የሶስት ጓደኞች ኣለም – ኢትዮጵያ

(Jossy Romanat)

እኔ፣ መስፍንና ካሕሳይ ጓደኛሞች ነን፡፡ ብዙ ጊዜ ኣብረን እናሳልፋለን፡፡ በብዙ የኣለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እንስማማለን – በቢራ ምርጫችንም እንዲሁ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ በተመለከተ ግን ብዙ ልዩነት ኣለን፡፡ ከማንስማማባቸው ጉዳዮች ኣንዱ ለቀድሞዎቹ ኣፄዎች ያለን ኣመለካከት ነው – ‘ኣፄኣዊ’ እይታችን የተለያየ ነው፡፡

የመስፍን እይታ – መስፍኔ የዲሞክራሲና ሰብኣዊ መብት ተከራካሪ ነው (ራሱን “ኣክቲቪስት” እያለ ነው የሚጠራው)፡፡ ኣባቱ በደርግ ጊዜ የባህር ሃይል ኣባል ነበሩ – ኣሁን በስደት ኣሜሪካን ኣገር ናቸው፡፡ መስፍን ወያኔን ኣብዝቶ ይጠላል፡፡ ወያኔ ብሄር ብሄረሰብ ብሎ በታተነን፣ በቋንቋቹ ተማሩ ብሎ እርስ በርሳችን እንዳንግባባ ኣደረገን፣ ያለ ወደብ፤ ያለ ኤርትራና ያለ ባህር ሃይል ኣስቀረን ይላል (ኤርትራውያ ነፃነት ፈልገው 30 ኣመት ሙሉ ያደረጉት ትግልና ለከፈሉት ደም እውቅና ኣይሰጥም)፡፡ መስፍን ሲበዛ የኣፄ ሚኒሊክ ኣድናቂ ነው፡፡ የዲሞክራሲና የሰብኣዊ መብት ኣክቲቪስት ነኝ ይላል እንጂ ኣፄ ሚኒሊክ ደቡብና ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ያደረሱት ሰብኣዊ እልቂትና የማንነት ማጥፋት ዘመቻ እንደ ችግር መቀበል ኣይፈልግም – እንደዉም “የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስፋትና ኣገሪቷን ኣንድ ለማድረግ የወሰዱት እርምጃ ስለሆነ ትክክል ነው” ብሎ ይከራከራል እንጂ ስህተት ነበር ብሎ መቀበል ኣይፈልግም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሰውዬው “የሞኣ ኣንበሳ -ዘነገደ ይሁዳ – የሰለሞን ዘር” ነኝ እንጂ እንደ ማንም ተራ ኢትዮጵያዊ ኣይደለሁም፡፡ ስልጣን የሚገባው ለኔና ለቤተሰቤ ብቻ ነው ማለታቸውን እንደ ችግር ኣያየውም፡፡ የሚሳሳላት ኤርትራ እንኳን በወቅቱ በኣፄ ሚኒሊክ ስምምነት/ፌርማ ከኢትዮጵያ እንደተለየች ማመን ኣይፈልግም፡፡ በሌላ በኩል መስፍን ኣፄ ዮሃንስን በጣም ይጠላቸዋል- እንደዉም ኣፄ ዮሃንስ ከኣፄ ቴዎድሮስ ስልጣን ለመንጠቅ ብለው ከእንግሊዞች ጋር ተባበሩ፣ እንግሊዞችን መንገድ መርተው ወደ መቅደላ ኣሻገሯቸው እያለ ይከሳቸዋል- ‘ባንዳ’ ነገር ናቸውም ይላል፡፡ ወሎ ላይ ህዝብን ሃይማኖቱ እንዲለውጥ ኣስገድደዋል፣ ገድለዋል ብሎም ይወቅሳቸዋል፡፡ በዚህ ዘመን ኣፄ ሚኒሊክ የሰሩት ጥፋት ሁሉ ተሸፋፍኖ የኢትዮጵያ ኣባት “እምዬ” ተብለው በክብር እንዲጠሩና እንዲከበሩ ይፈልጋል (በ21ኘው ዘመን በምእራቡ ኣለም የሰብኣዊ መብት ኣክቲቪስት ሆኖ የ19ኛው ዘመን ጨፍጫፊን የሚያደንቅ)፡፡

የካሕሳይ እይታ – ካሕስሽ ምርጥ የማእድን ምህንድስና ባለሙያና ሃይለኛ የወያነ ደጋፊ ነው፡፡ ወያነ ብሄር ብሄረሰቦች ከነበረባቸው የማንነት ጭቆና ነፃ ወጥተው በቋንቋቸውና በባህላቸው እንዲኮሩና እንዲጠቀሙ ኣድርጓል የሚል እምነት ኣለው፡፡ በልማትም ኣገራችን በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘች ነው- ኣንዳንድ የሚታዩ የዲሞክራሲ ችግሮች በሂደት የሚፈቱ ናቸው ብሎም ያምናል፡፡ ኣፄ ሚኒሊክን ኣብዝቶ ይጠላል፡፡ በደቡብና በምእራብ ኢትዮጵያ ያደረሱት በደል ያንገሸግሸዋል፡፡ ኤርትራ ለትንሽ መሳሪያ ድጋፍ ብለው ውጫሌ ላይ ተዋውለው ለጣልያን መሸጣቸው ያናድደኛል ይላል፡፡ ኣፄ ሚኒሊክ ፀረ-ትግራይ ነበሩ – ኤርትራ ካሉ ትግርኛ ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ሆን ብለው ለያዩን ብሎም ያዝናል (እሱም ኤርትራውያ ነፃነት ፈልገው 30 ኣመት ሙሉ ያደረጉት ትግልና ለከፈሉት ደም እውቅና ኣይሰጥም)፡፡ በሌላ በኩል ካሕሳይ ሲበዛ የኣፄ ዮሃንስ ኣድናቂ ነው፡፡ ያገርን ዳር ድንበር ያስከበሩ፣ ለኣገራቸው እየታገሉ የሞቱ ጀግና ይላቸዋል፡፡ ከመስፍን ጋር ሲከራከሩ “ኣፄ ዮሃንስ ወሎ ላይ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ያስቀየሩት፣ ያፈናቀሉትና ያስገደሉት የውጪ ኣገር ወረራ ስጋት ስለነበረባቸውና ለኢትዮጵያ ኣንድነት በመስጋት ነው – እናም ኣስፈላጊ ነበር” ብሎ ይከራከራል እንጂ ስህተት ነበር ማለት ኣይፈልግም፡፡ የ”ሞኣ ኣንበሳ ዘነገደ ይሁዳ” ነኝ እንጂ እንደ ማንም ተራ ኢትዮጵያዊ ኣይደለሁም – ስልጣን የሚገባው ለኔና ለኔ ቤተሰብ ብቻ ነው ማለታቸውን እንደ ችግር ኣያየውም፡፡ እንደዉም በዚህ ዘመን ኣፄ ዮሃንስ ምንም ጥፋት የሌለባቸው ያገር ድንበር ኣስከባሪ ተብለው በክብር ኣለመዘከራቸው ያንገሸግሸዋል (ሃይለኛ የህወሓት/ወያነ ደጋፊ ሆኖ እንዴት የኣፄው ኣድናቂ መሆን እንደሚቻል ባይገባኝም በቃ ካሕሳይ ግን እንደዛ ነው)፡፡

የኔ እይታ – መስፍን የኣፄ ሚኒሊክ ጥፋትና የኣፄ ዮሃንስ በጎ ስራ ኣይታየዉም፡፡ ካሕሳይም እንዲሁ የኣፄ ሚኒሊክ በጎ ስራና የኣፄ ዮሃንስ ስህተት የሚያይ ኣይን የለዉም፡፡ እኔ ደግሞ የባስኩ በሁለቱም ኣፄዎች መካከል ያለው ልዩነት ያልገባኝ ደነዝ ዜጋ፡፡ “እናንተን ለመግዛት ከእግዚኣብሄር የተላክን ምርጦቹ የሰለሞን ዘሮች ዘነገደ ይሁዳ ነን፣ የናንተ ፈንታ እኛን በግብርም በወታደርነትም ማገልገል ብቻ ነው” እያሉ ህዝቡን የገዙት ኣፄ ዮሃንስና ኣፄ ሚኒሊክ መካከል ያለው ልዩነት ኣልታይ ብሎኛል፡፡ ያው በኣጭሩ ሁሉም የራሳቸው ስርወ-መንግስት ማስቀጠል ብቻ የሚያልሙ ፊውዳሎች ነበሩ – ኣላማቸዉም ሲመች በሃይማኖት ስም ሲብስ ደግሞ በነፍጥ የሚያስፈፅሙ ጉልበተኞች፡፡ በዚህ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ በነበረባቸው የትግል ሂደት ውስጥ ከኣገር ውስጥ ተቀናቃኝም ከውጭ ኣገር ወራሪም ጋር ተዋግተዋል- በዚሁ ሂደት ኣገሪቷን ከቅኝ ግዛት ኣድነዋታል – ሁለቱም ብዙ ችግርና ትንሽ ኣስተዋፅኦ ያላቸው መሪዎች ናቸው – ለኔ፡፡ ፊውዳላዊ ዝምድናችውና ስርወ-መንግስታቸው ለማስቀጠል ሁለቱም ኣፄዎች በልጆቻቸውና በልጅ ሎጆቻቸው ኣማካኝነት የጋብቻ ትስስራቸውን ቀጥለው ነበር::: ይሄ ዝምድናና ፊውዳላዊ ትስስር ትግራይ ውስጥ ኢዲዩ በሚል ስም ሲንቀሳቀስ ከቆየ በኋላ በ1960ዎቹ መጨረሻ በህወሓት ተመትቶ ወደ ሱዳን ገብቶ ተበታትኗል፡፡ የሁለቱም ኣፄዎች የስልጣንና የፖለቲካ ጥያቄ መሰረት ከእስራኤል የመጣው “ሰለሞናዊና ይሁዳዊ ምርጥ ዘርነት” እንጂ ኢትዮጵያዊነታቸው (ወይም ሸዋና ትግራዋይነታቸው) ኣልነበረም- የስልጣንና የፖለቲካ ኣላማቸው የኢትዮጵያን ህዝብና የጭቁኑ ገበሬ ጥያቄና ችግር መፍታት ኣልነበረም፡፡ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የሰሩት ይህ ነው የሚባል ተግባር የላቸውም፡፡ ኣፄ ዮሃንስ ኣብዛኛው ጊዜኣቸው በጦርነት ነው ያሳለፉት (ከውጪና ከውስጥ ሃይሎች ጋር) – ኣፄ ሚኒሊክም መስፍኔ ለኢትዮጵያ ኣስተዋፅኦ ኣድርገዋል ብሎ የሚያነሳው ስልክም፣ መኪናም ሌሎች ዘመናዊ ቁሳቁሶች ለራሳቸው ምቾትና ቅንጦት እንጂ ለሰፊው ህዝብ ምኑም ነው፡፡ ገበሬውማ ገና ኣሁን ከ100 ኣመት በኋላም በቅጡ ኣልደረሰዉም፡፡ ደግሞስ መሬቱን ቀምተህ ቴሌፎን ብታስገባለት ምን በበላ ኣንጀቱ ሊያናግርበት ነው፡፡

ሚስኪኑ የሸዋ ህዝብ ከኣፄ ሚኒሊክ ያተረፈው ነገር ቢኖር በዋሉበት ጦርነት ሁሉ እየተከተለ መዋጋትና መሞት እንዲሁም ረሃብና ቸነፈር ነው፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ከኣፄ ሚኒሊክ ያተረፉት ነገር ከማንነታቸው በተጨማሪ ሰፋፊ መሬቶቻቸው በጥቂት የፊውዳል ቤተሰቦችና ጥቂት ነፍጥ ተሸካሚ ኣገልጋዮች እጅ መውደቁ ነው፡፡ የ1966ቱ ኣብዮት እስኪፈነዳ ድረስ ደቡቦች በገዛ መሬታቸው ጭሰኛ ሆነው ጥቂቶችን እያገለገሉ ኖረዋል፡፡ የትግራይ ገበሬዎችም ቢሆኑ ከኣፄ ዮሃንስ ያተረፉት ነገር ጦርነት በተነሳ ቁጥር ንብረታቸውንና ህይወታቸውን መገበርና ርሃብና እንግልት ነው፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ገበሬዎች ያህል ባይሆንም በኣፄ ሚኒሊክና ኣፄ ዮሃንስ የንጉስ ዘሮች ብዙውን መሬት ተቆጣጥረው ገበሬውን እያሳረሱ ኣንድ ሶስተኛውን ምርት ብቻ እንዲወስድ ኣድርገው ኣገልጋያቸው ኣድርገውታል፡፡ ሰው የተባለ በሶስት ከፋፍለው (ሰብ – ሰባሰብ – ኣንካኪኖስ) ሰብኣዊ ማንነቱን ኣዋርደው ገዝተውታል፡፡ የ1966ቱ ተከትሎ በከተሞች ኣካባቢ እንዲሁም ህወሓት ኢዲዩ የተባለውን ስብስብ ከትግራይ ምድር ጠራርጎ ኣስወጥቶ በ1970ዎቹ መጀመሪያ የገጠር መሬት ሸንሽኖ ጭቁኑ ገበሬ፣ ወጣቶችና ሴቶች የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ እስኪያደርግ ድረስ የትግራይ ገበሬዎችሞ በገዛ መሬታቸው የፊውዳሎች ኣገልጋይ ነበሩ፡፡

ኣዎ – በኣንድነት ስም የኢትዮጵያን ህዝብ በጨፈጨፉና በፈጁት በኣፄ ቴዎድሮስና ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም መካከል እንዲሁም በፊውዳሎቹና “ምርጥ ዘሮቹ” ኣፄ ዮሃንስ፣ ኣፄ ሚኒልክና ኣፄ ሃይለስላሴ መካከል ያለው ልዩነት እስከ ኣሁን ያልታየኝ ደንባራ ፍጡር ነኝ፡፡ የኣፄ ሚኒሊክና የኣፄ ዮሃንስ ኣድናቂዎች መሰረታዊ ልዩነት ኣልገባኝም፡፡ እኔ ሁለቱም ላይ ምንም ኣይነት ጥላቻ የለኝም – የሰሩት ጥሩና መጥፎ ነገር እንደ ኢትዮጵያ ታሪክነቱ ማየት ብቻ የምፈልግ ሰው ነኝ፡፡ ሆኖም ግን መስፍኔና ካሕስሽ በዚህ ዘመን የዚህ ትውልድ ኣባል ሆናችሁ ኣፄዎቹን እንደ ሞዴል ስትቆጥሩና በነሱ ዘመን እንድንኖር ስትወተውቱ ያንገሸግሸኛል – “የራሴን ዘመን ልኑርበት” ብለህ ጩህ ይለኛል፡፡ ኣፄዎቹ ጥሩም ሰሩ መጥፎ ኣሁን ያለቸው ኢትዮጵያ ዛሬና ነገ እንዴት የተሻለች መሆን ትችላለች የሚለው ነው ውድ ጊዚኣችሁን የሚፈልገው፡፡

**********

Jossy Romanat

more recommended stories