መንግሥት በሃይማኖት ተቋማት ካድሬዎችን የሚያስመርጥበት ምክንያት የለውም

(እውነቱ ብላታ ደበላ – የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳይ ጽ/ቤት ሚኒስትር ደኤታ)

[የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል እዚህ ያንብቡ]

1.2.2 የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቶች ምርጫ በመስጊድ መሆን ሲገባው በሌሎች አዳራሾች የተፈጸመው ሃይማኖታዊ አይደለም- በምርጫውም መንግሥት ጣልቃ ገብቷል በሚል የቀረበውን በተመለከተ፤

የአገራችንን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቶች ምርጫ የሚፈጸምበትን ስፍራ የመወሰን ሥልጣን ያለው ይህንኑ በበላይነት ሲያስተባብር የነበረው የኢትዮጵያ ዑላማዎች ምክር ቤት ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን የምርጫ ሕግም ይሁን የመምረጫ ቦታ የመወሰን ሥልጣንና ኃላፊነት የለውም፡፡ ይህ በሕገ-መንግሥታችንና በሕገ-ደንቦቻችን በማያሻማ መንገድ የተቀመጠና ባለፉት 20 ዓመታት በጥብቅ ዲሲፕሊን ተግባራዊ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ ሁላችንም እንደተከታተልነው የኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤት ሃይማኖታዊ ውሳኔ የሰጠበት ጉዳይ እንደሆነ የምንገነዘበው ነው፡፡ የአገራችን ዑላማዎች የሰጡትን ሃይማኖታዊ ውሳኔ የመንግሥት ውሳኔ አስመስሎ ማቅረብና ሃይማኖታዊ ውሳኔዎችን ላለመቀበል የሚሰራጨው መልዕክት ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በመቆርቆር ሳይሆን፤ በመስጊድ ሆነው የፈለጉትን ሁከትና ብጥብጥ ሲፈጽሙ አንድም የፀጥታ ኃይል እንዳይገባ መከላከያ ይሆነናል አሊያም ገብቶ ከተገኘ ጣልቃ ገብቷል በሚል ሕዝበ-ሙስሊሙን ለማደናገር ይመቸናል የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡

አክራሪው/ጽንፈኛው ኃይል ለሃይማኖት ተቆርቋሪና ተገዥ ቢሆን ኖሮ የአገራችን የዑላማዎች ምክር ቤት ያስተላለፉትን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ማክበር ይጠበቅበት ነበር፡፡ ሃይማኖታዊ ተግባር በሚፈጸምበት ቦታ ሆኖ ሰላማዊውን አማኝ ከማወክ በተጨማሪ የእምነት ቦታ የሚያረክስ ድርጊት መፈጸማቸው ከመጀመሪያውም የሃይማኖት ጉዳይ እንዳልሆነ ግልጽ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ ሰላም እያወኩና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት አደጋ ውስጥ በመጣል የሚደበቁበትና የማይደረስበት ቦታ እንደማይኖር መገንዘብ ነበረባቸው፡፡ ስለዚህ የሃይማኖታዊ የምርጫ ሕግም ይሁን የምርጫ ቦታ ጉዳይ መንግሥትን የማይመለከ ተውና የኢትዮጵያ ሕዝበ – ሙስሊምና መሪ ተቋማት ውሳኔ ብቻ መሆኑን በአንክሮ መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡

በዚህ ሂደት ከ8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ወጥቶ ከቀበሌ መዋቅር እስከ ፌዴራል ድረስ ሃይማኖታዊ አመራሮችን የመረጠበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ ዑላማዎች ምክር ቤት መግለጫ የቀረበበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ 8 ሚሊዮን ሕዝበ-ሙስሊማችን በንቃት ተሳትፎ አገር አቀፍ በሆነ መንገድ የተከናወነው ምርጫ በየትኛውም መስፈርት በዓለም ደረጃ እንደ ሞዴል የሚወሰድ ነው፡፡ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንደነበረም ጥርጣሬ ያለበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህን ምርጫ መንግሥት የራሱን ካድሬዎች ለማስመረጥ ተጠቅሞ በታል፤ ከመስጊድ ውጪ ያደረገውም ለዚሁ ነው በማለት የማደናገሪያ መልዕክት የሚያስተላልፉ አካላት መሠረታዊ ስህተቶችን እየፈጸሙ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት ሕገ-መንግሥትን የሚያከብርና የሚያስከብር ተቋም ከመሆን አልፎ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ካድሬዎችን ለማስመረጥ የሚንቀሳ ቀስበት ምክንያት የለውም፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥት ካድሬዎችም ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ በማይጠይቅ ሥርዓት ውስጥ እንዳለንም መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ አክራሪው ኃይል ስለ ምርጫው ቦታም ይሁን ጣልቃ-ገብነት የሚያሰራጫቸው አሉባልታዎች መሠረት የሌላቸው መሆኑን ሕዝበ-ሙስሊማችን ሊረዳ ይገባል፡፡

1.2.3 በአዲስ አበባ አወሊያ የሕዝበ-ሙስሊም ትምህርት ተቋም ተዘግቷል በሚል የቀረቡ  ጥያቄዎችና ሃሳቦችን በተመለከተ፤

አወሊያ የሕዝበ-ሙስሊም የመጀመሪያ የትምህርት ተቋም ሆኖ የተመሠረተው በ1957 ዓ.ም አካባቢ ሆኖ የ50 ዓመት ዕድሜ አለው፡፡ ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ የውጭ አገር ጐብኚዎች ትኩረት እያገኘ ከመጣ በኋላ የአመራርና የፋይናንስ ምንጩ በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከወደቀ በኋላ የተለያዩ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን ማስተናገድ ጀመረ፡፡ በሂደትም የኢትዮጵያ እስላማዊ አስተምህሮዎችን እያጠፉ በምትኩ በሰላም አብሮ መኖርንና ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በሚያፈርስ ተግባር ላይ መንቀሳቀሱን ቀጠለ፡፡ የሥልጠና ሥርዓቱን አክራሪነት/ጽንፈኝነት ብሎም ለአሸባሪነት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ተደርጐ ተቀየሰ፡፡ መምህራኑ፤ መጽሐፍቱና የትምህርት ካሪኩለሙ ሲፈተሽ የአገራችንን እስላማዊ አስተምህሮ የሚቃረንና በሂደት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል የመናድ ቅድመ-ዝግጅት የሚፈጽም የሰው ኃይል መፍለቂያ ተቋም ሆኖ ሥራውን ቀጥሎ ነበር፡፡ ለሽብርተኝነት ተግባር የሚውሉ ሕፃናትን በድብቅና ከሰው ጋር እንዳይገናኙ አድርጐ በሃይማኖትና በዓረብኛ ቋንቋ ሽፋን ያሰለጥን ነበር፡፡

በሌላ በኩል በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ሽፋን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር የነገሰበት ተቋምም ሆኖ ነበር፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል አክራሪነትን/ጽንፈኝነትን በሌላ በኩል ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢነትን በማጧጧፍ ላይ የተመሠረተ ተቋም ሆኖ የአገራችን ሕዝበ-ሙስሊሞች የተመኙትን መፈጸም ሳይሆን በራሱ ድብቅ ፍላጐት የተሰማራ ተቋም ሆነ፡፡

ይህን ድብቅ ሴራ ለሚያስፈጽሙ የተቋሙ አመራሮች በግልጽ ከሚከፈላቸው ደመወዝ በተጨማሪ የሥራ ግብር የማይከፈልበትን የወር ደመወዝ የሚከፍል ሲሆን፤ ለምሳሌ ለተቋሙ የበላይ አመራር እስከ 15ሺ የሳውዲ ሪያል በሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ሙለሐቅ በኩል በስውር ይከፈል ነበር፡፡ በ1965 በሕዝበ ሙስሊም ጥያቄ መሠረት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በወረዳ 15 መንግሥት የሰጠው የአወሊያ መሬት 110ሺ ሜትር ካሬ ቦታ ሲሆን፤ 54ሺ ሜትር ካሬ ለግለሰቦች ተሸጧል፡፡ በሽያጭ የተገኘውም ገንዘብ ግለሰቦች ተከፋፍለውታል፡፡ ሠራተኛው የጡረታ ጊዜ መጦሪያ ከደመወዙ ያዋጣው ገንዘብ ከባንክ ወጥቶ ለግለሰቦች መጠቀሚያ ሆኗል፡፡ በተለያዩ የእርዳታ ስሞች ለሕዝበ-ሙስሊም ትምህርት ቤት የመጡ ግብአቶች እየተዘረፉ የግለሰቦች መጠቀሚያ ሆነዋል፡፡ መኪና፣ የውሃ ፓምፕ፣ የእህል ወፍጮ፣ ወዘተ… በየዘመድ አዝማድ ተዘርፈዋል፡፡ ተቋሙን በገንዘብ ያግዙ የነበሩ ዓለም አቀፋዊ እስላማዊ እርዳታ ድርጅት በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያፈስ ቢታወቅም ገቢውና ወጪው የማይታወቅና ሲመዘበር የነበረ መሆኑ በበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ዳግም ምዝገባ ወቅት በግልጽ የታየ ጉዳይ ነበር፡፡

ይህ ተቋም እንደማንኛውም የበጐ አድራጐት ተቋም ዳግም እንዲመዘገብ ሲጠየቅ ትክክለኛው ባለቤት ከመሰወር ጀምሮ የተቋሙን ግልጽ ዓላማና ተግባርና አፈጻጸም በሂሳብ አጠቃቀም መዝገብ ጋር አያይዞ ሊያቀርብ የሚችል ግለሰብ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል ጊዜ ቢሰጠውም ሕጋዊ ቁመናና ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮን ማሳየት ባለመቻሉ በተደጋጋሚ ሙያዊ እገዛ ቢሰጠውም ከተዘፈቀበት ገሐድ የአክራሪነት/ጽንፈኝነት መፈልፈያ ተቋምነትና የኪራይ ሰብሳቢነት መናኸሪያነት በተለየ ገጽታ ራሱን መለየት ሳይችል የቀረበት ነባራዊ ሁኔታ ፍንትው ብሎ የታየበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡

ይህ ሁኔታ ሲያጋጥም የሚመለከተው መስሪያ ቤት የሆነው የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ መውሰድ የነበረበት እርምጃ በሕግ የተደነገገ ነው፡፡ አንዱ አማራጭ ተቋሙን መዝጋት ሲሆን፤  ሌላው አማራጭ ተመሳሳይ ተልዕኮ ወዳለው ተቋም ማስተላለፍ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ መመዝገብ ያቃተውን ተቋም የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ያደረገው ነገር ቢኖር ከመዝጋት ይልቅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዲያስተዳድረውና ውስጣዊ ችግሮቹን እንዲፈታ የማስተላለፍ ሥራ ነበር፡፡

ይህ ተቋም ዛሬም ሥራውን እየሰራ ሲሆን፤ አክራሪው ኃይል ለማደነጋገሪያነት እንደሚያስወራው አልተዘጋም፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በራሱ አሠራር መሠረት በልዩ አደረጃጀት እንዲመራና ጠቅላይ ምክር ቤቱ የበላይ ጠባቂ ሆኖ እንዲሰራ ወስኖ እየተንቀሳቀሰበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ መደበኛ ትምህርቱን እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን፣ ሃይማኖታዊ ትምህርትንና አረብኛ ቋንቋም እያስተማረ ነው፡፡ ማድረግ የማይችለው ነገር ቢኖር ሰላማችንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓታችንን የሚቃረን አስተምህሮ በሃይማኖት ሽፋን ማካሄድ ብቻ ነው፡፡ ይህ ተቋም በከፍተኛ ደረጃ አድጐ የሕዝበ-ሙስሊሙን ዓለማዊና ሃይማኖታዊ ጥማት የሚያሟላ እንዲሆን የዘወትር ምኞት ነው፡፡

ስለዚህ የአወሊያ የትምህርት ተቋም መንግሥት የዘጋውና ችግር የፈጠረበት ሳይሆን በራሱ ጊዜ ከሕዝበ-ሙስሊም ፍላጐትና ምኞት ውጪ በመንቀሳቀሱ ያጋጠመው ችግር ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ዛሬም የሕዝበ-ሙስሊም ተቋም ነው፡፡ መደበኛ አገልግሎ ቱንም እየሰጠ ይገኛል፡፡

1.2..4 መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን በዘፈቀደ ይቀይራል፣ የራሱን ካድሬዎች ለማስቀመጥ ይረባረባል በሚል የቀረቡ  ጥያቄዎችና ሃሳቦችን በተመለከተ፤

አክራሪው/ጽንፈኛው ኃይል ዋናው የትግል ሜዳ የሃይማኖት ተቋማት የሆኑበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ በሃይማኖት ተቋም ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እየፈጠረ የዜጎችን የሃይማኖት/የእምነት ነፃነት ሲደፈጥጥ የሕግ የበላይነት የማስከበር እንቅስቃሴ ሲደረግ በሃይማ ኖታችን ጣልቃ ተገብቷል በሚል ለማሳየት ምቹ  አጋጣሚ ይፈጥርልናል በማለት ነው፡፡ በዚሁ የሚሸማቀቅ የሕግ አስከባሪ ኃይልም መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው በሚል የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አፈና እንዳላዩት ሆነው እንዲያልፉና  ጫና ለማሳደር ነው፡፡ በየሃይማኖቱ በዓላት አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ሁከቶችና ብጥብጦች መነሻቸው ይኸው ነው፡፡ ይህንኑ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ-ገጾች በማስተጋባት የሕግ የበላይነት እንቅስቃሴን የጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴ አድርጎ በማሳየት ሕዝባችንን የማደናገር ስልት ነው፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የራሱ ካድሬዎች እንዲሆኑ የሚፈልግበት አንዳች ምክንያት የለውም፡፡ እንዲያውም ሕዝቡን በሃይማኖታዊ አስተምህሮ የሚገነቡ ሃይማኖታዊ መሪዎች መኖራቸው በሰላም አብሮ መኖር ሰላም ያጠናከራል፡፡ መንግሥትም ሕዝብም ይጠቀማል የሚል እምነት አለ፡፡ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቶችን የማክበርና የማስከበር ድርሻ የሁሉም ዜጋ መሆኑን መንግሥት ጠንቅቆ ስለሚረዳ ካድሬ የሃይማኖት መሪ ካልተቀመጠ የሥርዓቱ አደጋ ነው ብሎ አያምንም፡፡

የሃይማኖት መሪዎች ሥራቸው ሃይማኖታዊ ተልዕኮ እንጂ በዋናነት መንግሥታዊ ተልዕኮ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን በመሾምና በመሻር ድርጊት የሚሳተፍበት ነባራዊና ሕገ-መንግሥታዊ መነሻ የለውም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንደ መተዳደሪያ ደንባቸውና በሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው የመሾምና የመሻር ተግባር የአማኞቹ ብቻ ነው፡፡ አማኞቹ ይህንን ተግባር በሚፈጽሙበት ወቅት የአክራሪውን ፍላጐት ለማሟላት ዝግጁ የሆኑ አመራሮችን እንደማይመርጡ መንግሥት በጥብቅ ያምናል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ራሱ ከሃይማኖቱ እየተነሳ የሚፈጽመው ተግባር መንግሥት ተክቶ የሚሠራበት መነሻ፣ አሠራርና እውቀት የለውም፡፡ በሌላ በኩል ሕዝበ-ሙስሊሙም ይሁን ሕዝበ-ክርስቲያኑ ይመሩኛል ያላቸውን ሃይማኖታዊ መሪዎች ከመረጠ በኋላ ተመራጮች የመንግሥት ካድሬዎች ናቸው፤ ሃይማኖታዊ ዕውቀትም ሰብዕናም የላቸውም፤ ስለዚህ ለሃይማኖት ክብርና ጥቅም የቆምነው ተሟጋቾች እኛ ነን በሚል ሳይሰለቹ የማደናገሪያ መልዕክት የሚረጩ አክራሪዎች/ጽንፈኞች ራሳቸው ናቸው፡፡ አክራሪው/ ጽንፈኛው ኃይል በአማኙ ሕዝባችን ተነቅቶበት ሳይመረጥ ሲቀር፣ የተመረጡት ካድሬዎች ናቸው በሚል ማብጠልጠል የተለመደ ስልት ሆኖ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አማኙ ሕዝብ በመሪዎቹ አመኔታ እንዳይኖረው በማድረግ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት አንዱ ስልት ሆኖ እየተፈጸመ የሚገኝ ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝባችን ይህን ድብቅ ፍላጐታቸውን ተረድቶ በሃይማኖት ሽፋን የራሳቸውን ዓላማ  ለማሳካት የሚረባረቡትን አካላት መመከት ይጠበቅበታል፡፡

*********

* ይህ ጽሑፍ መጀመሪያ የታተመው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‹‹መንግሥታዊ ሃይማኖት፤ሃይማኖታዊ መንግሥትም አይኖርም – መንግሥት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ካድሬዎችን ለማስመረጥ የሚንቀሳቀስበት ምክንያት የለውም›› በሚል ርዕስ ነው፡፡

Ewnetu Bilata Debela is a Special Assistant to the Prime Minister. Previously, he served as State Minister of Government Communication Affairs Office and a senior official at the Ministry of Federal Affairs. Ewenetu studied Chemistry in Bahir dar University, Political Science at Addis Ababa Univercity and Economics at Civil Service University. He occasionally writes on HornAffairs.

more recommended stories