ማዕተብም መስቀልም በግለሰቦች ነፃነት ውስጥ የሚካተት ነው – ዶ/ር ሺፈራው ተክለማርያም

ማዕተብ ማሠር ይከለከላል የሚለው ወሬ መሠረተ-ቢስ ነው በማለት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለማርያም አስተባበሉ፡፡ Minister Shiferaw Teklemariam

ሐራ ዘተዋሕዶ የተሰኘ ሃይማኖት-ተኮር ብሎግ ባለፈው ቅዳሜ፤ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በተካሔደ የፖሊሲና ስትራተጂ ሥልጠና ላይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዕምነት ተከታዮች በአንገታቸው ላይ የሚያሥሩት ማዕተብ ወደፊት እንደሚከለከል ተናግረዋል የሚል ይዘት ያለው ዜና ካተመ በኋላ ርዕሰ-ጉዳዩ በተለያዩ ድረገጾች እና በፌስቡክ ላይ ሞቅ ያለ ውዝግብ አስነስቶ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ከኢትዮጲያ ፈርስት ድረ-ገጽ አዘጋጅ ቢኒያም ከበደ(ቤን) ጋር ሰኞ ዕለት አጠር ያለ ቃለ-ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም ጉዳዩን አስተባብለዋል፡፡

ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም በሰጡት ምላሽ የሚከተለው ይገኝበታል፡-

በተለያዩ ተቋሞቻችን የሴኩላሪዝም መርሆችን በተጨባጭ ተግባራዊ በምናደርግባቸው ሂደቶች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ከማዕተብና መስቀል ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ በየርዕሶቻችን ላይ በዚህ ረገድ ለይተን ያስተማርነው ነገር የለም፡፡ ማዕተብም መስቀልም ግለሰቦች ከሃይማኖታቸው ከዕምነታቸው ተነስተው የሚያደርጉት ነገር በግል ነፃነታቸው ውስጥ የሚካተት እንጂ መንግስት እዛ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ በዚህ ትወጣላችሁ በዚህ ትገባላችሁ የሚልበት ነገር አይደለም፡፡…..

በመንግስት (መሥሪያ ቤቶች) ይሁን በትምህርት ተቋማት ይሁን ስለማዕተብና መስቀል ተነስቶ የተደረገ ውይይት የለም፡፡ በዚህ ዓይነትም አድርጉ አታድርጉ ተብሎ የተነገረ ነገርም የለም፡፡ ግለሰቦች ዜጎች ግን (እነዚህን ነገሮች) ማድረግም መጠቀምም የራሳቸው ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡ ከመንግስተ ጋር የሚገናኝ ነገር (የለውም)፡፡”

(ሙሉ ይዘቱን ከታች ካለው የYouTube ፋይል ያድምጡ)

ሐራ ዘተዋሕዶ ብሎግ ያወጣው ዜና የሚከተለውን የያዘ ነበር፡-

በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በተካሔደውና 800 ያህል መካከለኛ አመራሮች በተሳተፉበት የፖሊሲና ስትራተጂ ሥልጠና ‹‹የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ግንባታና ፈተናዎቹ›› የሚለውን ሰነድ የሚያብራራና በፓወር ፖይንት የተደገፈ ጽሑፍ ያቀረቡት ሚኒስትሩ የመንግሥትን የሴኩላሪዝም መርሖ መነሻ ያደረገ ነው የተባለ ጥያቄ ከአንዲት ተሳታፊ ቀርቦላቸዋል፡፡

እንደ ስብሰባው ምንጮች፣ የተሳታፊዋ ጥያቄ፣ ‹‹በቢሮ ፊታቸውን ተሸፍነው የሚመጡ ሙስሊሞችን አለባበሳቸው ከቦታው አንፃር ያለውን ተገቢነት በማንሣት እንዲያወልቁ ስንጠይቃቸው ‘እኛ ይኼን የምናወልቅ ከኾነ ኦርቶዶክሱም ክሩን ይበጥስ’ ይሉናል፤ ይኼን እንዴት ነው የምንታገለው?›› የሚል ነበር፡፡

‹‹መንግሥታችን ሴኩላር ነው›› ሲሉ በጠያቂዋ የተጠቀሰውን ዐይነት አለባበስ የተቹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹እርሱም [ማተቡም] ቢኾን የጊዜ ጉዳይ ነው፤ እንደ የሃይማኖት መለያ እስካገለገለ ድረስ አደረጃጀታችንን ስንጨርስ ማተብም ቢኾን መውለቁ አይቀርም፤›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተገልጧል፡፡

**********

***********

Daniel Berhane

more recommended stories