ከታሪክ መጓተት ወጥተን ድህነትን እንዋጋ

(ኢብሳ ነመራ)

የዓመት እኩሌታ ወይም ስድስተኛው ወር – የካቲት በኢትዮጵያ ታሪክ ወሳኝ የሆኑ ሁነቶች የተስተናገዱበት ወር ነው። ከ118 ዓመት በፊት የተከናወነው ከኢትዮጵያም አልፎ በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የአድዋ ድል የየካቲት ወር ሁነት ነው። ከአርባ ዓመት በፊት በአገሪቱ ለክፍለ ዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረው ጨቋኝ ዘውዳዊ ሥርዓት ግብዓተ መሬት እንዲፈፀም ያደረገው አብዮት የተቀጣጠለው በየካቲት ወር ነበር፤ የካቲት 1966 ዓ.ም። ዘውዳዊውን ሥርዓት የተካው የወታደራዊ ቡድን አምባገነናዊ የደርግ ሥርዓትን ለመደምሰስ በተደረገው መራራ ትግል ውስጥ የጎላ ድርሻ የነበረው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)የተመሰረተውም በየካቲት ወር ነበር፣ የካቲት 11/1967 ዓ/ም። እነዚህ የየካቲት ትሩፋቶች ለዘለዓለም ሲዘክሩና ሲነገሩ የሚኖሩ አንኳር ታሪካዊ ሁነቶች ናቸው። ይህን ስል፣ የመገጣጠሙ ጉዳይ አስገርሞኝ እንጂ ለየካቲት ወር መለኮታዊ ኃይል ለመስጠት አስቤ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።

ያም ሆነ ይህ የእዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ የካቲት ወር ማተት ሳይሆን፣ በዚሁ ወር ከ118 ዓመት በፊት፣ ማለትም የካቲት 23/1888 ዓ.ም ኢትዮጵያ በኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ላይ የተቀዳጀችው የአድዋ ድልና በዚህ ድል ውስጥ ተጠቃሽ በሆኑት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዙሪያ የሚታየውን የታሪክ መጓተት የሚመለከቱ ጉዳዮችን ማንሳት ነው።

ከ118 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአፄ ምኒልክ መሪነት በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ ድንበር ጥሶ ወደ ውስጥ የዘለቀውን የላቀ የጦር መሣሪያ ቴክኖሎጂ የታጠቀና የሠለጠነ ሃያ ሺህ ያህል የኢጣሊያ ጦር በአድዋ ጦርነት ላይ ድል መትቷል። ይህ ድል ተራ ድል አልነበረም፤ ልዩ ድል ነው። ልዩ ድል የሚያደርገው ባህሪ በወቅቱ የላቀ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ የነበሩት አውሮፓውያን ጥቁር አፍሪካውያን ላይ ወረራ በመፈፀም አገር መቀራመት የጀመሩበትና አይበገሬ ሆነው በሚታዩበት ወቅት የተገኘ ከመሆኑ የመነጨ ነው።

የአድዋ ድል ጥቁሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይበገሬ ይመስሉ የነበሩት አውሮፓውያን ወራሪዎች ሊሸነፉ እንደሚችሉ ያረጋገጠ ነበር። በዚህም ምክንያት የአውሮፓ መንግሥታት በቅኝ ግዛትነት ተቀራምተው የያዙዋቸው የአፍሪካ፣ የእሲያና ደቡብ አሜሪካ አገራት ጥቁርና ሌሎች ባለቀለም ሕዝቦች ዘንድ «ቅኝ ገዢ አውሮፓውያንን ማሸነፍ ይቻላል» የሚል መነቃቃት ፈጥሯል። በዚህ ምክንያት ድሉ የኢትዮጵያውያን ድል ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰብ ነው። የአድዋን ድል ተራ ያልሆነ ልዩ ድል የሚያደርገው ዋነኛ ምክንያት ይህ ነው።

ኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈፀመው የኢጣሊያን ሠራዊት የመጨረሻውን መራራ የሽንፈት ፅዋ በጨለጠበት የአድዋ ውጊያ ላይ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ የሚኖሩ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተሳትፈዋል። በመሆኑም ድሉ የመላው ኢትዮጵያውያን ድል ነው። ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸውና ለመብታቸው ያላቸውን ቀናኢነት ያረጋገጡበት ድል ነው። ተገዢነትን ጭቆናን እንደሚጠየፉ ያሳዩበት ድል ነው። በእዚህ የኢትዮጵያውያን ድል ውስጥ ሕዝቡን አንቀሳቅሰው ባለድል ሊሆን በሚችልበት ሁኔታ የመሩት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ትልቅ ድርሻ አላቸው። ስለዚሀ ከአድዋ ድል ጋር ስማቸው ሲዘከር ይኖራል፤ ይህም ተገቢ ብቻ ሳይሆን የሚያኮራ ነው።

ከአፄ ምኒልክ ጋር በተያያዘ ሌላም የታሪክ ገፅታ አለ። ይህም ንጉሠ ነገሥቱ የሀገሪቱን ደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ አካባቢዎች ለመቆጣጠር ያካሄዱት መስፋፋት ነው። ይህ የአፄ ምኒልክ የግዛት ማስፋት እርምጃ በዲፕሎማሲ ማስገበርን የሚያጠቃልል ቢሆንም በሕዝብ ላይ ከፍተኛ እልቂት ያስከተሉ ጦርነቶችም ተካሂደውበታል። ዘግናኝ እልቂት ካስከተሉት በርካታ የመስፋፋት ጦርነቶች መካከል በሐረር ጨለንቆ የአፄ ምኒልክ ጦር፣ ከኦሮሞ ሐረሪና ሶማሌዎች ጋር ያደረገው ውጊያ እንዲሁም የአርሲው ጦርነት ተጠቃሾች ናቸው።

እነዚህ የአፄ የምኒልክ ግዛት የማስፋፋት ጦርነቶች በተጠቂዎቹ ታሪክ ውስጥ ሊረሳ የማይችል ዘግናኝ እልቂት ምክንያት ከመሆናቸው ባሻገር የኢትዮጵያ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ለብሔራዊ ጭቆና ዳርጓቸዋል። በምኒልክ ግዛት የማስፋፋት እርምጃ የንጉሠ ነገሥቱ የግዛት ወሰን ውስጥ የተካተቱት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከብሔራዊ ጭቆናው ጋር ተያይዞ ዝንተ ዓለም ዘርማንዘራቸው በኖረበት መሬት ላይ የመሬት ባለቤትነት መብታቸውን ተነጥቀው ለገባርነት ተዳርገዋል፣ ለኢኮኖሚ ጭቆና ምክንያት ሆኗል ማለት ነው።

እነዚህ በምኒልክ የግዛት መስፋፋት ለብሄራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና የተዳረጉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ግን የአድዋ ድል ባለቤቶችም ናቸው። በአድዋ ጦርነት በአውሮፓ ወራሪ ላይ የተቀዳጁት አኩሪ ድል ግን ወራሪውን እንዲወጉ መነሻ የሆናቸውን ከጭቆና ነፃ መሆን አላረጋገጠላቸውም። በሌላ አነጋገር፣ የአድዋ ድል በራሳቸው ወገን ከመጨቆን ነፃ አላደረጋቸውም። ይህ የአፄ ምኒልክ እርምጃ በቅሬታ ሲታወስ የሚኖር አስከፊ የታሪክ ገፅታ ፈጥሯል። ይህ አስከፊ የታሪክ ገፅታ ነባራዊ እውነታ ነው። የአፄ ምኒልክ ታሪክ ሁለት ገፅታ ነው ያለው ማለት ነው፤ ደግና ክፉ።

አፄ ምኒልክ በግዛት ማስፋፋት ያበጇት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ብሔራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ከምኒሊክ ሕልፈትም በኋላ በተኪው ንጉሠ ነገሥታዊ ዘውዳዊ ሥርዓት ውስጥ ቀጠለ። ለአኩሪው የአድዋ ድል ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች «መብትና ነፃነቴን አሳልፌ አልሰጥም» የሚል ስሜትም በጭቆናው ሳይደፈጠጥ ቀጠለ። በየአካባቢው ባልተደራጀ መልክ በዘውዳዊው ሥርዓት ላይ የተነሱ «የገበሬ አመፆች» ከብሔራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ለመላቀቅ ያለ ፍላጎትና የትግል ተነሳሽነት ውጤቶች ናቸው።

ይህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከብሔራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ለመውጣት የሚያካሂዱት ትግል እያደረ ከእያንዳንዱ ብሄር የተውጣጡ ልሂቃን በሚገኙባቸው የትምህርት ተቋማት ውስጥ መልክ እየያዙ መጡ። በ1966 የካቲት የንጉሠ ነገሥቱን ዘውዳዊ ሥርዓት ለመገርሰስ ያበቃው በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልሂቃን ቅርፅ ይዞ የወጣው ትግል ነው። የዘውዳዊው ስርዓት ውድቀት ግን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ፍፁም ከጭቆና ነፃ አላደረገም። የንጉሠ ነገሥቱ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ ሥርዓት የተካው የወታደራዊ ቡድን ፈላጭ ቆራጭ የደርግ ሥርዓት በወቅቱ 85 በመቶ ገደማ የሚሆነው የኢትዮጵያ አርሶ አደር በገዛ አገሩ ላይ ዝንተ ዓለም አጥቶት የነበረውን የባለመሬትነት መብት «በመሬት ለአራሹ» አዋጅ በማስከበር የኢኮኖሚ ጭቆናውን ለማቃለል ቢሞክርም ብሔራዊ ጭቆናውን ግን ችላ ብሎ ተወው።

ለመብትና ለነፃነታቸው ቀናኢ የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘውዳዊውን ሥርዓት ሲያገለግል በነበረው ወታደራዊ ቡድን አምባገነን ሥርዓት እንዲቀጥል የተደረገውን ብሔራዊ ጭቆና፣ እንዲሁም የመሬት ባለቤት ቢሆንም በሌላ መልኩ የተጫነባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ለመጣል መታገላቸውን ቀጠሉ። በወታደራዊው ደርግ የሥልጣን ዘመን የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ በብሔር የተደራጁ ከሃያ በላይ የነፃነት ግንባሮች የእዚህ ማሳያ ናቸው። የራሳቸው ባህልና ቋንቋ ባለቤት የሆኑና በአንድ መልከአምድራዊ ወሰን ውስጥ የሚኖሩ ልዩ የማንነት መገለጫ ያላቸው የኢትየጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ፍትሕን ጨምሮ የመንግሥት አገልግሎት በቋንቋቸው እንዲያገኙ፣ ልጆቻቸው በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ ባህላቸውና ታሪካቸውን እንዲጎለብት በአጠቃላይ ማንነታቸው ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቶት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ብሔራዊ ነፃነታቸው ተከብሮ የሚኖሩበት ሥርዓት እንዲመሰረት ነበር የታገሉት።

ከእዚህ ጎን ለጎን ዘውዳዊው ሥርዓት መሬት አልባ አድርጎ ጭኖባቸው የነበረው አኮኖሚያዊ ጭቆና «በመሬት ለአራሹ» አዋጅ ምላሽ ቢሰጠውም፣ አርሶ አደሩ በራሱ መሬት ላይ የሚያገኘው ምርት ላይ ሙሉ በሙሉ የባለቤትነት መብት እንዳይኖረው በማድረግ የተጫነበትን ኢኮኖሚያዊ ጭቆናም ነበር ሲዋጋ የነበረው። በወታደራዊ ደርግ የመንግሥት ሥርዓት አርሶ አደሩ በራሱ መሬት ላይ፣ በራሱ ጉልበት ሠርቶ ካገኘው ምርት ላይ፣ የመሬቱን ለምነት፣ የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም የአየር ንብረት ለውጥን ባላገናዘበ ሁኔታ በዘፈቀደ በአይነትና በመጠን ተቆርጦ የሚጣልበትን የሰብል ምርት ከገበያ ዋጋ በታች በሆነ ዋጋ ለመንግሥት የማቅረብ ግዴታ ተጥሎበት ነበር።

እንግዲህ በአፄ ምኒልክ ዘመን የተተከለውን ብሔራዊ ጭቆናና ለይስሙላ ብቻ ማሻሻያ የተደረገበትን የኢኮኖሚ ጭቆና ከላያቸው ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባደረጉት መራራ ትግል የወታደራዊውን ደርግ ሥርዓት ገርስሰው፣ መብትና ነፃነታቸው ወደተረጋገጠበት ስርዓት የሚያሻግራቸውን የአድዋ ድል ደገሙ።አሁን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከብሔራዊና ከማንኛውም አይነት አኮኖሚያዊ ጭቆና ነፃ የሚያደርጋቸውን ሕገ መንግሥት ቀርፀው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የሚኖሩበትን የኢፌዴሪ የመንግሥት ሥርዓት መስርተዋል። በዘውዳዊውና በወታደራዊው የመንግሥት ሥርዓት ተጭኖባቸው የነበረውን ጭቆና ታሪክ ባይረሳውም፣ »«ሞኝ ዘፈኑ አንድ ነው» እንዲሉ፣ ይህን አስከፊ የታሪክ ገፅታ እያስታወሱ ሲያላዝኑ መኖር አይፈልጉም። የለባቸውምም።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ በሆነው ሕገመንግሥት ላይ በመከባበርና በእኩልነት አብሮ ለመኖር የተስማሙበት በበጎ የጋራ ታሪካቸው ላይ ተመስርተው ነው። የአድዋ ድል ከበጎ የጋራ ታሪካቸው መካከል ተጠቃሹ ነው። አስከፊ ገፅታ ያለውን ታሪካቸውን በጋራ በሚኖሩባት ኢትዮጵያ ውስጥ ቂም በመቀስቀስ ለመቃቃርና እርስ በርስ ለመጠራጠር ምክንያት እንዲሆን አይሹም። ሞቶ የተቀበረ ሊመለስ የማይችል ታሪክ በመሆኑ እየቆሰቆሱ የማያያዝ ፍላጎት የላቸውም። ይህ እንደማይጠቅማቸው ያውቃሉ። የእዚህ ዓይነት የታሪክ መጓተት ውስጥ መግባት አይፈልጉም።

ይሁን እንጂ የታሪክ መጓተቱን ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም የሚፈልጉ ወገኖች አሉ። ካለፈ ታሪካችን ውስጥ የተወሰነውን ወገን ቅር ሊያሰኙ የሚችሉትን እየመዘዙ በአንድነት መኖር ያስቻላቸው በጎ የጋራ ታሪክ ላይ ጥላ እንዲያጠላበትና ይህ ሁኔታ ከሚፈጥረው ግጭት የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት የሚፈልጉ አሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ችላ ተብለው ሊታለፉና ምንም ጉዳት የማያስከትሉ ትነኮሳዎችን አጋግለው መዓት የወረደ አስመስለው ተንጫጭተው የሚያንጫጩም አሉ።

ሁለቱም ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥቅም የቆሙ አይደሉም። ከእዚህ ይልቅ ሕዝቡን አቃቅረውና አላትመው ለራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ በመሣሪያነት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እናም ከእነዚህ መሰሪዎች ሴራ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን አንድ ጠላት ብቻ ነው የቀረው፤ ድህነት። በበጎ ታሪኩ ላይ ተመስርቶ በመከባበርና በመቻቻል አብሮ በመኖር ስምምነት ያዋቀረው አንድነት ሰላምን ያረጋግጥለታል። ሰላም ደግሞ የፀረ ድህነት ትግሉ ላይ አተኩሮ ድህነትን በብልጽግና እንዲደፍቅ ያስችለዋል። እናም ከታሪክ መጓተት ወጥተን ብቸኛ የወቅቱ የጋራ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን እንዋጋ።
**********
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን – መጋቢት 2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories