* ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለጉዳቱ መባባስ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያን ተጠያቂ አድርገዋል
* “ቃጠሎው ከጃዝ አምባ አልተነሳም” የጃዝ አምባ ዋና ሥራ አስኪያጅ
* እሣቱ ከጣይቱ ኪችን አለመነሳቱን አረጋግጣለሁ – አቶ አያሌው ታደሰ የጣይቱ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ
* አጋጣሚው ምትክ የማላገኝላቸውን ነገሮች ያጣሁበት ክፉ አጋጣሚ ነው – የፊልም ፕሮዳክሽን ባለቤት
ባለፈው እሁድ ማለዳ ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ታሪካዊው የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል እሣት መነሻ እያወዛገበ ነው፡፡ ፖሊስ እሳቱ የተነሳው በጃዝ አምባ አዳራሽ ውስጥ በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮች መጠላለፍ ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ ቢገለፅም እሳቱ ከጃዝ አምባ አለመነሳቱን የጃዝ አምባ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርምያስ ፋንቱ ገልፀዋል፡፡
የጃዝ አምባ የኤሌክትሪክ ሲስተም አዲስና ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ለእንዲህ አይነት አደጋ የሚጋለጥበት ምንም ምክንያት እንደሌለና ላለፉት አራት ዓመታት ምንም ዓይነት ችግር አጋጥሞ እንደማያውቅ የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ፤ ፖሊስ እሳቱ የተነሳው ከጃዝ አምባ ነው ማለቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ “ከሙዚቃ መሳሪያ ጋር በተገናኘ እሳቱ ተነስቷል እንዳይባል እንኳን እሁድ ጠዋት የጃዝ አምባ ሰራተኛ የሆነው ልጅ ገብቶ መድረኩን ለቴአትር ዝግጁ ለማድረግ ሁሉንም የሙዚቃ መሳሪያ አነሳስቶ ነበር” ብለዋል፡፡
ሌላው እሳቱ ከጃዝ አምባ እንዳልተነሳ እርግጠኛ የሆኑበትን ምክንያት አቶ ኤርሚያስ ሲናገሩ፤ የህብረት ባንክና የጃዝ አምባ ሲስተም አንድ መሆኑን ጠቁመው፣ እሳቱ ተነስቶ ከጀርባ በኩል ጭስ ሲታይ ሰዎች ከኤቲኤም ማሽን ብር እያወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ እሳቱ ከጃዝ አምባ ቢነሳ ኖሮ ኤቲኤም ማሽኑ አይሰራም ነበር ሲሉ እሳቱ ከጃዝ አምባ ተነሳ መባሉን እንደማይቀበሉት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም በታዋቂዎቹ ሙዚቀኞች አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ሄኖክ ተመስገን፣ ግሩም መዝሙር፣ ዮናስ ጎርፌና ሳሙኤል ገዛኸኝ የተቋቋመው ጃዝ አምባ፤ በቃጠሎው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ውድመት ደርሶብኛል ብሏል፡፡ የጃዝ አምባው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ፋንቱ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በአደጋው የተለያዩ እጅግ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸው ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልፀው እሳቱ ገና በጀመረባቸው ደቂቃዎች ጉዳዩን ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ብናሳውቅም አፋጣኝ ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም ብለዋል፡፡
“እሳት አደጋዎች ዘግይተው መድረሳቸው ሳያንስ ከስፍራው ከደረሱም በኋላም አደጋውን ለመከላከል ያሳዩት ቸልተኝነት ጉዳቱ እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል፡፡ እነመርሃዊ ስጦታ፣ ጋሽ ባህታ፣ ግርማ ነጋሽና መሰል አንጋፋ የሙዚቃ ሰዎች ወደ ሙዚቃ እንዲመለሱና ሞራላቸው እንዲጠገን በማድረጉ በኩል ጃዝ አምባ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ፤ ቃጠሎው በእነዚህ ሰዎችም ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ጃዝ አምባውን ወደ ቀድሞው ሥራው ለመመለስ በኮንሰርትም ሆነ በሌላ መንገድ ገቢ ለማሰባሰብ ቃል መገባቱንና ብዙ ተዘግቶ ይቆያል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ ተስፋ ኮሙኒኬሽንና ኢንተርቴይመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ ተስፋ በበኩላቸው፤ በቃጠሎው ምትክ የሚያገኙላቸውን ውድ ነገሮች ማጣታቸውን ጠቁመው፣ “ይህ በህይወቴ ብዙ ነገሬን ያጣሁበት ክፉ አጋጣሚ ነው” ብለዋል፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ሞት ጊዜ አርቲስቶች የሰሩትን ስራ በኃላፊነት ተረክበው ሲሰሩ እንደነበር የተናገሩት አቶ አዲስ፤ ሥራው ያለ ቀሪ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልፀዋል፡፡ በቀርቡ ሠርተው ያጠናቀቁት “በቅኝትሽ” የተሰኘ አዲስ ፊልምን ጨምሮ የሠርግ ስነስርዓታቸውን ሲፈፅሙ የተቀረፁ የቪዲዮና የፎቶግራፍ ቅጂም ያለምንም ምትክ ወድሞብኛል ብለዋል፡፡ በገንዘብ ልተካቸው የማልችላቸው በርካታ ዘጋቢ ፊልሞችና ምትክ የማላገኝላቸው ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ወድመውብኛል ሲሉም ሁኔታውን በሃዘን ገልፀዋል:፡
የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ፤ በቃጠሎው ወቅት በፍጥነት ከቦታው አለመድረሳቸውንና ከደረሱም በኋላ እሣቱን ለማጥፋት ቸልተኝነት ማሣየታቸውን አስመልክቶ የቀረበባቸውን ቅሬታ፤ የሥራውን ባህርይ ካላማወቅና ከግንዛቤ ማነስ የተሰጠ አስተያየት ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
የእሣት አደጋው ጥሪ በተደረገልን በሁለት ደቂቃ ውስጥ ከሥፍራው ደርሰናል ያሉት ኦፊሰሩ፤ የሆቴሉ እድሜ፣ ርዝማኔና የተሠራበት ቁሳቁስ በፍጥነት ተቀጣጣይ መሆን አደጋውን አባብሶታል ብለዋል፡፡
ሠራተኞቹ ከሥፍራው እንደደረሱ ምንም አይነት ቸልተኝነት አላሣዩም ያሉት አቶ ንጋቱ፤ እሣት እንደ ሻማ እፍ ተብሎ የማይጠፋ በመሆኑና ህዝብ የማይረዳቸው ብዙ ቴክኒካል ነገሮች በመኖራቸው እነሱ እስከሚስተካከሉ ድረስ ደቂቃዎች ማለፋቸው አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
**********
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ፣ ጥቅምት 09-2007