ቃለ-መጠይቅ| ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና ጋዜጠኛ አሸናፊ ቱፋ

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ከአንድ ጎበዝ የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ ጋር ቃለ-መጠይቅ አድርገዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለ-መጠይቁን በሶስት ተከታታይ ዕትሞች አቅርቦታል፡፡ ይሁንና የሆርን አፌይርስ አንባቢዎች የኢንተርኔት ችግር ሊገጥማችሁ እንደሚችል በማሰብ፣ ቃለ-መጠይቁን ኮምፒውተራችሁ ላይ በአንድ ግዜ በማስቀመጥ (save በማድረግ) ማንበብ ትችሉ ዘንድ፤ ሙሉ ቃለ-መጠይቁን ከዚህ በታች አትመነዋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ መጠየቅ የምንፈልገው፤ ሆርን አፌይርስ ከፌስቡክ የተሰበሰቡ የሕዝብ ጥያቄዎችን ይዞ ከፍተኛ አመራሮችን ለመጠየቅ ሲፈልግ – ለምን ‹‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ዓይነት›› ሰበብ እንደሚቀርብ ነው፡፡

*************

አሸናፊ ቱፋ፡- የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ነው የቀረው (የተያዘውን ዓመት ሳይጨምር)። ያለፉት አመታት አፈፃፀም ግምገማ ምን ይመስላል? ባለው ቀሪ ጊዜስ የቀረውን መተግበር ይቻላል?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- የገመገምነው የሦስት ዓመቱን አፈፃፀም ነው። አሁን ያለንበት ዓመትና 2007 በጀት ዓመት ሙሉ አለን። የስድስት ወሩ አፈፃፀም ራሱ ገና አልተገመገመም፤ በቅርቡ ይገመገማል። የሆነው ሆኖ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በሁለት መንገድ ነው የምናየው። አንደኛው ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት አኳያ ሲሆን ሌላኛው ከመዋቅራዊ ለውጥ ጋር የተያያዘ ነው። አፈፃፀሙ የሚገመገመውም በሁለቱም አግባብ ነው።

ከዕድገት አንፃር ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ነጥብ ሰባት በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል። የሦስት ዓመቱን አጠቃላይ እድገት ስናየው ደግሞ በሁለት አሀዝ ነው ያደገው፤ አስር በመቶ። በሌላ አባባል የሁለት አሀዝ ዕድገቱ እንደቀጠለ ነው። እንዳጠቃላይ ስናየውም ከሰባት በመቶ በላይ ያለ ዕድገት ደግሞ ፈጣን ዕድገት ነው። ዕቅዱ የተለጠጠ ቢሆንም የፈጣን ዕድገት ጉዞአችንን አስጠብቀን እየሄድን ነው።

መዋቅራዊ ለውጡ በዋናነት የሚገለፀው በአገር ውስጥ ምርት የግብርና ድርሻ እየቀነሰ እንዲሄድና የኢንዱስትሪው ድርሻ እንዲጨምር ከማድረግ አንፃር ነው። የእነዚህን የኢኮኖሚ ዘርፎች ድርሻ ለመቀየር በመስራትም ይገለጻል። ከዚህ ውጪ ያለው ዕድገት ግን በነበረውም ሊመጣ የሚችል ነው፤ ቀላል ነው ለማለት ፈልጌ ግን አይደለም።

አሸናፊ ቱፋ፡- በዕቅዱ አፈፃፀም ላይ በተለይ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የታቀደውን ያህል አላደገም፤

ዶክተር ደብረጽዮን፡- አሁን እኮ እንደ አጠቃላይ ገለፅኩልህ። ዕድገታችን ከሰባት በመቶ በላይ እስከሆነ ድረስ ፈጣን ዕድገት ላይ ነን ማለት ነው። ከዚያ በላይ መሄድ ሌላ ጉዳይ ነው፤ ተጨማሪ ነው የሚሆነው ማለት ነው።

አሸናፊ ቱፋ፡- ታዲያ ከታቀደው ከ11 እስከ 14 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ዕድገት አንፃር የአንድ በመቶ ልዩነት በኢኮኖሚ ዕድገት ትንሽ ነው?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ዝቅተኛ የዕድገት አማራጭ ብለን ያስቀመጥነው የአስራ አንድ በመቶ ዕድገትን ነው። በአስር በመቶና በአስራ አንድ በመቶ መካከል ያለው ልዩነት የአንድ በመቶ ነው። በሒሳብ ስሌት ከሆነ አንድ በመቶ ይቀረዋል ማለት ነው። ቢሆንም ገና አንድ ዓመት ተኩል የመፈጸሚያ ጊዜ ይቀረዋል፤ የ2006እና 2007 ዓ.ምን አፈጻጸም ገና እናየዋለን። አሁን ባለው ሁኔታ ግን የአንድ በመቶ ልዩነት አለ። በእርግጥ በፈጣን ዕድገት ምህዋር ውስጥ ሆነህ የአስርና አስራ አንድ በመቶ ልዩነት ትንሽ ነው።

አሸናፊ ቱፋ፡- ለዕቅዱ ስኬታማነት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ድጋፍ ሰጪ ኢንስቲትዩቶች የሚጠበቅባቸውን ያህል እየሰሩ እንዳልሆነ ነው የሚነገረው። የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን ማንሳት ይቻላል፤ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ማህበሩ ነው በተሻለ እየተንቀሳቀሰ ያለው ይባላል። እንደዚህ አይነት ሁኔታዎችን እያያችሁበት ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ይህ ዕድገት የአንድ ኢንስቲትዩት ዕድገት አይደለም፤ እንደ አጠቃላይ ነው የሚታየው። እንደተባለው ማህበሩ በተሻለ ከተንቀሳቀሰ ጥሩ ነው፤ ይህ ይፈለጋል። ኢንስቲትዩቱ ከደከመ ግን የበለጠ መስራት አለበት። ስለዚህ ይሄንን ኢንስቲትዩት እንደ አንድ ዘርፍ ነው የምንወስደው። መዋቅራዊ ለውጥ እናምጣ ስንል የኢንዱስትሪ ልማትን እናጠናክር ማለት ነው። የቴክኖሎጂ፣ የአስተዳደርና የዓለም ገበያ ጉዳዮች አሉ፤ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች የኢንስቲትዩት ጉዳዮች አይደሉም። ኢንስቲትዩቱ ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች የአቅም ግንባታ፣ በተወሰነ ደረጃ ጥናት ሲያደረግና ስልጠና ሲሰጥ ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል።

የውጪዎቹን ባለሀብቶች ኢንስቲትዩቱ ሊደግፍ አይችልም። እነርሱ የተሻለ ቴክኖሎጂና አስተዳደር አላቸው፤ ስራውንም ሆነ ገበያውን ያውቁታል። የኢንስቲትዩቱ ድርሻ ትንሽ ነው ሊባል የሚችለውም ለእነርሱ ነው። በተለይ በአለም ላይ ታዋቂ የሆኑት እነዚህ ኩባንያዎች የኢንስቲ ትዩቶቹን ድጋፍ አይፈልጉም። ኢንስቲትዩቱም ለእነርሱ ድጋፍ ለመስጠት ውስንነት አለበት። እነርሱ ለልምዱም ሆነ ለገበያው ቅርብ ናቸው። እነርሱ የሚፈልጉት የማመቻቸት ስራዎችን ነው፤ ይሄ ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን የመንግስትም ነው። ድጋፍ የሚያስፈልገው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ድርሻ ደግሞ እናውቀዋለን፤ ገና ነው ብዙ የሚባል አይደለም። ወደ ኢንዱስትሪው ብዙ እየገቡ አይደለም፤ ገና ናቸው።

ኢንስቲትዩቱ ጠነከረም አልጠነከረም ወደ ኢንዱስትሪው ለማስገባት ብዙ መሰራት የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ። ምክንያቱም ተቋሙ ራሱ የሚገነባ ነው። በቀጣይ የሚኖረው ሚና እየጨመረ ይሄዳል እንጂ አሁን ባለበት ሁኔታ በኢንዱስትሪው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብለን እንደ መንግስት አናስብም። የሚችሉትን ያህል መደገፍ አለባቸው።

እነዚህ ኢንስቲትዩቶች ከሌሎች አለም አቀፍ ኢንስቲትዩቶች እየተገናኙ ልምድ እየወሰዱ ነው። እነርሱ በአቅም ግንባታ ላይ ናቸው እንጂ ድጋፍ እየሰጡ አይደለም፤ ቢሆንም ጎን ለጎን የሚችሉትን እያደረጉ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ኢንዱስትሪው በእነርሱ ላይ የተንጠላጠለ አይደለም። በሂደት ግን ጫናቸውና ተፅኗቸው እያደገ ነው የሚመጣው።

አሸናፊ ቱፋ፡- በየዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎር ሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ሲገመገም ያልተሳኩት ግቦች ወደ ሚቀጥለው ዓመት እንዲዛወሩና ለዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ ጋር ተደምረው እንዲፈፀሙ ይደረጋል። አሁን አሁን ደግሞ እየተጠናቀቀ ባለው በዚህኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አይሳኩም የሚባሉ ግቦች ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይዛወራሉ ሲባል ይሰማል፤ ይህ ምን ያመለክታል?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ራሱን የቻለ ነው። በዚህኛው የዕቅድ ጊዜ መሰራት ያለበት አሁን ነው መሰራት ያለበት። ወደ ሚቀጥለው እናካትተዋለን ያልንበት ሁኔታ የለም። እንደመንግስት በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መስራት የምንችለውን ያክል እንሰራለን፤ ቀሪ ካለም አልተሰራም ማለት በመሆኑ ወደ ሚቀጥለው ይዛወራል ለማለት ተፈልጎ ካልሆነ በስተቀር ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ገና አልተቀረፀም። በሂደት ላይ ያለ ነገር ነው፤ የቀረ ካለ ግን በሚቀጥለው መሰራቱ ግልፅ ነው። በመሆኑም የእኛ ትኩረት በአሁኑ ዕቅድ መሰራት ያለባቸውን መስራት ነው።

አሸናፊ ቱፋ፡- በአሁኑ የእድገትና ትራንስፎ ርሜሽን እቅድ ውስጥ የተቀመጡት ግቦች በእርግ ጠኝነት ይሳካሉ ብሎ መናገር ይቻላል? አመላካች ሁኔታዎችን አይቶ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ከተቀመጠው ግብ አንፃር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን እንኳ ማሳካት እንችላለን ብሎስ መናገር ይቻላል?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ከግማሽ በላይማ አሁንም ተሳክቷል። ዝርዝር ግምገማውን ብታየው በዕቅዱ ከተቀመጡት በላይም ያሳኩ ዘርፎች አሉ። ቢሆንም በዕቅዱ የተቀመጠው ግብ ይህ ስለሆነ ማቆም አለብን ማለት ባለመሆኑ በቀሪው ጊዜም የምንሰራውን እየጨመርን ነው ያለነው።

ለምሳሌ በዕቅዱ ከአጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም አስራ አምስት በመቶ እንዲሆን ግብ የተያዘለት ቁጠባ 17 ነጥብ አምስት በመቶ ደርሷል። ይህ ቀድሞ ተሳክቷል፤ ለኢንቨስትመንት ስለምንፈልገው ከዚህ በላይ እንዲሆንም ነው እየሰራን ያለነው። በሌሎች ዘርፎች ያለውንም አፈፃፀም ከወዲሁ ይሳካል ወይም አይሳካም ማለት አይቻልም፤ ገና ነው። በቀረው ጊዜ ሰማንያና ዘጠና በመቶ ሊሳኩ የሚችሉ ስራዎቻችን ብዙ ናቸው። የተወሰነ ተግዳሮት ያለው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው፤ ከኢንዱስትሪም የወጪ ንግዱ። እሱም ቢሆን ፈጣን ዕድገት ላይ ነው። በመሰረተ ልማት፣ በግብርና ወይም በአገልግሎት ያሉት ሁሉ ሊሳኩ የሚችሉ ግቦች ናቸው።

አሸናፊ ቱፋ፡- ለአገሪቱ እየመጣ ያለው ብድርና ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ይነገራል። ትርፉ ዕዳ ነው የሚሉም አሉ፤ እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- የአገራችን ዕድገት በብድር የመጣ አይደለም። እድገቱ በአገሪቱ የልማት ስትራቴጂ ላይ ተመስርቶ ከገጠር እስከ ከተማ መንግስት፣ ግለሰብ፣ ባለሀብት፣ አርሶ አደሩ፣ ጥቃቅንና አነስተኛውና ዜጎች ሁሉ ተረባርበው ያመጡት ነው። የእድገታችን መነሻ የልማት ስትራቴጂውንና አሁን ያለውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት አድርጎ የተሰራው ስራ ነው። እድገታችን በብድር ሳይሆን በልፋት የመጣ ነው።

ብድርና ዕድገት በቀጥታ አይተሳሰሩም። ከእኛ በላይ ተበድሮ በእኛ ደረጃ ይቅርና የእኛን ግማሽ እንኳ ያላደገ አገር አለ። የኢትዮጵያ ዕድገት የመጣው በብድር ሳይሆን በልማት ስትራቴጂና ሌት ተቀን ስለተደከመ ነው። በመሆኑም የዕድገቱን ምንጭ በተገቢው መልኩ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

ሁሉንም አይነት ብድር እኛ እንወስዳለን ማለት አይደለም። የመጣውን ብድር ሁሉ ደግሞ ኢትዮጵያ አትወስድም። ከእኛ ስትራቴጂ ጋር የሚስማማውን እንወስዳለን፤ የማይስማማውን አንወስድም። ከዓለም ባንክም ሆነ ከሌላ አካል የሚመጣ ብድር ከስትራ ቴጂያችን ጋር የሚሄድ ከሆነ ብቻ ነው የምንቀበለው።

የልማት አጋሮች አንዳንዴ ብድር የማይሰጡን መፈፀም ስለማንችል አይደለም፤ መፈፀም እንደምንችልማ ያውቁናል። ቅድመ ሁኔታዎች ያሉዋቸውን ብድሮች እኛ አንቀበልም። ይህ መንግስት በዚህ አይነት መልኩ እንደማይጓዝ በተግባር ካረጋገጠ ሃያ ዓመት አልፏል።

የአገራችን አርሶ አደር ዕድገቱን እያመጣ ያለው ለፍቶ ጥሮ ግሮ ነው። የሚመጣው ብድር ደግሞ መሰረተ ልማት ላይ ነው እየዋለ ያለው። ለመንገድ፣ ለመብራት፣ ለቴሌ ወይም ለባቡር ይውላል። መሰረተ ልማት ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ያለ መሰረተ ልማት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ እንቅስቃሴ አይኖርም። የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ፈጥኖ አለመሄዱ የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም ስራው ትልቅ ዋጋ አለው። ከዚህ በላይ መፍጠን አለበት እንጂ ብድሩ ከዕድገቱ ጋር አይመጣጠንም አይባልም። በመሆኑም ይህ ዕዳ ሳይሆን ዕድገቱን የማፍጠን ጉዳይ ነው። ተጨማሪ ኢንቨስት ማድረግ አለብን ማለት ነው።

የመሰረተ ልማት ስራዎች ቴክኖሎጂዎች ናቸው። የሕዝቡ የመሰረተ ልማት ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ አገሪቱ በራሷ አቅም ልትፈጽማቸው አትችልም። የተገኘው ብድርም ላይበቃ ይችላል። እናም ተጨማሪ ብድር ያስፈለጋል ማለት ነው። ስለዚህ በተመረጠ መልኩ መበደር ተገቢ ነው። ትላልቆቹ ብድሮቻችንም የመሰረተ ልማት ብድሮች ናቸው። ይህ ዕዳ ነው የሚል ካለ ደግሞ ተሳስቷል።

አሸናፊ ቱፋ፡- በመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፉ ኮንትራክተሮች ምርጫ ግልጽነት ይጎድለዋል። አንዳንድ ጊዜ የአበዳሪው አገር ኮንትራክተሮች ብቻ እንዲይዙት ይደረጋል። እንደዚያም ሆኖ ከእዚያ አገር ኮንትራክተሮች እንኳ ኮንትራቱን የሚይዙት ተቋማት የሚመረጡበት አግባብ ፍትሐዊነት የጎደለው ነው። በቅርቡ አሥራ አምስት የቻይና ኩባንያዎች አቀረቡ የተባለውን ቅሬታ ማንሳት ይቻላል፤

ዶክተር ደብረጽዮን፡- በየመንገዱ የሚወራውን ከመያዝ የመንግሥት አሠራር ምን ዓይነት ነው? ማለት ያስፈልጋል። አንዱ ገበያ ካላገኘ ችግር አለ ይላል። ገበያውን ለሁሉም መስጠት አይቻልም። በውድድር የሚሰጥ ነው፤ ውድድር ደግሞ የራሱ መመዘኛ አለው። እገሌ አጭር ስለሆነ እገሌ ረጅም ስለሆነ ብለህ አይደለም ገበያውን የምትሰጠው። ሁሉም የራሱን ሰነድ (ዶክመንት) ማቅረብ አለበት። ምርጫው የሚከናወነው ይሄ ተገምግሞ ነው።

የተባለውን የቻይና ኩባንያዎች ቅሬታ እኔም ሰምቼዋለው። ቀድመው የገቡት ማሳለፍ ከለከሉን የሚል ነው። እንደዚህ የሚባል ነገር የለም። በቴክኖሎጂው፣ በዋጋ ወይም በሚሰጠው አገልግሎት ሊሆን ይችላል ተመራጭ የሚያደርገው። የራሳቸውን ዶክመንት አቅርቡ ነው እያልን ያለነው፤ ከቻይናም ቢሆን። እዚህ ያሉትም ቢሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ሲሰጣቸው የበፊት አፈፃፀማቸው ይገመገማል።

አሸናፊ ቱፋ፡- ግን የአንዳንዶች አፈፃፀም ደካማ ሆኖ የተሻለ ፕሮጀክት ሲይዙ ይታያል። ለምሳሌ ማንሳት ይቻላል ዜድ ቲ ኢ የ800 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተሰጥቶታል። ከእዚህ በፊት በያዘው 120 ትምህርት ቤቶችን በስኩል ኔት የማስተሳሰር ፕሮጀክት መሥራት አልቻለም። ሌላው ቀረቶ ለፓይለት ፕሮጀክትነት(ለሙከራ) የተሰጠውን ሥራ በተባለው ጊዜና መሣሪያ አላጠናነቀቀም። ታዲያ ግምገማው ሠርቷል ማለት ይቻላል?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- እኛ የምንገመግመው የስኩል ኔቱን ብቻ አይደለም። የስኩል ኔቱን ጉዳይ በዝርዝር ባላውቀውም ከትምህርትሚኒስቴር በኩል ሰምቸዋለው። እርሱ እንደ አንድ ይታያል። ከእዚያ በላይ የሆነ ትልቅ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ደግሞ ሠርቷል። ቴሌ ዜድ ቲ ኢን ይገምግም ከተባለ በእዚህ ነው የሚገመግመው እንጂ አንዷን የ120 ትምህርት ቤቶችን ሥራ ብቻ አይደለም። እርሷም ብትሆን ግን እንደሰማሁት በሂደት ያለች ጉዳይ ናት።

አፈፃፀም ሳይገመገም ሥራ አይሰጥም፤ ይሄ የተለመደ ነው። ያሉት ችግሮች ደረጃ በደረጃ ተቀምጦና ተሰልቶ ነው ወደ ተግባር የሚገባው። ቢሆንም ይሄ አፈፃፀም እንደአጠቃላይ አይገልጻቸውም።

አሸናፊ ቱፋ፡- ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ፕሮጀክት ሲሰጣቸው በትናንሾቹ ሥራዎቻቸው የነበረባቸው ጉድለት አይታይም? ባለን መረጃ መሠረት በእዚህ ትንሽ ፕሮጀክት ለማቅረብ ተወዳድረው ያሸነፉት ዕቃ ዝርዝርና ያቀረቡት ዕቃ እንኳ ይለያያል፡፡

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ሊሆን ይችላል፤ ይሄ እኮ በኮንትራት ውስጥ ሊያጋጥም ይችላል። ኢትዮ ቴሌኮም ራሱ እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲገጥሙት ነበር። የቀረበው ዕቃ በዝርዝር ሁኔታው መሠረት ካላመጣ እንዲቀይር ይደረጋል። አልቀይርም ካለ ይቀጣል። ካልሆነ ችግር ውስጥ የሚገባው የፕሮጀክቱ ባለቤት ነው። ኢትዮ ቴሌኮም እኮ በፊት የቀጣቸው አሉ። ቢሆንም በአጠቃላይ አፈፃፀም ይታያል። ጉድለቱን በትክክል ማስቀመጥና መወሰንም ግድ ነው።

አሸናፊ ቱፋ፡- ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ካለው የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ተቋሙ ባለመሸጡ ከምታገኘው ጥቅም ይልቅ ያጣችው በጣም ይበልጣል ይባላል፤ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- በቴሌ ላይ ያለው የመንግሥት አቋም የሚታወቅ ነው። አገልግሎት አሰጣጡ ካለመሸጡ ጋር አይያያዝም። ለግሉ ዘርፍ ስላልተሸጠ «አገልግሎቱ እንደዚህ ሆኗል» የሚለው አይሠራም። ይሄ እንደዚህ የሆነው መሠረተ ልማቱ በዕድገት ላይ ያለ ኩባንያ በመሆኑ ነው።

ለምሳሌ የቦሌ መንገድ ሳይሠራ በፊት ሁለት መኪኖችን አጠገብ ላጠገብ ለማሳለፍ ይጠባል። ከቦሌ ወደ መስቀል አደባባይ ለመድረስ ቢያንስ ከሠላሳ እስከ 45 ደቂቃ ይወስዳል። መንገዱ አለ፤ ቢሆንም ለትራፊክ ፍሰቱ ጥሩ አልነበረም። አሁን ደግሞ መንገዱ ሰፍቶ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ቴሌም ከእዚህ የተለየ አይደለም፤ ከአቅሙ በላይ ከጫንከው እንደ መንገዱ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

በመሆኑም እንደ መንገዱ ማስፋፊያ ያስፈልገዋል። ችግሩ የተከሰተውም መንግሥት ስለያዘው ሳይሆን ልማት ስለሆነ ነው። ከአንድ ሚሊዮን ወደ ሃያ ምናምን ሚሊዮን ተገልጋይ የደረሰው ሠርተን ነው። አሁንም መሥራት አለብን ማለት ነው። መስፋት አለበት። በአንዴ ግን ልታሰፋው አትችልም። ካልሆነ ግን «የቦሌ መንገድ መጀመሪያውኑ ለምን እንደዚህ አልተሠራም» እንደማለት ነው። መፍትሄው ማሳደግ ነው፤ ለዚህም እየተሠራ ነው።

አሸናፊ ቱፋ፡- በ2004 ዓ.ም መጨረሻ የየዘርፉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም በቀረበበት ወቅት የቴሌ የሞባይል ደንበኞች ተጠቃሚ ቁጥር 18 ሚሊዮን ሲደርስ አገልግሎቱ ችግር ሊያጋጥመው እንደሚችል ተነግሮ ነበር። አሁን ያለው የቴሌ የሞባይል ደንበኞች ተጠቃሚ ቁጥር ሃያ ሰባት ሚሊዮን መድረሱ ነው የሚነገረው። ማስፋፊያው ለምን ቀድሞ አልታሰበበትም? የሞባይል መስመሩን የወሰደውም በኔት ወርክ መጨናነቅ ምክንያት እየተጠቀመበት አይደለም፤ ሽያጩንስ ለምን ማቆም አልተቻለም?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ሽያጭ አይቆምም። ሠላሳ ሚሊዮንም ቢሸጥ እነዚህ ሁሉ በአንድ ጊዜ ይደውላሉ የሚል አመክንዮ የለም። ማስተናገድ የሚችለውን አቅም ከግምት ማስገባት ነበረበት፤ ቢሆንም ማቋረጡ እንደ አማራጭ አይወሰድም። መደረግ ያለበት ማስፋፊያውን ማፋጠን ነው። የቴሌ ኮም ቴክኖሎጂ ወደ ሥራው ከተገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊስተካከል የሚችል ነው። ለዚህ ነው አዲስ አበባን በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እናስተካክላለን ያልነው። ለዚህም ነው ማቆም ሳይሆን ማፍጠን ነው የሚያስፈልገው የምንለው።

አሥራ ስምንት ሚሊዮን ቁጥር ሲደርስ ማስፋፊያውን ለመሥራት ተፈልጎ ነበር፤ ችግሩ ድርድሩ ረጅም ጊዜ መውሰዱ ነው። ድርድሩ ያን ያህል ጊዜ ባይወስድና በወቅቱ ተሠርቶ ቢሆን መጨናነቁ ባልተፈጠረ ነበር። እንደ መንገዱ አቅሙን ያገናዘበ ክፍተት እየፈጠሩ መሄድ ያስፈልጋል፤ ማፋጠን ግድ ነው። ይሄ ደግሞ ይታወቃል፤ ያልተሳካልንም ማፈጠኑ ነው። ድርድሩ መንግሥት ካሰበው በላይ አንድ ዓመት አካባቢ ነው የወሰደው። ግን ደግሞ ስምምነቱ ከሌለ ዝም ተብሎ ወደ ትግበራ አይገባም፤ ስምምነት ያስፈልጋል። ስምምነቱ ትክክለኛ መሆን አለበት። ሌላ አቋራጭ ስለሌለው ፈጥኖ እንዲያልቅ መረባረብ ብቻ ነው አማራጩ።

ማስፋፊያው በመሃል ዝም ተብሎ የተተወ ወይም ግድ የለም ቀስ ብለን እንሠራዋለን ብለንም አላዘገየነ ውም። በዕድገትና ትራንስፎር ሜሽን ዕቅዱም ያቀደነው አለ። መጨናነቁና የጥራቱ ጉዳይ ብቻም ሳይሆን በተደ ራሽነት ማድረስ የሚገባን ርቀትም አለ፤ ቀደሞ የታቀ ደም ነው። ያልተሳካው ሂደቱ ነው። ሂደቱ ተቋሙንም፣ ተጠቃሚ ውንም ዋጋ አስከፍሏል።

አሸናፊ ቱፋ፡- ታዲያ ተገቢውን አገልግሎት ባልሰጠበት ሁኔታ ቴሌ ትርፋማ ነኝ ማለት ይችላል? ብዙዎች እንደውም «አተረፍኩ ከሚል ዘረፍኩ ቢል እውነት ተናገረ» ይላሉ፤ ምክንያ ቱም በዚያኛው በኩል ያለውን ሰው ንግግር ሳይሰሙ የራሳቸውንም በትክክል ሳያስተላልፉ አንዳንዴ እንደውም ምንም ዓይነት ድምፅ ከወዲያኛው ጫፍ ሳይመጣ ዝም ብሎ ነው የሚቆጥረው?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ሳንጠቀምበት ከፈልን ማለት አይቻልም። እኔም እኮ እንደማንኛውም ሰው ተጠቃሚ ነኝ፤ የተለየ ኔት ዎርክ የለኝም። ኢንተርኔትም ሞባይልም ስጠቀም መቆራረጡ እንዳለ ሆኖ ነው እየተጠቀምኩ ያለሁት። በምንፈልገው ያህል ባይሆንም አገልግሎቱ አለ፤ እየተጠቀምን ሥራችንን እየሠራን ነው። እኔ ሥራዬን የምሠራው በኢንተርኔት ነው፤ የመስሪያ ቤቴ ሪፖርትም በኢሜይሌ ነው የሚላክልኝ። ችግሩ ሥራ የሚያስተጓጉል አይደለም። የተሻለ አገልግሎት ከሚፈልጉት ትላልቅ መረጃዎች ጋር በተያያዘ ችግር ያጋጥመናል። በመሆኑም አገልግሎቱ ከእዚህ በላይ መሆን አለበት። እየዘረፈን ነው የሚለው የተጋነነ ነው። ይሄንን እኔም እሰማለው።

በዲዛይን ራሱ ኔት ዎርክ የሌለባቸው አካባቢዎች አሉ፤ ይሄንን እናውቃለን። አገልግሎት መጀመሪያውኑ ማግኘት ስለማይችሉ አላግባብ ክፍያ የሚለው አይመለከታቸውም። አገልግሎቱ ባለባቸው አካባቢዎች ግን መቆራረጡ ራሱ መኖር የለበትም። ቢሆንም አገልግሎቱ መስተካከል አለበት። በተረፈ እኔ ራሴ የቴሌኮም አገልግሎቱ ጥሩ ነው፤ አይደለም ለማለት ግምገማ አያስፈልገኝም፤ ሞባይልና ኢንተርኔት ተጠቃሚ ነኝ።

የምንቀበላቸው የጥራት ችግሮች አሉ፤ መስተካከል አለባቸው። እንደኃላፊ ሳይሆን እንደ ተገልጋይ እንዲቋረጥ ብኝ እኔም አልፈልግም። ሲቋረጠብኝ ደግሜ ደውዬ አገኘዋለው ግን ይሄ መሆን አልነበረበትም። ባለፈው የሆነውን ነገረ ሰምቻለው፤ ችግር አጋጥሞን ነው። ከዓመት በፊት የወጣ አንድ ዓለም አቀፍ መረጃ የሞባይል ደንበኞች ቁጥር ፈጣን ዕድገት ከታየባቸው አንደኛው ኢትዮ ቴሌኮም እንደሆነ ይገልጻል። ቢሆንም በዝርፊያ የሚገለጽበት አግባብ ትክክል አይደለም።

አሸናፊ ቱፋ፡- የመብራት ኃይል አገልግሎት አሰጣጥ በብልሹ አሠራር የተተበተበ ነው። የትራንስፎርመር ግዢ፣ በየአካባቢው ባሉ ትራንስፎርመሮች ላይ የሚገጠሙ ፊዩዞች ከጥቅም ጋር የተሳሰሩ ናቸው። የግል ተቋማትና ነዋሪዎች በሚያቀርቡት መዋጮ መብራት የማይጠፋባቸው ቢጠፋም የማይቆይባቸው አካባቢዎች አሉ። ትራንስፎርመሮቹ ላይ በተገጠመላ ቸው የማይረባ ፊዩዝ (የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው) ቶሎ ቶሎ መብራት የሚጠፋባቸው ቶሎም የማይሠራ ላቸው አካባቢዎች አሉ። በእዚህ በኩል ተቋሙ ላይ ከተጀመረው ሥራ ባሻገር የበፊቱን አሠራር የገመገማ ችሁበት፤ በቀጣይ ደግሞ እንዳይኖር ያስቀመጣቸሁት አቅጣጫ አለ?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- አዎ አይተናል፤ ግን ለውጥ ማምጣት ያለብን በእዚያ ደረጃ አይደለም። ገንዘብ ስለሰጠ የተሻለ አገልግሎት የሚያገኘው የአሠራር ሥርዓቱ የተበላሸ በመሆኑ ነው። አገልግሎቱ ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ ነው መስተካከል ያለበት። የተባሉት እነዚህ ችግሮችም እንደየደረጃቸው ነው የሚፈቱት፤ ከእነዚህ የበለጡ ችግሮችም አሉ።

በመሆኑም ሙሉ አሠራሩን አፍርሰን እየገነባን ነው ያለነው። ለውጡ ተቋማዊ የሆነ የሽግግር ለውጥ መሆን አለበት። ካልሆነ አንዱን ብታስር፣ ሌላውን ብትቀጣ፣ ሌላውን ደግሞ ብታባርረውና ማስታወቂያ ብታወጣ ለውጥ ማምጣት አትችልም። ሙሉ የአሠራር ሥርዓቱን ነው ማስተካከል የሚያስፈለገው። ኩባንያው ለሁለት ተከፍሎ ከላይ እስከ ታች ያለውን ሙሉ አሠራር የተባለውን የደንበኞች አገልግሎት ችግር ጭምር እናስተካክለዋለን።

ትራንስፎርመርም ሆነ ኤሌክትሪክ ለማግኘት ወይም ለሌላ አገልግሎት የሚኖረውን ውጣ ወረድ ለማስተካከል የተጀመረ ሥራ አለ። አገልግሎት አሰጣጡ ጥራት ያለው መሆን አለበት። በቦታው ላሉ ሰዎች ገንዘብ በመስጠት የሚገኝ አገልግሎት ይቆማል። ለእዚህ የሚሆን ሥርዓት እየተዘረጋ ነው።

ለምሳሌ ቴሌ ውስጥ የጥሪ ማዕከሎች ተቋቁመዋል። የእኔ ስልክ ሲበላሽ ለዋና ሥራ አስፈፃሚው ሳይሆን ወደ ጥሪ ማዕከሉ ነው የምደውለው። እዚያ ያለው ባለሙያ ማን እንደሆነ አይታወቅም። ባለሙያው ደግሞ የሚቀያየር በመሆኑ ዘመዴ ነው የሚል ዕሳቤ አይኖርም። ባለሙያው ራሱ የሚሠራው ከሆነ ይሠራዋል፤ ካልሆነ ደግሞ ሌሎች እንዲሠሩት ያደርጋል፤ ይሄ ሥርዓት ነው። በዘመድ የሚሠራ አይኖርም፤ ምክንያቱም ብልሽቱ በጥሪ ማዕከሉ ተመዝግቧል። ለማንም ገንዘብ ስለተቀበለ ሄዶ ሊነካት አይችልም፤ እንደበፊቱ ዘመድ ጋ ተደውሎ ወይም በገንዘብ ማሠራት አይቻልም። ይሄንን ሥርዓት ለማምጣት ታች ያለውን ብልሹ አሠራር መታገል ብቻ ሳይሆን ከላይ ጀምሮ ለሁሉም የሚሆን የሚዘረጋ ሥርዓት ነው የሚያስፈለገው።

እዚህ ቦታ ጠፍቷል ለማለት እዚህና እዚያ እየተሯሯጡ ሲፈትሹ መዋል አያስፈልግም። ብልሽቱ ወይም ችግሩ ያለበት ቦታ የሚታወቅበትን ሁኔታ ለማምጣት ነው እየሠራን ያለነው። ከመጥፋቱ በፊት የኤሌክትሪክ ጭነት የበዛበትንም ቦታ ቀድመህ ታውቃለህ። ይሄንን ሁሉ ማስተካከል ያስፈልጋል በሚል እየተሠራ ነው።

ዘመኑ ረቅቋል፤ ብዙኃኑ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ነው። ቴሌፎን ተቋረጠ ተብሎ ኢንዱስትሪዎች አይቋረጡም፤ መብራት ሲጠፋ ግን ኢንዱስትሪዎች ይቆማሉ። ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ «እንጀራ አልጋገርንም፣ ምግብም አላበሰልንም» የሚሉ ቅሬታዎች ናቸው የሚመጡት።

እያደገ በሄደ ቁጥር ደግሞ ዘመናዊ መሆን አለበት። መፍትሄው ትራንስፎርሜሽን ነው፤ እግረ መንገዳችንን ያልሆነ ሥራ ሲሠሩ የተገኙት ላይ እርምጃ እንወስዳለን። ቅጣት ግን የመጨረሻ መፍትሄ መሆን አይችልም፤ አዲስም ሆነ ነባር ደንበኛ አገልግሎት ሲፈልግ ያለምንም ውጣ ውረድ መደለያም ይባል ማትጊያ ሳይከፍል አገልግሎቱን ማግኘት አለበት። መንግሥት ጉዳዩን በስፋት አይቶ ነው እየሠራ ያለው።

አሸናፊ ቱፋ፡- በባንኮች ያለው ብልሹ አሠራር የፋይናንስ ሥርዓቱን እየጎዳው ነው። ብሔራዊ ባንክ ራሱ ተቆጣጣሪ የሚያስፈልገው ተቋም ሆኗል እየተባለ ነው። ይሄንን የገመገማችሁትና የደረሳችሁበት ነገር አለ?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ይሄ ጉዳይ ከሁለትና ሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲነሳ ነበር። እንደ መንግሥት በድርድር ብድር የሚሰጥበትን አሠራሩንና አካሄዱን መፈተሽ ነው የሚቻለው። ከሁለት ዓመት በፊት እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ተፈጥረው እርምጃ ተወሰዶ ነበር። አሁን ግን የማውቀው ነገር የለም፤ አልገመገ ምንም። ችግር አይኖርም ግን ልል አልችልም። ወይ ያጋጠመው ሰው ዝም ብሏል ወይ እርሱም ተጠቃሚ ሆኗል። ነገ የምናገኛቸው ዛሬ ግን ያላገኘናቸው ይኖራሉ።

ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንደመንግሥትም ቅድሚያ አለው፤ እንዲቸገሩ አይፈለግም። ባንኮችንም የሚከታተል አካል አለ። ለማን ምን ያህል ሰጣችሁ? ይባላሉ። ባለሀብቱም አላገኘሁም ብሎ ሪፖርት ያደርጋል፤ እርሱ ቀጥታ የመንግሥት ክትትል አለው። ዝም ተብሎ ለባለሀብቱና ለባንኮች አልተተወም። ክትትሉ ማን ምን ያህል ወሰደ? እስከማለት ይደርሳል። ኤክስፖርተሩም የፈለግከውን አግኝተሃል ወይ ተብሎ ይጠየቃል።

ማኑፋክቸሪንግ ውስጥ ያለው ግን በሌላ ቋንቋ ብናስቀመጠው ለምኖ ሳይሆን እየተጠየቀም ነው የሚሰጠው። ምክንያቱም ኤክስፖርትን ለማሳካት መንግሥት ማድረግ ካለበት ነገር አንዱ የሚያስፈልገውን ብድር ማቅረብ ነው። ሌሎች እንደ ኤሌክትሪክ፣ መሬትና የመሳሰሉትን ማቅረብ እንዳለ ሆኖ። ይሄንን ሁሉ ችግር ለባለሀብቱ ልንተወው አንችልም። ስለምንፈልገውም መንግሥት ራሱ እንደባለሀብት ሆኖ ነው እየሠራ ያለው። ቢሆንም ችግሩ የለም አይባልም።

አሸናፊ ቱፋ፡- አንድ ብር ለአንድ ዶላር ስለሚባለው ነገር ያውቃሉ?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- እኔም ሰምቼዋለው። የገቢ ንግድ ላይ አያጋጥምም ማለት አይቻልም፤ በቀላሉ ስለማያገኙ። ትኩረት በምንሰጥባቸው ዘርፎች ማኑፋክቸሪንግና የወጪ ንግድ ላይ ግን የለም ማለት ይቻላል። መንግሥት ይከታተለዋል፤ ችግር ካለም ባለሀብቱ ራሱ አንድ ሚኒስትር ወዲያው ማግኘት ይችላል። በሌሎች ዘርፎች ግን መንግሥት በትኩረት አይከታተልም። ከሁለትና ሦስት ዓመት በፊት የተባለው ነገር ሲሰማ ጥናቶች ተካሂደው የተወሰዱ ማስተካከያዎች አሉ።

አሸናፊ ቱፋ፡- በሚሊዮኖች ተቋቁመው በቢሊዮኖች የሚያንቀሳቅሱት ባንኮች አመራሮች ራሳቸው የማይገባቸውን ህጋዊ የሚመስል ስህተት ሲሠሩ ይታያል፤ ቁጥጥርም የለባቸውም። አላግባብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብድር መውሰድ የመሳሰሉ ተግባራት እየተስተዋሉ ነው። እንደሚባለው እንደውም ነጋዴዎች ሆነዋል ማለት ይቻላል። አገሪቱ በአንድ ሌሊት ሚሊየነሮች የሚፈጠሩባት መሆኗን የሚናገሩ ሰዎች ቁጥጥር አለመኖሩን ያነሳሉ?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- አዎ፤ አየር ባየር ንግድ ላይ ይሄ ነገር አለ። አሁን ግን እያወራን ያለነውን የባንክ አሠራር በተለይ በማኑፋክቸሪንግና ኤክስፖርት ዘርፍ ምንም ችግር እንዳይኖር መንግሥት በትኩረት እየተከታተለው ነው፤ ባለሀብቱም ዝም አይልም። ኮንትራት ስላለውም ችግር ሲያጋጥመው ሮጦ ነው የሚመጣው። በንግዱ ላይም ውድድርና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮቸ ስላሉም ይሄ ሁኔታ ሊነሳ ይችላል። እንደአሠራር ግን ተፈትሿል፤ መለስተኛ ችግሮች ታይተዋል። በእዚህ ዓመት ግን የገጠመን የለም።

አሸናፊ ቱፋ፡- በአገሪቱ ሀብታሞችና ደሃዎች መካከል ያለው የሀብት ልዩነት በጣም እየሰፋ ነው። ብልሹ አሠራሮች ለእዚህ ዋነኛ መነሻ እንደሆኑም ነው የሚነገረው። መንግሥት በእዚህ ላይ ያለው አቋምና እየተሄደበት ያለው አግባብ ምን ይመስላል?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- በሀብታምና ደሃ መካከል ያለውን ልዩነት እናጥብብ ብለን አልተነሳንም። ሰው በለፋበት ልክ በአስተዋፅዖው መጠን ገቢ ማግኘት አለበት። ለእዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንጂ ከሀብታሙ ቀንሶ ለደሃው በመስጠት ማመጣጠን የነፃ ገበያው ኢኮኖሚ መርህ አይደለም። ግለሰቦች በልፋታቸው ቢሊየነር፣ አንድና ሁለት ሺ ገቢ ያላቸው ሆነው ሊወጡ ይችላሉ።

ሁሉም ለፍቶና ጥሮ ግሮ የልፋቱን ማግኘት አለበት። እኛ የምንቃወመው በባለሥልጣንም በለው በሌላ መንገድ በአቋራጭ መክበርን ነው። በልማታዊ መንገድ በሚያመርተውና በሚሰጠው አገልግሎት ቢሊየነር ከሆነ ለፍቶ ያመጣው ነው፤ መወቀስ የለበትም። በሌላ በኩል ደግሞ ድህነትን መቀነስ አለብን። ድህነት ቅነሳው ግባችን በመሆኑ መንግሥት እየሠራበት ነው። ከሁለቱም አቅጣጫ እንሠራለን። በአንድ በኩል የማመቻቸት ሥራ እንሠራለን።

ሀብታሙም ትክክለኛውን መንገድ ተከትሎ እንዲሠራ ነው የምንፈልገው። በኪራይ ሰብሳቢነት የመጣ ገንዘብ ከሆነ ሠርቶ ሳይሆን ዘርፎ ያመጣው በመሆኑ አንለቀውም። ልማታዊ በሆነ መንገድ ሠርቶ በዓለም ተጠቃሽ ከሚባሉት ሀብታሞች ተርታ ቢሰለፍ ደስ ይለናል። በሥራ ዕድል ፈጠራ በቴክኖሎጂና ሌሎች ሁኔታዎች ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታም ይፈጠራል። ከእዚህ ባለሀብት የምንቀንስበት ሁኔታም አይኖርም። ደሀውንም በራስህ ሂድ ብለን አንተወውም። ብዙ እጥረቶች በመኖራቸው መንግሥት እነዚያን መሙላት ይገባል። ከድህነት ማላቀቅ ያለብን ህብረተሰብ አለ።

የሀብት ክፍፍል ሲባል ዜጎችን ከድህነት ማስወጣት ማለት ነው። እ.አ.አ በ2015 የተቀመጠውን ድህነትን በግማሽ የመቀነስ ግብ ለማሳካት ውጤታማ ሥራ ነው እየሠራን ያለነው። በመሆኑም ከድህነት በታች የሚኖረው ሕዝብ በቀነሰ ቁጥር መሻሻል አለ ማለት ነው። መታየት ያለበትም ይሄ ነው። በደሃውና ሀብታሙ መካከል ያለው ልዩነት ሰፋ የሚለው ሳይሆን ደሃ እየቀነሰ ነው የሚለው ነው ትክክል። ሀብታሙ ሠርቶ እስካገኘ ድረስ ልንተወው ይገባል፤ ደሃውን ግን ልንተወው አንችልም። በመሆኑም ደሃ በቁጥር ቀንሷል፤ የነፍስ ወከፍ ገቢውም ጨምሯል፤ በነገራችን ላይ ይሄ አንዱ ስኬት ነው።

በ2007 ዓ.ም እንደርስበታለን ያልነውን ነው በ2005 ዓ.ም የደረስንበት። እኛ ዝም ብለን ድህነት ቅነሳ ብለን አንሄድም። ግልጽ በሆነ ሁኔታ የድሆች መጠን እየቀነሰ ነው። ለእዚህ ደግሞ የግብርና ስትራቴጂያችን ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ግብርና ላይ የሚሳተፈው ባለሀብቱ ሳይሆን አርሶ አደሩ ነው፤ የተቀየረውም እርሱ ነው። ስለዚህ በድህነት ላይ ነው እየሠራን ያለነው።

አርሶ አደሩም ሆነ ባለሀብቱ እንደልፋቱ ነው እያደገ ያለው። ነገር ግን ብዙ እጥረቶች ስላሉ መንግሥት ይገባል። የድህነት ቅነሳ ግብዓቶቹ የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች በመሆናቸው በስፋት እየሠራን ነው። የእኛ ስትራቴጂ ለአገሪቱ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ግልጽ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው ከድህነት እየወጡ ያሉት።

አሸናፊ ቱፋ፡- ደሃው ህብረተሰብ በጣም እየወረደ ደሃ ለመባል እንኳ ገና ይቀረኛል ብሎ እስከማመን ደርሷል፤ እየተባለ ነው

ዶክተር ደብረጽዮን፡- አሁን እየገለጽኩልህ እኮ ነው። ይሄ የግል አስተሳሰብና መሬት ላይ ያለው አንድ አይደለም። እንደተባለው ማንም ሊተረጉመው ይችላል። አንተም ልትተረጉመው ትችላለህ። ከድህነት የሚወጣው ሰው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው፤ ይሄ ማለት ደግሞ የደሃው ቁጥር እየቀነሰ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በመረጃ የሚታወቀው ደሃ እየሆነ ሳይሆን ከድህነት እየወጣ መሆኑ ነው።

ደግሞ ማየት የምንችለው ነገር እኮ አለ። አርሶ አደሩ ደሃ እየሆነ ነው እንዴ? ሁሉም ከድህነት አለመውጣቱ ግልጽ ነው፤ ግን እየተሻሻለ ነው። በራስህ አድማስ ውስጥ አይደለም የሚታየው። በነገራችን ላይ አሁን ስለ ስትራቴጂ የምናወራበት ጊዜ አይደለም፤ ውጤቱ በተጨባጭ ታይቷል። ሚሊየነር አርሶ አደር እኮ እየታየ ነው።

አሸናፊ ቱፋ፡- የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ አነስተኛና ጥቃቅን አንቀሳቃሾችን በመረቁበት ወቅት ከተመራቂዎቹ አንዱ «በእዚህ መስመር የገባሁት በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፈለጌ በቢሮክራሲ የተነሳ ስላልተሳካልኝ ነው። ይሄ አቋራጭ መንገድ ሆኖልኛል» ብሎኝ ነበር። ይሄንን በሀብታምና ደሃ መካከል ያለውን ልዩነት እየፈጠሩ ነው የሚባሉት ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ብልሹ አሠራሮች ናቸው። ይህን አካሄድ ለማቆም ምን ታስቧል?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ይሄ እኛን አይገልጸንም። አብዛኛው ህብረተሰብ ከድህነት እየወጣ ነው እንጂ ትልቅ ቦታ ኖሮ ተመልሶ መውረድ ያለ አይመስለኝም።

ብልሹ አሠራር በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሊኖር ይችላል። የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ በልማት ስትራቴጂያችን ውስጥ ያለ ነው። በእዚህ ውስጥ ደግሞ ብልሹ አሠራር የሚባል ነገር የለም። አርሶ አደሩን ከድህነት የማውጣት የልማት አቅጣጫ በየትኛው ብልሹ አሠራር ይያዛል? ይሄ ሁሉ የኤክስቴንሽን ሠራተኛ እየሠራ ያለው እኮ አርሶ አደሩን ከድህነት ለማውጣት ነው።

ብልሹ አሠራር በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ነው የሚያጋጥመው። እያወራን ያለነው ሚሊዮኖች እየተለወጡበት ስለሆነው ግብርና ነው። የትኛው ብልሹ አሠራር ነው የግብርናን ዕድገት የሚያቆመው? ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋ በተያያዘ ቦታ ያለማግኘትን የመሳሰሉ ችግሮች ያጋጥሙናል፤ ይህም በአቤቱታ እየተፈታ ነው። በሀብታምና ደሃ መካከል ያለውን ልዩነት በዋናነት የሚፈታው ስትራቴጂው ነው።

አሸናፊ ቱፋ፡- በከተማ ያለውስ ህብረተሰብ?

ዶክተር ደብረጽዮን፡- ከተማው መረሳት የለበትም፤ በኢትዮጵያ በግብርና ላይ ከሠራህ በድህነት ላይ ሠርተሃል ማለት ነው። ቢሆንም በእዚህ ብቻ ሳናቆም በከተማም ውስጥ ብዙ ሠርተናል። ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራ ይዞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሊቸገሩ ይችላሉ። ችግር ሲያጋጥም መታገል ነው፤ ስትራቴጂውም ያግዛቸዋል።

ብልሹ አሠራር ዛሬም ነገም የትም ቦታ ሊያጋጥም ይችላል። መንግሥት እየታገለ ነው፤ ዜጋውም «መብቴ ተረግጧል» ብሎ መምጣት አለበት። ችግሩ መፍትሄ ማግኘት ካልቻለ የአሠራር ሥርዓቱን እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን መበተን ደረጃ ላይ እንደርሳለን። አቅጣጫው አለ፤ ችግሩ የዲሲፕሊን ችግር ስለሚሆን ሁላችንም በየደረጃችን መታገል አለብን። ያ ካልሆነ የምንፈልገውን ዕድገት ማምጣት አንችልም።

አሸናፊ ቱፋ፡- አመሰግናለሁ።

ዶክተር ደብረጽዮን፡- እኔም አመሰግናለሁ።

***************

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories