የማንነት መገለጫ ዓይነቶች- በዓለም እና በኢትዮጵያ

(አዲስ ከድሬዳዋ)

የቀድሞ ዩጎዝላቪያ አካል የነበሩት ክሮሺያና ሰርቢያ (የቦስኒያ ሙስሊሞችን እና ሞንቴኔግሮዎችን ጨምሮ) ሶሻሊዝም ሲንኮታኮት ከተበታተኑት የዩጎዝላቪያ ሪፑብሊኮችና ራስገዝ አስተዳደሮች መካከል ናቸው፡፡ እነኚህን ሪፑብሊኮች ቀድሞዉኑ ምን አንድ አደረጋቸው፣ በኋላስ ለምን መለያየት ፈለጉ የሚለው ትንሽ ግራ ያልተለመደ የሚመስል ነገር አለው፡፡

ከዩጎዝላቭ ሪፑብሊኮች በህዝብ ብዛትና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ቀዳሚ የነበሩት ሰርቦች እና ክሮአቶች ቋንቋቸው የዲያሌክትን(ቀበሌኛን) ያህል እንኳ የማይለያይ ተመሳሳይ ነው፡፡የቋንቋ ምሁራንም ለየብቻ ማስቀመጥ ከብዷቸው ሰርቦክሮአት ይሉት ነበር ቋንቋውን(አሁን ለየብቻ ነው ብዙ ቦታ ላይ የሚፃፈው)፡፡ ዘራቸውም እንደስማቸው ሁለቱም ዩጎ ስላቮች(የደቡብ ስላቮች) ናቸው፡፡ ታሪካቸውን ያየን እንደሆነም ብዙ ነገሮችን ይጋራሉ፡፡ ኢኮኖሚያቸውን ያየን እንደሆነም ከአውሮፓ ድሀ እና በአንፃራዊነት ኋላቀር ከሚባሉ ህዝቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ታዲያ በምንድን ነው የሚለያዩት – በሐይማኖት- አለቀ፡፡ በሀይማኖት ብቻ፡፡ ሰርቦች ኦርቶዶክስ ናቸው፣ ክሮአቶች ደግሞ ካቶሊኮች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰርቦች የኦሮቶዶክሱ ቅዱስ በፈጠረው ሲርሊክ ፊደል ይፅፋሉ፣ ካቶሊኮቹ ክሮአቶች ደግሞ ሮማዊ በሆነው ላቲን ፊደል ይፅፋሉ፡፡Photo - Ethiopian nation nationalities

እነዚህ ህዝቦች የደቡብ ስላቭ አንድነት አቀንቃኝ በነበረው ቲቶ አንድ ሆነው ሲኖሩ ቆይተው(አንድነቱ ግን ወደህዝቡ ያልሰረጸ እና በቲቶ ተሰሚነት ላይ የተመሰረተ ስለነበረ) ማርሻል ቲቶ ሲሞት አንደኛው ህዝብ ከሌላኛው ብሔር በወጣ መሪ ለመተዳደር ዝግጁ ስላልነበር ዩጎዝላቪያ በእቁብ መመራት ጀመረች፤ ዘንድሮ ከሰርቢያ፣ ቀጥሎ ከሞንቴኔግሮ፣ ከዚያ ከክሮሺያ፣ ከዚያ ከሜቄዶኒያ፣ ከዛ ከስሎቬኒያ፣ . . .እያሉ በየአመቱ በፈረቃ ዩጎዝላቪያን ሲያስተዳድሩ ቆዩ፡፡ ያው አስተዳደራቸው ራሱ ምንያህል አንድነት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነውና ጊዜው ሲደርስ ሁሉም ሪፑብሊኮችና ራስገዝ አስተዳደሮች(ለምሳሌ ኮሶቮ) ፍቺ ፈፀሙ፡፡

ይህ ፍቺ ግን ሰላማዊ አልነበረም፡፡ ሰርቦች ክሮአቶችን ጨፍጭፈዋል፣ ክሮአቶችም ሰርቦችን ጨፍጭፈዋል፤ ሁለቱም ደግሞ(በተለይ ሰርቦች) በቦስኒያ ሙስሊሞች ላይ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል፡፡ በትላንትናው እለትም ሁለቱ ሀገሮች አንዱ ሌላኛውን የዘር ማጥፋት ፈፅሞብኛል ብለው ያቀረቡት ክስ በተባበሩት መንግስታት) የጦር ወንጀለኞች ፍርድቤት ውድቅ ተደርጓል፡፡(እግረመንገድ ድርጊቱ የተፈጸመው አፍሪካ ውስጥ ቢሆን ጄኖሳይድ አይደለም ተብሎ ይወሰን ነበር ወይ የሚለውን አስቡት)

ግን እነኚህ ህዝቦች እርስ በርስ እንደተለያዩ ህዝቦች ለመተያየት፣ ባስ ሲልም ለመጠላላት መነሻቸው ሐይማኖት እንጂ ሌላ ልዩነት የላቸውም፡፡ በርግጥ በዚህ ዘመን እየተጠላሉ ያሉትና የተጨፋጨፉት በሐይማኖታዊ ልዩነት መነሻ ሳይሆን ይህ ልዩነት በፈጠረው ራስን ከሌላው የተለየ ባዕድ አድርጎ የማሰብ እና ባስ ሲልም ያንን ባዕድ የመጥላት አባዜ ነው፡፡ ይህ እኛ ሐገር ቢሆን ኦሮሞ (ወይም አማራ) ሙስሊም ፣ኦርቶዶክስ፣ ወይም ፕሮቴስታንት በመሆኑ ብቻ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ እርስ በርሱ ሊጠላላ፣ ባስ ሲልም ሊገዳደል ይችላል ወይ ብለን ስንጠይቅ እኛ ሐገር ማንነትን ዲፋይን ለማድረግ ሐይማኖት እዚህ ግባ የሚባል ሚና እንደሌለው መረዳት እንችላለን፡፡

አውሮፓ ውስጥ ግን እንዳየነው ነው፡፡ ሌላ ምሳሌ ማየትም እንችላለን፤ አየርላንድ በ1921 ከዩናይትድ ኪንግደም(እንግሊዝ) ተገንጥለን የራሳችንን የአይሪሽ ሪፑብሊክ እንመሰርታለን ሲሉ እና ጥያቄአቸው ገፍቶ እንዲገነጠሉ ሲወሰን ፕሮቴስታንት የሆኑ አይሪሾች ከካቶሊክ አይሪሾች ጋር አብሮ ከመገንጠል ከፕሮቴስታንቶቹ እንግሊዞች(እና ስኮቶች) ጋር መቀጠልን ነበር የመረጡት፤ እናም አየርላንድ ለሁለት ተከፍላ ካቶሊኮቹ ተገነጠሉ፤ፕሮቴስታንት የሚበዛባቸው ሰሜኖች ግን ከእንግሊዝ ጋር ቀጠሉ፡፡ እዚህ ጋርም ማንነትን ለመወሰን(ዲፋይን ለማድረግ) ከአይሪሽነት(ብሔር) ይልቅ ሐይማኖት ክብደት እንደተሰጠው የሚያሳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል ዩናይትድ ኪንግደምን(በተለምዶ እንግሊዝን) ራሷን ስናያት አብሮ ብዙ ከመኖር ብዛት አየርላንዶች፣ ስኮትላንዶች፣ ዌልሶች የራሳቸውን ቋንቋ ትተው የአብዛኛዎቹ አፍ መፍቻ እንግሊዝኛ ቢሆንም ይህ የቋንቋ ተመሳስሏቸው ግን በፍፁም ራሳቸውን እንደ አንድ ህዝብ እንዲያዩ አላደረጋቸውም፡፡

ቋንቋም፣ ባህልም፣ ሐይማኖትም ተመሳሳይ ሆኖ እንኳ አንድነት ላይኖር እንደሚችል ደግሞ ከአረቦች በላይ ምስክር የለም፡፡በርካታ አረብኛ ተናጋሪ ሐገራት አሉ፤ በ1960ዎቹ ተቀጣጥሎ በነበረው የአረብ ብሔርተኝነት ለተወሰነ ጊዜ ተቀራርበው የነበረ ቢሆንም የሀገራቱ መለያ ግን ከወንድማማችነትና አንድነት ይልቅ ሽኩቻና ጥላቻ ነው፡፡ የተለያዩ የአረብ ሐገራት ቀርቶ በአንድ ሐገር ውስጥም እየኖሩ አረቦች በጎሳ ወይም በሐይማኖት ልዩነት ለምሳሌ በሱኒነትና ሺአነት እርስ በርስ አምርረው ሲጠላሉና ሲገዳደሉ ማየት አዲስ አይደለም፡፡ በአንፃሩ ከአፍሪካ አህጉር እጅግ የበለጠ ነዋሪ ያላት እና የ56 ብሔር ሐገር የሆነችው ቻይና ዜጎች ራሳቸውን እንደአንድ ህዝብ የሚያዩ መሆኑን ስናስብ አንድ ህዝብ ራሱን ዲፋይን የሚያደርግበት ሁኔታ ምን ያህል ሊሰፋ ወይም ሊጠብ የሚችል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

