ባህር ማዶ የሸፈተው ልባችን በሀገር ያሉ ዕድሎችን ያስተውል (ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር)

ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተላከ መግለጫ
ለሥራ ፍለጋ ባህር ማዶ የሸፈተው ልባችን በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ የስራ ዕድሎችን ያስተውል
ህዳር 2007

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተዘፈቀችበት ድህነትና ኋላቀርነት ተላቃ ዜጎቿ አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን የልማት ነጋሪት ከተጎሰመ ሰነባብቷል፡፡

በዚሁ መሠረት ዛሬ ሀገሪቷን እያስተዳደረ ያለው ልማታዊ መንግሥት የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት የሆነውን ድህነትና ኋላቀርነት በማስወገድ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተዘርግተው በሕዝቡ ሙሉ ተሳትፎ ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሀገራዊ ንቅናቄ መላው የሀገራችን ሕዝቦች የሚናፍቁትን የኢትዮጵያ ህዳሴ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

ይሁንና ብዙዎቹ የሀገራችን ሕዝቦች የዚህ ልማት ንቅናቄ ተሳታፊዎች ይሁኑ እንጂ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው ዜጎች ለሥራ ፍለጋ በሚል ሰበብ በሀገሪቱ ያሉትን የሥራ ዕድሎች ባለመረዳት ወይም ይህንኑ ወደ ጎን በመተው ወደ ውጭ ሲያማትሩ ይስተዋላል፡፡ በሀገር ቤት ብዙ ሊያሰራ የሚችል ከፍተኛ ገንዘብ በአቋራጭ ለመክበር የሚያስችል መረብ ለዘረጉ ህገ-ወጥ ደላሎች በመክፈል ጭምር በህገ-ወጥ መንገድ ወደ የተለያዩ ሀገሮች በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች፣ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካና የመሳሰሉት ሲኮበልሉ ይታያሉ፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ ለሥራ ፍለጋ ብለው ሀገራቸውን ትተው ወደተጠቀሱት ሀገራት የሚሄዱ ዜጎች ብዙዎቹ ለጉልበት ብዝበዛ፤ ለአካልና ለሥነ-ልቦና ጥቃት ይዳረጋሉ፡፡ በጉዞ ላይም ሆነ በደረሱበት ሀገር በተሰማሩበት ሥራ ላይ ለአሰቃቂ የሞት አደጋ የሚዳረጉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ድንበር አቋርጠው በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ወገኖቻችን ሰበዓዊነት በጎደላቸው ግለሰቦች እንደ ዕቃ በኮንቴነር ታሽገው ረጅሙን በረሃ ለማቋረጥ በሚያደርጉት ሙከራ የሚደርሱ አሰቃቂ አደጋዎችና ሰቆቃዎችን መስማት ከጀመርን ሰነባብተናል፡፡ በባህር ውስጥ መስጠም፤ በባዕድ ሀገር እስር ቤቶች ሰብአዊነት በጎደለው አያያዝ መንገላታት፤ መደፈርና እንደ ኩላሊት ያሉ የህይወት ዋጋን የሚያስከፍሉ የውስጥ አካላት ስርቆት ተጠቂዎች መሆን ወዘተ — ዜጎቻችን አሳዛኝ መስዋዕትነት እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት በጥልቀት ለተረዳው በስደት ላይ ባሉ ወገኖቻችን እየደረሰ ያለው መከራ የእያንዳንዳችንን ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ይህንንም በተለያዩ ጊዜያት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲሁም በተለያዩ ሚዲያዎች የሚቀርቡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በዚህ ረገድ በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ አገር ተባረው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ዜጎቻችን ሁኔታ አንዱ የዚህ ማሳያ ነው፡፡Photo - Expats Queue at Ethiopian Ministry of Labour and Social Affairs

በህገ-ወጥ መንገድ የሚደረግ የሰዎች ዝውውር በዜጎች ላይ ከሚያስከትለው ብዝበዛ፣ የሞት፤ የአካልና የሥነ-ልቦና ጉዳቶች ባሻገር ድርጊቱ ሀገራችን እያካሄደች ካለችው የሕዳሴ ጉዞ በተቃራኒ የሀገራችንን ገጽታ የሚያበላሽ ነው፡፡ ሀገራችን በሌላው ዓለም የረሃብ ተምሳሌት መደረጓ የሚያንገበግባቸው ልጆቿ ይህንን አሳፋሪ ታሪኳን ለመቀየር የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ባሉበት እና እየተተገበሩ ያሉ የልማት ውጥኖቻችን የፈነጠቁት የተስፋ ብርሃን ዕውቅና ባገኘበት ወቅት ይህ ዓይነቱ መጥፎ ገፅታ ለሀገራችን የሚመጥን አይደለም፡፡

ዛሬ በዚህች ሀገር ሰርቶ ለመለወጥ የፈለገ ሁሉ የአካልም ሆነ የሕይወት መስዋዕትነት መክፈል ሳይጠበቅበት የሚያድግበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እንደማንኛውም በዕድገት ጎዳና ላይ ያለች ሀገር መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ ነው ባይባልም በሀገራችን በተነደፉ የልማት ዕቅዶችና ኘሮግራሞች ላይ በመሳተፍ እራስንም ሆነ ሀገርን መጥቀም ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ልማታዊ መንግሥታችን የኢትዮጵያ ሕዳሴ መሠረት የሆነውን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማዘጋጀት ሀገራችንን ወደ ብልፅግና ምዕራፍ ሊያሸጋግሯት የሚችሉ ሕዝባዊ ተግባራትን እየተገበረ ይገኛል፡፡

ከእነዚህ ትልልቅ ተግባራት መካከል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታና ሌሎች የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፤ የቤቶች ልማት፤ በግብርናና በኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ዘርፎች እየተተገበሩ ያሉ የልማት ዕቅዶች እና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ መጠነ ሰፊ ሥራዎች በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሰው ኃይል እያሳተፉ በመሆናቸው ለሕብረተሰቡ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እየፈጠሩ ናቸው፡፡ በተለይ ወጣቶችና ሴቶች በእነዚህ መስኮች ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፉ በመጡት የሥራ ዕድሎች ላይ በመቀጠርም ሆነ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በመደራጀትና ሥራ ፈጣሪ በመሆን ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዜጎች ወደማያውቁት ሀገር በመሰደድ ለጉልበት ብዝበዛ፤ ለአካልና ለሥነ-ልቦና ጉዳት እንደዚሁም ለሕይወት መስዋዕትነት አደጋ መዳረግን መከላከልና ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድሎችን አጥብቆ በመያዝ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚችሉ ማሳያው ብዙ ነው፡፡ ዜጎቻችን በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች እየተፈጠሩ ያሉ ሰፊ የሥራ ዕድሎችን ሊጠቀሙባቸው ይገባል፡፡ ለሥራ ፍለጋ ባህር ማዶ የሸፈተው ልባችን በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን ያስተውል የሚለው መልዕክት ፈጥኖ ሊደመጥና ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የሀገራችን የልማት ግስጋሴና የሥራ ዕድል መስፋፋት ዜጎቻችን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ባዕድ ሀገር እየተሻገሩ ተዘርዝሮ ለማያልቅ ጉዳትና ለሞት የሚዳረጉበትን ሁኔታ ማስቀረት እንደሚቻል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ስለሆነም ህገ-ወጥ ስደትን ለቀቅ፤ ልማት ያመጣውን የሥራ ዕድል ጠበቅ ማድረግ ይበጃል እንላለን፡፡

በዚህ ረገድ ሕብረተሰቡ ልጆቹን መጠበቅ አለበት የሚለው ቀዳሚ መልዕክታችን ነው፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንዳንድ ቤተሰቦች የህገ-ወጥ ደላሎችን አፍራሽ ድርጊት እየደገሙና እያራመዱ በገዛ ልጆቻቸው ላይ የሚያስከትሉት አደጋ ፈጥኖ ሊወገድ ይገባል፡፡ ችግሩን ብሔራዊ ትጋት ተላብሰን በጋራ ከተረባረብንበትና አሁን የተጀመረው የሕዝብ ንቅናቄ ግለቱን ጠብቆ ከቀጠለ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ የሚገኘው ሰቆቃ እንደሚወገድ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም ፀረ-ልማት የሆነው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የወንጀል ድርጊት ከሀገራችን እንዲወገድ መላው ሕዝባችን፤ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት፤ ሲቪል ማህበረሰብ እና የሕዝብ አደረጃጀቶች ሁሉ በጋራ እንረባረብ የሚለው የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቅታዊ ጥሪ ነው፡፡

*********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories