ሙሼ ሰሙ፡- መንግስት የግል ባንኮችን ለማጥፋት ታጥቆ ተነስቷል

(አለማየሁ አንበሴ)

የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት የቁጠባ ፕሮግራም መንግስታዊ በሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ እንዲከናወን መደረጉ በግል ባንኮች ላይ ከፍተኛ ኪሣራ እያስከተለ እንደሆነና በአጭር ጊዜ የግል ባንክ ዘርፉን ህልውና አደጋ ላይ እንደሚጥል የባንክ ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ እስካሁን ከ750ሺህ በላይ ግለሰቦች የቤቶች ልማት ቁጠባ ሂሣብ በንግድ ባንክ እንደከፈቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የግል ባንክ ባለሙያ፤ እሣቸው በሚሠሩበት ባንክ ደንበኛ የነበሩ ግለሠቦች በቤቶች የቁጠባ ፕሮግራም ተሣታፊ ለመሆን ከባንኩ ገንዘብ በማውጣት በመንግስት ባንኮች እያስቀመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ሣምንታትም ባንኩ በዚህ አገልግሎት ተጠምዶ መቆየቱን የተናገሩት ባለሙያው፤ “በእነዚህ ጊዜያትም የባንክ ሂሣብ ለመክፈት ወደ ባንካችን የመጣ ደንበኛ አላጋጠመኝም” ብለዋል፡፡ በባንኩ ያላቸውን ገንዘብ ለማውጣት የሚመጡ ደንበኞች መበራከታቸውንና ይህም ባንኩ ራሱን ለማቋቋም ለዓመታት የደከመበትን ልፋቱ ከንቱ እንደሚያስቀረውና ቀጣይ ህልውናውንም አደጋ ላይ እንደሚጥለው ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ ስማቸውና የሚሠሩበት ባንክ እንዲገለፅ ያልፈለጉ ሌላ ባለሙያም፤ በአሁን ሠአት ባንካቸው የውጭ ምንዛሬ እና የሃዋላ አገልግሎቶችን ከመስጠት ባለፈ አዳዲስ የባንክ ሂሣብ የሚከፍቱ ደንበኞች እያስተናገደ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለም የባንኩ ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

የኢዴፓ ሊ/መንበርና ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሼ ሠሙ በበኩላቸው፤ መንግስት መንግስታዊ በሆነው የንግድ ባንክ በኩል ብቻ ዜጐች እንዲቆጥቡ ማወጁ ከነፃ ገበያ ስርአት ጋር የሚቃረን መሆኑን ገልፀው ይህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በግል ባንኮች ላይ ከፍተኛ የህልውና አደጋ መጋረጣቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ አካሄድ ከቀጠለም ያለ ጥርጥር ከሶስት እና አራት አመታት በኋላ የበርካታ የግል ባንኮች ህልውና እስከ መጨረሻው ሊያከትም ይችላል ብለዋል – አቶ ሙሼ፡፡ የቤቶች ልማት ቁጠባ ፕሮግራም ሁለት መሠረታዊ ተፅዕኖዎች አሉት የሚሉት አቶ ሙሼ፤ አንደኛው በግል ባንክ ውስጥ ከሚያስቀምጡ ደንበኞች ገንዘብ ላይ ማበደር አንዱ የባንኮች ተግባር መሆኑን ገልፀው፤ አሁን ግን ይህን ተግባር የሚያከናውኑበት ገንዘብ ወደ መንግስታዊ ባንክ እንዲሸሽ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

ይሄም ብቻ ሳይሆን የግል ባንኮች በብዙ ዓመታት ያፈሯቸውን ነባር ደንበኞችም እንዲያጡ ያደርጋል ብለዋል፡፡ መንግስት የቀረፀው የቤቶች ልማት ፕሮግራም የግል ባንኮች አዳዲስ ደንበኞችን እንዳያፈሩ ማድረጉ ሁለተኛው ተፅዕኖ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አዲዲስ ደንበኞችን እንዲያገኝ ይረዳዋል ብለዋል፡፡ ነባሩም ይሁን አዲስ ደንበኛ ከግል ባንኮች ወጥቶ ወደ መንግስት ባንክ መሄዱ የነፃ ገበያ ስርአት እንዲከስም ከማድረጉ ባሻገር ባንኮችም በህብረተሠቡ ዘንድ ለዘመናት የገነቡትን ጠንካራ እምነት እንዲያጡ ያደርጋል በማለት የግል ባንኮች ላይ የተጋረጠውን አደጋ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ መንግስት የግል ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ ላይ 27 በመቶ የህዳሴውን ግድብ ቦንድ እንዲገዙ ማዘዙን ያስታወሡት አቶ ሙሼ፤ የአሁኑ የግል ባንኮችን ያገለለው የቤቶች ቁጠባ ፕሮግራም ሲጨመርበት በባንኮቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የቱን ያህል እንደሆነ መገመት አያዳግትም ብለዋል፡፡ “መንግስት የግል ባንኮችን ለማጥፋት ታጥቆ መነሣቱ የሚገርመኝ ጉዳይ ነው” ያሉት አቶ ሙሼ፤ በዚህ አካሄድ ከሦስት እና አራት አመት በኋላ የግል ባንኮች ሊጠፉ እንደሚችሉ ምንም ጥያቄ የሚያስነሣ ጉዳይ አይደለም ይላሉ፡፡

ኢህአዴግ ጉልበትና አቅም ያለው የግል ዘርፍ እንዲፈጠር አይፈልግም የሚሉት አቶ ሙሼ፤ በግል ባንኮች ላይ እየደረሠ ያለው ጫናም የዚሁ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ አባባላቸው ማስረጃ ሲያቀርቡም በቅርቡ የወጣ ጥናት ኢትዮጵያ በመንግስት ኢንቨስትመንት ከአለም 2ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ በግል ኢንቨስትመንት ግን በመጨረሻው ረድፍ ከተዘረዘሩት ሃገራት አንዷ ነች ብለዋል፡፡ አቶ ቡልቻ ደመቅሣ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊትም ከቻይና ለሚመጣ ማንኛውም እቃ በንግድ ባንክ በኩል ብቻ ግብይቱ ይፈፀም የሚል ህግ መፅደቁን አስታውሠው፣ ያሁኑ ሲጨመርበት በእርግጥም የግል ባንክ ዘርፉ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦበታል ብለዋል፡፡ መንግስት በተደጋጋሚ በባንክ አሠራር ውስጥ ጣልቃ መግባቱ ለዘለቄታው የማያዋጣ ተግባር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቡልቻ፤ እንዲህ ማድረጉም አገሪቱን የዓለም ንግድ ድርጅትን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ማህበራት አባልነት እንዳገለላት በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

**********

Source: Addis Admas – June 29, 2013, titled “የግል ባንኮች ህልውና አደጋ ላይ ነው ተባለ”

Daniel Berhane

more recommended stories