ጥቂት ስለጀማ ስነ ልቦና (mob mentality) – ከግል ተሞክሮ

(ዳንኤል ብርሀነ)

በወዲያኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቴሌቪዝን የሚዲያ ዳሰሳ ፕሮግራም ላይ ስለ‹‹የጀማ ስነ‐ልቦና›› /mob mentality/  በጨረፍታ አንስቼ ነበር:: ይህን በጨረፍታ ያነሳሁትንና አንዳንዶች በደንብ ያልተረዱኝን፣ ሌሎች ደግሞ ‹ስላቅ› የመሰላቸውን ጽንሰ-ሀሳብ(concept) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ በተሳተፍኩበት የአድማ ታሪክ አስደግፌ ላፍታታው፡፡

ግዜው 1993 ነው፤ የአዲስ አበባ ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማ መተናል፡፡ባልሳሳት ጥያቄያዎቻችን ሶስት ነበሩ፡፡ ‹‹የግቢው ጥበቃ ፖሊስ መሆኑ ቀርቶ በሲቪል ይቀየር››፣ ‹‹የተማሪዎች ሕብረት በነፃነት ይሥራ›› እና (ድሮ ትታተም የነበረች) ‹ህሊና› የተሰኘች የተማሪዎች ጋዜጣ እንደገና ትጀምር የሚሉ ናቸው፡፡ ጥያቄው ተገቢ በመሆኑ መንግስት ከእሺታ እና ‹‹መች ከለከልኩ›› ዓይነት በቀር ሌላ መልስ አልነበረውም፡፡

እሺ ከማለቱ በፊት ግን – ገና አድማ በመታን በ2ኛ ወይም በ3ኛው ቀን – ፌዴራል ፖሊስ ድንገት ግቢ ገብቶ እርምጃ ይወስዳል፡፡ ፖሊስ ለመግባት ሰበብ/ምክንያት ሊኖረው ቢችልም(‹‹ሰላይ ናቸው›› ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች በተማሪው ተይዘው ምርመራ ቢጤ እየተደረገባቸው ነበር)፤ አፈጻጸሙ ግን የእውር ድንብር ከመሆኑ የተነሳ እኔ ምንም ሳልሆን በተቃራኒው ግን መኝታ ቤቱ በሰላም ተቀምጦ የነበረ ጓደኛዬ እጁን ተሰብሯል፡፡

ከዚያ በኋላ የትምህርት ሚኒስተሯ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ መጥተው ለጥያቄዎቻችንን ስምምነታቸውን ቢገልፁም እኛ በጀ የምንል አልነበርንም፡፡ እንዲያውም ‹‹የታሠሩት ልጆች  ካልተፈቱ አንወያይም›› ብለናቸው፣ እዛው ልደት አዳራሽ ቁጭ እንዳሉ ደውለው ካስፈቱልን በኋላም፤ ‹‹የግቢው ጥበቃ ፖሊስ በሲቪል ሳይቀየር ለመወያየት አንችልም›› ብለን አሰናበትናቸው፡፡

Addis Ababa University main campus - Students protest (year 2001)
Addis Ababa University main campus – Students protest (year 2001)

ዩኒቨርሲቲው ሲቪል ጥበቃ ለመቅጠር በይፋ ማስታወቂያ አውጥቶ ምዝገባ ቢጀምርም የእኛን አቋም ግን አላስለወጠም፡፡ እንደማስታውሰው ‹‹የቅጥር ሂደቱ ግዜ የሚወስድ ከሆነ፣ ለምን ከባንኮችና መሰል መንግስታዊ ተቋማት ሲቪል የጥበቃ ሀይል በግዜያዊነት አያመጡም›› የሚል ሀሳብ በተማሪው ዘንድ ይንሸራሸር ነበር፡፡

በዚህ መሀል ነው እንግዲህ፤ ፖሊስ ግቢ ገብቶ በወሰደው ዕርምጃ ሳቢያ እንድ ሴት ተማሪ ሞታለች የሚል ወሬ መናፈስ የጀመረው፡፡ ወዲያውኑም ከመፈክሮቻችን አንዱ ‹‹እህታችን ለምን ሞተች?!›› የሚል ሆነ፡፡ በነዚያ ቀናት ከ6ኪሎ ጓደኞቼ ጋር በእግር ወደ5ኪሎ አካባቢ ስንንሸራሸር የኢንጅነሪንግ ተማሪዎችን አገኘንና:- ‹‹የሞተችዋ ልጅ የት ሀገር ልጅ ነች?›› ብለን ጠየቅናቸው፡፡ እነርሱም:- ‹‹እንዴ?! እኛኮ የሰማነው ልጅቱ የ6 ኪሎ(የ4 ኪሎ?) ተማሪ እንደሆነች ነው›› አሉን፡፡ ሁላችንም ግራ ስለተጋባን በጋራ 4ኪሎ ሄድንና ጠየቅን፡፡ እነርሱ ደግሞ ልጅቱ የ6ኪሎ ተማሪ እንደሆነች ነበር የሰሙት፡፡ ተሳሳቅን፡፡ (የኋላ የኋላ እጅግ ዘግይተው የመንግስት/የዩኒቨርሲቲው አካላት ጉዳዩን ደረሱበትና ‹‹የሞተ ሰው የለም እኮ›› ማለት ጀመሩ፤ ግን ምን ያደርጋል….እኛ ወደሌላ መፈክር ተሻግረናል፡፡)

እንዲህ እንዲህ እያለን ከርመን፣ መጨረሻ ላይ ትምህርት ለመቀጠል ያቀረብነው ቅድመ-ሁኔታ ‹‹በአድማው ምክንያት ግዜው ስለባከነ ለፈተና መዘጋጃ 6ሳምንት ይሰጠን ወይም በቀጣዩ ዓመት በ3ሴሚስተር እንሸፍነው›› የሚል ሆነ፡፡ ዩኒቨርሲቲው/መንግስት ደግሞ ‹‹ከ3 ሳምንት በላይ መስጠት አልችልም›› አለ፡፡

በመሆኑም ተመራቂ ተማሪዎች እና የሕግ ተማሪዎች (በዚያው ‹ባንዳ› የሚል ስያሜ ሸምተው) ትምህርት ሲቀጥሉ፤ በግምት ከ90-95% በላይ የሚሆን ተማሪ በፈቃዱ ግቢውን ለቆ ወደቤቱ ሄደ፡፡ መንግስትም ‹‹መቀጣጫ ሊያደርገው›› ፈልጎ ነው መሰል፤ ያቋረጡትን ተማሪዎች በቀጣዩ ዓመት በተመሳሳይ ግዜ – የ2ኛው ሴሚስተር ግማሽ ላይ (ሚያዝያ ወር) – እንደገና ተመልሰው ሲመዝገቡ (በ Readmission) ብቻ ለማስተናገድ ወሰነ፡፡ አንድ ዓመት ‹‹ተቀጡ›› ማለት ነው፡፡

እርግጥ የአድማውን ሂደት በምልዐት ለመረዳት ከዚህ በበለጠ ዝርዝር ማየት እንዲሁም በእኛ አመጽ ወቅት እና በርካታ ወራት ቀደም ብለው የነበሩ ተከሰተቶችን (የስታዲየም ረብሻዎች፣ የኢሕአዴግ አመራር ውዝግብ፣ ወዘተ) ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡

ስለጀማ ስነ-ልቦና ከማሳየት ዓላማዬ አንጻር ግን ከላይ ያቀረብኩት ቁንጽል ትረካ ከበቂ በላይ ነውና፤ ትረካውን በዚህ ገትቼ የስነ-ልቦናውን ዋነኛ ዓላባዎች/መገለጫዎች በ5 ነጥቦች ላቅርብ፡፡

1/የትምህርት ሚኒስተሯን <<አንወያይም>> ብለን ስናሰናብት ብዙዎቻችን ግር ብሎን ነበር (ምክንያቱም ቀደም ባሉት ቀናት ደግሞ ከዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንቶች ጋር አንወያይም ብለናል፣ ጠ/ሚኒስተሩ ይምጡ ለማለት ሀሳብ አልነበረንም)፡፡ ይሁን እንጂ የተወሰኑ ከፊት የተቀመጡ ተማሪዎች ‹‹አንወያይም›› የሚለውን አቋም አራመዱ፤ ሌሎቻችንም አልተቃወምንም፡፡

ለምን? የአመጽ/አድማ ድባብ ባለው ጀማ ውስጥ ግትርና ጽንፍ አቋም የያዙ ሰዎች የአብዝሀውን ሰው ጆሮ ያገኛሉና፡፡

በሌላ አነጋገር፡- የአመጽ ድባብ ባለው ጀማ ውስጥ ያሉ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ሲታዩ አብዛኞቹ ለዘብተኞች ቢሆኑ እንኳን ለአመጽ ወይም ለተቃውሞ በተሰባሰበ ጀማ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ግትርና ጽንፍ የያዙ ጥቂቶችን የመከተል ዝንባሌ ያሳያሉ፡፡

2/‹‹የግቢው ጥበቃ አሁኑኑ ይቀየር›› እና ‹‹ከሌሎች ተቋማት ሲቪል ጥበቃ በግዜያዊነት ያምጡ›› የሚሉት ሀሳቦች ግትር እንደሆኑ ባይጠፋንም፣ አቋሞቹን ያራመድነው ግን ጽንፍ አቋም የያዙ ግለሰቦችን ተከትለን ብቻ አይመስለኝም፡፡ ሌላም ግብዐት ነበር፡፡

መንግስትን መታገል የተማሪው ሚና እንደሆነ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለዓመታት የተገነባ አስተሳሰብ ነው፡፡ እኛም ‹‹ወኔ ቢስ›› መባል ሰልችቶናል፡፡ ስለዚህ አድማው ጥያቄዎቻችንን ማስፈፀሚያ ስልት ብቻ ሳይሆን በራሱ ግብ ነው፡፡

አድማውን ከመጀመራችን ከቀናት በፊት የሰብዐዊ መብቶች ጉባዔ ለተማሪዎች ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እና ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ስለደካማነታችን የሰጡን ዲስኩር፣ በወቅቱ እንደተባለው (መንግስት በይፋ፣ ዶ/ር መኮንን ቢሻው ደግሞ በግል ሲሉ እንደሰማሁት) እኛን ወደአድማው የመራ አዲስ ወንጌል አልነበረም፡፡ እንዲያው በተማሪው ዘንድ ለዓመታት የቆየውን የ1960ዎቹን ተማሪዎች እንደ‹ሞዴል› የማየት አመለካከት አስታዋሽ (reminder) ብቻ ነው የነበረው፡፡

ባጭሩ፡- በአድማው ወቅት የወሰድናቸው አቋሞች፣ የወቅታዊ ምክንያታዊ ትንተና ብቻ ሳይሆን፤ እኛ ራሳችን ሙሉ በሙሉ ልብ የማንላቸውና ለረጅም ግዜ ሲገነቡ የቆዩ የተማሪው ስነ-ልቦና (collective consciousness) ውጤትም ነበሩ፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ካላመጸ <ታሪካዊ ሚናውን> እንዳልተወጣ የሚቆጥር የቆየ ልማድ ከውጭ ወደ ዩኒቨርስቲው ግቢ ዘልቆ እየገባም የጀማ ስነልቦናውን ይመግብ ነበር።

3/‹እህታችን ለምን ሞተች› የሚለው መፈክር የሟሸሸው፣ ወሬው ስህተት እንደሆነ ብዙ ተማሪዎች ቀስ በቀስ ከሰሙ በኋላ እና የመንግስት አካላት ‹‹የሞተ ሰው የለም እኮ›› ማለት ሲጀምሩ ነበር፡፡ እስከዛ ድረስ ግን ወሬው መሠረተ-ቢስ እንደሆነ ቀድመን የሰማን ተማሪዎች መፈክሩን ስንቃወም ወይም ስናርም ትዝ አይለኝም፡፡

ለምን? የሀሰት ፕሮፖጋንዳን እንደስልት ለመጠቀም በንቁ-ልቦና (consciously) ወስነን አይደለም፡፡ ዋነኞቹ ‹‹መሪዎች›› – የይፋና የሕቡዕ አደራጆች/አስተባባሪዎች – እንደዛ ሊያስቡ ቢችሉም፤ ያ ብዙዎቻችንን አይገልጽም፡፡ እንግዲያው ታዲያ ለምን ይህን ከመሰሉ ከግል መርሆዎቻችን (የሀቀኝነትና ሌሎች መርሆዎች) ጋር የማይሄዱ አካሄዶች አካል ሆነን በፈቃደኝነት ተጓዝን?

ከጀማ ስነ-ልቦና መገለጫዎች አንዱ የግል ሀላፊነት እና ተጠያቂነት ስሜትን ማጥፋቱ ነው፡፡ ድርጊቶቻችንን የሚመዘኑት በመደበኛው የአስተሳሰብ ሚዛናችን ሳይሆን ‹‹ሕዝቡ ነው ያለው››፣ ‹‹የተማሪው አቋም ነው››፣ ወዘተ፣ በሚሉ የጋራም ሆነ የግልም ተጠያቂነት በሚያደበዝዙ ምክንያቶች ነው፡፡

በሌላ አገላለጽ፡- የግል ሀላፊነት ስሜት ይደፈቅና በጀማው ስሜት ይተካል፡፡ የጀማው ስሜትና ውሳኔ ደግሞ የብዙ ጭንቅላቶች ፍጭት የሆነ ምጡቅ አስተሳሰብ አይሆንም፡፡ አንድም፡- ጀማው በጭፍን የሚከተላቸው ጥቂት ግለሰቦች ውሳኔን ነው፤ አልያም የጀማው አባላት ሁሉ የሚጋሩት ትንሹ(the least common denominator) የማገናዘብ ችሎታና ዕሴት መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡

4/የእኛን በትግልና በተጋፊነት የታጀበ የጀማ ስነ-ልቦና ስሜት በማጠናከር ረገድ ፖሊስ የራሱ ሚና ነበረው፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ዕርምጃ ወቅቱን ያልጠበቀ(premature) እና የዕውር-ድንብር በመሆኑ አድማውን በመበተን ፋንታ በአድማው የሚሳተፉ እና/ወይም የሞራል ድጋፍ የሚሰጡ ተማሪዎችን ቁጥርና ዕልህ የመጨመር ውጤት ነው የነበረው፡፡

ከዚያም በኋላ የተወሰዱ ውጤታማ ያልነበሩ ሙከራዎችን (መንግስት አንድ ቀን በቲቪ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠን፣ ሌላ ቀን ፖሊስ ሲልክ፣ ሌላ ግዜ በየዲፓርትመንቱ ማስጠንቀቂያ ሲያስፈርመን፣ ወዘተ) እያንዳንዳንዱን ስልት ባለፍን ቁጥር ይበልጥ ልበ-ሙሉነት እየተሰማን ሄደ፡፡ (እርግጥ አይፈረድብንም፣ አድማ ባንመታ መንግስት ምንያህል ጆሮ ይሰጠን ነበር?)

በአድማችንና በጀማ እንቅስቃሴያችን ምክንያት ሀይል እንዳገኘን(empowered እንደሆንን) እና የሀገርና የውጭ ሚዲያ ትኩረት ማዕከል እንደሆንን በተሰማን መጠን፣ ከጀማ ስነ-ልቦና ወጥተን ስለሁኔታው ግላዊ ምዘናና ውሳኔ የማድረግ አቅማችንንና ተነሳሽነታችንን ገደበው፡፡

አድማው ከመርዘሙ የተነሳ አንዳንዶቻችን ወደቤት ሄደን ከርመን ስንመጣ፣ ሌላው ደግሞ አዲስ አበባን ያካልል ነበር፡፡ ነገር ግን የጀማውን አካሄድ ትክክለኝነት ለመከለስ/ለመገምገም ብዙዎች ድፍረቱ አልነበረንም፡፡

የጀማ ስነ-ልቦና ምፀት፤ ተሳታፊ ግለሰቦች ‹‹ሀይል እንዳገኙ››(empowered እንደሆኑ) የሚሰማቸው መሆኑ፣  በተጨባጭ ግን ግለሰባዊ ሉዐላዊነታቸውን የሚያጡ መሆኑ ነው፡፡

5/ፈተና ለመፈተንና ላለመፈተን ተማሪው የወሰዳቸው የተለያዩ አቋሞች ደግሞ የጀማ ስነ-ልቦናን አድማስ እና ‹ማርከሻ› ለማስተዋል ያስችለናል፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት ከ90-95% የሚሆነው ተማሪ ‹‹ለዝግጅት 6ሳምንት ካልተሰጠን መፈተን አንችልም›› ብሎ ወደቤቱ ሄደ፡፡ በአንፃሩ የሕግ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ለፈተና ተቀመጡ፡፡ በሌላ በኩል የሁሉም ዲፓርትመንቶች ተመራቂ ተማሪዎች ከበርካታ ሳምንታት በፊት አመፁን ትተው ትምህርት ቀጥለው ነበር፡፡

በወቅቱ ከግል ውይይት መረዳት እንደተቻለው አብዛኛው ተማሪ ‹‹ለኔየ3 ሳምንት ዝግጅት ይበቃኛል›› የሚል የነበረ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲው 6ሳምንት ላለመስጠት ያቀረባቸው ምክንያቶች ውሀ የሚቋጥሩ እንደሆኑ ተሰምቶታል፡፡ መንግሰት ‹‹በቀጣዩ ዓመት በ3 ሴሚስተር አላስተናግድም›› በሚለው አቋሙ ሊፀና እንደሚችልም ልብ ብሎት ነበር፡፡(የኢዴፓው ልደቱ አያሌው ከተማሪዎች ጋር በግል ሲወያይ ያንን እንደተነበየ ትዝ ይለኛል)፡፡

ነገር ግን የተማሪው የጀማ ስነ-ልቦና ለለዘብተኛነት፣ ለምክያታዊነት እና ለግል ውሳኔ ቦታ አልነበረውም፡፡ ስለሆነም ተማሪው ከአድማው ሞቅታ መውጣት አቅቶትና አድማው የሰጠውን ሀይል አጋንኖ በማየት – አንድ ዓመት ሊያባክን እንደሚችል እየጠረጠረ – ወደቤቱ ሄደ፡፡

ብዙዎች ውሳኔያቸው ስህተት እንደነበር ለማመንና ለመናገር ድፍረት ያገኙት – እንዲያውም አንዳንዶች ‹‹እገሌ ባይገፋፋኝ እፈተን ነበር›› እስከማለት የደረሱት – ለእረፍት እንደመጣ ተማሪ ሳይሆን እንደሥራፈት እስከሚቆጠሩ ድረስ የሚያታክቱ 10 ወራትን ቤተሰብ ጋር አሳልፈው ከመጡ በኋላ ነበር፡፡ ባጭሩ ከጀማ ስነ-ልቦና ለመውጣት shock therapy አስፈልጎ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ (እያወራሁ ያለሁት የግል ዝንባሌያቸው በጀማው ስለተደፈቀ ሰዎች እንጂ ካለፈ በኋላም ‹‹ውሳኔው ትክክል ነበር›› የሚሉትን ለመተቸት አይደለም)፡፡

የተመራቂ ተማሪዎችን ትምህርት የመቀጠል ውሳኔ መንስዔ ብየ የማስበው፡- አድማው የተከሰተበት ወቅት፣ ራሳቸውን በጥቅሉ የ‹‹ዩኒቨርሲቲ ተማሪ›› ወይም የ‹‹እገሌ ዲፓርትመንት ተማሪ›› አድርገው ከማየት ወደ ግላዊ እጣፈንታን የማሰላሰላሰልና የመወሰን ምዕራፍ እየገቡ ባሉበት ሰዐት በመሆኑ እና ጠንካራ የቤተሰብ ግፊት ታከሎበት ነው፡፡ ስለሆነም ከጀማው ስነ-ልቦና ለመውጣትና የጉዳዩን ግላዊ ፋይዳ ለመመዘን 10 ወራት አላስፈለጋቸውም፡፡ ማለትም ተመራቂዎቹ ከጀማ ስነ-ልቦና ለማፈንገጥ የሚያስችል በቂ ዓቅም በውስጣዊና በውጫዊ ምክያቶች ሳቢያ አግኝተዋል፡፡

የሆነ ሆኖ ተማሪው ‹‹ተመራቂዎች እንደሌላው ተማሪ ትምህርት እንዲያቋርጡ አይጠበቅባቸውም›› የሚል ግልጽ ያልሆነ አመለካከት በመያዙ ጉዳዩ ብዙም መወያያ አልሆነም፡፡ ይልቁንም እስከዛሬ የሚያከራክረው የሕግ ተማሪዎች ውሳኔ ነው፡፡

ለሕግ ተማሪዎች ማፈንገጥ ብዙ መላምቶች ቢቀርቡም (‹አምስት አመት ስለሚማሩ ነው›፣ ‹ሕግ ስለሚያውቁ ነው›፣ ‹በርከት ያሉ የኢሕዴግ ደጋፊዎች ስላሉ ነው›፣ ወዘተ) አንዳቸውም አሳማኝ አይደሉም፡፡

ያኔም አሁንም እንደምከራከረው ክስተቱ የሁለት ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ አንድ – የሕግ ተማሪዎች የሚያዳብሩት የግለኝነት ስሜት፤ ሁለት – ራሳቸውን እንደዩኒቨርሲቲው ተማሪ ሳይሆን እንደሕግ ፋካልቲ ተማሪ የማየት (ተገንጣይ ስነ-ልቦና ልበለው) ዝንባሌ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ (ማለትም እነሱን ይበልጥ የሚጫነው የትንሹ(የፋካልቲው) ጀማ ዝንባሌ ነው፡፡)

ስለሆነም ጥቂት የማይባል ተማሪ እየተንጠባጠበ በግል ውሳኔ ትምህርት ሲቀጥል፣ የተቀረነው ደግሞ ትምህርት ለመቀጠል በክፍል ደረጃ ስብሰባ አድርገን መወሰን በቂ ሆኖ አገኘነው፡፡

እዚህ ላይ፡- የኔ ክፍል ተማሪዎች ትምህርት ለመቀጠል የወሰኑበት ስባሰባ ላይ(ውሳኔውን አስቀድሞ መገመት ይቻል ነበር) ሆነ ብዬ መቅረቴን ዛሬ ሳስበው ይገርመኛል፡፡

እንደኔ ዓይነቱ የግሉን እውነት የመከተል ባህሪ ያለው ሰው – ‹‹ትምህርት መቀጠል ተገቢ ነው›› ብሎ ባመነበት ቅጽበት ተግባራዊ ሊያደርግ ይቅርና – በተገላቢጦሹ ‹‹ትምህርት በመቀጠል ረገድ የመጨረሻው ሰው የመሆን›› ኢ-ምክንያታዊ ፍላጎት ማሳየቱ፣ ከላይ የዘረዘርኳቸው የወቅቱ የጀማ አስተሳሰቦች ድምር ውጤት እንዲሁም የጀማ ስነ-ልቦናን ተጽዕኖ ጥልቀት ማሳያ ነው፡፡

እንግዲያ ታዲያ፡- ‹‹ ሰዉ እንደሆነው መሆን›› የሚባል ጋርዮሻዊ መርህን ከልቡ ሲከተል ለኖረ ሀበሻማ – አንዴ ከገባበት የጀማ ስነ-ልቦና ማፈንገጥ እንዴት ይከብድ?

*********

* ይህ ሳይታሰብ የረዘመ ጽሑፍ፣ የስነ-ልቦና ባለሙያ ከሆኑ እና/ወይም በ1993ቱ አድማ ተሳታፊ ከነበሩ አንባቢዎች ጠንከር ያለ ትችት እንደሚጋብዝ እሰጋለሁ፡፡ ያ ግን የጽሑፉ ማዕከላዊ ነጥብ ሳይሳትና ግንዛቤያችንን በሚሰፋ መልኩ ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡
(የዚህ ብሎግ አጋር የሆነው ወልደብርሀን ሰሁል ይህን ጽሑፍ በመገምገም ድጋፍ ሰጥቷል፡፡)

Daniel Berhane

more recommended stories