ሕገ-መንግስት እንዲያከብሩ ሲመከሩ – በሃይማኖታችን ጣልቃ ተገባ ይላሉ

(እውነቱ ብላታ ደበላ – የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳይ ጽ/ቤት ሚኒስትር ደኤታ)

ሃይማኖት በመሠረቱ የሠላም ምንጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ሃይማኖትን ለሌላ ድብቅ ፍላጎት ማሣኪያ ሽፋን አድርገው የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥቂት አይደሉም፡፡ በአገራችን የሃይማኖት ተከታዮች ብዝሐነት በማይከበርበት ወቅትም ጭምር በሠላም አብሮ በመኖር የሚታወቁ ናቸው፡፡ ይህንን ዓለም አቀፋዊ ወርቃማ ተሞክሮ የኢፌዴሪ ሕገመንግሥታችን እውቅናና ዋስትና የሰጠው በመሆኑ በሠላም አብሮ የመኖር መስተጋብ ራችን  የበለጠ ስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታትም የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነት በይፋ ተከብሯል፡፡

ይህ ነባራዊ ሁኔታ ቢኖርም በሃይማኖት ሽፋን የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎታቸውን ለማሣካት፣ የአቋራጭ የፖለቲካ ሥልጣን ለመቀዳጀት መረባረብና መንግሥታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት ለማቋቋም የሚንቀሳቀሱ አካላት ተስተውለዋል፡፡ የእነዚህ ኃይሎች  ድምር ውጤት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን ለአደጋ መዳረግና የሕዳሴ ጉዞአችንን በማጨናገፍ  አገራችንን ወደ ባሰ ድህነትና ኋላቀርነት ተመልሳ እንድትገባ ማድረግ ነው፡፡ Ewenetu Blata - Minister

እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ከሚጠቀሙት ስልቶች ዋነኛው ሕዝባችንን በተለያዩ የማደናገሪያ መልእክቶች በመጠቀም ሃይማኖታዊ ይሁንታን ለማግኘት ርብርብ በማድረግ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ይሁንታን በአሳሳች መንገድ ከሕዝባችን ማግኘት የሚፈልጉት ለሃይማኖቱ በሚል በቀላሉ ሕዝቡን ማነሳሳት እንችላለን የሚል ግምገማ ስላላቸው ነው፡፡ በሃይማኖት ጉዳይ አማኙ ሕዝብ ሚዛናዊ አስተሳሰብ ስለሚጐድለው በማነሳሳት መንግሥትንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት ድብቅ ዓላማችንን እናሣካለን የሚል እንቅስቃሴ ነው፡፡እነዚህን አሳሳች መልእክቶች በተሟላ ሁኔታ በትክክለኛ መልክእት ተክተን ሕዝባችን ውስጥ ግልጽነትን እስካልፈጠርን ድረስ ለአክራሪና ጽንፈኛ ኃይል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

በቅርቡ እየተካሄደ ባለው ስልጠና በአንድ ቡድን ውይይት ወቅት ከተነሱት ከአንድ መቶ በላይ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ውስጥ አንኳር የሆኑትንና ለጋራ መግባባት ወሳኝ ይሆናሉ ያልኩዋቸውን እንደሚከተ ለው አሰናድቼ አቅርቤያለሁ፤ መልሶቼና አስተያየቴ በተነሱት ጥያቄዎች፤ አስተያየቶችና አመለካከቶች ላይ ብቻ እንጂ በጠየቁት ወይንም ሃሳቡን ባነሱት ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ እንድትረዱልኝ እማጸናለሁ፤

1. መንግስት በሃይማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል በሚል የቀረቡ  ጥያቄዎችና ሃሳቦችን በተመለከተ፤

1.1 የአገራችን ሕዝቦችና ሁሉም የሃይማኖት እምነት ተከታዮች ብዝሐነትን የማይቀበሉ ሥርዓቶችን በተራዘመ ትግልና በትልቅ መስዋዕትነት ያስወገዱበት ታሪክ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ የአጼው ሥርዓት የአንድ ሃይማኖት ፍልስፍና የተከተለ ሆኖ የአገራችንን ሕዝቦች በእኩልነትና በአንድነት ማስተዳደር ያልቻለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የደርግ ሥርዓት ሁሉንም ሃይማኖ ቶች ከሞላ ጐደል ፀረ-ልማትና ጐታች ናቸው በሚል ፈርጆ መቀመጫና መቆሚያ የነፈጋቸው እንደነበርም ግልጽ ነው፡፡ የአጼውም ይሁን የደርግ ሥርዓት በፀረ-ዴሞክራሲ ባህሪያቸው ላይመለሱ ተሸኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሕገ-መንግስታችን አንቀጽ 11 በግልጽ እንደተ ደነገገው መንግስትና ሃይማኖት እንዲለያዩ ተደርጓል፡፡ በአገራችን መንግስታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡ ሃይማኖታዊ መንግስትም አይኖርም፡፡ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማ ኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ በአንቀጽ 25 በዜጐቻችን መካከል ሌሎች ብዝሐነቶችንም ጨምሮ በሃይማኖት/እምነቱ ምክንያት ማንኛውም ዓይነት ልዩነት እንደማይደረግና በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው ተደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 27 ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን ሃይማኖት/እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በኃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል እንደማይቻል ተደ ንግጓል፡፡ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር፣ ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡

እነዚህ መርሆዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስትና መሪ ድርጅት ኢህአዴግ እንዲሁም አጋር ድርጅቶች በጥብቅ የሚተገብሩትና ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተጨባጭ የተፈጸሙ ናቸው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 5 የተቀመጠው ሃይማኖትና እምነት የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ደግሞ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ገደብ ለሁሉም ሃይማኖቶች ነፃነትና እኩልነት ተብሎ የሚቀመጥ ሲሆን በተለየ መንገድ አንድን ሃይማኖት ለመደገፍ ወይም ሌላውን ለመጨቆን የተቀመጠ አይደለም፡፡ ስለዚህ የህዝብን ደህንነት፣ የህዝብን ሰላም፣ የህዝብ ጤና፣ የህዝብ ትምህርት፣ የህዝብ የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጐችን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች እንዲሁም መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆና ቸውን በሃይማኖት ሽፋን የሚቃረን አካሄድ ገደብ ተጥሎበታል፡፡

እንግዲህ አንዳንድ በሃይማኖት ሽፋን በሕገ-መንግስታችን ገደብ የተጣለባቸውን ድርጊቶች ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላት ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ለማስከበርና ለማክበር ሲባል ከድርጊቶቻ ቸው እንዲቆጠቡ ሲመከሩ መንግስት በሃይማኖታችን ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል በማለት ህዝባችንን ለማደናገር የሚሞክሩት መነሻው ይኸው ነው፡፡

ይህንን የአክራሪዎች/ጽንፈኞች መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል በሚል የሚያሰራ ጩትን አደገኛ መልዕክት በሁለት መንገድ ማየት ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ አንደኛው ጉዳይ ይህን መልዕክት ለምን መረጡ የሚለው ሲሆን 2ኛው ደግሞ መንግስት ጣልቃ ገብቷል በሚል የሚቀርቡ ጉዳዮችን ትክክለኛውን ገጽታ ማስረዳት ነው፡፡

የመጀመሪያው ጉዳይ ከአገራችን ህዝቦች እጅግ የሚበዛው መጠን የሃይማኖት/እምነት ተከታዮች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይህንን ሃይማኖቱን/ እምነቱን ሁሉም ዜጋ እንዲነካበት አይፈልግም፡፡ ሌሎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ጨምሮ በሃይማኖቱና እምነቱ ጉዳይ የመጡበትን ሥርዓቶች በሙሉ ገርስሶ በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲተካ መስዋዕትነትን የከፈለ ሕዝብ ነው፡፡

አብዛኛው ሕዝባችን ሃይማኖት/እምነት እንደ ሕልውናው መገለጫም ጭምር አድርጐ የሚቀበልና የቅዱሳን መጽሐፍትንም ትዕዛዝ አክብሮ የሚኖር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አክራሪው ኃይል ይህንን የሕዝባችን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ሃይማኖት/እምነት ላይ ጫና እየደረሰብህ ነው በሚል መቀስቀስ ከሁሉም መልዕክቶች በላይ ያዋጣኛል ብሎ ከደመደመ ውሎ አድሯል፡፡ “የትግላችን ማዕከል ሃይማኖታችንን መታደግ ነው፤ የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታችንን መታደግ ተስኖአቸዋል፡፡ ብቸኞች ተቆርቋሪዎችና መፍትሔ አፈላላጊዎች እኛ ነን” በሚል ህዝባችንን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግና የድብቅ ፍላጐታቸው ተገዢ ለማድረግ ይንቀሳቀሳሉ፡፡

የመልዕክት አቀራረጽ ሥርዓቱም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያለውና ሕዝብን ለማተራመስ የሚጠቀሙት ስልት ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊ ይሁንታ ለማፈላለግና ለማቀናጀት ይሆናል በሚል የሚሰራጭ መልዕክት ነው፡፡ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ህዝባችን ሚዛናዊ አስተሳሰብ የለውም የሚል መደምደሚያም አለው፡፡ህዝቡ ሚዛናዊ አስተሳሰብ መያዝ ስለማይችል ሃይማኖትህ ተነካብህ ካልነው እንደፈለግነው እናሽከረክራለን የሚል ግምገማ አላቸው፡፡ በተለያዩ ወቅቶች ለሕዝባችን እንደተገለጸው የነዚህ አስተሳሰቦች ምንጫቸው ብዝሃነት የአገራችን ተጨባጭ መገለጫ መሆኑን አለመቀበል፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የአለመግባባቶች አፈታት የሰለጠነ አካሄድ ያለመፈለግና ከሁሉም በላይ ለሕገ-መንግስታችን ያላቸው የማይታረቅ ቅራኔና ርዕዮተ-ዓለማዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስለዚህ መልካቸውን በየወቅቱ በሚቀያይሩ የማደናገሪያ መልዕክቶች በሃይማኖታችን ጣልቃ ተገብቷል በሚል የሚተላ ለፈው ፕሮፓጋንዳ ስሌት ከህዝባችን በተሳሳተ መንገድ ሃይማኖታዊ ይሁንታን ፍለጋ ሲሆን ምንጩ ደግሞ ህዝባችን በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ሚዛናዊ አስተሳሰብ የለውም ከሚል ዓለም አቀፋዊ የሁከትና ብጥብጥ ስልት የሚመነጭ ነው፡፡

ስለዚህ መንግስት በሃይማኖታችን ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል የሚለው መልዕክት አንደኛው መነሻ በቀላሉ አማኙን ህዝብ ከጐናችን በማሰለፍ መንግስትንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት የምንፈልጋቸው የአክራሪነት/ጽንፈኝነት ግቦቻችን በቀላሉ ማሳካት እንችላለን የሚል ስሌት መሆኑን ሕዝባችን ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡

1.2 በሁለተኛው ገጽታ መንግስት በሃይማኖቶች ውስጥ ጣልቃ ገብቷል በሚል በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ያለውን ትክክለኛ ገጽታ እንመልከት፣

  እንደ  ጣልቃ  ገብነት ማሳያ ተደርገው በጥያቄ የተነሱ ጉዳዮች 1/ አል – ሀበሽ የሚባል አዲስ ሃይማኖት ተጭኖብናል፡፡ 2/ የእስልምና ምክር ቤቶች ምርጫ በመስጊድ መሆን ሲገባው በቀበሌ አዳራሾች ተፈጽሟል፡፡ 3/ አወሊያ የትምህርት ተቋም ለፌዴራል መጅሊስ መተላለፉ ትክክል አይደለም፡፡ 4/ መንግስት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን በዘፈቀደ ይቀያይራል 5/መንግስት በሃይማኖት ተቋማት ስር የተደራጁ የወጣት ማኅበራትን በአክራሪነት/ጽንፈኝነት ፈርጆ ለማፍረስ ይንቀሳቀሳል የሚሉ  ሲሆኑ አምስቱንም ነጥቦች አንድ በአንድ በአጭር በአጭሩ እንዳስሳቸው፡፡

1.2.1     አል-ሀበሽ የሚባል አዲስ ሃይማኖት ተጭኗል የሚለውን በተመለከተ፤

ይህ ጉዳይ በጥሬው ሲታይ መንግስትን የሚመ ለከተው ጉዳይ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ የሃይማኖት/ የእምነት ተቋም የሚከተለውን ሃይማ ኖታዊ አስተምህሮ ራሱ የሚወስነው እንጂ መንግስት የሚወስ ነው ጉዳይ እንዳልሆነ ቀድመን የተግባባንበት ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማ ይገባ፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ እንደማ ይገባ በሕግ ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአገራችን ሕዝበ-ሙስሊሞች መሪ ተቋም እንደመሆኑ ይበጀኛል ብሎ ያሰበውን እስላማዊ አስተምህሮ ቢያስተምር እንደ አዲስ ነገር ሊታይበት አይችልም፡፡ በአገራችን ያሉ ሁሉም የሃይማኖትና/እምነት ተቋማት በተደራጀና በቋሚነት የሚያደርጉት የሃይማኖታዊ ምሁራን ልውውጥ በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በተለየ መንገድ የሚፈረጅ አይሆንም፡፡ እዚሁ ላይ ለህዝባችን ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ የትኛውንም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በማስገደድ ሕዝብን ለመጋት የሚሞክር ካለ በጋራ የምንታገለው ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡

አልሀበሽ የሚባለውን እስላማዊ አስተምህሮ ሙስሊሞችን በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ካስተማረ በኋላ ሕዝበ-ሙስሊማችን የሚቀበለው አይደለም ብሎ ከወሰነ ማንም አስገዳጅ ሊኖር አይችልም፡፡ በፈቃደኝነት ትምህርቱን ወስዶ ይጠቅመኛል ብሎ ከወሰነም ለምን ይህንን አስተምህሮ ተቀበልክ ብሎ ማደናገር፣ ማሸማቀቅና ማሸበርም በተመሳሳይ የተከለከለ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ውሳኔውን ለባለቤቱ መተውና ይህንኑ በጸጋ ተቀብሎ በሰላም አብሮ መኖር ነው፡፡ ስለዚህ አል-ሀበሽ የሚባል አዲስ ሃይማኖት መንግስት ጭኗል የሚለው መልዕክት ከእውነት የራቀና የመንግስታችንና የገዢው ፓርቲ ባህሪይ የማይገልጽ ነው፡፡

*********

* ይህ ጽሑፍ መጀመሪያ የታተመው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‹‹መንግስታዊ ሃይማኖት፤ሃይማኖታዊ መንግስትም አይኖርም • ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን እንዲያከብሩ ሲመከሩ መንግስት በሃይማኖታችን ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል ይላሉ›› በሚል ርዕስ ነው፡፡

Ewnetu Bilata Debela is a Special Assistant to the Prime Minister. Previously, he served as State Minister of Government Communication Affairs Office and a senior official at the Ministry of Federal Affairs. Ewenetu studied Chemistry in Bahir dar University, Political Science at Addis Ababa Univercity and Economics at Civil Service University. He occasionally writes on HornAffairs.

more recommended stories