጣቸዋል። በምርጫ ሕጉ አንቀፅ 49 ላይ በተቀመጠው መሠረት ቅድሚያ ከግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ይልቅ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ይሰጣል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ከ12 በላይ ከሆኑ ባለፈው ምርጫ ተወዳድረው ባገኙት ውጤት መሠረት ስድስቱ እንደሚለዩ ሕጉ ይገልጻል። በዚህ መሠረት በ2002 በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ተወዳድረው ባገኙት ድምፅ ከአንድ እስከ ስድስት ያሉት ዕጩዎች ይለያሉ። ከዚያ በኋላ የሚወዳደሩት ስድስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ዕጩዎች በዕጣ ይለያሉ፡፡ ዕጣው በየምርጫ ክልሉ እዚያው እንዲያልቅ ይደረጋል፡፡ በዚያ መሠረት ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ የተወዳዳሪ ዕጩዎችን ያሳውቃል፡፡ ይህ የሚሆነው በብዛት በአዲስ አበባ ሲሆን ምናልባት ካጋጠመ ተብሎ በሕጉ በግልፅ የተቀመጠ በመሆኑ በቀላሉ ማስተካከል ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዕጩ የተመዘገበው በየትኛዎቹ አካባቢዎች ነው?Image - Ballot box

አቶ ወንድሙ፡- አጠቃላይ መረጃው ባይኖርም አሁን ከደረሰው ሪፖርት አንፃር በምርጫ ክልል ሁለት አስራ ሰባት ዕጩዎች ተመዝግበዋል፡፡ ምርጫ ክልል ሰባት አስራ ስምንት ዕጩዎች እንዳሉ ያሳያል፤ ምርጫ ክልል ስምንት አስራ ስድስት ሲሆኑ፤ ምርጫ ክልል አስር ላይ ደግሞ አስራ አራት ዕጩዎች ተመዝግበዋል፡፡ ምርጫ ክልል ሃያ አምስትም አስራ ሦስት ሰው አለ፡፡ አስራ ዘጠኝ ዕጩዎች ያሉበት የምርጫ ክልልም አለ፡፡ በአብዛኛው ሲታይ ግን በአዲስ አበባ በየምርጫ ክልሉ የተመዘገቡት ዕጩዎች ቁጥር ከ12 በላይ መሆኑ እየታየ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርሶ ከነገሩኝ አማራጭ በተጨማሪ በሕጉ ላይ ብዛት ያላቸው ዕጩዎች ሲኖሩ ማስተናገድ የሚቻልበት ሌላ መንገድ የለም?

አቶ ወንድሙ፡- ሕጉ ላይ ከተቀመጠው ውጪ ሌላ አማራጭ የሚወሰድበት ሁኔታ የለም፡፡ በሕጉ ላይ የተቀመጠው በአንድ ክልል አስራ ሁለት ዕጩዎች ብቻ መኖር እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህ የተቀመጠው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ ተግብሩት የሚለው ብቻ የሚተገበር ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ነበር? ሕጉስ ተግባራዊ ተደርጎ ያውቃል?

አቶ ወንድሙ፡- አሁን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ግን አጋጥሞ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን በተባለው መሠረት በአንድ የምርጫ ክልል አስራ ሁለት ዕጩዎች እንዲለዩ ሲደረግ በፓርቲዎች በኩል ቅሬታ አያስነሳም?

አቶ ወንድሙ፡- ይህ የሚታወቅና ሕጉ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው፡፡ ሕጉ ይህን ፓርቲ ለመጥቀም ወይም ሌላውን ለመጉዳት ተብሎ የተቀመጠ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕጉን መሠረት አድርጎ በሚሰራበት ጊዜ ፓርቲዎች ሕጉን መቀበል አለባቸው፡፡ ሌላው ዋናው ጉዳይ ግን ዕጩዎች እንዲለዩ ሲደረግ ፓርቲዎች ተወካዮቻቸውን ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የምርጫ ዕጩዎች ቁጥር በአዲስ አበባ የበዛበት ምክንያት ምንድን ነው ?

አቶ ወንድሙ፡- በአብዛኛው የፓርቲዎች ፍላጎት አዲስ አበባ ላይ መወዳደር በመሆኑ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተረፈ ደግሞ ምናልባትም ከፓርቲዎች የቁጥር መብዛት ጋርም የሚገናኝ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አመሰግናለሁ።

አቶ ወንድሙ፡- ምንም አይደል።

***************
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን – የካቲት 2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories