የብሄራዊ ሰታዲየም ግንባታ ዝርዝር ዲዛይን በመጪው የካቲት ወር ይጠናቀቃል

(ሠመረ ሞገስ)

የብሄራዊ ስታዲየም ፕሮጀክት ዝርዝር የዲዛይን ስራዎች በመጪው የካቲት ወር አጋማሽ እንደሚጠናቀቅ የፕሮጀክቱ አማካሪ አስታወቀ፡፡

በስታዲየሙ ዙሪያ የሚታጠረው የአጥር ግንባታ 91 በመቶ ደርሷል።

በአዲስ አበባ ቦሌ ገርጂ አካባቢ በመገንባት ላይ ያለው ብሄራዊ ስታዲም 60 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ሲኖረው ለግንባታው 2 ቢሊዮን ብር ወጪ ተይዞለታል።

የስታዲየሙ ግንባታ በሁለት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።Addis Ababa New Stadium design

የፕሮጀክቱ አማካሪ ሜ.ኤች ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር መሰለ ኃይሌ እንደተናገሩት ”የቅድመ ዲዛይን ስራዎች ተጠናቆ የዝርዝር ዲዛይን ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው”::

ዝርዝር ዲዛይኑ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ፣ የሜዳ ስፋት፣ የመሬት ጥናት፣ በጦር ውርወራ ጊዜ ርቀቶችን መለካት የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችና የሽብር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችና ሌሎች ዲዛይኖች ያካተተ ነው።

የመጨረሻ ዝርዝር ዲዛይን ስራ በመጪው የካቲት ወር እንደሚጠናቀቅ ነው ዶክተር ኢንጀነር መሰለ የተናገሩት።

ስለሆነም ግንባታውን ለማስጀመር በመጪው መጋቢት ወር ጨረታ ይወጣል።

60 ሄክታር ላይ የሚያርፈው አዲሱ ብሄራዊ ስታዲየም የመሬት ጥናቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡

እንደ ኢንጂነሩ ገለጻ ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቆ የዓለም ዋንጫና የኦሎምፒክ መክፈቻና መዝጊያ ውድድሮችን እንዲያስተናግድና የተጀመሩ ዝርዝር ዲዛይን ስራዎች ጥራታቸውን ተጠብቆ እንዲሰሩ ለማድረግ ከኮሪያ፣ ከአውስትራሊያ እና ከእንግሊዝ አገር አማካሪዎችን አካትቷል፡፡

ድርጅቱ የመጨረሻ ዝርዝር ዲዛይን እየሰራ ያለው ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንና ከከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተያየት ከተሰጠው በኋላ ነው።

በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የግንባታዎች ፋሲሊቲ የስራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ ጥበበ ጎርፉ በበኩላቸው እንደተናገሩት በስታዲየሙ ዙሪያ የሚታጠረው የአጥር ግንባታ 91 በመቶ ደርሷል።

ለአጥር ግንባታው 25 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።

ፕሮጀክቱ ሶስት ምዕራፎች ማለትም የቦታ ዝግጅት፣ የዲዛይን ዝግጅትና የኮንስትራክሽን ዝግጅት የያዘ ነው።

እንደ አቶ ጥበቡ ገለጻ በቦታው ከነበሩ 692 ነዋሪዎች 678ቱ ተነስተው ቤት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የተቀሩት 14 ቤቶች በአጭር ጊዜ ለመጨረስ በሂደት ላይ መሆኑን ነው አቶ ጥበበ የገለጹት።

ስታዲየሙ ሲጠናቀቅ አዲሱን የጎል ላይን፣ የሽብር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በር ላይ የሚገጠሙ ቴክኖሎጂዎችና በጦር ውርወራ ጊዜ ርቀቶችን መለካት የሚያስችሉ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ይኖሩታል።

ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በአምስት ዓመታት ውስጥ ካስገነባቸው ስታዲየሞች መካከል አምስቱ ትላልቅ ስታዲዮሞች በአሁኑ ወቅት  ግንባታቸው ከ80 እስከ 90 በመቶ ተጠናቋል።

*******

ምንጭ፡- ኢዜአ – ጥር 18/2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories