የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ የኃይል መቆራረጥ ችግርን የሚፈታ ‹ቆጣሪ› ማምረት ጀመረ

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ ይገባ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ (ቆጣሪ) ሙሉ ለሙሉ መተካት የሚችል ዘመናዊ ቆጣሪ ማምረት መጀመሩን የኢፌዴሪ ብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች መመረት የጀመረውን ቆጣሪ በማስመልከት ትናንት በሂልተን ሆቴል በሰጡት መግለጫ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያው መመረት የውጭ ምንዛሪን የሚያስቀርና የኃይል መቆራረጥ ችግርን የሚፈታ መሆኑን አስረድተዋል።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ ቆጣሪው ፍትሐዊ የኃይል ሥርጭት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ያለው ሲሆን፣ እስካሁን ይሰራበት ከነበረው ቴክኖሎጂ በተሻለ ሁኔታ መስራት የሚችልና የወደፊቱን የቴክኖሎጂ ዕድገት ታሳቢ ያደረገ ነው።FDRE Metals and Engineering Corporation

በአንድ አካባቢ መብራት እንዲጠፋ የሚያስገድድ ችግር ሲያጋጥም ወይም የቴክኒክ ብልሽት ሲከሰት በአካባቢው ላይ አስፈላጊ የሆነ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል። ኢነርጂ ሜትሩ ከንድፍ እስከ ምርት ድረስ ሙሉ በሙሉ በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽንና በሥሩ ባሉ ተቋማት አማካኝነት የተፈበረከ ነው።

«የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያው የውጭ ምንዛሬን በከፍተኛ ደረጃ ያስቀራል» ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን ከ1ሺ 200 ኢነርጂሜትሮችን የማምረት ብቃት ያለው በመሆኑ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና በዕድገትና ትራንስፎ ርሜሽን እቅዱ በኃይል አቅርቦት ረገድ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አስታውቀዋል።

ቆጣሪው የተሠራው በአገር ውስጥ ሶፍትዌር በመሆኑ ለደህንነት አስጊ እንደማይሆን የተናገሩት ብርጋዴር ጄኔራሉ፣ ሶፍትዌሩን በተፈለገው ቦታ ላይ መጠቀምና መዝጋት የሚያስችልና ተጠቃሚዎች ምን ያህል ኃይል እንደተጠቀሙ የሚያሳይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኮርፖሬሽኑ የሃይ-ቴክ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ በሪሁ ግደይ እንደገለፁት፣ ቆጣሪው ዘመናዊና አገሪቷ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍ እንዲሁም ለነባርና ለአዳዲስ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆን ነው። ቆጣሪዎቹ በቴክኖሎጂ የተገናኙና እርስ በርሳቸው የሚናበቡ በመሆናቸውም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ በማስቀረት ፍትሐዊ አቅርቦት እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን ሻለቃ በሪሁን አመልክተዋል።

በብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የኃይል ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ አሰፋ ዮሐንስ እንዳስታወቁት፣ ቆጣሪው በአገር ሀብትና በአገር ውስጥ ባለሙያዎች መሠራቱ የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባትና ወጪን ለመቀነስ የሚያስችል ሲሆን፣ ብልሽት ቢያጋጥመው እንኳን በቀላሉ ሊጠገን የሚችል ነው። የኢነርጂ ስርቆትን የሚከላከልና ብክነትንም የሚቀንስ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋየር ቢዝነስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቢትወደድ ገብረሀሊፍ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ስማርት ኢነርጂሜትሩ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚወስድ በመሆኑ የኢነርጂ ብክነትን ይቀንሳል። የሰው ንክኪ በሚኖርበት ጊዜ ራሱን የሚቆጣጠር በመሆኑ ከአደጋ ስጋት የፀዳና ኋላ ቀር አሰራርን የሚያስቀር ነው።

እንደ አቶ ቢትወደድ ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ከፍተኛ የቆጣሪ ፍላጎት በመኖሩ አገር ውስጥ መመረት መጀመሩ ችግሩን ያቃልላል። ቆጣሪው የጥራት ደረጃውን ጠብቆ በመሰራቱም ከፍተኛና ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችን በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል።

በብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የሃይ-ቴክ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ የሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል ቆጣሪው «አይ ቲ ፕላስ ስማርት ኢነርጂ ሜትር» የሚባል ሲሆን የወደፊቱን የቴክኖሎጂ ዕድገት ታሳቢ ያደረገና በርቀት መቆጣጠሪያ አማካኝነት ከማዕከል ጣቢያ ጋር የሚገናኝ መሆኑም ተገልጿል።

********
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን – ነሐሴ 16/2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories