ድሬዳዋ ጨርቃ-ጨርቅ አደጋ ላይ ነው – ልማት ባንክ 5 ግዜ ብድር ከልክሎታል

(ዘላለም ግዛው)

በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘውንና በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰሞኑን ጎብኝቼአለው፡፡ ይህ ፋብሪካ እ.ኤ.እ በ1939 በኢጣሊያኖች ነው የተቋቋመው፡፡ በጉብኝቴ ወቅት በፋብሪካው ውስጥ ጥጥ የሚፈተልበትና የሚቀለምበትን ክፍል አይቻለሁ። በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ኋላቀር የአመራረት ሂደትና እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ የተመረቱ ማሽኖች እንዳሉ ታዝቤያለሁ። በርግጥ ምልከታዬ ፋብሪካው ዕድሜ ጠገብ መሆኑን መስክሮልኛል።

የፋብሪካውን የአሰራር ሂደት ጎብኝቼ ያጠናቀቅኩት የዘመኑን ቴክኖሎጂ የተከተለ አሰራር እንደናፈቀኝ ነው።

የጥንት ዘመን የልብስ አሰራርን ለትውስታ በተንቀሳቃሽ ምስል የተመለከትኩ እንጂ ማሽኖቹ በዚህ ዘመን በሥራ ላይ መኖራቸው አግራሞትን ፈጥሮብኛል። ይሄንን እውነታ የሚመለከቱት በኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀዳሚ በሆነው የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ነው። የፋብሪካው የማምረቻ መሣሪያዎች አርጅተዋል። በምርት ክፍል ውስጥ አዲስ ነው የሚባለው ማምረቻ 33ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ነው። ይህ መሣሪያ አዲስ የተባለውም ከሌሎቹ ዕድሜ ጠገብ ማምረቻዎች ጋር ሲነጻጸር ነው።

በአንፃሩ ፋብሪካው ረጅም ዕድሜን ያስቆጠረ ቢሆንም ጥራት ያለው ምርትም እያመረተ ለውጭ ገበያ ያቀርባል። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ 10 ምርጦች ብሎ ከለያቸው ፋብሪካዎች መካከል የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅም ተመርጦ እንደነበር የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈቃደ ገብረ ሕይወት ያስታውሳሉ።

ሆኖም ግን ይላሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ድርጅቱ ስለገጠመው ችግር ሲያስረዱ ማምረቻ መሣሪያዎቹ አርጅተዋል። በመሆኑም ብዛት ያለው የጨርቃ ጨርቅ ምርት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ አልተ ቻለም። ስለሆነም ማሽኖቹ በዘመናዊ የማምረቻ መሣሪያዎች ሊተኩ ይገባል። አሁን ባለበት ሁኔታ ፋብሪካው አዳዲስ የማምረቻ መሣሪያዎች የመግዛት አቅም የለውም። ያረጁትን ማሽኖች በአዲስ ለመተካት ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልገዋል። የጨርቃጨርቅ ማምረቻ መሣሪያ ዎቹን በአዲስ ለመተካት ከልማት ባንክ ብድር ለማግኘት አምስት ጥናቶች አቅርበን አልተሳካልንም።

አቶ ፈቃደ ባንኩ ብድር የከለከለበትን ምክንያት እንደሚያስረዱት የቀረበው ጥናት አያዋጣም ከሚል መነሻ አይደለም። ጥናቱ አዋጭ መሆኑን አምኖበታል። ነገር ግን ፋብሪካው ያልከፈለው ዕዳ በመኖሩ ምክንያት ነው። ፋብሪካው ወደ ሊዝ እንደዞረ ተበላሽተው የቆሙ ማሽኖችን ለማስጠገን የወሰደውን ብድር እስካሁን አልከፈለም።

እንዲሁም ፋብሪካው በሀገሪቱ የጥጥ እጥረት አጋጥሞ በነበረበት ወቅት መንግሥት ለጥጥ መግዣ የፈቀደውን ብድርም ወስዶል። ነገር ግን ፋብሪካው በወቅቱ በኪሎ57ብር ዋጋ የገዛው ጥጥ ተመርቶ ገበያ ላይ እስኪውል ድረስ የጥጥ ዋጋ ቀንሶ በኪሎ 37 ብር በመድረሱ ምክንያት ፋብሪካው ስድስት ሚሊዮን ብር ከስሯል። በዚህ ሳቢያም ፋብሪካው ለጥጥ መግዣ የወሰደውን ብድር ለመክፈል አልቻለም።

ፋብሪካው ወደ ሊዝ የዞረበት ክፍያም ሙሉ ለሙሉ አልተከፈለም። እንደገናም በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር በማጋጠሙ ምክንያት402ቀናት ሥራ አልሠራም። ፋብሪካው ቀደም ሲል የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸውን ማምረቻ መሣሪያዎችን ለመሸጥ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርቦ እንዳይሸጥ ሳይፈቀድለት ቆይቷል።ይህ አካል «መሸጥ ይችላል ብሎ የፈቀደልን በቅርቡ ነው። እነዚህን ያረጁ የማምረቻ መሣሪያዎች እንደጠየቅን ከሁለት ዓመት በፊት ፈቅደውልን ሸጠን ቢሆን ኖሮ ከ40ሚሊዮን ብር በላይ ይሸጥ ነበር። ይህም ዕዳችንን ለማቃለል ይረዳን ነበር» ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ። እነዚህ ችግሮች ሁሉ ተደማምረው ፋብሪካው ዕዳውን ሳይከፍል እንዲቆይ ተገዷል።

በመሆኑም «ባንኩ ፋብሪካው ቀደም ሲል ያለበትን ብድር ከፍሎ ሳያጠናቅቅ እንደገና አላበድርም» ብሎናል ይላሉ። ፋብሪካው አሁን ብድር ቢያገኝ ቀደም ሲል ያሉበትን ዕዳዎች አዲስ ከሚበደረው ጋር አካትቶ እንደሚከፍል ለባንኩ ቃል ቢገባም ልማት ባንክ የብድር ጥያቄውን ሊቀበለው እንዳልቻለ ነው የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ። አሁንም ለአምስተኛ ጊዜ ያቀረቡትን ጥናት ምላሽ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ነው የሚያስረዱት።

ፋብሪካው በሥሩ አንድ ሺ500 ሠራተኞችን ያስተዳድራል፣ በሀገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ቀዳሚ ቢሆንም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለሠራተኞች አመርቂ የሚባል ደመወዝ ለመክፈል እየተቸገረ ይገኛል። አብዛኞቹ ሠራተኞች ረጅም ዓመት ያገለገሉ በመሆናቸው «የኖርኩበትን ቤት ሳልለውጥ ወይም ጡረታዬን ሳላስከብር አልወጣም» ያሉ ካልሆኑ በስተቀር የባለሙያ ፍልሰትም ለፋብሪካው ህልውና ከፍተኛ ስጋት ሆኗል። ይላሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ።

ፋብሪካው እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉበት መንግሥት ከፋብሪካው በዓመት ሁለት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይጠብቃል። ሆኖም ፋብሪካው የጥጥ ምርት እና የሥራ ማስኬጃ እጥረት አጋጥሞታል። በዚህ ሁኔታ መንግሥት ከፋብሪካው የሚጠብቀውን ገንዘብ ማግኘት አይታሰብም። እናም ፋብሪካው ከገጠመው ችግር እንዲወጣ ከተፈለገ ልማት ባንክ ብድር ሊሰጠው ይገባል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሰድ ዚያድ በበኩላቸው ድሬዳዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ይላሉ። የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡ ኢኮኖሚውን ይጎዳል፣ አምርተው ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያዎች ባቀዱት መሰረት ለማከናወን ይቸገራሉ፣ የማምረቻ መሣሪያዎቻቸው ለጉዳት ይዳረጋሉ፣ ነዋሪውም ውሃ ችግር እንዲያጋጥመው ምክንያት ሆኗል። በከተማዋ የትራንስፎርመርና የቆጣሪ እጥረቶች አሉ። ችግሩን ለመፍታት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላቶች ጋር በመወያየት እየተፈታ ይገኛል።

አቶ አሰድ እንደሚሉት በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከሚልኩ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች መካከል ምርጥ አስር ተብለው ከተለዩትና ከተሸለሙት መካከል የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አንዱ ነበር። ፋብሪካው ዕድሜ ጠገብ ከመሆኑ አኳያ እስካሁን እያመረተ ያለው በቀድሞ ማምረቻ መሣሪያዎቹ ነው። በመሆኑም ፋብሪካው አዲስ ማምረቻ አስገብቶ አሰራሩን በዘመናዊ መልኩ ሊያካሂድ ይገባል። ከባንክ ብድር ለማግኘት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን አስተዳደሩም ያውቀዋል። ሆኖም ችግሩን ለመፍታትም ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቻለውን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ ይሰማናል። ፋብሪካው እንዲያድግ እንፈልጋለን። ምክንያቱም ለዜጎች በርካታ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በአስተዳደሩ በኩልም ቢሆን የሚቻለውን ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው እንዳብራሩት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የኢንዱስትሪዎች ፈተና ሆኗል። በጥናት ለማረጋገጥ እንደተቻለው በአሁኑ ጊዜ ኢንዱስትሪዎች እየሰፉ በመምጣታቸው ምክንያት ከፍተኛ መጠን ያለው የኃይል አቅርቦት ይፈልጋሉ። በኃይል አቅርቦቱ በኩል የገጠመው ችግር የኃይል መቆራረጥ ችግር ብቻ ሳይሆን ኃይል እያለም ማሽን የማስነሳት አቅም ማነስ ጭምር ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማሟላት ኢንዱስትሪ አካባቢዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ቢሆንም የሚፈለገው የኃይል መጠንና ትራንስፎርመሩ ያለው አቅም አለመጣጣም የችግሩ ምንጭ ሆኗል። ይህንን ችግር ለማሻሻል እስከ መጋቢት 30ቀን 2006 ዓ.ም በተለይ የኢንዱስትሪ አካባቢዎች የመስመር ማስተካከልና ትራንስፎርመር የመቀየር ሥራ በማከናወን ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ነው።

የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተያዘ ነው። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የፋብሪካ ግዢ ሲፈጽሙ ከውጭ ባለሀብቶች በተለየ መልኩ በአከፋፈል ላይ ማበረታቻ አላቸው። የውጭ ባለሀብቶች ጨረታ ሲያሸንፉ ሙሉ ክፍያ እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ። በአንፃሩ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ግን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነውን ዕዳቸውን እንዲከፍሉ በብድር መልኩ ይሰጣቸዋል። ቅድሚያ የሚከፍሉት35በመቶ ብቻ ነው። የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካም በባለሀብቶች የተያዘው በዚህ አሰራር መሰረት ነው። የአምስት ዓመት የክፍያ ጊዜ ገደባቸው አልቋል። «በኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት በሙሉ አቅሜ እንዳልሠራ አድርጎኛል» የሚልና ሌሎች ተያያዥ ምክንያታቸውን ጠቅሰው፤ ለሁለት ዓመት የማራዘሚያ ጊዜ እንዲሰጣቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ጉዳያቸው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደርሶ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ የጊዜ ማራዘሚያው ተፈቅዶላቸዋል ሲሉ ሚኒስትሩ ያብራራሉ።

የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ማሽኖች ቢሸጡ የገንዘብ እጥረታቸውን እንደሚያቃልል በመጥቀስ ሽያጩ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። በመጀመሪያ ጥያቄው ምላሽ ባያገኝም በኋላ ላይ ግን ሥራ ላይ ያልዋሉ ንብረቶችን ቢሸጡ እንደማይጎዱ ስለታመነበት የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲና ልማት ባንክ ተስማምተው እንዲሸጥ ወስነዋል።

የፋብሪካው አመራሮች የማስፋፊያ ብድር እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል። ነገር ግን የማስፋፊያ ብድር ለማግኘት በመጀመሪያ ያለባቸውን 65በመቶ የመንግሥት ዕዳ መክፈል ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ከዓመት በፊት ለጥጥ መግዢያ በሚል የወሰዱትን መንግሥት የፈቀደውን ብድር አልመለሱም። እነዚህ ሁሉ ያልተከፈሉ ብድሮች ቢደመሩ ባለሀብቶቹ ለፋብሪካው ለግዢ የፈጸሙትን 35 በመቶ ክፍያ ተጠቅመውታል ነው ባንኩ የሚለው።

ሙንባይ የሚገኝ ኩባንያ ያገለገለ ማሽን ይዞ በመግባት ከፋብሪካው ጋር በጣምራ ለመሥራት እንደሚፈልግና በጋራም ለማስፋፊያ ብድር እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። ይህንንም አልተከለከሉም የተባሉት የብሔራዊ ባንክን የብድር ፖሊሲ አክብሩ ነው፡፡ ይህ ማድረግ ካልቻሉ ብሔራዊ ጥቅማችንን ይጎዳል። አሁንም የተሰጣቸው ዕድል አለ ከሙንባይ የሚመጣው ኩባንያ ለመሥራት ፍላጎት ካለውና የሚያስገባው ማሽን ዋጋ ያለው ከሆነ አምጥቶ እንዲተክል ይመከራል። ያኔ የእነርሱ ድርሻ ያድጋል፣ የገንዘብ አቅማቸውም ይሻሻላል በመሆኑም የሚጎድላቸው የማምረቻ ማሽን ቢኖር እንኳን ባንኩ ሊያበድ ራቸው ዝግጁ ነው። ከዚህ ውጪ ሊደረግላቸው የሚችል ነገር የለም። ልማት ባንክም ከፖሊሲው ውጪ ሊሠራ አይችልም። እኛም ብንሆን ከፖሊሲ ውጪ ስሩ ብለን አንመክርም። ምክንያቱም ሕግና ሥርዓት መከበር ስላለበት ነው በማለት ነው አቶ አህመድ የተናገሩት።

ፋብሪካው በመብራት መቆራረጥና የጥጥ ዋጋ በመዋዠቁ ምክንያት ለኪሳራ በመዳረጉ የዕዳ ክፍያ ጊዜ እንዲራዘምለት በጠየቀው መሰረት የመክፈያ ጊዜው ተራዝሞለታል። ይህ ውሳኔ የሚደገፍ ነው። ሆኖም ግን ፋብሪካው በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ በመሆኑ፣ ንብረትነቱ የኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች መሆኑና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠሩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ችግሩን ተረድቶት ካለበት አዘቅት እንዲወጣ እንዲደግፈው ይመከራል።

*********

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 14-2014፣ ‹‹የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ህልውና ስጋት ውስጥ ወድቋል›› በዘላለም ግዛው

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories