የቻይና ባንክ ለህዳሴ ግድብ የኃይል ማከፋፈያ-ማሰራጫ መስመር ብድር ለመልቀቅ ተስማማ

(ውድነህ ዘነበ)

የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ከተከፋፈለ በኋላ የውጭ አገር የፋይናንስ ተቋማት ቀደም ሲል የፈቀዱትን ብድር በማቋረጣቸው፣ የተቋረጠውን ብድር ለማስለቀቅ የኮርፖሬሽኑን ኃላፊነት የተረከበው አዲሱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ ፈጽመዋቸው የነበሩ ስምምነቶችን ኢንተርፕራይዙ በማደስ ላይ እንደሚገኝ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ የሚገኙበትን የልዑካን ቡድን፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ በመምራት ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ወደ ቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ ተጉዟል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ከቻይና መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችና ከኢምፖርት ኤክስፖርት (ኤግዚም) ባንክ  ኃላፊዎች ጋር በጉዳዩ  ላይ በመወያየት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዓመት በፊት ተፈርሞ ሳይለቀቅ የቆየው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማከፋፈያና ማሰራጫ መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ብድር እንዲለቀቅ መግባባት ላይ ተደርሷል ተብሏል፡፡

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የማከፋፈያና የማሠራጫ ግንባታ ፕሮጀክት የተፈረመው ስምምነት 1.4 ቢሊዮን ዶላር የሚሸፍን ሲሆን፣ ሥራውን የቻይና ስቴት ግሪድ ኩባንያ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪ በቻይና መንግሥት ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ በመካሄድ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ሁሉ የተቋረጠባቸው ገንዘብ እንደሚለቀቅ ማረጋገጫ የተሰጠ ሲሆን፣ አዲስ የተሾሙት ወ/ሮ አዜብ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበ ፊርማ ለመተካት የፊርማቸውን ናሙና ለኤግዚም ባንክ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

የቻይና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄዱ በርካታ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተሳታፊ ናቸው፡፡ በቻይና ኩባንያዎች የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ በመቋረጡ ምክንያት አለመስተጓጎሉንና የሚያስፈልገውን ወጪ ኩባንያዎቹ ከራሳቸው የገንዘብ ምንጮች እየተጠቀሙ መቆየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ነገር ግን ውስጥ አዋቂዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያዎቹ ከራሳቸው የገንዘብ ምንጭ ለሥራው ለሚያውሉት ወጪ የኢትዮጵያ መንግሥት ወለድ ይከፍላል፡፡

ከቻይና መንግሥት የፋይናንስ ተቋማት በተጨማሪ የአፍሪካ ልማት ባንክና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ዘርፍ ፋይናንስ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህም  የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ መልቀቃቸውን ያቋረጡ በመሆናቸው መንግሥት ከእነዚህ አበዳሪዎች ጋር ያለውን ስምምነት በማደስ ፋይናንሱን ለማስለቀቅ እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት በሚከፈልበት ወቅት አበዳሪዎች  ማብራሪያ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ተከፍሎ የተቋቋሙት ሁለት ኢንተርፕራይዞችን ህልውና በማፅደቁና በዚህ ምክንያትም ፋይናንሶቹ አዲስ ደንበኛቸውን በትክክል እስኪያውቁ ድረስ ገንዘብ መልቀቃቸውን ማቋረጣቸው ይነገራል፡፡ አዲሱ ኢንተርፕራይዝ የፈረሰውን ኮርፖሬሽን ተክቶ እንደሚሠራ ማረጋገጫ በመስጠቱ ምክንያት፣ የቻይና የፋይናንስ ተቋማት የያዙትን ብድር ለመልቀቅ ይሁንታቸውን እንደገለጹ ተጠቁሟል፡፡

*******
* ምንጭ፡- ሪፖርተር  – መጋቢት 10/2006 – ‹‹አዲሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ኢንተርፕራይዝ የተቋረጠውን ብድር ለማስለቀቅ እንቅስቃሴ ጀመረ››

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories