የላሊበላና የፋሲል ግቢ ቅርሶች እስከ ዛሬ ለምን ካርታ አልኖራቸውም?

(አርአያ ጌታቸው)

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዋና ጸሐፊ ታሌብ ራፋይ ኢትዮጵያን ጎብኝተው ከተመለሱ ጥቂት ሳምንታት አልፈዋል። ዋና ጸሐፊው በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ እጅግ ደስተኛ እንደነበሩ በወቅቱ ሲናገሩም አዳምጠ ናቸዋል። ጥያቄው ግን ይሀንን ግርምታቸውንና አድናቆታቸውን ወደ ቢሯቸው ሲመለሱ ይደግሙታል ወይ? የሚለው ነበር። ምክንያቱም ብዙ የውጭ አገር ሰዎች እዚህ እያሉና ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ የሚሉትና የሚጽፉት ለየቅል ነውና።

ግን ደግሞ ሚስተር ታሌብ ኢትዮጵያ እያሉ ስለኢትዮጵያና የቱሪስት መስህቦቿ የቸሩትን አድናቆት ከጉብኝታቸው መልስም አልነፈጓትም። የመጨረሻ አስተያየታቸው በድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ ተጭኖ እንዲህ ይነበባል፦

«…ቱሪዝም ሕዝቦችን ከድህነት በማውጣት አዲስ ዕድል መፍጠር የሚችል ቁልፍ መሣሪያ ነው። በኢትዮጵያ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃ ዎችም የሚያሳዩት ይሄንኑ ነው። ኢትየጵያ የቱሪስት መስህቦችን ጥበቃ ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ በቱሪዝም መስክ ያሉ የገበያ ድርጅቶችን በመመስረት ብሎም ብሔራዊ የቱሪዝም ምክር ቤት በማቋቋም፣ በትምህርትና በቱሪዝም መስክ ያሉ የሥልጠና ተቋሞችን በማሳደግ እያከናወነች ያለው ተግባር አብነት መሆን የሚችል ነው። ከዚህ ተግባር ተነስተን ቱሪዝም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንዱ ዋልታ መሆን እንደሚችል በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ለዚህ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እምርታ የመንግሥት የፖለቲካ ድጋፍ ተጠቃሽ ሚና አለው። አገሪቷ በልማት ፖሊሲዎቿ ውስጥ ቱሪዝምን አንዱ አካል አድርጋ ማካተቷ ትልቅ ተግባር ሆኖ አግኝቸዋለሁ…»

ሚስተር ታሌብ እንዳሉት ኢትዮጵያ ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚዋ ዋልታ አድርጋ መስራት ከጀመረች ዓመታትን አስቆጥራለች። የዚህ ሥራዋን ውጤት ማጣጣም ከጀመረች ግን ገና ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው ያለፉት። ለአብነት ያህልም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ይገኛል። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ እንኳ ያለውን እውነታ ብንመለከት ኢትዮጵያን ከጎበኙ የልዩ ልዩ አገር ቱሪስቶች ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሏን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር ይናገራሉ።Fasiledes-castle-Gondar.jpg

ሚኒስትሩ በዘርፉ በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለመሰብሰብ የታቀደው ወይንም ለማግኘት የተቀመጠው ገንዘብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህንንም በአሁኑ በጀት ዓመት ማሳካት ይቻላል ባይ ናቸው (ይሄንን ጊዜው ሲደርስ የሚታይFasiledes castle – Gondar ይሆናል)።

በዓለም በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ባለፉት አስርት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እድገት እያሳየ ይገኛል። እ.አ.አ በ2013 ሃምሳ ስድስት ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ወደ አፍሪካ አገሮች ተመዋል። ይህ ቁጥር እ.አ.አ በ2000 ሃያ ስድስት ሚሊዮን ብቻ ነበር። ከገቢ አንጻርም አኳያም ቢሰላም አፍሪካ በዚሁ ዓመት ብቻ 34 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች።

ወደ አፍሪካ ከተጓዙ 56 ሚሊዮን ቱሪስቶች መካከል ኢትዮጵያን መጎብኘት የቻሉት 724 ሺ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ይህንን ቁጥር በ2007 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን ለማድረስ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያለው የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ካላት በርካታ የቱሪስት መስህቦች አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያን የጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር ትልቅ ነው ተብሎ መከራከሪያ ሊቀርብለት አይችልም። በመሆኑም አገሪቷ ያሏትን ሀብቶች በአግባቡ ይዞና ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራዎችን ሠርቶ በዓለም ላይ ያለውን ትልቅ ሀብት መጠቀም የግድ ይላል። ምክንያቱም የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 56 ሚሊዮን ጎብኝዎች አፍሪካን ጎብኘተዋል ሲል ያስቀመጠው ቁጥር እ.አ.አ በ2030 ወደ 134 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ተንብይዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያም ድርሻ በዚያው ልክ አብሮ ሊያድግ ይገባል። ይሄንን ለማሳካት ደግሞ መሠራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች ቀላል አይሆኑም።

ከሥራዎቹ መካከል አንዱና ዋነኛው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቅርሶችን በተገቢው መንገድ ማስተዳደር የሚለው ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘጠኝ የተመዘገቡ ቅርሶች ባለቤት ናት። በጣም የሚገርመው ግን ከእነዚህ ቅርሶች መካከል የጎንደሩ የፋሲል ግቢና ሌሎች መካነ ቅርሶች፣ ላሊበላ፣ አከሱምና የጢያ ትክል ድንጋዮች የወሰን ካርታ ዛሬም ድረስ የላቸውም። ለምን? መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው።

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ይሄንን መረጃ ያገኘው ከዓመት በፊት ነበር። ጉዳዩን ለመከታተልም በግል ጉዳይ ምክንያት ሳልችል ቀረሁ። ከዓመት በኋላ ዕድሉን አግኝቻለሁ። በመሆኑም ይህንን ጥያቄ በመያዝም ወደ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አመራሁ። ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የባለሥልጣኑን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታን ሳነጋግር በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የማይንቀሳቀስ ቅርስ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወደሆኑት ወይዘሮ ፀሐይ እሸቴ መሩኝ። ወይዘሮ ፀሐይም በሙሉ ፈቃደኝነት መረጃውን ሰጥተውኛል።

በወይዘሮ ፀሐይ ማብራሪያ መሠረት ቅርሶችን የምንከልለው ያሉንን ቅርሶች ወይንም ሀብቶች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ነው። በተለይ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሆኑ ቅርሶች የራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ አላቸው። እ.አ.አ በ1972 የተፈረመ ዓለም አቀፍ ስምምነት አለ። ይህ ስምምነትም የማስፈጸሚያ መመሪያ አለው። በመመሪያው ውስጥ ደግሞ ዝርዝር ነገሮች አሉ። ከእነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ የወሰን ማካለል አንዱ ነው።

ቅርሶች ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆነው መቀጠል ካለባቸው ከዓለም አቀፉ ስምምነቶች አኳያ መመለስ አለባቸው። ይሄንን የሚጠይቀው ደግሞ ለቅርሶቹ እውቅና የሰጠው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ነው። ስለዚህ ለእዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እነዚህን ቅርሶችም ሆኑ ሌሎች ዓለም አቀፍ ቅርሶችን መከለል አስፈላጊ ነው።Lalibela-rockhewn-churches.jpg

ከዚህ ተነስተን የፋሲል ግቢና ሌሎች መካነ ቅርሶች፣ ላሊበላን፣ አክሱምንና ጢያን ለመከለል ነሐሴ 2004 ዓ.ም ወደ ስፍራው ሄደን ሥራውን ለመስራት ሞክረናል። ሥራው ሙያን የሚጠይቅ ስለሆነ የካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ ባለሙያዎችም በቦታው መገኘት ሥራው በአግባቡ ተከናውኖ ነበር። ከዚያ መልስም በስፍራው የተሰበሰበው መረጃ ወይንም ክለላው በአዋጅ መልክ እንዲወጣ ጉዳዩ ለሚመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላከ። ምክር ቤቱ ግን በክለላው ላይ የየክልሎቹ ነዋሪዎች ተወያይተው በመረጃው ላይ መስማማታቸውን የሚገልጽ መረጃ እንፈልጋለን አለን። ስለዚህ እንደገና ወደ ክልሎቹ መወረድ ነበረበትና ኅብረተሰቡን እንዲያወያዩ መረጃው ለክልሎች ተላከላቸው።

ተመልሶ ሲሄድ ግን ጥያቄ አስነስቷል። በተለይ በአማራ ክልል በሚገኙት የላሊበላና የፋሲል ግቢ በክለላው ላይ ጥያቄዎች በመነሳቱ ክለላው ሊጓተት ችሏል። የአክሱምና ጢያ ግን ምንም ችግር አልታየባቸውም። የክልሉ አስተዳደር ፈርሞና አጽድቆ መረጃውን ልኮልናል። የአማራ ክልል ግን ቅርሶቹ የሚገኙት በከተሞች አካባቢ በመሆኑ ሲቀጥልም ከተሞቹ በእድገት ላይ በመሆናቸው ክልሉ የግድ ኅብረተሰቡን ማነጋገር ነበረበት። ያንን ሲያደርጉ ደግሞ ኅብረተሰቡ የተሠራውን ሥራ አናውቀውም የሚል ምላሽ ሰጣቸው።

በዚህ መንገድ ሂደቱ ቀጥሎ በተመሳሳይ ከካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ ጋር በመሆን በየካቲት ወር 2006 ዓ.ም ወደ ቦታው በመሄድ እንደገና የዳግም ክለላ ስራ ተሠራ። በዚህኛው የክለላ ሥራ ላይ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎችም እንደነበሩ መረጃው ደርሶናል። ነገር ግን ይሄ ሁለተኛው መረጃም ተግባራዊ መሆን ስላልቻለ ለሦስተኛ ጊዜ ድንበሩ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት በድጋሚ በዚህ ዓመት ሐምሌ መጀመሪያ አካባቢ ባለሙያዎች ተልከዋል።

«…ኅብረተሰቡን ለማሳመንም ክለላው የተካሄደው ድንበሩን ቀለም በመቀባት ጭምር ነበር። አሁን ቡድኑ ሥራውን ጨርሶ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል። እስከዛሬ ድረስ ብዙ የተሄደበትና ብዙ ጊዜም የፈጀ በመሆኑ እኛ የምንጠብቀው ክልሉ ክለላውን አጽድቆ እንዲልክለን ነው። ከተላከልን መረጃውን ወደ ተወካዮች ምክር ቤት በማድረስ ቅርሶቹን ከሚያስተዳድራቸው አካል ጋር በመሆን አዋጁ ይወጣል።»

ዳይሬክተሯ እንዳሉትም ኅብረተሰቡን ማሳመን የክልሉ ሥራ ነው። እነርሱ ግን ላሊበላ በነበራቸው ቆይታ የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ጠርተውና አወያይተው ተማምነው ተለያይተዋል። «…ነገር ግን መረጃው ጸድቆ እጃችን ካልገባ እርግጠኛ መሆን አንችልም። ጥያቄው በነበረን ጉባኤም የተነሳም አልነበረም። የጎንደርም ቢሆን በተመሳሳይ የሚመለከታቸውን አካላት ጠርተን ግልጽ ያልሆነላቸውን ሁሉ በእግር እየዞርን ተወያይተን ተማምነናል።»

መረጃው ዳግም ባይላክ ወይንም ክለላው አሁንም ፉርሽ ቢሆን ተጠያቂው ማነው? ወይንም በሌላ አነጋገር ቀጣዩ እርምጃችሁ ምን ይሆናል? ብለን የጠየቅናቸው ወይዘሮ ፀሐይ እንዲህ የሚል ምላሽ አላቸው፤ «…ዓለም አቀፍ ቅርሶች የሚተዳደሩበት ሕግ ስላለ በዚያ የሚታይ ይመስለኛል። የበላይ አመራሩ ሊሄድበትም ይችላል። ውሳኔውን ከእኔ በላይ ያሉ አመራሮች የሚወስኑት ይሆናል…።» Lalibela rockhewn churches

ቅርሶቹ የሚገኙበት የአማራ ክልልን በዚህ ዙሪያ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልናል። በክልሉ የባህል፣ ቱሪዝምና ፓርኮች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ዋጋው ኃይሉ በቅርሶቹ ክለላ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ እንዲህ ገልጸውታል።

አቶ ዋጋው ሂደቱ ገና ባይጠናቀቅም አሁን በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል ይላሉ። «…እስካሁን ለመጓተቱም ምክንያቱ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ የተካሄደ ባለመሆኑ፤ እነርሱ ባስጠኑት ማስተር ፕላን መሠረትም የሚሄድ ባለመሆኑ ነው። አሁን ግን ከእነርሱ ጋር በመነጋገርና በመስማማት መንግሥትን ከፍተኛ ወጪ በማይጠይቅ ሁኔታ ኅብረተሰቡንም ከተለያዩ ልማቶች ሊያደናቅፍ በማይችል መልኩ ተሠርቷል። ኅብረተሰቡ ክለላውን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎት ተግባራዊ ሊያደርገው በሚችል መልኩ ላሊበላ ላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይሄንን ስምምነታቸውንም ለክልሉ አስታውቀዋል።

«…በጎንደርም አሁን ያለውን ሁኔታ ተቀብለውታል። ስምምነታቸውን ግን ገና በጽሑፍ አልገለጹም። መጨረሻውን የከተማው ምክርቤት ያሳውቀናል ብለን እንጠብቃለን። አጠቃላይ ሥራውም በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ብለን እናምናለን…»

አቶ ዋጋውን ለሥራው መጓተት ዋናው ምክንያት በእርግጥም ኅብረተሰቡ በክለላው ላይ አለመወያየቱ ከሆነ ያንን ማድረግ ያልቻላችሁት ለምን ይሆን ብለናቸው ነበር። እርሳቸውም «…የሥራው ዋና ተግባር በቅርስ ጥናትና ጥበቃ የተያዘ ስለነበረ ኅብረተሰቡን የማወየያት ሥራም የእነርሱ ሥራ ነበር። የማኔጅመንቱ ነገር የእነርሱ ሥራ ነውና። … ነባራዊ ሁኔታው ነው ያንን ሁኔታ እንዲፈጠር ያደረገው። ሥራው በእኛ ተጀምሮ የሚያልቅ ስላልሆነ ነው እስካሁንም የቆየው…» ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።

አቶ ዋጋው አያይዘውም «…ሥራው እስካሁን የቆየበት ምክንያት ከተጠያቂነት ለመዳንም ሲባል ነው። የጋራ ኃላፊነት ለመውሰድ እንጂ ላለመቀበል ያደረግነው አይደለም። ማን ያስተዳድረዋል? የሚለውም ጥያቄያችን ነበር። አሁን ይህ ጥያቄ በከፊል ተፈትቷል። የጋራ ኃላፊነትና የሥራ ክፍፍል ካለ ችግሩ አይኖርም። ካርታውን በጉጉት የምንጠብቀው እንጂ በስጋት የምናየው አይደለም…»

ሌላው ለክለላው መጓተት በክልሉ ዘንድ የነበሩት ምክንያቶች ወይንም ስጋቶች ካርታው የገበያ ቦታዎችን በመጨመሩ፤ በቅርሱ አካባቢም ከሁለት ፎቅ በላይ ግንባታ ማካሄድ ስለማይፈቀድ የከተሞችን እድገት የሚገታ በመሆኑ፤ ቅርሱን ማን ያስተዳድረዋል የሚሉት በክልሉ ዘንድ የነበሩት ምክንያቶች ወይንም ስጋቶች ነበሩ። እነዚህ ስጋቶችስ በአዲሱ ክለላ ላይ ምን ያህል ተፈትቷል የሚለው የእኛም ጥያቄ ነበር።

አቶ ዋጋውም «…የግንባታ ችግሩንም ሆነ ሌሎችን በተግባር ካላየን ችግሩ ተፈትቷል ማለት አንችልም። የማኔጅመንት ፕላን የሌለው ቅርስ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ አይቀጥልም። ይሄንን እናውቃለን። እየተሠራ ያለውም ይሄው ነው። ይሄንን ደግሞ እኛ የምንፈልገው ነገር ነው። እኛ በማኔጅመንት ፕላን በኩል የሚወሰነውን ለመቀበል ዝግጁ ነን። ይጠቅመናልና…» ብለውናል።

ያም ተባለ ይህ ግን ሁሉንም ወገን የሚያስማማ አንድ ሀቅ አለ። ዓለም እንደ ትንግርት የሚያያቸውና የሚያደንቃቸው እነዚህ ቅርሶች ዛሬ ድረስ የክለላ ስፍራ ወይንም ያንን የሚያሳይ የድንበር ካርታ የሌላቸው መሆኑ አስደንጋጭም ብቻ ሳይሆን አሳዛኝም ጭምር ነው። ይህ ካርታ ባለመዘጋጀቱ ብቻ በቅርሶቹ ላይ ሊደርስ ከሚችለው ጉዳት ባሻገር ከዓለም አቀፍ ቅርስነት የመሰረዝም አደጋ አለውና ጉዳዩን የያዙት አካላት በጋራ መግባባት በአስቸኳይ እልባት ሊሰጡት ይገባል። ሳይቃጠል በቅጠል ነውና።
********
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን

Areaya Getachew (MA) is a public relations expert at a foreign embassy. He studied second degree at Addis Ababa University and was deputy editor in-chief of Addis Zemen newspaper.

more recommended stories