ሰንደቅ ጋዜጣ:- ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በሠነዘሩት አሉባልታ ሊከሰሱ ነው

(ፋኑኤል ክንፉ)

በኢትዮጵያ የነፃ ፕሬስ እድገት፣ በፕሬሱ ላይ በሚታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እና የወደፊት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የሚወያይ የሬዲዮ ፋና ፕሮግራም ላይ እሁድ መጋቢት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ለውይይት ተጋብዘው የነበሩት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ሰንደቅ ጋዜጣን በውይይቱ መካከል ነጥለው በማውጣት በጋዜጣው ላይ ውይይት ይደረግበት ብለው ከመጋበዛቸው ባሻገር ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ባለሃብት ስምን በመጥቀስ ስም እየሰጡ የማሸማቀቅ (Naming and Shaming) ያረጀ ያፈጀ ፖለቲካ በጋዜጣው ላይ ለማሳረፍ እና ባልተረጋገጠ ሰነድ የተቋሙን ስም ለማጥፋት መሞከራቸው ለክስ ምስረታው መነሻ መሆኑን ከተቋሙ የሕግ ክፍል እየተዘጋጀ የሚገኘው የክስ መመስረቻ ሰነድ ያሳያል።

ዶክተር ዳኛቸው በተቋሙ የመመስረቻ ሰነድ ሆነ የንግድ ፈቃድ ስማቸው ባልተገለጸ ግለሰብ ላይ በአደባባይ በማያውቁት መረጃ ሆን ብለው የሰንደቅ ጋዜጣን መልካም ስም ለማጥፋት አሉባልታ ማሰራጨታቸው የወከሉትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲንም ማኅበረሰብ አንገት ያስደፋ መሆኑን አንዳንድ ጉዳዩን የተከታተሉ የዩኒቨርስቲ መምህራን ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

ዝግጅት ክፍላችንም ለዶ/ር ዳኛቸው በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በመደወል ከምን መነሻ ይህን መሰል አስተያየት እንደሰነዘሩ ጠይቀናቸው፤ “ስድባችሁን ብጥቀጥሉ ይሻላል። ሁለት ባርኔጣ አድርግ፣ትንሽ ነው። እኛ ትልቅ ነን። …ተኩሱ፣ እየተኮሳችሁ ነው። ተጋጥመናል፤ ቀጥሉ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በመጨረሻም “የምፈራ መሰላችሁ” ብለው ስልኩ ተቋርጧል።

ከቀና ልቦና ሳይነሱ የግለሰብና የተቋምን ስም ለማጠልሸት መነሳታቸው በነፃ ፕሬስ እድገት ላይ ያላቸውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል፣ የማይመጥናቸው ተግባር መሆኑን አንዳንድ የሬዲዮ ፕሮግራሙን የተከታተሉ የጋዜጣችን አንባቢዎች ባደረሱን የስልክ መልዕክት ገልፀውልናል።
*******
ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ፣ መጋቢት 26/2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories