ኃይለማርያም ደሳለኝ:- ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ተቃርባለች

ኢትዮጵያ በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ራሷን ለመቻል መቃረቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ስታዲዬም በተዘጋጀው 23ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል የማጠቃለያ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ተግባራዊ በመደረጋቸው ስኬታማ መሆን ተችሏል። PM Hailemariam Desalegn

ከ3 አመታት በፊት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በ60 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በድርቅ ክፉኛ ተመቶ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ያለአንዳች መሰናክል ችግሩን ማለፍ መቻሏን ገልጸዋል።

ከ23 አመታት አገሪቱ ከነበረችበት ከፍተኛ ተመጽዋችነት በመነሳት ደረጃ በደረጃ ምርትና ምርታማነትን በማሳደጓ በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ በአመት ከ250 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ምርት ማመረት መቻሏንም ጠቅሰዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል መቃረቧን የሚያብስር ስለመሆኑ ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አርሶ አደሩ ከፍተኛ ገቢ ወደሚያስገኙ ምርቶች መሸጋገሩንና በቀጣይም ጠንካራ አገር በቀል ባለሃብቶችን በማፍራት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል።

ለሁለት አስርት ዓመታት በተካሄደው አልህ አስጨራሽ ትግልም አገሪቱ በዓለም ህብረተሰብ ዘንድ ትታወቅበት ከነበረው ርሃብና ቁስቁልና በመውጣት ከኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላትም የርሃብተኝነት ምሳሌ መሆኗ እንዲፋቅ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ይህም ለኢትዮጵያውያን ታላቅ እመርታ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በቀጣይም ኢትዮጵያ ከሚፈለገው የምርታማነትና የብልፅግና ደረጃ ለመድረስና ግሎባላይዜሽን የደቀነውን የውድድር ፈተና በብቃት ለማለፍ  ሁሉም ዜጋ ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩሉን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ከ23 አመታት በፊት በግለሰብ ደረጀ ከ500 ሺ ብር ካፒታል በላይ ማንቀሳቀስ የማይቻልበት ወቅት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ከግንቦት ድል በኃላ በከተማም ሆነ በገጠር ብዙ ሚሊዬነር ባለሃብቶችን ማፍራት እንደተቻለም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት በትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በማስወገድ ወጣቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣በፈጠራ በእውቀትና ክህሎት የታንጹና ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማድረግ ዋነኛው የመንግስት ትኩረት ነው።

በኢትዮጵያ ህዳሴ ዙሪያ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት፣መገናኛ ብዙሐን፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች ተቋማት የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በ23 አመታት ጊዜ ውስጥ የተገኙ ስኬቶችን ማጠጣም ብቻ ሳይሆን በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመፍታትም  ከምንጊዜውም በላይ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።

አቶ ሃይለማሪያም በንግግራቸው እንደጠቀሱት በቀጣዩ አመት የሚካሄደው 5ኛው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊ፣ነጻና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግስት በሚቻለው አቅም ሁሉ ርብርብ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የምታደርገውን ግስጋሴ በርካታ አገራት አድናቆት እየቸሩት መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በኢኮኖሚ፣በማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰኮች እንዲስተካከሉ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መንግስት የተለያዩ ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የተጠናከረ ስራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲዬም በተዘጋጀው 23ኛው የግንቦት 20 ማጠቃለያ ልዩ ስነ-ስርዓት ላይ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የበርካታ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በ10ሺዎች የሚቆጠር  የከተማዋ ነዋሪ ህዝብ ተገኝቷል።
*********
ምንጭ፡- ኢዜአ፣ ግንቦት 20፣ 2006 – “
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል ተቃርባለች

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories