የኬሚካል ክምችትና የአደጋ ስጋት በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች

(እፀገነት አክሊሉ)

«ተማሪዎቻችን በኬሚስትሪ ቤተ ሙከራ የተለያዩ ኬሚካሎችን ቀምመውና አዋህደው የሚያገኙትን እውቀት ማጣታቸው አይደለም እያሳሰበን ያለው ህይወታቸው እንጂ» ያሉት የደጃዝማች ወንድይራድ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሰለሞን ወልደሰንበት።

ለእዚህ አባባላቸው መነሻ የሆነው በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣል፣ በርካታ የኬሚስትሪ ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪዎችን… ያፈራል ተብሎ ከረጅም ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኬሚስትሪ ቤተ ሙከራ አሁን ከታለመው አላማ በተቃራኒው ለተማሪዎች፣ ለመምህራን እንዲሁም ለአካባቢው ነዋሪዎች ሁሉ የስጋት ምንጭ መሆኑ ነው።

አዎ ቤተ ሙከራው ዛሬ እንደልብ ተማሪዎች በውስጡ እየገቡ እየቀመሙና እያዋሀዱ የሚያገኙትን እውቀት የሚገበዩበት የመማሪያ ስፍራ ሊሆን አልቻለም። ይልቁንም በውስጡ በያዛቸው አደገኛ ኬሚካሎች ምክንያት በበሩ እንኳን ለማለፍ የሚያሰጋ፤ መሽቶ ሲነጋ «ዛሬ ደግሞ እንዴት እንውል ይሆን?» የሚል ስጋት የሚያጭር ሆኗል።

An Ethiopian school
An Ethiopian school

በትንሹ 20ዓመት የኬሚካሎቹ ዕድሜ ነው። ምናልባትም ከዚያም ሊበልጥ ይችላል የሚል ግምት አለ። የእነዚህን ዘመን ያስቆጠሩ ኬሚካሎች አደገኝነት የተረዳው ትምህርት ቤቱ እንዲወገዱ ከተለያዩ የትምህርት አካላት ጋር የደብዳቤ ልውውጦችን አድርጓል። ሆኖም ኬሚካሎቹን የማስወገዱ ኃላፊነት የማን እንደሆነ በውል አልተለየምና መፍትሔ ሊሰጠው አልቻለም። እናም ከነችግራቸውና አደጋቸው ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ስጋት እንደሆኑ አሁንም በግቢው ውስጥ ይገኛሉ።

የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከደብዳቤ ባለፈ ዶክመንተሪ ፊልም በማዘጋጀትም «እባካችሁ ተመልከቱኝ» ብሏል፤ ሰሚ ጆሮ ያገኘ ባይመስልም።

በነገራችን ላይ ይህ የኬሚስትሪ ኬሚካል ክምችትና የአደጋ ስጋት በእዚህ ትምህርት ቤት ብቻ ተወስኖ የቀረ አይደለም። ኮከበ ጽባህ፣ዳግማዊ ምኒልክና ቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤቶችም የችግሩ ገፈት ቀማሾች ሆነዋል።

ችግሩ ጎልቶ የወጣበት የደጃዝማች ወንድይራድ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሰለሞን «እኛ ተማሪዎችን ከማስተማርና ትምህርት ቤቱን በኃላፊነት ከመምራት ባሻገር የኬሚካል ባለሙያዎች አይደለንም። ኬሚካሎቹ እንዲወገዱልን አቤት ብለናል። ሰሚ ካጣንም የሚያስከትሉትን አደጋ ቁጭ ብለን ከመጠበቅ የዘለለ አቅም የለንም» በማለት ነው ጉዳዩ ትኩረት እንዳልተሰጠው ያብራሩት።

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ፣ ለየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት አስተዳደር በተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ተጽፈዋል፤ እነርሱም ችግሩን በመረዳት ለአካባቢ ጥበቃ ሪፖርት አድርገዋል። ይህንን ተከትሎም ከተለያዩ ቦታዎች ኮሚቴዎች እየተዋቀሩ ይመጣሉ፤ አሳሳቢነቱንም ይናገራሉ። ሆኖም የመፍትሔ አካል የሆነ አልተገኘም ይላሉ ርዕሰ መምህሩ።

ኬሚካሎቹ በእዚሁ ሁኔታ ታሽገው ከተቀመጡ እንኳን ዓመታትን እያስቆጠሩ ነው። ታዲያ አደጋ ሳያደርሱ ምን ያህል ጊዜ ይቆያሉ? የሚለውን መገመት ከባድ ነው። ምናልባትም ዛሬ፣ ነገ፣… ፈንድተው አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪዎቻችን በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን የኬሚስትሪ ትምህርት በተግባር ማየት አልቻሉም፤ ይህም ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ይላሉ አቶ ሰለሞን።

በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ በባዮሎጂም ሆነ በፊዚክስ ቤተ ሙከራዎች እጅግ የተሟላ ቢሆንም ቤተ ሙከራዎቹ አደጋ ካንዣበበበት ቤተ ሙከራ አጠገብ በመሆናቸው መምህራኑም ተረጋግተው እውቀትን ማስተላለፍ፤ ተማሪዎቹም እንደ ልባቸው ሙሉ ጊዜያቸውን በቤተ ሙከራዎቹ ውስጥ ማሳለፍ አልቻሉም።

«ግቢው ከ 2ሺ 5OO በላይ ተማሪዎችን ሲያስተናግድ የሚውል ነው። ይህ ኬሚካል አንድ ቀን ሊፈነዳ ይችላል። ታዲያ ይህንን ኃላፊነት የሚወስደው ማነው? የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር፣ ትምህርት ቢሮ ወይስ የካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት? ማነው?» ሲሉ ይጠይቃሉ፤ «የት ሄደን መጮህ እንዳለብን ማወቅ አቅቶናል» በማለትም በምሬት ይናገራሉ።

«በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እስከ መቼ ነው የሚዘለቀው?» የሚሉት አቶ ሰለሞን ትምህርት ቤቱ እከሌ ችግሬን ይፍታልኝ ብሎ እጁን አጣጥፎ አለመቀመጡንም ይገልጻሉ። በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ አንስቶ እንወያይ ይላል፣ደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት ይጽፋል፣የሚላኩት ኮሚቴዎች ወደ አካባቢው የመቅረብ ስጋት ስላለባቸው የቪዲዮ ዶክመንታሪ ሰርቶ አሳይቷል። ከእዚህ በላይ ምን ማድረግ ይቻላል? በማለት ሃሳባቸውን አጠቃልለዋል።

የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ተክሊት ይፍጠር በበኩላቸው «በአሁኑ ወቅት ከቤተ ሙከራው ወደ ውጪ የሚወጣ መጥፎ ጠረንን የያዘ ብናኝ አለ። ይህ ደግሞ በአካባቢው በሚያልፉት ሰዎች ላይ የራስ ህመም፣ የመደበት ስሜት እያስከተለ ነው። በመሆኑም በአካባቢው ተማሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ፤ ቁጭ ብለውም እንዳያጠኑ ከልክለናል» በማለት የጉዳዩን አስጊነት ያስረዳሉ።

«በአገሪቱ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። የኬሚስትሪ ባለሙያዎቻችሁን ላኩልንና በትምህርት ቤቱ አቅም ሊወገዱ የሚችሉ ካሉ ምረጡልንና እናስወግድ ብለን ነበር። ሆኖም ሊልኩልን ፍቃደኛ አልሆኑም፤ ትንሽም ተመልካች ያገኘነው ዶክመንታሪ ሲዲው እንዲታይ ካደረግን በኋላ ነው። ነገር ግን መጥተው ከማየትና ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ከማለት የዘለለ መፍትሔ ሊሰጡን አልቻሉም»።

ምክትል ርዕሰ መምህሩ የባለሙያዎችን ማብራሪያ ተንተርሰው እንዳሉትም ኬሚካሎቹ ይህንን ያህል ጊዜ ሳይፈነዱ ለመቆየታቸው ዋናው ምክንያት የአካባቢው ቀዝቃዛ መሆንና ቤቱ መሬት ይዞ የተሰራ መሆኑ ነው። ይህ አስተያየት ይፈነዳል የሚለውን ስጋት በመጠኑም ቢሆን የቀነሰላቸው ቢሆንም ብናኙና መጥፎ ጠረኑ ግን እንዳሳሰባቸው ነው። በትምህርት ቤት ግቢው ውስጥ ተወስኖ መቅረቱም ያጠያይቃል ነው የሚሉት። ያም ሆኖ ግን እስከዛሬ አልፈነዳም ማለት ለወደፊቱ ዋስትና አይሆንምና የጉዳዩ አሳሳቢነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

« ጉዳዩን ለማግነን አይደለም የምንፈልገው፤ ኬሚካሎቹ አደገኛ ናቸው። ማንኛውም ሰው ደፍሮ እርምጃ ሊወስድባቸው፣ አውጥቶ ሊደፋቸው የሚችሉ አይደሉም። በተማሪዎቻችንና በመምህራን ጤና ላይ ስጋት ፈጥረዋል። በመማር ማስተማሩ ስራ ላይም እያሳደሩ ያሉት ተጽዕኖ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ምላሽ ይስጡን» ሲሉ ጥሪ ያቀርባሉ።

የኮከበ ጽባህ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሽመላሽ በቀለ በበኩላቸው እንደሚሉት ትምህርት ቤቱ ከዓመታት በፊት ያስገባቸው ኬሚካሎች ጊዜያቸው በማለፉና በአግባቡም ባለመወገዳቸው ምክንያት ከፍተኛ ስጋት ላይ ነው። እንዴት መወገድ እንዳለባቸው ለመነጋገር ለተለያዩ አካላት ቢጽፉም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም ።

ትምህርት ቤቱም ሆነ የከተማው ትምህርት ቢሮ በራሳቸው አቅም እነዚህን ከጥቅም ውጪ የሆኑና የአደጋ ስጋት እየፈጠሩ ያሉ ኬሚካሎችን ማስወገድ አይችሉም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በጣም ጊዜ እየወሰደ በመሆኑምና ስጋቱም ያንኑ ያህል ከፍ እያለ ስለሆነ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

እስከ አሁን ቤተ ሙከራው ስራውን አለማቆሙን የሚናገሩት ርዕሰ መምህሩ እነዚህ የአደጋ ስጋት የሆኑ ኬሚካሎችን በአንድ ክፍል ውስጥ በመዝጋት በቀጣዩ ክፍል የቤተ ሙከራ ትምህርቱ እየተሰጠ ነው። ሆኖም ይህ ሙሉ በሙሉ ከአደጋ ነጻ ነው ማለት እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

«ኬሚካሎቹ አደገኛ በመሆናቸው መወገድ ያለባቸው ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ነው፤ ማንኛውም ሰው ተነስቶ ላስወግድ ማለትም ከባድ ነው። በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር አወጣዋለሁ ያለውን ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቶ ወይም በአገር ውስጥ የሚወገዱበት ሁኔታ ተመቻችቶ መወገድ አለባቸው። ይህ ባልሆነ መጠን ግን በተማሪዎች ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ እጅግ አሳሳቢ ነው።»

ከእዚህ በኋላም ቢሆን ለትምህርት ቤቶች እነዚህ ኬሚካሎች ሲቀርቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በሚገዙበትም ሆነ በሚከፋፈሉበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊኖር ይገባል በማለት ለወደፊቱ መደረግ ያለበትን አመላክተዋል።

«ባለሙያውም፣ ተማሪዎቹም፣ መምህራኑም በከፍተኛ ስጋት ላይ ናቸው፤ የትምህርት ቤት አስተዳደሩም ከ 2004ዓ.ም ጀምሮ የአስወግዱልኝ ጥያቄውን ከማቅረብ ተቆጥቦ አያውቅም ምላሽ አልተገኘም እንጂ» ይላሉ አቶ ሺመላሽ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አምላኩ ተበጀ እንዳሉትም ችግሩ በአዲስ አበባ ብቻ የሚስተዋል አይደለም። በክልል ባሉ ትምህርት ቤቶችም ችግሩ እየታየና አቤቱታም እያሰሙ ነው። ሆኖም ጉዳዩን በባለቤትነት ይዞ የሚንቀሳቀስ አካል ጠፍቷል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ አቶ አምላኩ ገለጻ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ እንደ ዳግማዊ ምኒልክ፣ ቦሌ፣ ደጃዝማች ወንድይራድ፣ ኮከበ ጽባህ ያሉ የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች የችግሩ ሰለባ ከመሆናቸውም በላይ በተማሪዎቻቸው ህይወት ላይም አደጋው እያንዣበበ ነው። ይህንን ሁኔታ ለማወቅ ትምህርት ቢሮው ጥናት አስጠንቷል። በዚህም ብዙ መረጃ ተገኝቷል።

ትምህርት ቤቶች በየጊዜው አቤቱታዎችን ለትምህርት ቢሮ ያቀርባሉ። ቢሮውም ችግሩን ለመፍታት ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ኬሚካሎቹ ሳይወገዱ ረጅም ዓመታትን እንዲያስቆጥሩ ምክንያት ሆኗል ነው የሚሉት አቶ አምላኩ ።

«ያም ሆነ ይህ ግን እነዚህ ኬሚካሎች ከፍተኛ አደጋ ከማድረሳቸው በፊት ከትምህርት ቤቶች መወገድ አለባቸው። ማስወገጃ መንገዱ ደግሞ ሳይንሳዊ መሆን አለበት፤ ይህንን መፈጸም ያለበት አካል ደግሞ እስከ አሁን አልተገኘም። ትምህርት ቢሮውም ኃላፊነቱን ተወጥቷል የሚል እምነት የለኝም» በማለትም ያክላሉ።

ቢሮው በተለይም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ለመስራት ያደረገው ጥረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ «ዓለም አቀፍ ጨረታን አውጥቼ አስወግደዋለሁ» በማለቱ ሳይሳካ ቢቀርም አሁንም ከኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ያለውን ፈርነስ ማቅለጫ ተጠቅሞ የማስወገድ ስራውን እንዲሰራ በከፍተኛ ኃላፊዎች ደረጃ ውይይት መጀመሩንም ነው የሚናገሩት።

አቶ አምላኩ «ቢሮው የቱንም ያህል ቢሄድ አሁንም ክፍተቶች ይታያሉ። ስራዎችም በአግባቡ ተከናውነዋል ማለት አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም በእዚህ መካከል የሚጎዳ አካል ሊኖር አይገባም። ትምህርት ቢሮውም ሆነ ትምህርት ሚኒስቴር የሚገባቸውን መፈጸም አለባቸው» የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እኔም ተዘዋውሬ የተመለከትኳቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ መጠቀሚያ ጊዜያቸው ባለፈ ኬሚካሎች የመፈንዳት ስጋት የተሸበቡ ናቸው። ይህ የመማር ማስተማር ሂደቱንም እየጎዳው ይገኛል ። በእርግጥም ችግሩ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባው አይደለም። ምክንያቱም ይህ የህይወት ጉዳይ ነው።

ለመሆኑ የእዚህ ጉዳይ ባለቤት ማነው? እንደ አገርስ ይህንን ስራ መስራት ያለበት አካል ሊኖር አይገባም? «ጉዳዩ ይመለከተኛል» የሚል አካል ከሌለ መንግሥት ቀጥታ ገብቶ እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። ሁሉንም በወቅቱ ማከናወን ከከፋ አደጋና ከጸጸት ያድናልና በድጋሚ ትኩረት ይሰጠው እንላለን።
*******

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን፣ መስከረም 30፣ 2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories