Full text: አወዛጋቢው የግል መጽሔቶች የአዝማሚያ ትንተና

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ(እሮብ) የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፊት ገጽ ዜና በኢትዮጲያ ፕሬስ ድርጅት እና በኢትዮጲያ ዜና አገልግሎት የተሠራውን ‹‹የሰባት መጽሄቶች በተከታታይ ህትመቶቻቸው በአሉታና በተደጋጋሚ ያነሷቸው ጉዳዮች የአዝማሚያ ትንተና›› ጥናት በተመለከተ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ጥናቱ በአንዳንድ የግል ሚዲያዎች እና አስተያየት ሰጪዎች ዘንድ እንደ‹‹ማስጠንቀቂያ›› ከመቆጠሩና መለስተኛ ውዝግብ ከማስነሳቱ አንፃር ሙሉ ጽሑፉን ከውስጥ አዋቂ ምንጮች በማግኝት እዚህ አትመነዋል፡፡
*********

ሰባት መጽሄቶች በተከታታይ ህትመቶቻቸው በአሉታና በተደጋጋሚ ያነሷቸው ጉዳዮች የአዝማሚያ ትንተና
(ከመስከረም1/2006- ህዳር 30/2006)
ታህሳስ 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

መግቢያ
ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአመለካከት አና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቶ መሰራት ከጀመረ በኋላ በዘርፉ ያለው እድገት አበረታች ነው። አመለካከትና ሃሳብ ከሚገለፅባቸውና ከሚራመድባቸው መድረኮች ውስጥ ደግሞ አንዱ ሚዲያው ነው። ተፈለገም አልተፈለገ ሚዲያ ሀሳብ የሚራመድበት የገበያ ስፍራ ነው። በዚህም ሀሳቦች በአንድ መድረክ ይፋለማሉ/ይፋጫሉ፡፡

ሚዲያ ለአንድ አገር እና ህዝብ እድገት ወይም ውድቀት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።በሚዲያዎች የሚስተጋቡ ሃሳቦች ሚዛናዊነትና ምክንያታዊነት ጥሩ ከሆነ ከሚዲያው የሚገኘው የሃሳብ ምርት ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እድገትና መበልፀግ የማያሻማ አዎንታዊ ሚና አለው። ከሚዲያ ዘርፎች ውስጥ አንዱ የሆነው የህትመት ሚዲያው የማህበረሰቡን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችንና ጥቅሞችን በማስከበር፤ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በሃገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕቅዶችን፣ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለመቅረጽ አቅጣጫ የሚያመላከቱና የአቅጣጫዎችን ገቢራዊነት ለማሳዎቅ ያላቸው ድርሻም ትልቅ ነው።

ሚዲያው በአግባቡና በኃላፊነት ስሜት ከሰራ ፍትሕ፣ ሰላምና ዲሞክራሲ በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲሰፍን የማድረግና ወደ አንድ የጋራ አመለካከት እንዲያመራ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ህትመቶች የየአገራቸውን ተጨባጭ ሁኔታዎች በተለያዩ አቀራረቦች እስከ ታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የማድረግና ግንዛቤ የማስፋት አቅም አላቸው። እስከ አሁን ድረስ በተመዘገበው የአገራችን ለውጥ ውስጥም ይህ የህትመት ሚዲያ የነበረው ድርሻ ትልቅ ነው።ሆኖም ግን የኢንዱስትሪው እድገት ተፈቅዶለት፣ ነፃነቱ በህግና በአሰራር ተጠብቆለት ስራ ከጀመረበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ባይባል አንዳንድ የግል ህትመቶች ለሚዲያው እድገትና ነፃነት የሰጠውን ህገ መንግስታዊ ስርዓት ለመናድ፣ የአገሪቱን ህዝቦች ዘላቂ ሰላም ለመገዳደር ሲሰሩ ይታያሉ። ሆኖም የራሱን ህልውና ራሱ መክሮና ዘክሮ ባፀደቀው ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ዕውን ያረገው ህዝብ ከራሱ ጥቅም ተነስቶ መመዘን በመቻሉ ፅንፈኛና ጨለምተኛ የሆኑ ህትመቶች እየከሰሙ ሚዛናዊና ምክንያታዊ የሆኑት ደግሞ ከነችግራቸውም ቢሆን እስከ አሁን ድረስ እንዲመጡ አድርጓል።

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማም በአገራችን የህትመት ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው መጽሄቶች በአገራችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ሚና ማዎቅ ነው። ለዚህም ስባት የግል መጽሄቶች ማለትም አዲስ ጉዳይ፣ ፋክት፣ ሎሚ፣ ቆንጆ፣ ጃኖ፣ ዕንቁ እና ሊያ ከመስከረም 1 እስከ ህዳር 30 ድረስ ባሉ ተከታታይ ህትመቶቻቸው በተደጋጋሚ የዘገቧቸውን ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት ለማካሄድ ተሞክሯል።

የአዝማሚያ ጥናቱ የተካሄደው በአምድ ወይም ደግሞ በቋሚ ርዕሶቻቸው ይዘት ላይ ሆኖ ህገ መንግስቱ ዙሪያ፣ በአገሪቱ ነባራዊ የኢኮኖሚ ለውጦች ዙሪያ፣ በፖለቲካ ስርዓቱ ዙሪያ፣ ከሽብርተኝነት አኳያ እና የመንግስት ኃላፊዎችን በተመለከተ በፃፏቸው ጽሁፎች ውስጥ ጉዳዮቹን በምን አይነት የአቀራረብ ሁኔታና በምን ያህል የድግግሞሽ መጠን እንዳዎጡ ለማዎቅ በሚያስችል መልኩ ነው። በተጨማሪም የመጽሄቶቹ የጋራ የመረጃ ምንጮችና የጋራ ባህሪያትን ለመለየት ተሞክሯል። የአዝማሚያ ጥናቱ ዋና ዋና ግኝቶች ቀጥሎ ቀርቧል።

የአዝማሚያ ጥናቱ ዋና ዋና ግኝቶች

I. አዲስ ጉዳይ መጽሄት ከመስከረም 1/2006 – ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት

አዲስ ጉዳይ በሮዝ አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማህበር አሳታሚነትና በብራና ማተሚያ ድርጅት የሚታተም ሳምንታዊ መጽሄት ነው። መጽሄቱ ከመስከረም 1/2006 ዓ.ም እስከ ህዳር 30/2006 ዓ.ም ድረስ 12 መጽሄቶችን አሳትሟል። በዚህ የአዝማሚያ ጥናት የተሸፈኑት ህትመቶች 11 ተከታታይ ህትመቶች ናቸው።

ግራፍ 1፦ አዲስ ጉዳይ መጽሄት ከመስከረም 1/2006-ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ

በአዝማሚያ ጥናቱ ግራፍ ማዬት እንደሚቻለው መጽሄቱ በ7 የተለያዩ ህትመቶች የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ ሰርቷል። የድግግሞሹ ጠቅላላ ብዛት መጠኑም 77 ነው።

መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ዘገባዎችን ከመስራት ቀጥሎ የአመፅ ጥሪዎችን የሚጠሩ በ5 የተለያዩ ህትመቶች ስር በ11 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን የሚያጥላሉ በአራት ህትመቶች በ12 የድግግሞሽ መጠን፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያዋድቁና የሚያጥላሉ ጹሁፎችን በ6 የተለያዩ ህትመቶች በ8 ጊዜ ድግግሞሽ፣ ህገ መንግስቱን የሚያጥላሉ በ5 የተለያዩ ህትመቶች በ5 ጊዜ ድግግሞሽ እና ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ ጹፎችን በ3 ህትመቶች በስድስት ጊዜ ድግግሞሽ አቅርቧል።

II. ቆንጆ መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት

ቆንጆ መጽሄት በቴዎድሮስ ኢንተርቴንመንትና ፕሬስ ስራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበር አሳታሚነት እና አሳዬ ጀነራል ፕሪንቲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በየ ሁለት ሳምንቱ የሚታተም መጽሄት ነው። መጽሄቱ ከመስከረም 1/2006 ዓ.ም እስከ ህዳር 30/2006 ዓ.ም ድረስ 6 መጽሄቶችን አሳትሟል። በዚህ የአዝማሚያ ጥናት የተሸፈኑት ህትመቶች 5 ተከታታይ ህትመቶች ናቸው።

በአዝማሚያ ጥናቱ ግራፍ ማየት እንደሚቻለው መጽሄቱ በ5 የተለያዩ ህትመቶች ውስጥ አመፅን የሚያበረታቱ ዘገባዎችን በ16 የተለያዩ ርዕሶች በ5 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ያቀረበ ሲሆን ጠቅላላ የድግግሞሽ ብዛቱ 80 ነው። መጽሄቱ አመፅን የሚያበረታቱ ዘገባዎችን ከመስራት ቀጥሎ የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ጹሁፎችን በ12 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ5 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ለ60 ጊዜ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን የሚያጥላሉ በ9 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ3 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ለ27 ጊዜ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ ጹሁፎችን በ7 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ6 ጊዜ ድግግሞሽ ለ42 ጊዜ፣ ህገ መንግስቱን የሚያጥላሉ በ8 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ5 ጊዜ ድግግሞሽ እና የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያዋድቁ ጹፎችን በ4 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በዘጠኝ ጊዜ ድግግሞሽ አቅርቧል። ቀጥሎ ያለው ግራፍ የሚያሳዬውም መጽሄቱ በ5 ተከታታይ ህትመቶቹ ውስጥ ከላይ የተገለጹትን ጉዳዮች ያነሳበትን ብዛትና ጉዳዮቹን ያነሳበትን የድግግሞሽ መጠን ነው።

ግራፍ 2፦ ቆንጆ መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ

III. ሎሚ መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት

ሎሚ መጽሄት በዳዲሞስ ኢንተርቴንመንትና እና ፕሬስ ስራዎች ኃ/የተ/የግ/ማ አሳታሚነት የሚታተም ሳምንታዊ መጽሄት ነው። መጽሄቱ ከመስከረም 1/2006 ዓ.ም እስከ ህዳር 30/2006 ዓ.ም ድረስ 12 መጽሄቶችን አሳትሟል። በዚህ የአዝማሚያ ጥናት የተሸፈኑት ህትመቶች ብዛት 12 ተከታታይ ህትመቶች ናቸው።

ግራፍ 3፦ ሎሚ መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ

ከግራፉ መረዳት እንደሚቻለው መጽሄቱ በ11 የተለያዩ ህትመቶች ውስጥ ልክ እንደ ቆንጆ መጽሄት ሁሉ በቀዳሚነት የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጥላሉ ናቸው። በዚሁ መሰረት መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ዘገባዎችን በ11 የተለያዩ ርዕሶች በ25 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን አቅርቧል። የድግግሞሽ ብዛቱም 275 ነው። መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ጽሁፎችን ማቅረብ ቀጥሎ በተደጋጋሚ ያነሳው ጉዳይ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ ጹሁፎች ናቸው። ይህንንም በ13 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ10 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 130 ጊዜ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያዋድቁ ጹሁፎችን በ11 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ8 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 88 ጊዜ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን የሚያጥላሉ ጹሁፎችን በ9 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ8 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 72 ጊዜ፣ አመፅን የሚያበረታቱ ጹሁፎችን በ11 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ6 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 66 ጊዜ እና ህግ መንግስቱን የሚያጥላሉ ጹፎችን በ4 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ7 ጊዜ ድግግሞሽ አቅርቧል ማለትም 28 ጊዜ አቅርቧል።

IV. ዕንቁ መጽሔት ከመስከረም 1/2006-ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት

ዕንቁ መጽሄት በአለማየሁ ሕትመትና ማስታወቂያ ኃ/የተ/የግ/ማህበር አሳታሚነት እና በፋኖስ ሰርቪስስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር አታሚነት በየ15 ቀኑ የሚታተም መጽሄት ነው። መጽሄቱ ከመስከረም 1/2006 ዓ.ም እስከ ህዳር 30/2006 ዓ.ም ድረስ 6 መጽሔቶችን አሳትሟል። በዚህ የአዝማሚያ ጥናት የተሸፈኑት ህትመቶች ብዛትም 6 ተከታታይ ህትመቶች ናቸው።

መጽሄቱ በ6 የተለያዩ ህትመቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጥላሉ ናቸው። በዚሁ መሰረት መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ዘገባዎችን በ12 የተለያዩ ርዕሶች በ72 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን አቅርቧል። መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ጽሁፎችን ማቅረብ ቀጥሎ በተደጋጋሚ ያነሳው ጉዳይ ህግ-መንግስቱን የሚያጥላሉ ጽሑፎች ጹሁፎች ናቸው። ይህንንም በ9 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ6 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 54 ጊዜ፣ የመለስን ራዕይ የሚያጣጥሉ ጽሑፎችን በ6 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ6 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 36 ጊዜ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ6 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 30 ጊዜ፣ አመፅን የሚያበረታቱ ጹሁፎችን በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ6 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 30 ጊዜ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያዋድቁ ጹሁፎችን በ4 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ6 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 24 ጊዜ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን የሚያጥላሉ ጹሁፎችን በ3 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ6 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 18 ጊዜ አቅርቧል።

ግራፍ4፦ ዕንቁ መጽሔት ከመስከረም 1/2006-ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ

V. ሊያ መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት

ሊያ መጽሄት በሊያ የህትመትና የማስታወቂያ አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማህበር አሳታሚነትና በልዋ ማተሚያ ድርጅት በየ15 ቀኑ የሚታተም መጽሄት ነው። መጽሄቱ ከመስከረም 1/2006 ዓ.ም እስከ ህዳር 30/2006 ዓ.ም ድረስ 5 መጽሄቶችን አሳትሟል። በዚህ የአዝማሚያ ጥናት የተሸፈኑት ህትመቶች 5 ተከታታይ ህትመቶች ናቸው።

መጽሄቱ በ5 የተለያዩ ህትመቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ህግ-መንግስቱን የሚያጥላሉ ናቸው። በዚሁ መሰረት መጽሄቱ ህግ-መንግስቱን የሚያጥላሉ ዘገባዎችን በ9 የተለያዩ ርዕሶች በ5 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ለ45 ጊዜ አቅርቧል። መጽሄቱ ህግ-መንግስቱን የሚያጥላሉ ጽሁፎችን ከማቅረብ ቀጥሎ በተደጋጋሚ ያነሳው ጉዳይ የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጥላሉ ጽሁፎች ናቸው። ይህንንም በ8 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ5 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 40 ጊዜ፣ የመለስን ሌጋሲ የሚያጣጥሉ ጽሑፎችን በ6 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ5 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 30 ጊዜ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን የሚያጥላሉ ጹሁፎችን በ7 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ4 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 28 ጊዜ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ5 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 25 ጊዜ፣ አመፅን የሚያበረታቱ ጹሁፎችን በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ5 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 25 ጊዜ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያዋድቁ ጹሁፎችን በ4 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ5 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 20 ጊዜ አቅርቧል።

ግራፍ5፦ ሊያ መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት

VI. ፋክት መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ

ፋክት መጽሄት በዮፋ ኢንተርቴንመንትና ፕሬስ ስራዎች ኃ.የተ.የግ.ማህበር አሳታሚነት እና በሔርቴጅ ህትመትና ንግድ ኃ/የተ/የግ/ማ ማተሚያ ድርጅት በየሳምንቱ የሚታተም መጽሄት ነው። መጽሄቱ ከመስከረም 1/2006 ዓ.ም እስከ ህዳር 30/2006 ዓ.ም ድረስ 12 መጽሄቶችን አሳትሟል። በዚህ የአዝማሚያ ጥናት የተሸፈኑት ህትመቶች 12 ተከታታይ ህትመቶች ናቸው።

መጽሄቱ በ12 የተለያዩ ህትመቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጥላሉ ናቸው። በዚሁ መሰረት መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን ዘገባዎች በ9 የተለያዩ ርዕሶች ስር በ12 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ለ108 ጊዜ አቅርቧል። መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን ጽሁፎችን ከማቅረብ ቀጥሎ በተደጋጋሚ ያነሳው ጉዳይ ህገ-መንግስቱን የሚያጥላሉ ጽሁፎች ናቸው። ይህንንም በ8 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ12 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 96 ጊዜ፣ አመፅን የሚያበረታቱ ጹሁፎችን በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ11 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 55 ጊዜ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ10 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 50 ጊዜ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያዋድቁ ጹሁፎችን በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ9 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 45 ጊዜ፣ የመለስን ሌጋሲ የሚያጣጥሉ ጽሑፎችን በ4 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ11 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 44 ጊዜ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን የሚያጥላሉ ጹሁፎችን በ3 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ8 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 24 ጊዜ አቅርቧል።

ግራፍ 6፦ ፋክት መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ

VII. ጃኖ መጽሄት ከመስከረም 1/2006 እስከ ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት

ጃኖ መጽሄት በአስናቀ ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ሥራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበር አሳታሚነት እና በፋኖስ የህትመት ሥራዎች አታሚነት በየ15 ቀኑ የሚታተም መጽሄት ነው። መጽሄቱ ከመስከረም 1/2006 ዓ.ም እስከ ህዳር 30/2006 ዓ.ም ድረስ 7 መጽሄቶችን አሳትሟል። በዚህ የአዝማሚያ ጥናት የተሸፈኑት ህትመቶች ብዛትም 7 ተከታታይ ህትመቶች ናቸው።

ግራፍ 7፦ ጃኖ መጽሄት ከመስከረም 1/2006-ህዳር 30 /2006 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ህትመቶች ያነሳቸው ጉዳዮች አዝማሚያ

መጽሄቱ በ7 የተለያዩ ህትመቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጥላሉ ናቸው። በዚሁ መሰረት መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን ዘገባዎችን በ13 የተለያዩ ርዕሶች በ7 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ለ91 ጊዜ አቅርቧል። መጽሄቱ የፖለቲካ ስርዓቱን ጽሁፎችን ከማቅረብ ቀጥሎ በተደጋጋሚ ያነሳው ጉዳይ የመለስን ሌጋሲ የሚያጣጥሉ ጽሑፎችን ማውጣት ነው። ይህንንም በ10 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ7 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 70 ጊዜ፣ ህገ-መንግስቱን የሚያጥላሉ ጽሁፎች በ9 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስር በ7 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 63 ጊዜ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን የሚያጥላሉ ጹሁፎችን በ8 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ5 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 40 ጊዜ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ7 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 35 ጊዜ፣ አመፅን የሚያበረታቱ ጹሁፎችን በ5 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ6 ጊዜ ድግግሞሽ ማለትም 30 ጊዜ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚያዋድቁ ጹሁፎችን በ4 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በ7 ጊዜ የድግግሞሽ መጠን ማለትም 28 ጊዜ አቅርቧል።

መጽሄቶቹ በጋራ ያነሷቸው ተደጋጋሚ ጉዳዮች አዝማሚያ

I. ህገ-መንግስቱን ከሚያጥላሉ፣ ከሚያወግዙ እና ሚያራክሱ ጹሁፎች የተወሰደ

§ “ዋስትና አልባ ህይወታችን፣ ዋስትና አልባ ፖለቲካችን” (ፋክት ቅፅ 2 ቁጥር 16፣ ገጽ 14)

§ “… ብዙ የተባለለት፣ መስዋዕት ተከፍሎ ተገኘ የተባለው ሕገ-መንግስት ነጻ የሚያወጣው ሌላ መስዋዕት ከፋይ ትውልድ እየጠበቀ ዕድሜውን ይቆጥራል፡፡” (ዕንቁ ቁጥር 103፣ ገጽ 11)

§ “ይኸውና ለኢህአዴግና በእሱም ለሚመራው መንግስት መከታና ከለላ ከመሆን ባለፈ ለህዝብ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ማግኘት ዋስትና መሆን ያልቻለው ሕገ-መንግስት አሥራ ዘጠነኛ ዕድሜውን እዳሰቆጠረ ሁሉ፣ የጩኸትና የጥይት ፍራቻ ፖለቲካ አዚምም በአገሪቱ ላይ እንደነገሠ ላለመቀጠሉ መተማመኛው ሠነድ የለም፡፡” (ዕንቁ ቁጥር 103፣ ገጽ 11)

§ ‘ፈራሽ ህገ-መንግስት’ በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሥልጣን ቢይዙ የህገ-መንግስቱ ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በማተት “… የህገ መንግስቱን ‘ምሰሶ’ አፍርሶ አዲስ ሕገ-መንግስት ከማርቀቅ ውጪ ሌላ ምርጫ እንዳይኖር ያስገድዳል፡፡” ይላል፡፡ ከዚህም ሌላ ‘የህወሓት ህገ-መንግስት’ በሚለው ን/ርዕስ ስር ህገ-መንግስቱ የአንድ ፓርቲ ፕሮግራም ከመሆኑም ሌላ “‘የህገ-መንግስቱ አረቃቀቅ ሂደትም ሆነ ራሱ ህገ-መንግስቱ የተዋቀረው የመለስን የሥልጣን ጠቅላይነት ህጋዊነት ለማልበስ’ እንደሆነ ይናገራሉ” (ፋክት ቅፅ 2 ቁጥር 23 ገጽ 15፣ ህዳር 2006)

§ ባንዲራችን መሃሉ ላይ በተለጠፈው አርማ ምክንያት ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ሳይሆን መከፋፈላችን የሚያሳይ በመሆኑ ልንከልሰው ይገባል፤

§ ህገ-መንግስቱ ማለት የኢህአዴግን ስልጣን የሚጠብቅ የኢህአዴግ ስልጣን ማለት ነው፤

§ ህገ መንግስቱ ፈራሽ፣ የህወሓት ህገ-መንግስት እንደሆነ ይታመናል የሚሉት ህግ መንግስቱን በማጣጣል ረገድ ከተፃፉት ጹፎች የተወሰዱ ናቸው።

I. በአገሪቱ የተመዘገበ የኢኮኖሚ እድገት የለም በሚል የክህደት አቀራረብ ከቀረቡት ውስጥ የተወሰዱ

§ ኢትዮጵያ በርካታ ዜጎቿ በዘመናዊ ባርነት የሚኖሩባት አገር ሆናለች፤

§ አገሪቱ ከዓለም 10 የተራቡ አገሮች አንዷ ናት፤

§ በማህበራዊ እድገት ከዓለም የመጨረሻዋ አገር ናት፤

§ ኢትዮጵያ በኢህአዴግ አመራር በሰብአዊ ልማት ደረጃ 173ኛው አገር ሆናለች፤

§ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እንደተመዘገበ የሚገለፀው ኢኮኖሚያዊ እድገት የቁጥር ጨዋታ ላይ የተመሰረተ እንጅ በተጨባጭ የሌለ እድገት ነው፤ እድገቱም ፍትህአዊነት በእጅጉ ይጎድለዋል፤ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ እድገት እንዲኖር ያደረገ ነው፤

§ በአገሪቱ ያለው የተዛባ የኢኮኖሚ ስርዓት በአገሪቱ ዜጎች ገቢ መካከል የሰማይና የምድር ያክል ልዩነት ፈጥሮ ጥቂቶች እንደፈለጉ የሚዘሉባትና የሚቦርቁባት አብዛህኛው ዜጋ ደግሞ መፈጠሩን የሚጠላበት አገር ሆናለች፤

§ ኢትዮጵያ በዓመት ከ10 በመቶ በላይ አድጋለች ተብሎ የሚወራልን አሃዛዊ መወዳደሪያ ዕድገትን አያሳይም። ሕወሓት/ኢህአዴግ ድክመቱን በስታቲስቲክስ ለመሸፈን የሚያደርገው ጥረት ነው። በዘመነ መለስ ኢትዮጵያ ክፉኛ ደህይታለች፤

§ አገራችን ላለፉት 22 ዓመታት የኋሊት እየተጓዘች ነው። ችግር እያንዳንዱን ቤት አንኳኳቷል። መንግስት ኃላፊነቱን ረስቷል፤

§ አገዛዙ የሚሰራቸው ፕሮጀክቶች የህዝቡን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ይበልጥ እያወሳሰቡት ነው የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው።

II. የፖለቲካ ስርዓቱን ከሚያራክሱ፣ ከሚያጥላሉና ከሚያወግዙ ጹሑፎች የተወሰዱ

§ መንግስትን በእውነት « የእኛ ነው» የሚያሰኘው ብሄራዊ መግባባት የዜጎች አጠቃላይ ስምምነት ፖለቲካዊ መስፈሪያ የለም፤

§ ኢህአዴግ መንበረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ ወዲህ ባሉት 21 ዓመታት የሀገሪቱ 85 ሚሊዮን ህዝብ አማራጭ ነፃ የመረጃ ምንጭ ሳይኖረው ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ እንዲመገብ እየተደረገ ነው፤

§ ወያኔ ስልጣኑን የሚጠቀመው የኢትዮጵያን ህዝብና ኩራት ለመጠበቅ አይደለም፡፡ ወያኔ ታሪክ የሌለው፣ ባህል የሌለው፣ ሃይማኖት የሌለው፣ ሰብዓዊነት በእጅጉ የተሳነው ነው፤

§ ኢህአዴግ ፈርቷል። በመሆኑም የተለያዩ አፈናዎችን እያደረገ ይገኛል። ሰላማዊ ሰልፍን ብቻ ሳይሆን አደባባይ ጭምር መፍራት ጀምሯል። የሚፈራውን እንኳን መለየት አልቻለም፤

§ ሕወሓት ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያለ የጥንቱን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ፅንፈኛ እና ጎጠኛ አካሄድ ያላቸው ሰዎች አሉ። ለእነሱ የትግራይ በተለይም የትውልድ መንደራቸው እንጂ የኢትዮጵያ ዕጣ ችግራቸው ወይም የሚያሳስባቸው ጉዳይ አይደለም። የጎጠኝነት እንጂ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ የላቸውም።

§ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅና የደህንነት አዋጆች የወጡት የተወሰነ ቡድንን /የሠራዊቱንና የደህንነት ሠራተኞችን/ ከተጠያቂነት ለማዳንና ያለማንም ሃይ ባይ ያሻቸውን የሚያደርጉበት ዕድል ለማመቻቸት ነው፤

§ ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥር ስፍር የሌላቸው እስረኞች አሉ። እስሩ ፖለቲካዊ አይደለም ይባል እንጂ ፖለቲካዊ ነው። እኔ የማውቃቸው ሰዎች አሉ። ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስር ቤት ገብተው ዛሬም የታሰሩበትን ምክንያት ሣያውቁ እስር ቤት የሚማቅቁ ዜጎች አሉ። (አቶ ሙሼ ሰሙ)

§ ..በሀገሪቱ ያለው ሁሉም አሠራር አምባገነናዊ አሠራር ነው፣ (አቶ ቡልቻ ደመቅሳን በመጠየቅ የቀረበ)

§ ኢህአዴግ ፈርቷል። በመሆኑም የተለያዩ አፈናዎችን እያደረገ ይገኛል። ሰላማዊ ሰልፍን ብቻ ሳይሆን አደባባይ ጭምር መፍራት ጀምሯል። የሚፈራውን እንኳን መለየት አልቻለም፤

§ አሁን ያለው አምባገነን ስርዓት ያልተረጋጋና ጉልበት አልባ በመሆኑ የለውጡ አይቀሬነት ማሳያ ነው፤

§ 1 ለ5 አደረጃጀት የግለሰቦችን ነፃነት ለማፈን የመጣ የአምባገነኖች መሣሪያ ነው፤

§ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባልተካሄደባት ሀገር የባቡር ቀለም ምረጡ ሲባል በህዝብ ላይ ማፌዝ ነው፤

§ ኢህአዴግ ማንኛውንም ለፖለቲካ ስጋቱ የሁኑትን በመፈራጅ ማስፈራረትን ተግባሩ አድርጎታል። ተቃውሞ ስለበዛበት ያለው አማራጭ ማፈን ነው። እንደ መንደር እንጂ እንደ ሀገር መነጋገር አይፈልግም፤

§ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል። ሰላማዊ ትግል ማድረግ አይቻልም። ነፃነት የለም፤

§ የመንግስት ባለስልጣናት ከ1997 በፊት ይፈፅሙት የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና አፈናዎች መንግስት ከ1997 በኋላ ህጋዊ አድርጎታል፤

§ አቶ በረከት ስምኦን፣ ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ እና አቶ አባይ ፀሓዬ የጠ/ሚ/ሩ አማካሪ ሆነው የተሾሙት ስልጣኑን ለመቀራመት ነው፤

§ የሕወሓት የፖለቲካ ልዩነት አፈታት በተንኮል ነው። በኢትዮጵያ በነፃነት የመንቀሳቀስና የመስራት መብት የተገደበባት ሀገር ናት። ኢህአዴግ የብሔር መብትን ለማስከበር ጀማሪ አይደለም። አሁን እየተከተለ ያለው ስርዓት የፋሽስት ጣሊያንን ነው። የዜጎች ክብር ተነክቷል። በነፃነት መናገርና መፃፍ አይቻልም፤

§ አሁን በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረው የዕርስ በርስ ሽኩቻ በፓርቲው የወቅቱ ሊ/መንበር አባይ ወልዱ እና በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል መካከል እየተደረገ ያለ ነው። ሕወሓት ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያለ የጥንቱን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ፅንፈኛ እና ጎጠኛ አካሄድ ያላቸው ሰዎች አሉ። ለእነሱ የትግራይ በተለይም የትውልድ መንደራቸው እንጂ የኢትዮጵያ ዕጣ ችግራቸው ወይም የሚያሳስባቸው ጉዳይ አይደለም። የጎጠኝነት እንጂ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ የላቸውም። መለስ አምባገናን መሪ እንደነበሩ መናገር ሙት ወቃሽ ቢያስብልም እውነት ስለሆነ ልንክደው አንችልም።

§ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ወንጀል ሆኖ ባለሙያዎች ዘብጥያ እየተወረወሩ ቃሊትም የጀግኖች ማጎሪያ ሆናለች የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

III. ሽብርተኝነትን በማበረታታት ረገድ
(የተከሰሱ ግለሰቦችን በማጉላት፣ ተሸለሙ፣ ለሽልማት ታጩ…)

IV. ሽብርተኝነትን ከሚያበረታቱና ሽብርተኞችን ከሚያሞካሹ ጹሑፎች የተወሰዱ

§ በሽብር ተግባር ተከሰው የተፈረደባቸውን ግልሰቦች በማሞካሸት ለምሳሌ “ከህሊና ዕዳ ነፃ ሆኖ የዕድሜ ልክ እስር የተፈረደበት ወንድማችን አንዱዓለም አራጌ…” (ፋክት ቅፅ 2 ቁጥር 22፣ ገጽ 9) የህ/ተ/ም/ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ የጻፉት

§ “… ኢህአዴግ ራሱ በፈለሰፈው እና የተቀረው ዓለም በማይስማማበት ሽብርተኝነት ስም እየነገደ … መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡” (ጃኖ ቅፅ 1 ቁጥር 19 ገጽ 12፤ ህዳር 2006 ዓ.ም.)

§ “ኢህአዴግ ዛሬ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ሽብር፣ የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄን ሽብር፣ ጋዜጠኝነትን ሽብር፣ መደራጀትን ሽብር፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽን ሽብር በማለት ህዝብን ሲያሸብር ይታያል፡፡ … የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዴግ መሸበሩንና መማረሩን እየገለፀ ነው፡፡” (ጃኖ ቅጽ 1 ቁጥር 14 ገጽ 5)፣

§ “ኢህአዴግ የሚያሳስበው የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳይ ሳይሆን የብዝበዛ መዋቅራቸውን የሚነካ ኃይል ሁሉ በአሸባሪነት በመፈረጅ የብዝበዛ ተግባራቸውን ከግብ ለማድረስ የመንግስት ሽብርተኝነትን እያቀጣጠሉ መሆኑ ነው፡፡” (ጃኖ ቅፅ 1 ቁጥር 14፣ ገጽ 5)

§ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነት ያሰጋታል ከተባለ ስጋቱ ከመንግስታችን አምባገነን ባህሪ የሚመነጭ ነው፤

§ አንዱዓለም አራጌ እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በአኩሪ ተግባራቸው ትልቅ ቦታ እንሰጣቸዋለን። ለመንግስት አሸባሪ ቢሆንም ለእኛ ግን የሰላም ታጋይ ነው፤

§ የፀረ-ሽብር ህጉ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ አይደለም። የፀረ-ሽብር ህጉ ራሱ ህገ-ወጥ ነው የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

V. አመፅን ከሚያበረታቱ፣ ከሚጠሩና ለአመፅ ከሚያነሰሳ ጹሑፎች የተወሰዱ

§ በአዲሱ 2006 ዓመት የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም አካል ሊነሳ ይገባል፤ አገሪቱ የፖለቲካና የስርዓት ለውጥ ያስፈልጋታል (አዲስ ጉዳይ መስከረም 2006)

§ “የለውጥ ሃዋርያት ወደአደባባዩ ይጎርፉ ዘንድ ወቅቱ ግድ ብሏል፤” (ፋክት ቅጽ 2 ቁጥር 17፣ ገጽ 32 አንድ በሉ በሚለው አምድ ስር ተመስገን ደሣለኝ የፃፈው)

§ “ከኢህአዴግ በኋላ የሚተካው አማራጭ ተዘጋጅቷል? … ይህንን ቀዳዳ አስቀድሞ መድፈኑን አስቸኳይ ያደረገው፣ ለውጡ የሚመጣበት መንገድ ከህዝባዊ እምቢተኝነት ይሆናል የሚለው ቅድመ-ግምት ነው፡፡” (ፋክት ቅፅ 2 ቁጥር 12፣ ገጽ 5 መስከረም 2006 ዓ.ም. አንድ በሉ በሚለው አምድ ስር ተመስገን ደሣለኝ የጻፈው)

§ አሁን ባለው ሁኔታ ትግሉን በህዝቡ መካካል በማካሄድ አመፁ ህዝቡ ባለባቸው ቦታዎች በሙሉ በተቀናጀና በተፋጠነ መንገድ ማካሄድ ያስፈልጋል፤

§ “ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና ፓርቲያቸው አንድነት ‘ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግር እንዲደረግ ምኞታቸው ከፍተኛ ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ የዘጋው ዴሞክራሲያዊ መንገድና ዜጎች እየደረሰባቸው ካለው ስቃይ አንጻር ወደህዝባዊ አመፅ የሚቀየር ነገር ኖሮ ወደሦስተኛው አብዮት ነገሮች ቢገፉ ተጠያቂው መንግስት እንደሚሆን ሊታወቅ እንደሚገባ’ አቤት በማለት ላይ ናቸው፡፡” (ዕንቁ 6ኛ ዓመት ቁጥር 103፣ ገጽ 10፤ ጥቅምት 2006)

§ “መንግስት ያለው በጠመንጃ ነው፡፡ ህዝብ የመረጠው መንግስት አይደለም፡፡” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከሰጠው ቃለ ምልልስ የተወሰደ (ዕንቁ ቁጥር 105፣ ገጽ 20)

§ “ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ አቅም መገንባት ያልቻለ መንግስት፣ የተሻለ የዲፕሎማሲ አቅም የሌለው ገዥ ፓርቲ፣ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የማያስብ አስተዳደር ተሸክሞ ከመኖር አንዴ ሸክሙን አራግፎ መገላገል ይሻላል። አለበለዚያ እኛ የአባቶቻችን ልጆች አይደለንም ማለት ነው።” (ፋክት ቅፅ 2 ቁጥር 21፣ ገጽ 15፤ ህዳር 2006)

§ በአገሪቱ ታሪክ በሰላማዊ የትግል መንገድ ወይም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስርዓት ሲለወጥ አይተን አናውቅም፤ ስለዚህ ይህንንም ስርዓት ለመለወጥ ካለፉት የስርዓት ተሞክሮዎቻችን ልንማር ይገባል፤

§ ኢትዮጵያ ታማለች፣ ተወጥራለች፣ በአደገኛ መርዝ ተበክላለች፣ ውስጧ ነፍሯል፣ እያቃተተች ነው፣ ቆዳዋ ሳስቷል፡፡ የሚደርስላትና የሚሰማት ስላጣች የያዘችውን ይዛ ልትነጉድ ከጫፍ ላይ ነች፡፡ ማጣፊያው ሳያጥር ሁሉም መንገዱን ይመርምር፤

§ የለውጥ መንገዶች ሁሉ ሄደው ሄደው ወደአደባባይ የሚገፉ ሆነዋል፤ መንግስትን ተሸክሞ ከመኖር አንዴ አራግፈን ካልጣልን የአባቶቻችን ልጆች አይደለንም፡፡ ለለውጥ ካልተነሳን ስደቱ፣ ርሃቡ፣ ችግሩ፣ የተበላሸው ፖለቲካ ይቀጥላል፤

§ በተበከለ ትዕዛዝ የቆሰለ ህዝብ የሚፈወሰው ንፅህናው በተጠበቀ አዲስ መንግስትና አዲስ ትዕዛዝ በመሆኑ ተቃውሞህን በወቅቱ ማፈንዳት አማራጭ የሌላው ነው፤

§ ከሩቅም፣ ከቅርብ ያለን ነፃነትን የተራብን ኢትዮጵያውያን ሁሉ የዶ/ር ነጋሶ ፓርቲ መስከረም 19 ቀን በጠራው ሰልፍ በመሳተፍ፣ መሳታፍ ያልቻልን በሙያችንና በምንችለው መንገድ ከያለንበት ድጋፍ በመስጠት አጋርነታችንን እንግለፅ!..ሁላችንም በየተራ መታሰራችን ይቀጥላል፤

§ የነጻነትን ዋጋ ነጻነቱን ከተቀማ ህዝብ በላይ የሚያውቀው የለምና አሁንም ነጻነቴን ይላል፤

§ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ተረድቶ እጁን መስጠት አለበት፡፡ ትርጉም የሌለው የሃይማኖት፣ የብሄርና የኢኮኖሚ ዕድገት ፕሮፓጋንዳ አይቀሬ ከሆነው ውድቀት አያድኑም የሚሉት ተጠቅሰዋል።

VI. የመንግስትን ኃላፊዎች የሚያጥላሉ ጽፎችን በተመለከተ

§ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚ/ር ስራ ከመስራት ይልቅ በሁሉም ነገር መለስን መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማርያም ለአሸናፊው ኃይል አገልጋይ ከመሆን ያለፈ ሚና የለውም፤

§ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ትልቁ ደካማ ጎናቸው መለስን ሲያዩ መርበትበትና ነባር ታጋዮችን መፍራት ነው፤ የፕሬዝደንቱ ሹመት ምንም ተፅዕኖ መፍጠር አያስችልም፤ ወንበሩም የቀልድ ስልጣኑም የቀልድ ነው፤

§ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከአምባገነንነትም በላይ ሰዎቹ እንደታመሙ ነው የተረዳሁት፤ ሥር የሰደደ የቁስ ሰቀቀንና የሥልጣን ጥም የተጣባቸው፣ የትኛውንም ዓይነት ውርደት ለመቀበል የቆረጡና የሞራል ልዕልናቸውን ሙሉ በሙሉ ያጡ ናቸው። (ፋክት መጽሄት)

§ በስርዓቱ ውስጥ በየደረጃው ያለው የአመራር አካል በራሱ የማይተማመን፣ ለህግና ስርዓት ደንታ የሌለው፣ ተጠያቂነትና ተቆርቋሪነት የማይሰማው፣ ለህዝብ ያለው ውግንና የወረደ ነው፤

§ ከመንግስት ጋር በልማትና በሰላም የተባበሩ የሀይማኖት አባቶችን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን፣ ድርጅቶችንና ተቋማትን ጭምር በማንሳት የማብጠልጠል ስራዎች በተደጋጋሚ ተሰርቷል።

የመጽሄቶቹ የጋራ መለያ ባህሪያት

ü የመረጃ ምንጮቻቸው

የሁሉም መጽሄቶች የጋራ የመረጃ ምንጮች የሚከተሉት ናቸው።

s የኒዮ ሊበራል አክራሪ ኃይሎች ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች፣

s ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ እጅግ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች፣

s በሽብር ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቀዳሚ የመረጃ ምንጨቻቸው ናቸው።

የሁሉም ጹፎች ይዘት የሚያተኩሩት በሚከተሉት ጉዳዮች ነው።

s አሉታዊ ጉዳዮችን በማራገብ፣

s መረጃዎችን አዛብቶ በማቅረብ፣

s መንግስት በልማት፣ በሰላምና በዴሞክራሲ መስኮች ያመጣቸውን ለውጦች የሌሉና መሬት ላይ የማይታዩ እንደሆኑ በማስመሰል፤

s ህዝቡ ከችግር ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ላይ የሚያሾፉና የሚያንኳስሱ፣

s ለአገሪቱን ዜጎች እና ለውጭው ማህበረሰብ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት በስርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጣና ጥያቄ እንዲያነሳ የሚያበረታቱ፣

s ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ዜጎቿ በስቃይና በእሮሮ የሚኖሩባት ምድር እንደሆነች፣ ያለህግና ስርዓት ዜጎች የሚታሰሩባት፣ የሚገደሉባትና የዴሞክራሲ ጭላንጭል የማይታይባት፣ በጥቅሉ ተስፋ የሌላት አገር እንደሆነች የሚገልፁ ሀሰተኛ መረጃዎችን መስጠት፣

s የአገሪቱ የተለያዩ ተቋማት(ህገ መንግስቱን ጨምሮ የፍትህ ተቋማት፣የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የህዝብና የመንግስት ሚዲያው፣ የመከላከያ ሰራዊቱ፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች) ታምኝነት የሌላቸው፣ ነፃና ገለልተኛ ሆነው የማይሰሩ እንደሆነ በተለያዩ መልኩ ገልፀዋል።

ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች እንደተጠበቀ ሆኖ መጽሄቶቹ አጀንዳ የሚቀባበሉ እንደሆነ የሚያመላክቱ ነጥቦች አለ። ስም ወይም ማንነታቸውን የማይገልጹ ጹሁፎችን ይዞ መውጣት በብዛት ይታያል። መጽሄቶቹ በብዙ ባህሪያቸው የግል ሚዲያ ሳይሆን የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳናት ሆነዋል። በአጭሩ ህትመቶቹ በሚያቀርቧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ይዘት ህዝቡ በስርዓቱ እምነት አጥቶ ለአመፅ እንዲነሳሳ እና በሌሎች የቀለም አብዮት ባስተናገዱ አገሮች የታዬውን ቅኝት የሚከተሉ ሆነው ይታያሉ።

***********

Daniel Berhane

more recommended stories