ተቃዋሚዎችና የህዳሴ ግድብ፡- ቅብብሎሹ ከየት ወዴት ነው?

(By እናት ከመሳለሚያ)

ዘንድሮ 22ኛው የግንቦት 20 በዓል የተከበረው የህዳሴ ግድቡ ከደረሰበት የላቀ ደረጃ ጋር በማስተሳሰር ነበር፡፡ የግድቡን ግንባታ ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገው በተወሰነ ኪሎ ሜትር ውስጥ የውሃውን ፍሰት የማስቀየስ ሥራ በእዚሁ የድል በዓል ወቅት መከናወኑ ዕለቱን ልዩ ትርጉም አሰጥቶቷል፡፡

ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ ሥራ አመቺነትን ለማረጋገጥ ያከናወነችውን ተግባር ተከትሎ የግብፅ መንግሥት እና አንዳንድ የሀገር ውስጥም ሆኑ ሌሎች ኃይሎች ጫና ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ተስተውሏል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ መንግሥት ጉዳዩን በሰከነ ሁኔታ በመከታተል አስተዋይነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በእዚህም ጥረት የግብፅ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን እዚሁ አዲስ አበባ በመላክ ከሀገራችን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡

በእዚህ ሽኩቻ ግን የአገራችን አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዩን ለራሳቸው የረከሰ ፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል ደፋ ቀና ሲሉ ለመታዘብ ችለናል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች እንደተለመደው አንድ ፓርቲ ሊኖረው የሚገባውን ባህሪ ይዘው አይተናቸው አናውቅም፡፡ የልማት እና የዴሞክራሲ አጀንዳን የሀገር ጉዳይ ነው ብለው እምነት ቢኖራቸው እንደ ፓርቲ አማራጭ ፖሊሲም ለማፍለቅ በጣሩ ነበር፡፡ ለነገሩ ይህን ለማድረግ የሀገር ፍቅርንና አቅም ይጠይቃል፡፡

እስኪ ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ እያሳዩት ወዳለው ተግባር እንመለስ፡፡ የመድረክ ፓርቲ የግብፅ መንግሥትን ግራ የተጋባ አቋም እና መግለጫ ተከትሎ እንዳስታወቀው፤ ፓርቲው ከዚህ ቀደም የህዳሴ ግድብን ግንባታ አዋጭነት እምነት የለውም፡፡ ዛሬ ደግሞ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር እንደ ቅድመ ሁኔታ ለመጠቀም ማሰቡን አመልክቷል፡፡ «የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ለማሳካት ከኢህአዴግ ጋር መደራደር አለብኝ፤ ከግብፅ በኩል የሚመጣውን ስጋት ለመመከት ድርድሩ ግድ ነው»ሲል አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡

ከመድረክ ቀድሞ መግለጫ ያወጣው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ «ግድቡ ከመሰራቱ አስቀድሞ መሰራት የነበረባቸው የዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች አልተከናወኑም፤ በእዚህ ምክንያት ነው ከግብፅ ጋር ችግሩ የተከሰተው» በማለት ትችቱን ሰንዝሯል፡፡ይህ ወቀሳ ግን እውነታውን ያላገናዘበና የኢትዮጵያ መንግሥት ቢያንስ በናይል ኢንሼቲቭ ለ10 ዓመታት ያደረገውን ጥረት የዘነጋ ነበር።

ምንም እንኳ የሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ ፉከራና ሽለላ የበዛበት ቢሆንም ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ ያስቀመጠውን ጉዳይ እንመልከት፡፡«በዓባይ ላይ የተጀመረው ግድብ ሥልጣን ለማራዘምና ለፖለቲካ ፍጆታ እየዋለ ነው» ሲል የፓርቲው እምነት እንደሆነ በመግለጫው ያትታል፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች እያቀነቀኑት ያለውን ጉዳይ በቅጡ የተረዱት አይመስለኝም፡፡ ዓባይን በፍትሐ ዊነት የመጠቀም ጉዳይ በመሰረቱ የሀገር ኢኮኖሚንና የሕዝብ ኑሮን የመቀየር ጉዳይ ነው። በእዚሁ መሠረት ደካማም ሆነ ጠንካራ ፓርቲ ይኑሩ፤ በቁጥር በዛ ያሉ ፓርቲዎችም ይኑር የዓባይ ጉዳይ የአገር እና የሕዝብ ጥቅም፤ አለፍ ሲልም የሉዓላዊነት ጉዳይ፣ የህልውናም ጭምር መሆኑን ፓርቲዎቹ አላወቁም፡፡ ቢያውቁትም ሊመሰክሩ አልፈለጉም።

ዓባይን የመጠቀም ጉዳይ ኢትዮጵያና ግብፅን ብቻ የሚመለከታቸው ይመስል የእኛ አገር ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግብፅን አቋም በተለያየ መልኩ ሲያራግቡ እናያለን፡፡ የግብፅስ መንግሥት ቢሆን የሚፈልገውና በመግለጫው ጭምር ያሳወቀው የአገራችንን ተቃዋሚዎች መጠቀም አይደል፡፡ ከዚህ ቀደም እነዚህ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን ጥቅም ከሚጠሉ አካላት ጋር የመወዳጀት ባህሪያቸው አያስገርምም፡፡ አሁንም እየሆነ ያለው ይህ ነው፡፡

የግብፅን ጥያቄ በግልጽ ለማስረዳት ይረዳን ዘንድ በ1929 እና 1959 ወቅቶች የተፈረሙ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን በወፍ በረር እንመልከት፡፡ እ.አ.አ በ1929 ጠንካራ የቅኝ ግዛት በትር የነበራት እንግሊዝ የናይልን የውሃ ተጠቃሚነት በባለቤትነት እንድታስተዳድር ብቻ ሳይሆን የበላይ እንድትሆንም ግብፅን ትልቅ ሥልጣን ችሯታል፡፡

ልብ በሉ እንግሊዝ ይህን ስታደርግ በወቅቱ ቅኝ የገዛቻቸው አገራትን መብት ጭምር አሳልፋ ለግብፅ በመስጠት ነበር፡፡ ዛሬስ እነዚህ አገራት በቅኝ ግዛት ውስጥ ናቸው እንዴ? አይደሉም፡፡ የሀገራችን አንዳንድ ፓርቲዎች ግብፅ ዛሬ የምታነሳው «የዓባይን አትጠቀሙ» ጥያቄ ሉዓላዊ የሆኑ አገራትን መብት ዳግም ለመንጠቅ የምታደርገው «የቅኝ ግዛት አባዜ» መሆኑን መረዳት ነበረባቸው። አገራዊ ጥቅምን ለማሳጣት ከመሮጥ ይልቅ የሕዝብ ጥቅም ለማስከበር የሚተጉትም ይህ ሲሆን ነበር፡፡ ለእዚህም ነው ተቃዋሚዎቻችን ጉዳዩን በቅጡ አልተረዱትም የምለው፡፡

ግብፅ ይህን ጥያቄ ስታነሳ የዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የሰጡትን ምላሽ በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ «ግብፅ የትምክህት አስተያየቶችን ከመስጠት መቆጠብ አለባት» ነበር ያሉት፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህን ምላሽ ሲሰጡ ለኢትዮጵያ ጥቅም ብቻ ብለው አይደለም፡፡ ዛሬ እንደ 1929 የአገራትን ሉዓላዊ መብት መንጠቅ እንደማይቻል በሚገባና በግልጽ ለማስገንዘብ ነው፡፡

እጅግ ካሳፈረኝ የአንድነት መግለጫ ውስጥ በዓባይ ጉዳይ ኢህአዴግ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ባለማከናወኑ ነው ሲል የሰጠው ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? አንድነት የኢትዮጵያ መንግሥት በዲፕሎማሲው ረገድ ምን ዓይነት ተጨባጭ ሥራዎችን እንደሰራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭራሽ የማያውቅና ከመረጃ የራቀ መሰላቸው እንዴ፡፡

ኢትዮጵያ የተፋሰሱ አባል አገራትን በማስተባበር ኢ=ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም በነበሩ አኳኋን እንዳይቀጥል ብርቱ ትግል አድርጋለች። ግብፅ እና ሱዳንን ጨምሮ እ.አ.አ በ1997 የናይል የትብብር ማዕቀፍ በፕሮጀክት ደረጃ ተቀርፆ የዓባይ ተፋሰስ አገራት ዘላቂና ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም የሕግ ማዕቀፍ የማርቀቅ እና የድርድር ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ እንዲያው አንድነት አሊያም መሰል ተቃዋሚ ኃይሎቹ እንደሚያወሩት «ያላዋቂ ሳሚ» አስተያየት እጅግ ኋላ ቀር እንደሆኑ አጋልጧቸዋል፡፡ እኛም አፍረንባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚኖራት የፍትሐዊነት ጥያቄ ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚለው የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ጥቅም ጉዳይ አይደለም፡፡ ልማትን ለማምጣት አንድ ፓርቲ የሚዘረጋው ፖሊሲም ሆነ ስትራቴጂ የሚለካው በአስገኘው ውጤት በመሆኑ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሪው ፓርቲ መሆኑ ግን አይካድም። ጉዳዩ ግን ይህ አይደለም፡፡ ተቃዋሚዎቹ በተለይ ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ የዓባይን ጉዳይ የትኛውም ፓርቲ ቢመጣም ቢሄድም የሕዝብ ጥቅም መሆኑን መረዳት ግድ ይላቸዋል፡፡

የትም ሳንሄድ ግብፅ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገዥውም ጭምር በዓባይ ጉዳይ ልዩነት አላየንባቸውም፡፡ አንድ ሆነው ነው ኢትዮጵያን ሲያስፈራሩ የሰነበቱት፡፡ እንዲያውም የአገራችንን ተቃዋሚዎች ሕዝባዊ መሰረተ ቢስና የሀገር ጥቅም ማስከበር እንደማይችሉ ስለሚያውቁ «ለግብፅ ጥቅም የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች እንጠቀማለን» ሲሉ በግላጭ ተናግረዋል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው፡፡

እስኪ ግብፅ ኢትዮጵያን ለማዳከም ያስቀመጠቻ ቸው ስድስት ነጥቦች ምን ይዘት አላቸው ብለን እንመርምር፡፡ አንዳንድ የግብፅ ፓርቲዎች «የሃይማ ኖትና የብሔር ብዝሀነትን እንጠቀማለን» አሉ፡፡ የእኛዎቹም ተቃዋሚዎች በቀጥታ በመግለጫቸው እንዲያም ሲል በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር እናስተጋባለን ያሉት የግብፅን ጉዳይ አይደለም እንዴ?ለፌዴራላዊ ሥርዓቱ ዕውቅና ለመስጠት የሚዳዳቸው ትንሿን ግጭትና የግለሰብ ሳይቀር የብሔር ብጥብጥ አስመስለው የሚለኩቱ ስንቶች ናቸው።

«መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ የሃይማኖት ነፃነት እንዲረጋገጥ ጠይቀው የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ ሰልፉን ጠርቻለሁ» ብሏል አንድነት፡፡ እናስ ከየት ወዴት ነው ቅብብሎሹ? ከግብፅ መንግሥት የወረደን መመሪያ ለማስፈፀም፤ የሕዝብን ጥቅም ማሳጣት አይቻልም፤ መታሰቡ በራሱ አሳፋሪ ነው፡፡ ይህ ግን ኢትዮጵያውያን የማያውቁት ከሕዝብ የተሰወረ አይደለም፡፡ አንድነትም ሆነ ሰማያዊ ፓርቲ ጠርተናል በሚሉት ለሰላማዊ ሰልፍ ድብቁን ተልዕኳችሁን ተረድተናል ማለት እወዳለሁ፡፡

ሌላው እርስ በርሱ የተምታታን አንድ ጉዳይ ላንሳ፡፡ መድረክም ሆነ አንድነት ቀደም ሲል በግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት የሰጡት መግለጫ ከነአካቴው በግድቡ አዋጭነት ላይ እምነት እንደሌላቸው የሚገልፅ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር መድረክ በቅድመ ሁኔታነት ለመጠቀም እየሞከረ ነው፡፡ መድረክም አንድነትም ግድቡ የሚያጋጥመው ጥቃት ካለ ግን እንደሚመክቱ ይናገራሉ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም «የህዳሴውን ግድብ የኢህአዴግ ፖለቲካ ማስፈፀሚያ ፕሮፓጋንዳ ነው» ይላል፡፡

በድምሩ ሲታዩ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከላይ ያላቸውን አቋም ስታዘብ ያገኘሁትን የተምታታ ጉዳይ ልጠቁማችሁ፡፡ «የህዳሴ ግድቡ አዋጭ አይደለም፤ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል የተፈጠረ ነው፤ የሕዝብ ሳይሆን የኢህአዴግ ፕሮጀክት ነው» ብለዋል፡፡ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ግድቡን ግብፅ ከምትሰነዝረው ጥቃት እንደሚከላከሉም ዘራፍ ሲሉ ይስተዋላሉ፡፡

እኔ የሚመስለኝ የህዳሴ ግድቡ አገራዊ፣ ሕዝባዊና ክፍለ አህጉራዊ ዓላማ እንዳለው ነው፡፡ ይህን መሰል ዓላማ ያለውን ግድብ ከጥቃት ለመከላከል ቅድሚያ በዓላማው መስማማትን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ያላመንክበትን ጉዳይ ከአደጋ ልከላከል ብለህ አትነሳም፡፡ እውነት ግን ጉዳዩ ይህ ነው፡፡ ግድቡ በየዕለቱ ያለውን እድገት እንደ እግር እሳት እየለበ ለባቸው ሳለ ‹«ፈንዲሻ ውስጧ እያረረ…›» አይነት «ቂቤ ጠባሽነት» ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወቅታዊና ከድህነት ለመውጣት ላሉ የተለያዩ አማራጮች እና ጥያቄዎች ምላሽ አይደለም፡፡

እውነት እነነጋገር ከተባለ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ሥራቸው የሕዝብን የልማት እና የዴሞክራሲ አጀንዳ ማስቀየስ መሆን አልነበረበትም፡፡ ይህ ተግባራቸው ተደጋጋሚ ስለሆነ ተነቅቷል፡፡ሥራቸው መሆን የሚገባው አዲስ የልማት አስተሳሰብ ለመቅረፅ እንጓዝበታለን በሚሉት ርዕዮት ዓለም ጠገግ ከተቻላቸው አንድ ሁለት ማሳያ ፖሊሲ ቢያወጡም የተሻለ ነበር፡፡

ዓለም እየኮነነው ያለውን የሽብርተኝነት ተግባር ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የፀረ ሽብር ሕግ አውጥታ ለመታገል በተነሳችበት ወቅት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና አመራሮች ጭምር ኢትዮጵያን በሽብር ተግባር እናተራምሳለን ካሉ ኃይሎች ጋር ወግነው ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ በሕግ ጥላ ስር እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ ይህ የሆነው በፓርቲ ስም በመንቀሳቀስ የወገንን ሕይወት ለመቅጠፍ ሲያስቡ የተገኙትን ጭምር ነበር፤ ግን አልሆነም በሕዝብ እና በፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ጥረት በበቂ ሕጋዊ ማስረጃ ተይዘዋል፤ ተፈርዶባቸውም ማረሚያ ይገኛሉ፡፡

የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ተከትሎ በነበረው የግብፅ ተግባር የአገራችን ተቃዋሚዎች ርዕስ አድርገው የተነሱት ሕግን የማሻር ዘመቻ ነው፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉ የኢትዮጵያውያንን እልቂት እና ውድመት ያስቀረ ነው፡፡ ማናችንም የማንዘነጋቸው በተለያዩ ወቅቶች የተሰነዘሩት የሽብር ጥቃቶች በከተማችን የተለያዩ ቦታዎች ላይ ዜጎች ከቤት እንደወጡ አስቀርተዋል፤ ከፍተኛ ንብረትም እንዲወድም አድርገዋል፡፡ ይህን የሽብር ተግባር በሕግ ማዕቀፍ ለመግታት እንደ መንግሥት የተሰራው ሥራ ተገቢና አስፈላጊም ነበር፡፡

ተቃዋሚነት ግን ገዥው ፓርቲ በሥልጣን ላይ ሳለ የሚሰራቸውን ተግባራት በሙሉ «መቃወም» እንዳልሆነ ለተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የሚጠፋቸው ይሆን? አስገራሚው ነገር አንድ አገርን ለወደፊቱ ልመራ እችላለሁ ብሎ የተቋቋመ ፓርቲ የሀገርን ሕግ ለመጣስ እና ሕጉ ይሻሻልም ሳይሆን ይሰረዝ ብሎ መሯሯጥና ሕዝብን ማደናገሩ ነው፡፡

እኔ እንደምገነዘበው አንድነትም ሆነ ሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕግን ለመጣስ የሚያደርጉት ድፍረት አሁንም ከተጠያቂነት እንደማያስቀራቸው ነው፡፡ የሽብር ተግባር ውስጥ ገብተው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሽብር ሊፈፅሙ ሲሉ የተያዙ ሰዎች ይፈቱ ማለትንስ ምን አመጣው፡፡ በሃይማኖት አክራሪነት የሌላውን ሃይማኖት አማኝ ወይም ተከታይ «የእኔን ተከተል» ብሎ በተግባር ጭምር ሲያስገድድ እና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ግለሰቦችን «ነፃ ናቸው» በማለት መፈረጅ እና እንዲፈቱ መወትወት ከምን የመነጨ ነው?

በጥቅሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይ አንድነት ፓርቲ በተግባሩ ሲመዘን ትክክለኛ የፖለቲካ ፓርቲ ባህሪን አንግቧል ማለት አይቻልም፡፡ አሁንም በሚገባ መታየት አለበት ባይ ነኝ፡፡ የፓርቲው ተፈጥሯዊ ባህሪን በሚገባ ልንገነዘበው ይገባል ማለት ነው፡፡

ሰሞኑን የግብፅ በህዳሴ ግድቡ ላይ የነበራት የቅኝ ግዛት አባዜ ለአገራችን ተቃዋሚዎች ሽር ጉድ እንዲሉ እንደ መልካም እድል እየተጠቀሙበት ነው፡፡ በተለይ ለአንድነት፣ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ ሠርግ እና ምላሽ አስመስሎታል፡፡ ግብፅ እኮ ያነሳችው ጉዳይ ዓባይን ነው፤ ተቃዋሚዎቻችን ሰልፍ የጠሩበት ጉዳይ ደግሞ ግብፅ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን ተጠቅሜ ኢትዮጵያን አዳክማለሁ ባለችው ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ የእኛ ተቃዋሚዎች መቼ ነው ለሀገራዊ ጥቅም የሚቆሙት? ሀገራዊ ጥቅምን ማስከበር የግድ ሥልጣን ሲያዝ ብቻ ይሆን?

**************

Source: Addis Zemen – July 1, 2013, titled “ቅብብሎሹ ከየት ወዴት ነው? የግብፅ መንግሥትን አጀንዳ ለማስፈፀም፤ የሕዝብን ጥቅም ማሳጣት አይቻልም!”

Daniel Berhane

more recommended stories