በሚ/ር ደኤታ ብርሃነ ገ/ክርስቶስ የሚመራ ልዑክ ሳዑዲ ዐረቢያ ገባ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች አያያዝን በተመለከተ ከአገሪቱ አቻቸው ልዑል ሳውድ አል ፋይሰል ጋር በስልክ ተወያዩ።

ሚኒስትሮቹ የሳዑዲ ፖሊስ የስራና የመኖሪያ ፈቃድ የላቸውም በተባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ እየወሰደ ስላለው እርምጃ በዝርዝር ተነጋግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 120 ደቂቃ እንደተናገሩት ፥ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች ከተወያዩ በኋላ በኢትዮጵያውያኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ረገብ ብሏል።

በተያያዘ ዜና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተመራ ልዑክ ወደ ሳኡዲ አረቢያ አምርቷል። ልዑኩ ወደስፍራው ያመራው በሃገሪቱ የኢትዮጵያ ዜጎች የሚያዙበት ስርዓት ላይ ንግግር ለማድረግ ነው።

በተጨማሪም ልዑኩ የዜጎችን ወደሃገር ውስጥ የመመለሻ ጊዜ ለማፋጠን በሳኡዲ አረቢያ ካለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ስራዎችን እንደሚሰራም ታውቋል። አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደነገሩን የመኖሪያና መስሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተመዘገቡ ነው።

ማምሻውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስ ቡክ ገፁ ይፋ እንዳደረገው፥ በሪያድ የሚገኘው ኢምባሲ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ተጠቅመው የመስሪያና መኖሪያ ፈቃዳቸውን ማደስ ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን ደህንነታቸውና ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ ከሀገር የሚወጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በዚያው ከሚገኘው የኢትዮጵያውያን ማህብረሰብ ጋር በጋራ እየሰራ ነው።

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መሀመድ ሀሰን እንዳሉትም ፥ ባለፉት ሁለት ቀናት ሁኔታዎች እየተረጋጉ የመጡ ሲሆን፥ በነዚህ ቀናትም ሌላ አደጋ አልተከሰተም።

ኢትዮጵያውያኑ በሰላማዊ ሁኔታ አገሪቱን መልቀቅ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም አምባሳደሩ ከሌሎች ዲፕሎማቶች ጋር በመሆን የሪያድ አገረ ገዢንና የፖሊስ አዛዥን አግኝተው አነጋግረዋል።

አምባሳደሩ ከሪያድ አገረ ገዢ ጋር በመሆንም የተያዙ ኢትዮጵያውያን ያሚገኙበትን ማዕከላት በመጎብኘት ያሉበትን ሁኔታ ገምግመዋል።

በአገሪቱ መንግስት የተቀመጠውን የአራት ወራት የመስሪያና መኖሪያ ፈቃድ ማግኛ ጊዜን መጠቀም ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን እንዲመዘገቡና በአገሪቱ መቆየት የማይችሉትም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማስቻል ኢምባሲው ተጨማሪ የምዝገባ ማዕከላትን እንደከፈተ ነው ያስታወቀው።

በዚያው ከሚገኙ የኢትዮጵያውያን ማህብረሰቦች ጋር በመተባበርም የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የመመዝገብና ወደ ማቆያ ማዕከላት ኢትዮጵያውያኑ ሲወሰዱ የሳዑዲ የፀጥታ ሀይሎች የሚፈፅሙትን ኢሰብዓዊ ድርጊት ለማስቆም እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ የሚመራውና ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያመራው ልዑክ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝቶ ስለሁኔታው ይመክራል።

ኢትዮጰያውያንን ወደ አገር ቤት የመመለሱንም ሂደት የማቀላጥፍ ስራን ያከናውናል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት 22 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንም ከሪያድ ማምሻውን ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በኳታርና አቡዳቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኞችም ወደ ሪያድ በመሄድ ድጋፍ የሚያደርጉ ይሆናል።

********

Source: Fana, Nov. 12, 2013, titled “ዶክተር ቴድሮስ በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝን በተመለከተ ከሳዑዲ አቻቸው ጋር መከሩ”

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories