የኢህኣዴግ ፖሊሲዎች Vs የማስፈፀምና የኣቅም ችግር

ዞሮ ዞሮ ግን የማስፈፀም ስራው ብዙ ከተጓዘና ችግር ከተፈጠረ በኋላ “ግምገማ” ያካሂዱና ያ “ፀረ-ልማት” ያሉት ሰውዬ የነገራቸውን ነገር ትልቅ ችግር እንደነበረ በግምገማ ማረጋገጣቸውን ይነግሩንና ጉዞው ይቀጥላል፡፡

(Jossy Romanat)

በኔ እምነት ብዙዎቹ የኢህኣዴግ ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች በትክክል የህብረተሰቡን ችግርና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ናቸው ማለት ይቻላል – ብዙ ጊዜም ደሃ -ተኮር ናቸው ፡፡ በፖሊሲ ደረጃ የተለየ ኣማራጭ ኣምጥተህ ኢህኣዴግን መርታት ከባድ ነው፡፡ ፖሊሲዎች የሚወርዱት ከላይ ወደ ታች ነው (Cascade Approach)፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጁ ፖሊሲዎች በየደረጃው ላሉ ኣመራሮች በየደረጃው ስልጠና ይሰጣቸውና ያስፈፅማሉ፡፡ ችግሩ ያለው ከላይ ወደ ታች ስትወርድ የሃላፊዎቹና የኣስፈፃሚዎቹ ኣቅም፣ ችሎታና የግንዛቤ ብቃት በጣም እያሽቆለቆለ የሚሄድ መሆኑ ነው፡፡ ከላይ የተሰጣቸውን ስልጠናና ኮንፈረንስ እንዳለ መቀበልና ማስተጋባት እንጂ ስለዛ ጉዳይ የራሳቸው እውቀትና ክህሎት ጨምረው ያላቸውን ግንዛቤ የማስፋት ፍላጎትና ባህል የሌላቸው ሰዎች ጉዳዩን ኣስፍተው/በጥልቀት ኣይረዱትም፡፡ እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ዋና ኣስፈፃሚዎች በመሆናቸው ኣንዳንድ ጊዜ በደንብ ሳይገባቸውና ለምን እንደሚያስፈፅሙት ሳያውቁ (ከላይ ስለመጣ ብቻ) ብዙ ሃብት ኣባክነው ፖሊሲው ሲፈፀም የሚጠበቀው ለውጥ ሳይመጣ ይቀራል፡፡ ለምን ኣልተሳካም ሲባል የኣፈፃፀም ችግር ነው ይባላል፡፡

በእርግጥ በየደረጃው ያሉት ሹመኞችና ማሰፈፀም ያለባቸው የድርጅታቸውን ፖሊሲና ትእዛዝ ነው – ሆኖም ግን የኣቅምና የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰዎችን መመደብ ብዙ ጉልበትና ሃብት እንዲባክንና ድርጅቱም የሚፈልገውን ለውጥ እንዳያመጣ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ችግሩ የሚባባሰው ደግሞ በማስፈፀሙ ሂደት ላይ እንደዚህ ኣይነት ችግር ኣለ ብሎ የሚነግራቸው ሰው ኣለመውደድና እንደ ጠላትና ፀረ-ልማት ሃይል ማየታቸው ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የማስፈፀም ስራው ብዙ ከተጓዘና ችግር ከተፈጠረ በኋላ “ግምገማ” ያካሂዱና ያ “ፀረ-ልማት” ያሉት ሰውዬ የነገራቸውን ነገር ትልቅ ችግር እንደነበረ በግምገማ ማረጋገጣቸውን ይነግሩንና ጉዞው ይቀጥላል፡፡

ኣስተሳሰቦችና ፖሊሲዎች በተዋረድ ከላይ ወደ ታች በሚወርዱበት ጊዜ (Cascade Approach) በሚታየው የኣቅም ማነስና ያንን ተከትሎ የሚፈጠር በትክክል ያለመገንዘብ ችግር በምናባዊ ምሳሌ ብናይ (በከፊል እውነት ሊሆን ይችላል) እንዲህ ይመስለኛል፡፡

ኣንድ በጣም ብቁ የሆነ የኢህኣዴግና የመንግስት ከፍተኛ አመራርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የክልል ሃላፊዎችና ኣሰፈፃሚዎችን ሰብስቦ ስለ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራተጂ ገለፃ ያደርግላቸውና በማጠቃለያው እንዲህ ይላል … “እኛ የኒዮሊበራል ኣስተሳሰብ ኣንደግፍም፡፡ ኒዮሊበራሎች የገበያ ኣክራሪነት (Market conservatism) ኣስተሳሰብ ኣላቸው፡፡ መንግስት ከገበያ እጁን ማውጣት ኣለበት፣ ኣሳላጭ ነው መሆን ያለበት፣ ተመልካች ነው መሆን ያለበት ነው የሚሉት፡፡ እኛ ደግሞ ገበያ ውስጥ ያሉትን ችግሮች (Market failures) ለመፍታት Government Intervention ያስፈልጋል ነው የምንለው፡፡ ይሄ ማለት መንግስት በገበያው በሰፊው ገብቶ እርምጃ መውሰድ ኣለበት፣ ትላልቅ የመሰረተ ልማት ስራዎችን መስራት ኣለበት እንላለን፡፡ እነሱ ይሄን ይቃወማሉ፡፡ ስለዚህ ትግላችን ከኒዮሊበራሊዝምም ጋር ነው፡፡”

ከሳምንት በኋላ በስልጠናው የተካፈለ የክልሉ ባለስልጣን የወረዳ ሃላፊዎችን ሰብስቦ እንዲህ ይላቸዋል – … “ኣሁን የስርኣታችን ትልቁ ኣደጋ ኒዮሊበራሊዝም ነው፡፡ ኣንዳንድ የገበያ ኣክራሪ ኒዮሊበራል ሃይሎች መንግስት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚወሰዳቸውን እርምጃዎች ኣይደግፉም – የምንገነባቸውን መሰረተ ልማቶች ይቃወማሉ፡፡ ስለዚህ አቋም ወስደን መታገል ያለብን እነዚህ ኒዮሊበራል የገበያ ኣክራሪዎችን ነው፡፡”

ከሁለት ሳምንት በኋላ የወረዳው ሃላፊ የቀበሌ ሊቀመንበሮችን ሰብስቦ እንዲህ ይላል – … “እነዚህ ኒዮሊበራል የሚባሉት የገበያ ኣክራሪዎችና ኣሸባሪዎች የመንግስትን የልማት እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ መንግስት ደርሶበታል፡፡ ስለዚህ የህብረተሰብ ንቅናቄ ፈጥረን በየቀበሌው ልንታገላቸው ይገባል፡፡”

የቀበሌው ሊ/መንበር በቀበሌው ያሉ ሃላፊዎች፣ ኣስፈፃሚዎችና ጠርናፊዎችን ሰብስቦ እንዲህ ሊላቸው ይችላል- … “የመንግስትና የህብረተሰቡን የልማት እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል የሚፈልጉ ኣንዳንድ ኣክራሪና ኣሸባሪ ኒዮሊበራሎች በህብረተሰቡ መካከል ገብተው እየሰሩ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ሊታገላቸውና ሊያጋልጣቸው ስለሚገባ ይሄን በተመለከተ መላውን ህብረተሰብን ያሳተፈ የሁለት ሳምንት ስብሰባ እንዲካሄድ ይደረግ፡፡”

በመጨረሻም …. “በባስኬቶ ልዩ ወረዳ የሚገኙ ሴት ኣርሶ-ኣደሮች የገበያ ኣክራሪነትንና ኒዮሊበራሊዝምን ተደራጅተው ለመታገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለፁ”… (ኢቲቪ ዜና)

**********

Jossy Romanat

more recommended stories