የታጁራ-አሳይታ-መቀለ የባቡር መስመር ግንባታ

(ጌትነት ምህረቴ)

ባቡር ከየብስ የትራንስፖርት በዋጋ ርካሽ እንደሆነ ይነገራል። ፍጥነቱም ከተሽከርካሪ ይበልጣል። በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎችን ሆነ ሸቀጦችን በመጫን የማጓጓዝ አቅም አለው። በተለይ የባቡር ትራንስፖርት ለታዳጊ ሀገሮች የመገንቢያው ወጪ ከፍተኛ ቢሆንም ተመራጭ የትራንስፖርት ዘርፍ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት ተከትሎ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች በእጅጉ እየጨመሩ ይገኛሉ። የማዕድን ምርቶችን በተሽከርካሪዎች ብቻ ማጓጓዝ ወጭው ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ይህም የሚያ ሳየው ከኢኮኖሚው ዕድገቱ ጋር የተጣጣመ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያስፈልግ አጠያያቂ ያለመሆኑን ነው።

መንግስትም ይህን በመገንዘብ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ እንዳስቀመጠው በሀገሪቱ በሶስት ኮሪደሮች በአምስት መስመሮች ሁለት ሺ 395 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባቡር ኔት ወርክ ለመገንባት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ለመገንባት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ከዕቅዱ አኳያ ቢዘገዩም በአንፃሩ ደግሞ ግንባታቸው የተጀመረ ፕሮጀክቶች አሉ። ከተጀመሩት መካከል የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመርና የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ ይገኙበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ዝርዝር የዲዛይን ጥናታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙም ፕሮጀክቶች ይገኛሉ።

ከእነዚህ መካከል አንዱ ከአሳይታ-ታጁራ ድረስ የሚዘረጋው የ260 ኪሎ ሜትር የባቡር ፕሮጀክት ነው። ለእዚህ ፕሮጀክት ማስፈፅሚያ የሚውል ገንዘብ የህንድ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ በብድር ለመስጠት ስምምነት ላይ ተደር ሷል። ባንኩ ብድሩን ለመስጠት በመስማማ ቱም የመጀመሪያውን 300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ማስገኘት የሚያስችለውን የብድር ስምምነት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተፈራርሟል።

ከአሳይታ ታጁራ ድረስ የሚዘረጋው የባቡር መስመር ከመቀሌ-ታጁራ ሊዘረጋ የታቀደውን የባቡር መስመር አንድ ክፍል ነው። የባቡር መስመሩ ከሀገራችን ወደ ጂቡቲና ከጅቡቲ ወደ ሀገራችን የሚጓጓዙ ሸቀጦች በዝቅተኛ ዋጋና በብዛት በማጓጓዝ ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ መቀነስ ያስችላል። እንዲሁም የአፍሪካ ሀገሮችን በባቡር መስመር ለማገናኘት ከተነደፈው ከጅቡቲ-ዳካር የባቡር መስመር አካል በመሆን በአፍሪካ አገሮች መካከል የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ረገድም የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

ከመቀሌ -ታጁራ ድረስ ያለው ርቀት 683 ሲሆን ከዚህ ውስጥ 160 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር በጅቡቲ ግዛት ውስጥ የሚዘረጋ ነው። የባቡር መስመሩ ባለ አንድ ሀዲድ ሆኖ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ያህል ፍጥነት ይኖረዋል። ለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ያስፈልጋል ተብሎ ከተገመተው አንድ ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር የህንድ መንግስት ሰጥቷል። የፕሮጀክቱ ዝርዝር ጥናት ሲጠናቀቅ ተጨማሪ የ300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚሰጥ በህንድ መንግስት በኩል ቃል ተገብቷል። የፕሮጀክቱ ቀሪው የገንዘብ ልዩነት በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።

ከህንድ መንግስት በብድር የተገኘው 300 ሚሊዮን ዶላር በዓመት አንድ ነጥብ 75 በመቶ ወለድ ይከፈልበታል። ከአምስት ዓመት የችሮታ ጊዜ በኋላም በ15 ዓመታት ውስጥ ተመልሶ የሚከፈል ነው። ብድሩ ከኢትዮጵያ የብድር ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ከመሆኑ ባሻገር አነስተኛ ወለድ የሚከፈልበት ነው። በዕድገትና ትራንስፎ ርሜሽን ዕቅድ ከተቀመጡት የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ ብድሩ ከአሳይታ እስከ ታጁራ ድረስ ያለው የባቡር መስመር ግንባታ ለፍፃሜ እንዲበቃ የሚያስችል ነው። የባቡር መስመር ግንባታው ሲጠናቀቅም የወጪና የገቢ ምርቶችን በፍጥነትና በአነስተኛ ወጪ በማጓጓዝ ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል። በግንባታ ሂደትም ለብዙ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል። በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠርም ይረዳል ሲሉ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድሙ ገዛኽኝ ይገልፃሉ። ይህን መሰረት በማድረግም የረቂቅ የብድር ስምምነቱን ማፅደቂያ አዋጁን ምክር ቤቱ እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል። የምክር ቤቱ አባላትም ብድሩን በተመለከተ ዝርዝር ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም የባቡር ግንባታው ምን ያህል አዋጭነቱ ታይቶ ነው እስከ ጅቡቲ ድረስ የባቡር ሀዲድ የምንገነባው? በሁለቱ መንግስታት በኩል ምን አይነት ስምምነት ተደርሶ ነው?፤ የባቡር መስመር ግንባታው የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከመፍጠር አኳያ አስተዋፅኦ ይኖረዋል?

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስተር አቶ ሱፊያን ለጥያቄዎቹ ምላሽ ሲሰጡ እንዳሉት ይህ የባቡር መስመር የሀገራችን ሰሜንና ሰሜናዊ ምስራቅን ከማገናኘቱ ባለፈ ጅቡቲ ውስጥ ወደሚገኘው አዲሱ የታጁራ ወደብ ድረስ የሚዘረጋነው። ይህም ኢትዮጵያ ይህን ወደብ በመጠቀም ወደ ውጭ የምትልካቸውን የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማጓጓዝ ያስችላል። እንዲሁም ሀገሪቱ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባቸ ውን ሸቀጦች በቀላሉ ለማጓጓዝ የሚያስችል ነው። በተጨማሪም በአፋር ክልል አካባቢ የተገኘውን የፖታሽ ሀብት ለውጭ ገበያ ለማቅረብና መስመሩ በሚያልፍባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ማለትም ለትግራይ፤ ለአማራ ለአፋር ነዋሪዎች እና ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ተጓዦች የባቡር ትራንስፖ ርት አገልግሎት የሚሰጥ ነው ። የሚዘረጋው የባቡር መስመር በኤሌክትሪክ የሚሰራ በመሆኑ ለጭነት ተሽከርካሪዎች ነዳጅ እና መለዋወጫ ይወጣ የነበረውን ወጪ ያድናል። ይህም ገንዘብን ለሌላ ልማት በማዋል የኢኮኖሚ ዕድገቱን እንዲፋ ጠን ያግዛል።

የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ክፍሎች አሉት። አንዱ ሀዲድ መዘርጋት ሲሆን ሌላው ደግሞ የባቡር መስመሩ የራሱ የሆነ ባለ 123 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመርና የመገናኛ መስመር እንዲሁም የመቆጣጠሪያ ስርዓት ይኖረዋል። የባቡር መስመሩ በሚያልፍበት አካባቢዎች በሚገኙ 37 ከተሞች ጣቢያዎች ይኖሩታል። የባቡሩ መስመር ከተሰራ በኋላ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በድሬዳዋ አድርጎ ጅቡቲ ድረስ በሚዘረጋው የባቡር መስመር ጭምር ኢትዮጵያና ጅቡቲ ቀደም ሲል እንደነበረው አካሄድ ሳይሆን የተለየ ስምምነት አድርገዋል። ሀዲድን በተመለከተ ጅቡቲዎች እስከ ራሳቸው ወሰን ድረስ ራሳቸው ያስተዳድራሉ። ነገር ግን ሀዲዱ ከተሰራ በኋላ ማጓጓዙን በተመለከተ ሁለቱ ሀገሮች በጋራ ኩባንያ ያቋቁማሉ። ኩባንያው የንግድ ኩባንያ ነው። በዘመናዊ የኩባንያ አሰራር የሚመሰረትና ሁለቱ መንግስታት የሚወኩሉት ድርጅቶች የሚያስተዳድሩት ይሆናል። ኢትዮጵያን የሚወክለው ድርጅት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረው የኢትዮጵያ የባቡር ኮርፖሬሽን ነው። በጅቡቲ በኩልም እንዲሁ ተመሳሳይ አይነት ድርጅት አቋቁመዋል።

መንግስትን ወክለው እነዚህ ሁለት ኩባንያዎች የጋራ ኩባንያ ፈጥረው ያንን ኩባንያ ያስተዳድራሉ። የኩባንያው ሀብትና ዕዳ የሚወሰነው ሁለቱ ሀገሮች በሚያዋጡት ገንዘብ ይሆናል ይላሉ። «በእኛ ግምት አብዛኛው እስከ 90 በመቶ ሊሆን የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፍነው ይሆናል ብለን ነው የምንገምተው።ለስራው እንዲመችና ለማስተባበር እንዲቻል የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ አድር ጎልን አስተባብሮ ይስራ የሚል ጥያቄ ከእነሱም በኩል ስለቀረበና በእኛም በኩል ተቀባይነት ስላገኘ በጋራ እየሰራን ነው። በዚህ መሰረትም ከጅቡቲ ጋር የጋራ ኮሚቴ አቋቁመናል። በእነሱ በኩል ያለውን ወጪ እነሱ ይችላሉ። በእኛ በኩል ያለውን ወጪም እኛ እንችላለን ነው» ያሉት አቶ ሱፊያን።

የመቀሌ-ታጁራ የባቡር መስመር የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ሀገሮችን በባቡር መስመር ለማገናኘት ከነደፋቸው ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የጅቡቲ ዳካር የባቡር መስመር አካል ነው። ይህም ሀገሪቷ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር የኢኮኖሚ ትስስር እንድትፈጥር ያስችላታል። የዚህ ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህ ጥናት መሰረት ከመቀሌ እስከ ሀራ ገበያ ፤ ከሀራ ገበያ እስከ አሳይታ እንዲሁም ከአሳይታ እስከ ታጁራ ድረስ ያለው የባቡር መስመር በሶስት ከፍሎች ተከፋፍሎ የሚገነባ ይሆናል። ግንባታውን ለመጀመር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

ከምክር ቤት ለቀረቡት ጥያቄዎች ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ረቂቅ የብድር ስምምነት ማፅደቂያ አዋጁን ምክር ቤቱ አፅድቆታል።

የባቡር ትራንስፖርት የምርት ግብዓቶችንና ምርቶችን በአነስተኛ ዋጋ በአጭር ጊዜ በገፍ ለማማጓጓዝ የሚያስችል ተመራጭ ትራንስፖርት ነው። በዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅዱ ሀገራዊ የባቡር መስመር ዝርጋታው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ቢገኘም ከዕቅዱ አንፃር እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ስራ ያልተጀመረባቸው ፕሮጀክቶች እንዳሉ በመገንዘብ በቀሪ ሁለት ዓመት የዕቅድ ዘመን በዘርፋ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ስራ ማከናውን ከመንግስት የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል።

*************

*Originally published on Addis Zemen newspaper.

Daniel Berhane

more recommended stories