እስኪ የኛን ሀገር አንዳንድ ገፅታዎች እንይ::

1. እኛ ሐገር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩት ወላይታዎች፣ ጋሞዎች(ዶርዜዎች)፣ ጎፋዎችና ዳውሮዎች(የቋንቋቸው ልዩነት አንዳንድ ቃላትን አጥብቆ እና አላልቶ ከመጥራት ብዙም ያልዘለለ እንደሆነ እና ልዩነቱም ከዲያሌክትነት(ቀበሌኛነት) ያልዘለለ እንደሆነ ከተናጋሪዎቹ ከራሳቸውም ሰምቻለሁ) እራሳቸውን እንደ አንድ ብሔር ሳይሆን እንደተለያየ ብሔር ነው የሚያዩት፡፡ የአንድ ህዝብን ማንነት ዲፋይን ለማድረግ ወሳኙ የምሁራን ቀመር ሳይሆን የሕዝቡ ስሜት ነውና ምሁራን ቋንቋዎቻቸው አንድ ስለሆኑ ልጆቻቸውን በተመሳሳይ መፅሐፍ እናስተምራቸው፣ የሚማሩበትን ቋንቋ ስምም ከአራቱም ብሔር የመጀመሪያ ፊደል ወስደን ወጋጎዳ እንበለው ብለው ተስማምተው፣ መፃህፍት ታትመው፣ ሌሎች ወጪዎችም ወጥተው ይህንን በጠረጴዛ ዙሪያ የተወሰነ ውሳኔ ወደመሬት ለማውረድ ሲሞከር ምን ያህል ረብሻ እንዳስከተለና የሰው ህይወት ሁሉ እንዳለፈ እናስታውሳለን፡፡ ህዝቡ ራሱን እንደተለያየ ህዝብ የሚስብ ከሆነ ይህንን ልትቀበለው እንጂ ተሳስተሃል ብለህ የራስህን ስሜት ልትጭንበት አይገባም፡፡

2. በሌላ በኩል ሐገራችን ፌደራላዊ ስርዓትን ስትዘረጋ ከተመሰረቱት ክልሎች አንዱ የሆነው አማራ ክልል ህዝቦቹ ራሳቸውን ከአማራነት ይልቅ በወሎየነት፣ ጎጃሜነት፣ ጎንደሬነት ዲፋይን የሚያደርጉ፣ አማራነትም ከኦርቶዶክስነት ጋር የተያያዘ ፍቺ እንደነበረው የታወቀ ነው፡፡(የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ አማራ የለም ብለው ከሚያምኑት ፕሮፌሰር መስፍን ጋር በጉዳዩ ላይ ሲከራከሩ ሰዎች ራሳቸውን እስላም- አማራ የሚሉት ወሎ ውስጥ ሙስሊም የነበሩት ቀድሞ ኦሮሞዎች ስለነበሩ እንደሆነ ቢናገሩም ይህ አጠቃቀም ግን ከወሎ ውጪ በጎጃምና ጎንደር እንዲሁም ሀረርጌና ባሌ ሁሉ ያገለግል የነበረ አጠቃቀም ከመሆኑ አንፃር መከራከሪያቸው አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም)፤ ሆኖም ህዝቡ ቋንቋውን አማርኛ ብሎ ይጠራል፣ ልክ እንደ ሰርቦችና ክሮአቶች ሁሉ ራሱን ከጋራ አማራነቱ ይልቅ በወሎዬነትና ጎንደሬነት/ ጎጃሜነት ዲፋይን አድርጎ የኖረ ህዝብ ነው (ይህ ልዩነት ደግሞ በታሪክ እርስ በርስ እስከመወጋጋት ይደርስ እንደነበር የታወቀ ነው)፡፡ ሆኖም አሁን በዘመናችን የሚስተዋለው ልዩነት በወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋና ዳውሮ ህዝቦች ዘንድ የነበረውን ያህል ባለመሆኑ አንድ ህዝብ ናችሁ ሲባሉ የተነሳ የጎላ ችግር አልነበረም፡፡ ሆኖም ቀድሞ በ1960ዎቹ ለአስተዳደር አመቺነት ሲባል ዘንዘልማ የምትባል ገጠር ቀበሌ ሩቅ ከሆነችው ሀሙሲት ከተማ ይልቅ አጠገቧ ባለችው ባህርዳር ስር ትሁን ሲባል ውሳኔው ከጎንደሬነት ወደጎጃሜነት መቀየርም ጭምር ስለሆነ የቀበሌዋ ነዋሪ በውሳኔው ላይ በማመፅ የደርግ ጥይቶች ሰለባ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ክልሉን እያስተዳደረ ያለው ብአዴንም ከፖለቲካዊ ግቦቹ አንዱ የአማራውን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲያብብ ማስቻል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለሀገር ግንዛቤ ያለው ከተሜ አማራ ግን ብዙ ጊዜ ከአማራነቱ ይልቅ የክፍለሀገር ማንነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን እንደሚያስቀድም ይታወቃል፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊነቱን ማጉላቱ ግን በአንዳንድ ብሔርተኛ ኤሊቶች ዘንድ እንደ አንድ መገለጫ ከመቀበል ይልቅ የትምክህተኝነት ማሳያ እንደሆነ ተደርጎ ሲወሰድ ይስተዋላል፡፡

3. ከዚህ ጋር በተያያዘ የቀድሞው ስሜን ራሱን እንደቻለ ህዝብ እንጂ ራሱን እንደጎንደሬ ወይም ትግሬ የሚመለከት ስላልነበር የስሜኑ ራስ ውቤ ትግራይን ሲያስተዳድሩ የትግራይ መኳንንት እንዴት እኛ እያለን አገራችንን ትግሬ ያልሆነ ሰው ያስተዳድራታል ብለው ከተንቤን እስከ ሀማሴን ያሉ መሳፍንት ጦር አዋጥተው የራስ ውቤን ተወካይ በጋር ወግተው እንዳባረሩት ተፅፏል፡፡ አካባቢው ብዙ ህዝብ ስለማይኖርበት እንዲሁም ፣ ከሀይለስላሴ ዘመን ጀምሮ ራሱን ችሎ የማያውቅ ስለሆነ የስሜንነት ስሜቱ አሁን ምንያህል እንደሆነ አላውቅም፡ ግን በቀድሞው ስሜት ከሆነ ህዝቡ ትግሪኛ ቢናገርም ራሱን እንደ ትግሬ የሚያይ ህዝብ እንዳልነበር ማስታወስ ይቻላል (አማርኛ የሚናገረውም ቢሆን ራሱን እንደጎንደሬ አያይም ነበር)፡፡

4. በተመሳሳይ እጅግ ህብረብሔራዊ በሆነችው ሀገራችን ራሳቸውን በዋናነት ከብሔርም ይልቅ በጎሳ አይደንቲፋይ ማድረግ የሚመርጡ ህዝቦች(ለምሳሌ ሶማሌ) ይህንን ጎሳ ግምት ውስጥ ያስገባ አስተዳደር ዘርግተው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ከራሳቸውም አልፈው ጎሳ በሶማሌ ማንነት ውስጥ ያለውን ትልቅ ቦታ ግምት ውስጥ በማስገባት ጎረቤት ሶማሊያም በጎሳ ላይ የተመሰረተ ሁሉም ራሱን የሚያስተዳድርበት ፌደራሊዝም እንድትከተል እየተደረገች ነው፡፡

5. ኦሮሚያ ውስጥ ከኦሮሞ መስፋፋት በኋላ የነበረው የኮንፌዴሬሽን አይነት ትስስር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እየሳሳ መጥቶ በምዕራብና ምስራቅ ኦሮሚያ ህዝቦች መካከል ራስን እንደተለያዩ ህዝቦች ማየትን ሊያስከትል የሚችል ልዩነቶች ማቆጥቆጥ ጀምሮ እንደነበረና ይህ ግን በምኒልክ መስፋፋትና እሱን ተከትሎ በተገኘው የኦሮሞ ህዝብ በአንድ ሀገር ስር መጠቃለል፣ እንዲሁም ብዙም ሳይቆይ ማቆጥቆጥ በጀመረው የኦሮሙማ (የኦሮሞነት) ንቅናቄዎች ሊከስም ችሏል፡፡ በርግጥም አስቀድሞ ግብፅና እንግሊዝ በተስማሙት መሰረት ግብፅ ታስተዳድራቸው የነበሩትን ምጽዋንና ምስራቅ ኢትዮጵያን ለጣልያን ከማስተላለፏ በፊት የኢትዮጵያ/የሚኒልክ ጦር ምስራቅ ኢትዮጵያን መቆጣጠሩ ምስራቅ ኦሮሚያ የጣልያን ግዛት የነበረው ደቡብ ሶማሊያ አካል እንዳይሆን ያደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀድሞውንም የሐረርጌ ኦሮሞ ሶማሌ አቦ ነው ዘራቸውም የሶማሌ ነው የሚል ይገባኛል ያነሱ ለነበሩት ጥቂት የሶማሌ ብሔርተኞች እና በዚያ ዘመን ለነበሩ አንዳንድ የአመለካከቱ ተጋሪ ኦሮሞዎች ሰፊ በር የሚከፍትና የአካባቢው እጣፋንታም ከሌላው ኦሮሞ ጋር ሳይሆን ከሶማሊያ ጋር የተሳሰረ እንዲሆን ሊያደርግ ይችል የነበረ ነው፡፡

6. በቀድሞ ፊውዳላዊ ስርዓት ከወለጋም ከአርሲም ከደቡብም(ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀዲያ፣ ከምባታ፣ . . .) በርካታ ቦታዎች ወደሸዋ ጠቅላይ ግዛት ስር እንዲገቡ ቢደረግም ራስን እንደሸዌ አይደንቲፋይ በማድረግ ረገድ ግን ከአማራዎቹ እና ነባሮቹ የሸዋ ኦሮሞዎች በስተቀር ሌሎች ላይ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣም፤ ምናልባት ከወለጋ ወደ ሸዋ የተካለሉት ላይ ቀድሞውንም ከነበረው ትስስር ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል ለውጥ ያለ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ነበር ሸዋ በተለያዩ ክልሎችና ዞኖች ሲከፋፈል አንዳች ኮሽታ ያልተሰማው፡፡

7. አሁን የምንከተለው ብሔርን መሰረት ያደረገ ፌደራላዊ ስርዓት ጠንካራ ብሔራዊ ስሜት ላላቸው ህዝቦች አመቺ የሆነውን ያህል ቀድሞ እንደአንድ ብሔር ይታዩ ለነበሩት ቤተ ጉራጌዎች ግን ከፍተኛ ክፍፍልን ነበር ያስከተለባቸው፤ ምንጫቸው ሰሜን ኢትዮጵያ ነው የሚባሉት ጉራጌዎች ስር ነበሩ የሚባሉት ሆኖም ምንጫቸው ምስራቅ ኢትዮጵያ የሆኑት ስልጤዎች፣ እንዲሁም ኩሻዊ ናቸው የሚባሉት ማረቆዎችና ቀቤናዎች ራሳቸውን ከጉራጌነት ሲለዩ፣ አንዱ የሶዶ ንዑስ ጎሳ ደግሞ ኦሮሞነቱን አውጇል(በርግጥ አብዛኛው ኦሮምኛ ተናጋሪ ነው)፡፡ አንዳንዶችም ወለንኛ ተናጋሪዎች ጉራጌ አይደለንም የሚል እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ አካሔድ ቀድሞ በጎጎት ተራራ ቃል ተገብቷል እንደሚባለው ቤተጉራጌነት የአንድ ብሔር ስያሜ ሳይሆን የጋራ ማንነት አምብሬላ ነበር ከሚለው አነጋገር ጋር የሚቃረንና ጉራጌነት የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ መለያ ሆኖ እንዲታይ እያደረገ ነው፡፡ ባጠቃላይ አንዳንዶች ራሳቸውን በቤተጉራጌነት ሳይሆን በማረቆነት፣ ቀቤናነት፣ ስልጤነት መታወቅ ሲፈልጉ ሌሎች ደግሞ አሁንም በቤተጉራጌነት(ጉራጌነት) ይበልጥ መታወቅን ይመርጣሉ፡፡ ይህም የህዝብ ስሜት ነው፡፡

8. በከተማ የሚኖረው እና የተቀላቀለው ኢትዮጵያዊ ደግሞ በአብዛኛው ከብሔር ማንነቱ ይልቅ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያስቀድምና አንዳንዴ ብሔርተኛ ከሆኑት የእሱ ብሔር ተወላጆች ይልቅ ከእሱ ጋር በአስተሳሰብ የሚቀርቡትን የሌላ ብሔር ተወላጆች መቅረብ ሲመርጥ የሚስተዋል ነው፡፡ ይህ አካል በሀገሪቱ ላይ ያለው የኢኮኖሚና የስነልቦና የበላይነት ከቁጥሩ በላይ ሚና እንዲኖረው ያስቻለ ነው፡፡ ኢህአዴግ ቀድሞ 85 ፐርሰንቱን የገጠር ነዋሪ ከያዝኩ በሚል አስተሳሰብ ከተሜውን ችላ ብሎ የነበረበት ታሪክ መሬት ላይ ባለው እውነታ ላይ ያልተመሰረተ እና ንድፈሀሳባዊነት የተጫነው፣ እንዲሁም ከተሜውና የገጠሩ ነዋሪ በስነልቦና፣ በመረጃ፣ በስጋ፣ . . .ያላቸውን ትስስር የዘነጋ በመሆኑ ዋጋ እንዳስከፈለው ይታወሳል፡፡ በርግጥ በዚህ ረገድ የከተሜው፣ በተለይ ደግሞ የአዲስአበቤው ተፅዕኖ ፈጣሪነት በትንሹም ቢሆን መቀነስ እንደጀመረ መካድ አይቻልም፡፡

9. አበሻነት ቀድሞ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የጋራ መጠሪያ ሆኖ ያገለግል የነበረ ሲሆን አሁን ግን አንዳንድ ፖለቲከኞች አበሻነትን ለሴማውያን ብቻ ሲሰጡት ይስተዋላል፡፡ ሆኖም በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው የሐበሻነት አስተሳሰብና አጠቃቀም ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ ሶማሌዎች ራሳቸውን ቀድሞውንም ሀበሻ ብለው ጠርተው አያውቁም፤ በተቃራኒው ሀበሻነትን ከአማራነት ጋር አያይዘው ሲጠቀሙ መስማት አዲስ አይደለም(አንድ ሶማሌ አፍ ሐበሽ መገረን ቢልህ አማርኛ ትችላለህ ወይ ማለቱ ነው- በሚዲያ ሁሉ አልፎ አልፎ የአማርኛ ፕሮግራምን አፍ ሐበሽ(የሀበሻ አፍ) ሲሉ መስማት አዲስ አይደለም) ፡፡ይህ ስሜት ግን ከሶማሌ ባሻገር ሌሎች የጠረፋማ አካባቢ ነዋሪዎችም(ለምሳሌ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣. . .) እንደሚጠቀሙት ነው የምሰማው፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም ሴማውያን እንዲሁም የሰሜንና ማዕከላዊ ኩሻውያን ራሳቸውን ሀበሻ ብለው የሚጠሩ ሲሆን በእነኚህ አካባቢዎችሐገር በቀል የሆኑ እና መጤ የሆኑ ነገሮችን ለምሳሌ ጎመን፣ ላም፣ ዶሮ፣ . . . .ወዘተ የፈረንጅ እና የሐበሻ ብሎ መለየት የተለመደ ነው፡፡በዚህ ረገድ ወደ ዳር ሀገር እየራቁ ሲሄዱ አጠቃቀሙም እየፈዘዘ ነው የሚሄደው፡፡ ሆኖም አሁን አሁን ልዩነት ላይ ማተኮር የሚፈልጉ ልሂቃን ሀበሻነት የጋራ መለያ መሆኑን ስለማይፈልጉት መሬት ላይ ካለው አጠቃቀም የተለየ አጠቃቀም ስር እንዲሰድ ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡ የተለዩ ህዝብ መሆናቸው ጎልቶ እንዲታይ የሚፈልጉ አንዳንድ ኤርትራውያንም ሀበሻ አይደለንም እንደሚሉ ይታወቃል፡፡ እነኚህ አጠቃቀሞች ብዙ ጊዜ ለፖለቲካ አላማ ተብለው ወደህዝቡ እንዲሰርፁ እየተደረጉ ያሉ እንጂ ህዝቡ ጋር የሌሉ መሆናቸውን ማየት ያሻል፡፡

ባጠቃላይ በሀገራችን ራስን በአካባቢ፣ በቋንቋ፣ በጎሳ፣ በሀገር፣ መለየት(አይደንቲፋይ ማድረግ) እያስተዋልናቸው ያሉ እውነታዎች ሲሆኑ እነኚህን ስሜቶች በመረዳትና ልዩነትን(ከባህል ወይም የቋንቋ ልዩነት ይልቅ የአስተሳሰብ ልዩነትን) በመረዳትና በመቀበል ረገድ ግን አንዳንድ ክፍተቶች አሉ፡፡ የብሔርተኝነት አቀንቃኞችን በጠባብነት፣ የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኞችን ደግሞ በትምክህተኝነት ለመፈረጅ የሚጣደፉ ቀላል አይደሉም፡፡ ለአሁኑ ግን ሐገራችን ሙሉ በሙሉ ተሰርታ ያላለቀች፣ አሁንም ገና እየተለወጠች ያለች ሐገር ነች፤ ተለውጣ ስታበቃ የነገዋን ኢትዮጵያ ዜጎች ከብሔር አልፈው በጎጥ፣ በእምነት ጭምር የሚናከሱ ህዝቦች ልናደርጋቸው እንችላለን፡፡ መብትና ግዴታውን የሚያውቅና የሚከባበር ህዝብ ልገነባም እንችላለን፡፡ ሁለቱም የማይቻሉ አይደሉም፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዝባችንን ስነልቦና፣ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና፣ . . .ወዘተ መረዳት እና ከዚህ አንፃር በሰከነ መንፈስ መንቀሳቀስ አዋቂነት ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶቻችን ስሜታችንን ተከትለን ይሔ ብሔር ወይም ኢትዮጵያ እንዲህ ትሁን እንደዛ ይሁን ማለት ላይ አተኩረን እየሰራን ሲሆን ይህ ግን ከአጭርና ረጂም ጊዜ አንፃር ያለውን ጠቀሜታ/ጉዳት ያስተዋልን አንመስልም፡፡ ለምሳሌ ለኢትዮጵያ አንድነት የምንጨነቅ ሰዎች ይህ አንድነት እኛ ሌላው ላይ የምንጭነው ሳይሆን ሁሉም ብሔር የሚፈልገው እንዲሆን ማድረግ እንዳለብን (ሊሆን እንደሚገባ)ተገንዝበን ነው ወይ እየተንቀሳቀስን ያለነው፣ ብሔርተኞችስ ግባችንን ለማሳካት እየተከተልነው ያለው ብሔርተኝነት እንዲጠናከር የማድረግ ስራ በህዝቦች መካከል ጥላቻን ሊያሰርፅ መቻሉና ይህም እንወክለዋለን የምንለው ህዝብ ከወንድም ህዝቦች ጋር በጉርብትና እንኳ በሰላም እንዳይኖር እስከማድረግ ሊያደርስ እንደሚችልና ይህም ለህዝባችን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አስበነው እናውቃለን ወይ?

ከዚህ ባሻገር እንዳለፈው ትውልድ በወረተኛ(ፋሽነብል) የፖለቲካ ፍልስፍናዎች ተመስጠን ኢትዮጵያን ሳይሆን ሶቭዬት ህብረትን የመሰለ ሶሻሊዝም ለመገንባት፣ ለሁሉም ነገር አውሮፓን በማጣቀስ አቅጣጫ ለመዘርጋት መጣደፍ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በዚህ ረገድ አዲሱ ትውልድ የ1960ዎቹ ትውልድ የፈፀመውን ስህተት ልንማርበት እና ለሁሉም ነገር ራሳችንን ማየትን ቅድመ ሁኔታ ልናደርገው እንደሚገባ አስባለሁ፡፡

************

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories