አጭር ቃለ-ምልልስ ከ“ኢፈርት” ኩባንያ የቀድሞ ባለሙያ ጋር

ባለፉት በርካታ ሳምንታት  “ትዕምት” ወይም “ኢፈርት” በሚል የምህፃረ-ቃል መጠሪያዎቹ የሚታወቀው “ትካል ዕግሪ ምትካል ትግራይ(ትዕምት)” ኩባንያ በሹም ሽር እንደተጠመደ ይወራል::

ሂደቱ ስላልተጠናቀቀ እና/ወይም በተዛማጅ ምክንያቶች የተረጋገጠ ዜና ማቅረብ ሆነ ይፋዊ መረጃ ለማግኘት ቢያዳግትም ከኩባንያው ቅርበት ያለው ግለሰብ በመጋበዝ አጠቃላይ በሆኑ እና የዚህን ብሎግ አንባቢያን ትኩረት በሚስሉ ነጥቦች ላይ አጠር ያለ ቃለ-ምልልስ አድርገናል::

“ትካል ዕግሪ ምትካል ትግራይ(ትዕምት)” ወይም (Endowment Fund for the Rehabilitation of Tigrai (EFFORT) የተሰኘው ኩባንያ – ህወሓት የሚባለው የኢሕአዴግ ፓርቲ በትጥቅ ትግል ወቅት ባፈራው ሀብት የተመሰረተ “የዘለቄታ በጐ አድራጐት ድርጅት”(Endowment) ሲሆን በኩባንያው ላይ በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትችቶች እንደሚሰነዘሩ ይታወቃል:: በመሆኑም ይህ ቃለ-ምልልስ እንደመነሻ በመውሰድ አንባቢያን የሚሰነዝሩት ሀሳብ በቀጣይ ለሚቀርቡ ቃለ-ምልልሶችና ዘገባዎቸች የትኩረት ነጥብ ይሆናሉ::

ጌታቸው አረጋዊ ለሶስት ዓመታት ገደማ የኩባንያውን የሚዲያ ጉዳዮችን ሲያስፈጽም የነበረ ሲሆን አሁን “ውራይና” የተሰኘ የትግርኛ የግል መጽሔት ዋና አዘጋጅ ነው::

ዳንኤል – በትዕምት ኩባንያ ውስጥ የአመራር ለውጥ እየተካሄደ ነው ይባላል፡፡ ስለዚያ ልትነግረን ትችላለህ?

ጌታቸው – የኣመራር ለውጥ እየተደረገ እንደሆነ ሰምቻለሁ። ለምሳሌ ከከፍተኛ ኣመራሮች ኣቶ ይተባረክ ኣመሃ ከም/ስራኣስፈፃሚነት እንደተነሱ ኣቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ግን በም/ስራኣስፈፃሚነት እንደቀጠሉ ነው የሰማሁ። ስለ ወ/ሮ ኣዜብም ኣንድ ግዜ ከዋና ስራ ኣስፈፃሚነት ተነስተዋል ይባላል ሌላ ግዜ ደግሞ ቀጥለዋል ይባላል:: ለሚመለከታቸው ስጠይቅ ሁለቱም ኣይነት መረጃ ኣገኛለሁ:: ብዙም ኣልገባኝም። ኣንትም ስለ እዚህ ከሌሎች ብትጠይቅ። ኦፊሻሊ ግን የተነገረ ነገር የለም።

ዳንኤል – የተነሱበት ምክንያት ምንድነው?

ጌታቸው – ለያንዳምዳቸው ምን ምን ተብለው/ተገምግመው እንደተነሱ ኣላወቅኩም። ኣቶ ይትባረክ ኣምሃ ወደ ስቪል ሰርቪስ ቢሮ ነው የተዘዋወሩ። በትዕምት በጣም ችግር እንዳለ በጀትም እንደታጣ ግን ለመገንዘብ ችየ ኣለሁ።

ዳንኤል – ወደአጠቃላይ ጥያቄዎች ልሂድና – ማነው የትዕምትን ቦርድና ሥራ አስኪያጅ የሚሾመው?

ጌታቸው – ትዕምት የራሱ ምክር ቤት ኣለው፤ ምክር ቤቱ ቦርድ ይመርጣል፤ ቦርዱ ደግሞ ስራ ኣስከያጅ ይሾማል እናም ለምክር ቤቱ ያሳውቃል። የትዕምት ምክር ቤት ከህዝቡ ነው የሚወጣው:: ማለትም ምክር ቤቱ (ከየወረዳው የሚወከሉ፡ ኢሮብ እና ኩናማ ጨምሮ)፣ ከሲቪክ ማህበራት ( የወጣቶች ማህበር፣ የሴቶች ማህበር፣ የገበሬዎች ወዘተ)፣ ከሀይማኖት ተቃማት፣ ከነባር የህወሃት ታጋዮች፣ ከምሁራን የትግራይ ፓትሪዮት ወዘተ የተውጣጡ ኣባላት የያዘ ነወ።

ዳንኤል – ምክር ቤቱ የተመረጠው መቼ ነው?

ጌታቸው – ምክር ቤቱ እኮ በህዝባዊ ምርጫ ኣይደለም የሚመረጠው። ከላይ እንደጠቀስኩት ከየሚመለከታቸወ ኣካላት/ድርጅቶችና ማህበራት ተወክለው ነው የሚያቃቁሙት። በዚህ ደግሞ ትዕምት በህግ ከተቃቃመበት ግዜ ጀምሮ ነው የተቃቃመው። በተሃድሶ ማግሰት በ2003 ዓ/ም ደግሞ በከፍተኛ ቁጥር የምክር ቤቱ ኣባላት እንዲቀየሩ ተደርገዋል። ኣመራሩም በዛው ልክ።

ዳንኤል – የህወሓት አመራሮች የትዕምት የቦርድ አባል ናቸው – አክሲዮን አላቸው ሲባል እንሰማለን፡፡ ይህ ማለት የድርጅቱ ባለቤቶች ናቸው ማለት ነው?

ጌታቸው – በኣሁኑ ሰዓት በትዕምት ሼር/ኣክስዮን/ ያለው የህወሓት ኣመራር የለም። ቦርድ ኣባላት ግን የህወሓት ከፍተኛ ኣመራሮች ናቸው። ይሄ እውነት ነው። ይሄ ማለት ግን የድርጅቱ ባለቤቶች ናቸው ለማለት ኣያስችልም። ባለቤቱ የትግራይ ህዝብ ነው። ግልፅ ነው።

ዳንኤል – ግን’ኮ አንዳንድ የሕወሓት አመራሮች በትዕምት ኩባንያዎች ኣክስዮን እንዳላቸው ይወራል። የቦርድ አባል ለመሆን ባለአክሲዮን መሆን አያስፈልግም ወይ?

ጌታቸው – የቦርድ ኣባል ለመመረጥ አክሲዮን ኖሮህ ወደ ጠቅላላ ስብሰባ መግባት መቻል እንዳለብህ ግልፅ ነው። ይሄ ድግሞ እንደ ግለሰብ በሚኖርህ አክሲዮን ወይም በምትመራው ድርጅት ስምም ሊሆንና በዚያ መሰረት ልትገባና ልትመረጥ ትችላለህ። ለምሳሌ ኣፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያ በወጋገን ባንክ ትልቅ ሼር ኣለው፤ ስለዚህ የኣፍሪካ ኢንሹራንስ ስራኣስከያጅ በወጋገን ባንክ የቦርድ ኣመራር ለመመረጥ ትልቅ እድል ይኖረዋል ማለት ነው። በዛ መልክ ነው።

ዳንኤል – የትዕምት ድርጅቶች ትርፍ ለማን ገቢ ይደረጋል? ለምን ዓላማ ወጪ ይደረጋል?

ጌታቸው – ምን መሰለህ የትዕምት ድርጅቶች ትርፍ ወደ የትዕምት ኢንቨስትመንት ማዕከል/ካዝና/ ነው የሚገባው። ማዕከሉ ደግሞ ለካምፓኒዎች ኢንቨስትመንት ማስፋፍያ እና ለአዲስ ኢንቨስትመንት እንደአግባቡ ያዉለዋል። በጀት ሲመደብ በትዕምት ኢነቨስትመንት ማእከል ማኔጅመንት ተጠንቶ ይቀርብ እና በትዕምት ምክር ቤት ይፀድቃል። የትዕምት መተዳደርያ ደንብ ለግብረሰናይ ስራዎችም በጀት እንዲኖር ያዝዛል:: እስከኣሁን ግን ብዙ ኣይደለም። ለኣንድኣንድ ነገሮች ሰፖንሰር ከማረግ በስተቀር።

ዳንኤል – የህወሓትን ሥራ ማስኬጃ ወጪ ትዕምት ነው የሚሸፍነው ይባላል?

ጌታቸው – ይሄ ብዙ እዉነታ የለዉም። ህወሓት ወጪው የሚችለው ከኣባላቱ በሚሰበሰብ መዋጮ ነው። የተለየ ዝግጅት ኖሮት ከደጋፊዎቹ እና ከባለሃብቶች ገቢ ሲያሰባስብ ትዕምትም እንደ ሌሎች ድርጅቶች አስተዋጽኦ የሚያደርግበት ሁኔታ ኣለ። በተለየ መልኩ ግን ህወሓትን ኣይደግፍም።

ዳንኤል – አብዛኞቹ የትዕምት ድርጅቶች ከሥረው ለመዘጋት በቋፍ ላይ ናቸው ይባላል?

ጌታቸው – እንደምናስታውሰው ባለፈው ዓመት የ2005 ዓ/ም በጀት ግምገማን ወ/ሮ ኣዜብ ሲያቀርቡ በትዕምት ኩባንያዎች ጥሩ ዕንቅስቃሴ እንዳለ ገልፀው ነበር። ኦፊሻል የሰማነው እና የተከታተልነው ይሄ ነው። ከዛ በሃላ እንደሰማነው ከሆነ ደግሞ ለ2006 በጀት ገንዘብ እንዳነሰ ነው። በርግጥ የተምታታ ነገር ያለ ይመስላል፤ የተወሰነ ኪሳራ እንዳለም ኣያጠራጥርም። ከስረው ሊዘጉ በቋፍ ላይ ናቸወ የሚለውን እንካን እኔ ኣላምንበትም። ምክንያቱም በተለያየ ምክንያት ለግዜው ሊከስሩ ይችሉ ይሆናል እንጂ መዘጋት ኣይታሰብም:: ብዙ እህት ኩባንያዎች ስላሉ ኣንዱ ቢከስር ለኣንዱ እያበደረ ወደ ትርፍ እንዲገባ ያግዘዋል። የሄ ከኣሁን በፊትም ሲሰራበት የነበረ ኣሰራር ነው።

ዳንኤል –  የትዕምት ኩባንያዎች በትግራይ የግሉ ዘርፍ እንዳያድግ የገበያ ዕድል የማጣበብ ተፅዕኖ አሳድረዋል ይባላል፡፡ እንዴት ታየዋለህ?

ጌታቸው – እንደውም የተገላቢጦሽ ነው። ትዕምት በትግራይ መኖሩ ባለሃብቶች እንዲመጡ ነው የሚያበረታታ። ይሄ ጥያቄ የሚያነሳ የእንዱስትሪ ባህሪን የማያውቅ ነው። ኢንዱስትሪዎች በባህሪያቸው ወደኣንድ የሚሰበሰቡት እንደ በግ። ይሄ ሎጂክ እንዳለ ሁኖ፡ እንዲያውም ትዕምት ሆን ብሎ የግል ባለሀብቶችን ያበረታታል ለራሱም ስለየሚያስፈልገው ጭምር። በተለይ ደግሞ ለጥቃቅንና ኣነስተኛ ተቃማት በተደራጀ መልኩ ነው የሚያግዘው። ሁለተኛ ደግሞ ትዕምት የተሰማራበት ኢንቨስትመንት በጣም ትልቅ ነው – በሀገር ደረጃም ቢሆን የግል ባለሀብት ሊደፍረው የማይችል ነው።

ዳንኤል –  የግሉን ዘርፍ ካነሳን ላይቀር – በትግራይ ክልል ከትዕምት ውጭ ጉልህ የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲኖር አይፈለግም ይባላል?

ጌታቸው – ትግራይ እንድትለማ የሚፈልግ ሰው ከሆነ ትዕምት በመኖሩ ሊከለክለው ኣይችልም ሊያግዘው ካልሆነ በስተቀር። የትግራይን ልማት ለማደናቀፍ በመፈለግ ትዕምትን ሰበብ ኣድርጎ ሌላ ባለሀብት እንዳይመጣ የሚያዳክም ካለ ያ ሌላ ጉዳይ ነው። በክልሉም መንግስትም ይሁን በትዕምት የግል ባለሃብቶችን የሚገድብ ህግም ሆነ ፍላጎት የለም፤ ሊኖርም ኣችልም። እንዳውም ቅድም ከገለፅኩት የኢንዲስትሪ ባህሪ ተነስተው ሌሎች ባለሃብቶችን ለመሳብ ነው የሚጣጣሩት።

ዳንኤል –  በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች የውጭ ኢንቨስተሮች በሰፋፊ እርሻዎች ልማት ሲሳተፉ በትግራይ ግን አልተፈቀደላቸውም የሚል ሀሜት አለ፡፡ ምን ያህል እውነት አለው?

ጌታቸው – በትግራይ እንደ ሌሎች ክልሎች ሰፋፊ መሬት እንደሌለ የታወቀ ነው። ስለዚህ መሬት ከሌለ ከየት ነው የሚሰጣችው? እንጂ የተለየ ፖሊሲ በትግራይ ኖሮ ኣይደለም። በምዕራብ እና በደቡብ ትግራይ ካሉ የተወሰኑ የእርሻ መሬቶች ግን የተወሰኑ ትንሽ ትንሽ መሬቶች የያዙ ኣሉ። በቅርቡ እንካን የተሰጡ ኣሉ:: በሁመራም በራያ ኣካባቢም። ስለዚህ ከማጣት እንጂ ካለመፈለግ ኣይመስለኝም።

ዳንኤል –  እስኪ ስለ”ውራይና” መጽሔት ትንሽ ንረገን::  ማን ነው አሳታሚው? ለምንድን ነው በትግርኛ የሆነው?

ጌታቸው –  “ዉራይና” መጽሔት የሚታተመው በwurayna media and Arts plc ነው። በግለሰቦች የተመሰረተ ነው። ለምንድን ነው በትግርኛ የሆነው? ለሚለው፤ በዋነኝነት ስለ ትግራይ ስለ የሚያወራ ለትግርኛ ኣንባቢዎች/ተናጋሪዎች ነው ስለሚታተም ነው። እግረመንገዱ ደግሞ የትግርኛ ስነ ፅሑፍ እና ቋንቋ ለማዳበር እንዲረዳ ነው። ጥያቄህ ገብቶኝ ከሆነ እንደዛ ነው።

ዳንኤል – ትግራይ ውስጥ መጽሔት ማዘጋጀት ቀርቶ አዲስ አበባ የሚታተሙትን እንካን ማሰራጨት እንደማይፈቀድ ነው የምንሰማው:: ለአንተ/ለ”ውራይና” እንዴት ተፈቀደ?

ጌታቸው –  ኣቶ ዳንኤል የሰማሀው እጅግ በጣም ስህተት ነው። ኣዲስ ኣበባ የሚሰራጭ ሁሉም ኣይነት መጽሔትም ጋዜጣም መቀለ ይሰራጫል። ይሄ በተግባር የሚታይ ስለሆነ ሄደህ ማረጋገጥ ነው ሮማናት በሚባል ኣደባባይ ተዘርግተው ታገኛለህ። ስለ እዚ “ውራይና” መጽሔትንም የሚከለክል ነገር ኣይኖርም። ኣገሪትዋ እኮ ያላት ኣንድ ሕገ መንግስት ነው ትግራይ ለብቻው ልከለክል ቢልስ ማን ይሰመዋል፤ እምቢ ሕገ መንግስታዊ መብታችን ነው የምንለው እንጂ። የትግራይ መንግስት በልዩ ትኩረት ያበረታታል? ኣያበረታታም? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል። ይሄን ደግሞ ገና ወደፊት እናየዋለን። እስከኣሁን “ዉራይና” ለመንግስት እንድያግዛት ጥያቄ ኣላቀረበችም። ሁኔታው ግን ጥሩ ይመስላል።

**********

ማስታወሻ – በዚህ ቃለ-ምልልስ ላይ ሆነ ተዛማጅ ጉዳዮች ላይበ ቀጣይ በሚቀርቡ ቃለ-ምልልሶችና ዘገባዎቸች ላይ እንዲተኮርበት የምትሹትን ነጥብ ከታች በአስተያየት መስጫው እንድትጠቁሙ እንጋብዛለን::

Daniel Berhane

more recommended stories