የደመወዝ ጭማሪ እንደአጀንዳ | አህያውን ፈርቶ …

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ ስለመንግስት ሰራተኞችና ጡረተኞች የደመወዝ ጭማሪ ሐምሌ 26/2006 በሰጡት መግለጫ እንደታወቀው የመንግስት ሰራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን በፊት ከነበረበት 420ብር ወደ 615ብር አድጓል፡፡ ከፍተኛው የደመወዝ መጠን ደግሞ በፊት ከነበረበት 4,434ብር ወደ 5,897ብር አድጓል፡፡ ይህ እንግዲህ በቅደም ተከተሉ የ46በመቶና የ33በመቶ ጭማሪ ነው፡፡ ዝቅተኛ የጡረታ ክፍያ በፊት ከነበረበት 294ብር በ71በመቶ አድጎ 530ብር ደርሷል፡፡ የደመወዝ ጭማሪው ሲወራለት ከሰነበተው ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ ነው፡፡

ማህበራዊ ድረ ገፆችን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲወራ የነበረው የደመወዝ ጭማሪ ከ76በመቶ እስከ 129በመቶ ነበር፡፡ ይህ አሁን ካለው እውነታ ጋር እጅግ የተራራቀ የድረ ገፆችና የግል መገናኛ ብዙሃን ዘገባ በግልፅ የሚታዩ ሁለት አቢይ ችግሮችን ፈጥሯል፡፡ አንደኛ ስግብግብ ነጋዴዎች ገና ደመወዙ ሰራተኛው እጅ ከመድረሱ በፊት በሸቀጦችና በአገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውና ጭማሬያቸውም የተጋነነውን የደመወዝ ጭማሪ መጠን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው የመንግስት ሰራተኛው ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪን በጉጉት እንዲጠብቅ በማድረግ አሁን የተደረገውን ጭማሪ ፋይዳ ዝቅ ብሎ እንዲታይ ማድረጉ ነው፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት የእነዚህ ሁለት አቢይ ችግሮች ፈጣሪ ይህን ሀሰተኛ ዘገባ ያራገቡ መገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡ ነገር ግን የደመወዝ ጭማሪው ይፋ ከሆነ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች የሚወጡ ፅሁፎችና የሚሰጡ አስተያየቶች መንግስትን ለችግሩ ተጠያቂ ለማድረግ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡ ይባስ ብሎ የተደረገውን ጭማሪ ዋጋ በማሳጣት መንግስት ለሰራተኞቹ ደንታ እንደሌለው አድርጎ በመሳል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረጉ መጣጣሮች አሉ፡፡ ይሄ ለእኔ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ሆኖብኛል፡፡ የመገናኛ ብዙሃኑ ተጠያቂ ያደረኩበትን ምክንያት ከላይ ስለገለፅኩ መንግስት ለምን ተወቃሽ አይደለም እንዳልኩ ላብራራ፡፡ Ethiopia salary increment table

በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ በጀት አመት ለሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ያስታወቁት ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ ጠ/ሚ/ሩ የሲቪል ሰርቪስ በዓል ሲከበር ባደረጉት ንግግር መንግስት የሰራተኞችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የደመወዝ ጭማሪን፤ የቤትና የትራንስፖርት አቅርቦትን አቀናጅቶ እርምጃ እንደሚወስድ ገልፀዋል፡፡ በወቅቱ ስለደመወዝ ጭማሪው መጠን ምንም አላሉም፡፡ በተመሳሳይ ጠ/ሚ/ሩ በቅርቡ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የደመወዝ ጭማሪው የዋጋ ግሽበትን በማያስከትል መልኩ እንደሚፈፀም ከማብራራት ባለፈ ስለምጣኔው የተናገሩት ነገር የለም፡፡

ሌላው መጠቀስ ያለበት የመንግስት ኮሚዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ያወጣው መግለጫ ነው፡፡ ፅ/ቤቱ “ለ2007 ከተመደበው አገራዊ በጀት ላይ የአገሪቱን አጠቃላይ እድገትና የቀጣይ እድገት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ትርጉም ያለው የደመወዝ ጭማሪ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ወስኗል” ብሏል፡፡ በዚህ አረፍተ ነገር ውስጥ ያለው ‘ትርጉም ያለው’ የሚል ሀረግ ስንት ወይም ምን ማለት ነው? የሚለው እንደሰዉ /subjective/ አረዳድ የሚወሰን ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን የጭማሬውን መጠን ተገልጧል የሚል ክርክር የሚያስነሳ አይደለም፡፡

መንግስት ምጣኔውን አለማሳወቅ ብቻ ሳይሆን መገናኛ ብዙሃኑ ያዛቡትን መረጃም በወቅቱ አስተባብሏል፡፡ የተሰራጨው መረጃ “ምንጩ የማይታወቅ፤ የተሳሳተና መሰረተ ቢስ” እንደሆነና መንግስት በሁለት ሳምንት ውስጥ ጥናቱን አጠናቆ ይፋ እንደሚያደርግ መግለጫ ሰጥቶበታል፡፡ ስለሆነም መንግስት ቃል ገብቶ ያጓደለው ሁኔታ የለም፡፡ በርግጥ ይህ መግለጫም የሀሰት ዘገባውን የመቀልበስና የህዝቡን አመለካከት የመቀየር ጥንካሬ ነበረው ወይ? የሚለው አከራካሪ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ጭማሬው በራሱ አነስተኛ የሚባል አይደለም፡፡ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ሰራተኞች ላሏት ኢትዮጵያ ቀርቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ተቀጣሪዎች ባለበት አገር እንኳን ከ33በመቶ እስከ 46በመቶ የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ የተለመደ አይደለም፡፡ ከሶስት አመት በፊት እዚሁ አገራችን ከተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ጋር እንኳን ሲነፃፀር የአሁኑ የተሻለ መሆኑን ለመረዳት በ2003 የተደረገው ጭማሪ ከ35በመቶ እስከ 39በመቶ እንደነበር ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በ2003ቱ ለግማሽ አመቱ ለጭማሪው 4.7ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት የጠየቀ ሲሆን የአሁን ደግሞ 10.3 ቢሊዮን ብር ነው የጠየቀው፡፡ ስለሆነም የደመወዝ ጭማሪውን ፋይዳ የሚያሳንስና መንግስትን ለሰራተኞቹ ባለማሰብ የሚያስተቸው ተጨባጭ ምክንያት የለም፡፡

መንግስት የደመወዝ ጭማሪ ሲያደርግ የመክፈል አቅሙን ግምት ውስጥ ማስገባቱ የማይቀር ነው፡፡ በዚህ አመት ለሰራተኞች ክፍያ የተጨመረው ገንዘብ መጠን ብቻ /10.3 ቢሊዮን ብር/ ከ1987ዓ.ም የአገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ በጀት ጋር እኩል መሆኑን ለተገነዘበ የመንግስት የመክፈል አቅም በፍጥነት እያደገ መሄዱን ለመገንዘብ አያዳግተውም፡፡ ሆኖም ይህ አቅም ሌላ ተጨማሪ አገራዊ አቅም በሚፈጥር መስክ ኢንቨስት መደረግ ያለበት እንጂ በአስተዳደራዊ ወጪዎች መሟጠጥ ያለበት አይደለም፡፡ ስለሆነም መንግስት በጥናት ላይ ተመስርቶ የመክፈል አቅሙንና የሰራተኞቹን የኑሮ ሁኔታ ያጣጣመ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉ ዘለቄታዊ አዋጭነት ያለው ነው፡፡

እዚህ ላይ አጠቃላይ የመንግስት ሰራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ማየት ይገባል፡፡ አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ሰራተኛው ይበልጥ ተጠቂ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በምርት ስራ ላይ ያልተሳተፈ፤ ቢሳተፍም እንኳን የምርቱ ቀጥተኛ ባለቤት ያልሆነ የህዝብ አገልጋይ በመሆኑ በሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ በየጊዜው የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ሰለባ ሆኗል፡፡ የሚከፈለው ደመወዝም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶቹን ሁሉ የሚያሟላ አይደለም፡፡ ቢሆኖም ይህን ችግር በተጋነነ የደመወዝ ጭማሪ ብቻ ለመፍታት መሞከር በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የገንዘብ መጠን በማናር በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ አስተዋፆ ይኖረዋል፡፡ በአቅርቦት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ባልመጣበት ሁኔታ ከአሁኑ 10ቢሊዮን ብር በተጨማሪ ሌሎች ቢሊዮኖች ተዳምረው ገበያው ውስጥ ሲረጩ በተለይ በመንግስት ሰራተኛው በሚፈለጉ መሰረታዊ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ የመንግስትን ተቀጣሪዎችን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም የህብረተሰብ ክፍል ይጎዳል፡፡

ይልቁንም ይህን መፍታት የሚቻለው በሰራተኛው ላይ ጫና የሚፈጥሩ ችግሮችን ለይቶ የተቀናጀ መፍትሄ በማበጀት ነው፡፡ በተለይ የሰራተኛውን 15በመቶ በምትይዘው አዲስ አበባ በዚህ ረገድ የሚስተዋሉት ችግሮች የትራንስፖርትና የመኖሪያ ቤት ናቸው፡፡ አቶ ሱፍያን በመግለጫቸው ከመጭው መስከረም ወር ጀምሮ 420 ያህል መኪናዎች በአዲስ አበባ ተመድበው በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓቶች ሁሉንም የመንግስት ሰራተኞች ያገለግላሉ ብለዋል፡፡ የቤት አቅርቦትን በተመለከተም የመንግስት ሰራተኞች በጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ውስጥ የ20በመቶ ቅድሚያ እድል እንዲያገኙ ሆኗል፡፡ እዚህ ላይ በአንድ በኩል የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ማፋጠን፤ በሌላ በኩል ሌሎች አማራጮችንም ማማተርን ይጠይቃል፡፡ ለአብነት ተቋማት ቤት እየገነቡ ለሰራተኞቻቸው በብድር የሚሰጡበትንና ሰራተኞችም ተደራጅተው ቤት መገንባት የሚችሉበትን አማራጮች መቀየስ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በሰራተኞች ተቆራጭ ታክስ ምጣኔ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የተጀመረውን ጥናት አጠናቆ መተግበር፤ የጅምላ ንግድ ተቋሞችን በማቋቋምና ተደራሽነት በማስፋት ረገድ የተጀመረውን ስራ ዳር ማድረስ ይገባል፡፡ በተለይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ መንግስት የጀመረውን እርምጃ ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ አንፃር በህግ ክፍተትና በሃላፊነት ወሰን መደበላለቅ ተተብትቦ የሚጠበቅበት አገልግሎት እየተወጣ ያልሆነውን የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣንን ችግሮች በመቅረፍ ጥርስ እንዲያበቅል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሸማቾች በተናጠልም ይሁን ተደራጅተው ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን መታገል የሚችሉት ባለስልጣኑ ሲደግፋቸው ነውና፡፡

በመጨረሻም ከላይ ላነሳኋቸው ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ምንጭ ስለሆኑት ድረ ገፆችና የግል መገናኛ ብዙሃን ጥቂት ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የፕሬስ ነፃነት ፍፁማዊ መብት አይደለም /Freedom of the press is not an absolute right/፡፡ የፕረስ ነፃነት በህግ ገደብ የሚጣልበትና በባለቤቶቹም ላይ ሃላፊነትን የሚጥል ነው፡፡ ይህም ከሀሰተኛና በህብረተሰብ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉ ዘገባዎች ራስን ማቀብን ያካትታል፡፡ በኢፌዴሪ የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ላይ መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡት ዘገባ ትክክለኛ ካልሆነ እርማት ወይም መልስ የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል ተብሏል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትም ፕሬስ ገደብ ሊጣልበት የሚገባበት ሁኔታዎች እንዳሉ አስቀጧል፡፡

ይህን ሀሰተኛ ዘገባ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ቢቀባበሉትም ሁሉም ምንጭ አድርገው የጠቀሱት ግን ‘ካፒታል ኢትዮጵያ’ን ነው፡፡ ሌሎቹ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ ምንጫቸውን እስካስቀመጡ ድረስ ቢያንስ በህግ አግባብ ተጠያቂ ላይሆኑ እንደሚችሉ እረዳለሁ፡፡ ይህን መረጃ አስቀድሞ በማውጣት ለሌሎች መገናኛ ብዙሃን ምንጭ የሆነው ‘ካፒታል ኢትዮጵያ’ ግን የዘገባውን ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሃላፊነት አለበት፡፡ ምንአልባት ምንጩ ከመንግስት ተቋም የወጣ የጥናት ሰነድ ከሆነም ይህን ይፋዊ ያልሆነ ሰነድ አሳልፎ የሰጠ አካል ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ ይህም በአስተዳደራዊ መልኩ ሳይሆን ሌሎችንም በሚያስተምር አግባብ በህግ ፊት መፈፀም ይኖርበታል፡፡

ካልሆነ ለዋጋ ንረት የዳረገንን እና የደመወዝ ጭማሪውን ፋይዳ እንዳናይ አይናችንን የከለለውን የተዛባ መረጃ ያሰራጨውን መገናኛ ብዙሃን ትተን የሰራተኞችን ችግር በተቀናጀ ሁኔታ ለመፍታት በመስራት ላይ ያለውን መንግስት ጥረት ማጣጣል አህያውን ፈርቶ እንደሚባለው ነው የሚሆነው፡፡

*****

Kebede Kassa

more recommended stories