የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች በአንገታቸው ላይ የሚያሥሩት ማዕተብ ወደፊት ይከለከላል የሚለውን ወሬ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለማርያም ከማስተባበላቸው ቀደም ብሎ የተጀመረ ክርክር ነበር:: ይህ ክርክር ‹‹ በሙስሊም ሴቶች የሚለበሰው ሂጃብ የሚከለከል ከሆነ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ማዕተብ በዚያ መልኩ ሊታይ ይገባዋል›› የሚል ነው;; ይህን አይነት ክርክር በተለያዩ ማህበራዊ አውታሮች በተለይም በፌስቡክ እየቀረበ ነው፡፡

በብዙዎች የማህበራዊ አውታር አስተያየቶች ማዕተብንና ሂጃብን አንድና ዕኩል የሆኑ ነገሮች አድርጎ ወደማሰብ መንደርደር ተጀምሯል:: በርግጥ ይህ የአንዳንዶች ቀቢጸ ተስፋ ነው:: ለሁለቱም የሀይማኖት መገለጫዎች ወገንተኝነት የለኝም:: ይሁንና በንጽጽር ሂጃብ ከማዕተብ ከ ይልቅ የግለሰብ መብትን ይጋፋል እላለሁ::Types of Hijab - Muslim woman veil

የሆነ ሆኖ እንዲህ አይነት ጉዳይ በሃይማኖት ህግ/ደንብ መደንገግ የለባቸውም:: በፈቃድ የሚተገበሩ መሆን ነው ያለባቸው:: ሒጃብ ጾታ ለይቶ ነው የተደነገገውና የጾታ ዕኩልነትን ይቃረናል:: ማተብ ሁሉንም ኦርቶዶክሳዊ ይመለከታል:: ጾታ ወይም ማህበረሰብ አይለይም:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማዕተብ አለማሰር ያን ያህል ቁጥጥር የሚደረግበት ጉዳይም አይደለም:: ማተብ ምልክት ነው:: ፈልገህ ታስራለህ ሳትፈልግ ትተወዋለህ::

በዚያው መጠን የሀገር ሴኩላር ህጎችም የሀይማኖት ሪችዋልስ/ወጎች/ ከፍላጎት ውጭ በጫና ወይም ማህበረሰብን ለይቶ መከናወን እንዳሌለባቸው በማስረገጥ ላይ ያተኩሩ:: በዚህ ረገድ በሴቶችና በሌሎች በህብረተሰቡ ውስጥ በስፋት ‘ደካማ’ በሚባሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች አያያዝ ማህበረሰቡን ከፍ ወዳለ ንቃት የሚመሩ የህግ ማዕቀፎችን አቅጣጫና ፖሊሲዎችን ማውጣት ተገቢ ይሆናል::

ሂጃብ አጥብቆ የተያዘ የሀይማኖት ህግ ነው:: በሙስሊም ክለሪኮችና በሙላዎች የሙስሊም ሴቶች ግዴታ ተደርጎ በኃይልም በውዴታም የሚጫን ነው:: ሂጃብ በብዙ ሙስሊሞች ብዙኋን በሆኑባቸው ሀገሮች ሳይቀር ተከልክሏል:: ለምሳሌ ቱርክ ከ1997 ጀምሮ በቱኒዚያ ከ1982 ጀምሮ ተከልክሎ በ2011ዱ አብዮት ተነስቷል:: ሌላዋ ከልካይና ሊበራል ሀገር ፈረንሳይ ትሁን እንጂ በቤልጅየም በስዊስና በሌሎችም የአውሮፓ ሀገራትና ክልሎች ክልከላ ተደርጓል::

ሌላኛው መነሻ የህገ መንግስት የበላይነት ነው:: በዛሬ ጊዜ ህገ መንግስት የህጎች ሁሉ የበላይ ነው የሚለው አያከራክርም:: ሕገ መንግስቱ ስህተት አይኖርበትም ወይም የተወሰኑ መብቶችን ስፋት አላግባብ አያጠብም ማለት አይደለም:: ይሁንና ብዙ ጊዜ ሕገ መንግስት የመጨረሻውንና ልንደርስበት ያለውን የዜጎችን መብት ስፋትና ጣሪያ አመልካች ነው:: የግለሰብና የማህበረሰብ መብቶች የመጨረሻ ድንበር ነው::

ዜጎችና ማህበረሰቦች የሚመርጡት ማዕቀፍ የሚሰጠው መብት ከህገመንግስቱ የጠበበ እስከሆነ ድረስ የህግ ማዕቀፋቸውን የመምረጥ መብት አላቸው:: የሌሎች ጥቃቅን ተቋማት ህግ ከህገ መንግስቱ የሰፋ መብት የሚሰጥ ከሆነ የህገ መንግስቱ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ይህ ማዕቀፍ የሚሰጠው መብት ግን በህገ መንግስቱ ከተቀመጠው መብት የሚያንስ የማያፈናፍን ሲሆን ዜጎች በህገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን የተሻለ መብት ክሌይም ማድረግ መብታቸው ነው::

ብዙ ጊዜ የሀይማኖትም ሆነ የማህበረሰብ ተቋማት ህጎችና ወጎች በህገ መንግስት የተቀመጠ የሰዎችን መብት የመገደብ ኃይል አላቸው:: ይህ ገደብ መጽናት ያለበት ግለሰቡ አሜን ብሎ እስከተቀበለው ድረስ ብቻ ነው ብሎ መተው ይቻላል:: ችግሩ ብዙዎቹ የሀይማኖትና የማህበረሰብ ህጎች በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙትን በኃይል አሰላለፍ ‘ደካማ’ የምንላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመጨቆን የተቋሙን ቆይታ ለማራዘም ይታትራል:: ከዚህ በሚነሳ አመለካከት ሴቶች የማህበረሰብና የሀይማኖት ተቋማት ቀጥተኛና ዋነኛ ዒላማ ናቸው::

ሒጃብ ኒቃብና ቡርቃ በሴቶች ላይ የታወጀ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሴቶች ድምጽ ሳይሰማ ድምዳሜ የተወሰደበት የመብት ክርከማ ነው:: እንደሚታወቀው ሴቶች በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያላቸው ተሰሚነት ዝቅተኛ ነው :: የራሳቸውንም አቋም መያዝ እንዳይችሉ ከተቋሙ ሀይማኖታዊም አስተዳደራዊም ኃላፊነት ተገለዋል:: ይህ ማለት በሀይማኖት ህግ ስም ህግ የሚያወጡላቸው ሴቶችን መቆጣጠር የሚፈልጉ ባሎቻቸው ወንድሞቻቸውና አባቶቻቸው ናቸው:: ስለዚህም ሌሎቻችንና ለሴቶች መብት የቆሙ ሁሉ ይህን ህግ አሜን ብለን እንድንቆም መጠበቅ ትክክል አይደለም::

ሂጃብን በተመለከተ ሙስሊም ሴቶች የራሳቸውን መብት በነጻነት አልመረጡም ወይም ሲመርጡ አልታዩም:: በብዙ የምዕራብ ሊበራል ሀገሮች ሂጃብን መጠቀም የሚፈልጉት ሙስሊም ሴቶች ዝቅተኛ ፕሮፖርሽን ነው ያላቸው:: በርግጥ ብዙ ሙስሊም ሴቶች በህግ ሲከለከል ህጉን ለመቃወም ሂጃብን መጠቀም የጀመሩበት ሁኔታም አለ:: ይህ የህጉ ክፉ ማስታወቂያ ነው:: ብዙም ጊዜ የተከለከለን ጉዳይ የመተግበር የእምቢተኝነት ግፊት አለ:: ይህን ለማስቆም ህብረተሰቡን በተለይም ሙስሊም ሴቶችን ስለመብታቸው እንዲታገሉ ማንቃት ያስፈልጋል::

ማህበረሰባዊም ሆነ ሀይማኖታዊ ጫና እና ቀንበር የሚጭኑ እሰከሆኑና የሀገሪቱ ማህበረሰብ ከሰጣቸው ሰፋ ያለ መብት የሚቀንሱ ህግጋት ከሆኑ መታገድ ይገባቸዋል:: ለመከራከር እንኳን የሚሆነው የሙስሊም ሙላዎች ከተቀመጠው ማህበረሰባዊና ሌሎች ሴኩላር ህጎች የተሻለ መብትን የሚያሰፋ ህግ አምጥተው ቢሆን ነበር:: በወግ አጥባቂነት የህዝብን የንቃት ጉዞ የሚገታና በነሱ እስርና ቁጥጥር ስር የሚያደርግ ህግ ሊታገድ ይገባል:: ይህ የሀይማኖት መሪዎችን ሁሉ ይመለከታል::

በዚያው መጠን ማህብረሰቡና የሀይማኖት ተቋማት በዚያ ህብረተሰብ አካላት ላይ በጣለው የረጅም ጊዜ ቀንበር ምክንያት አንዳንድ አባላቱ ያለዚያ ተግባር መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ አለ:: ለምሳሌ ምንም እንኳን በቅርብ አመታት የተጀመረ ቢሆንም በርካታ ሙስሊም እህቶቻችን ሂጃብን ለረጅም ጊዜ በመጠቀማቸው ምክንያት ራሳቸውን ከዚያ መለየት ይከብዳቸዋል:: ህግ ወይም ደንብ ሲወጣ ለነዚህ ሰዎችም ዕድልና ክፍተት መስጠት ብሎም ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው::

እኒህ እህቶች በፈቃዳቸው መከናነብ መቀጠላቸው ህግ ተጭኖባቸው እንዳልሆነ ያስረዳል:: ሆኖም የክለሪኮችና በተለይም በተባዕታይ ጾታ ላይ የተመሰረተው የማህበረሰባችንና የሀይማኖቶቻችን እሴቶችና ወጎች ክንድና የማይታይ የተጽዕኖ ድባብ ከግምት ሲገባ ይህንንም አመለካከት አስቸጋሪ ያደርገዋል:: ዋናው ጉዳይ ኦርጂናሌው ሁኔታ ማንም ሰው ያለ ግለሰቡ ወይም ማህበረሰቡ ይሁንታ በማንም እኩል ህግ በሚገዛው ሌላ ዜጋ ወይም ማህበረሰብ ላይ የሚጫን ህግ ማውጣት የለበትም:: በዚህ ረገድ ማዕተብና ሂጃብ ይለያያሉ::

ሌላኛው ህጉ የወጣበት ስነልቡናና ዓላማ ነው:: ይህ የሂጃብ ህግ የወጣበት ስነልቡና የሴቶች ነጻ ህልውና ካለመቀበል በሚነሳ ስሌት ነው:: ሕጉ የመጣው ሴቶች ራሳቸውን የመቆጣጠር ድክመት አለባቸው ከሚል አመለካከት ነው:: ህጉ የተፈለገው ያልተፈለገ ተፈጥሮዓዊ ባህሪይን ለመቆጣጠር ነው:: ህጉ የተፈለገው በአጠቃላይ ከወግ አጥባቂ አዕምሮ ነው:: ይህ ደግሞ በዛሬው ዓለም ሊደገፍ አይችልም:: ብዙ ሰዎችና የኢስላም ታሪክ ጸሀፊዎች ሙስሊም ምሁራን ሴቶችን ጨምሮ ይህን እያሽሞነሞኑ ዘመናዊነት ለማድረግ ይሞክራሉ::

ይህን ህግ በኃይል ለማስከበር የሚደረገው ማግለል የተለያዩ የተጽዕኖ መስመሮችን መጠቀማቸውና ለይቶ በከፊል መከናወኑ ኋላቀር መሆኑን ያረጋግጣል:: ከዚህ ጋር ጉዳይ ያላቸው ፖለቲከኞችም የሰዎችን መብት ማክበር ዓላማቸው ስለሆነ ሳይሆን አንድም የፖለቲካል እስላም አቀንቃኝ በመሆናቸው አልያም በሴኩላር መንገዶች መወጣት ያልቻሉትን የፖለቲካ እጥፍ ዘርጋ ወደ ሀይማኖት ቅርቃር ተመልሰው ሊያንሰራሩት እየሞከሩ መሆኑ ግልጽ ነው:: ይህ የሚያዛልቅ አይደለም::

ሂጃብ ሲከለከል የሚከለከልበት ምክንያት ሴቶችን ለይቶ ስለሚያስገድድና የሴቶችን እኩልነት ስለሚያጓድል ነው መሆን ያለበት:: በግሌ ሂጃብ ይከልከል አይከልከል የሚለውን ሙስሊም ሴቶች ነጻ ውሳኔ ቢተው መልካም ነበር:: ነገር ግን ብዙ ጊዜ የሀይማኖት ህግጋት በወንዶች የበላይነት የሚከናወን በመሆኑ ሴቶች በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖራቸው ወሳኝነት በሙስሊም በተለይም በአክራሪ ሙስሊም ወንዶች ተጽዕኖ ስር ሊያርፍ እንደሚችል እገምታለሁ::

እንደ መርህ መታየት ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ሀይማኖትና መንግስት የምር መለያየት ስላለባቸው ነው:: የግለሰብን የጾታ ወይም የአንድ ማህበረሰብን መብትን የሚገድብ ህግ ደንብና ማሳሰቢያ መውጣት ካለበት መውጣት ያለበት

(1) የራሱን የግለሰቡን/የማህበረሰቡን/ ደህንነት ለመጠበቅ

(2) የሌሎችንና ከዚህ ግለሰብ/ማህበረሰብ ጋር ግንኙነት የሚፈጥረውን ግለሰብ/ማህበረሰብ ለመጠበቅ

እንግዲህ ሴቶች ይህን ሁኑ ወይም ይህን አድርጉ ተብለው ለብቻቸው ከሌሎች ሴቶች እህቶቻቸው በተለየ ሁኔታ ለሚጨቁኑ ወይም ለሚያስገድዱ የሀይማኖት ህጎች ያለማንም ከልካይ መተዋቸው ትክክል አይደለም:: በመስጊድና በጸሎት ስፍራ መከልከል መጠነኛ የሞራል መሰረት አለው:: በአደባባይ በተለይም በመንግስት ተቋማትና በትምህርት ቤቶች ግን የወደዱትን እንዲያድርጉ መተዋቸው ተገቢ ነው::በቸር ቆዩኝ!
******

Reagan Solomon

more recommended stories