ኢህአዴግ:- መድረክና አንድነት መቼም ከግድቡ ጎን አይቆሙም

Highlights:
* መድረክ ዘንድሮም እንደተለመደው የነገሮችን አወዳደቅ ካየ በኋላ ባወጣው መግለጫ ከዚህ በፊት አላምንበትም ያለውን ግድብ ግንባታ ለማሳካት ከኢህአዴግ ጋር መደራደር አለብኝ፤ ከግብፅ ወገን የሚመጣ ስጋትን ለመመከት ከኔ ጋር መደራደር የግድ ነው ብሎ ተነስቷል፡፡

* የአገራችን ህዝቦች ግድቡን የማንንም እጅ ሳያዩ ለመገንባት ቆርጠው እንደተነሱ ሁሉ ለግድቡ ግንባታ በኩርፍያ ጥግ ይዘው የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይሁንታ ማግኘትም አያስፈልጋቸውም፡፡

* ታላቁ የህዳሴ ግድብ የህዝብ ፕሮጀክት ነው፡፡ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቅርስ፣ መንፈስ፣ ክህሎትና ቁጭት የፈሰሰበት በማንኛውም መልኩ የአንዱ ወይም የሌላው ፓርቲ ሃብት ሊሆን የማይችል ታላቅ ሃገራዊ ክንዋኔ ነው፡

* አንድነት/መድረክ በመግለጫው ግብፅና ኢትዮጵያ ከፀብ አጫሪነት ተግባር ሊታቀቡ ይገባል በማለት የግብፅን መንግስት ኢፍትሃዊ የጉዳይ አያያዝ በቀጥታ ላለመንቀፍ ተንቀሳቅሷል፡፡

* ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት የሌለውንና ለፖለቲካ ጥቅም የዋለ ነው የሚለውን ፕሮጀክት፤ የህዝብ ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅት ንብረት ነው ብሎ የሚያስበውን ፕሮጀክት ከጥቃት ለመከላከል አንድነት/መድረክ ፍላጐቱም ወኔውም እንደሌለው ለሁላችንም ግልፅ ነው፡፡

* የህዳሴው ግድብ ግንባታ እና በየወቅቱ እየታየ ያለው እድገት የሚያንገበግበው መድረክ ግድቡን ከጥቃት ለመከላከል መቼውንም እንደማይነሳ ኢህአዴግም የኢትዮጵያ ህዝቦችም አሳምረው ያውቃሉ፡፡

——–

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለገበያ ድርድር የማይቀርብ የህዝብ ፕሮጀክት ነው

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሰሞኑን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ መንግስት ጋር የተፈጠረውን ውጥረት መሰረት በማድረግ መግለጫ አውጥቷል፡፡ መድረክ ባወጣው መግለጫ ላይ አባይን ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ማልማት የሚቻለው በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል አገራዊ መግባባት ሲፈጠር ነው በማለት የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በፓርቲዎች መካከል ከሚደረግ ድርድር ጋር ለማቆራኘት ሞክሯል፡፡ ድርጅቱ ከዚያም አልፎ ከግብፅ በኩል የሚመጣውን ስጋት በብቃት ለመመከት በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል መግባባት መኖር አለበት በማለት የአገር ሉዓላዊነትና ክብርን ጉዳይ ለተራ የፖለቲካ ጥቅም ለማዋል ያለውን ርካሽ ፍላጐት በአደባባይ ግልፅ አድርጓል፡፡EPRDF logo

የህዳሴውን ግድብ ለመስራት ታላቁ መሪ በቦታው ተገኝተው የመሰረት ድንጋይ ባኖሩበት ወቅት መላ የአገራችን ህዝቦች ከዳር እስከዳር ይህንን ብስራት በታላቅ ሃገራዊ ወኔና የቁጭት መንፈስ እንደሚደግፉ ለጠላትም ለወዳጅም ባስገረመ ትዕይንተህዝብ ሲገልፁ መድረክ በግድቡ ግንባታ ላይ ያለውን አቋም ለመግለፅ 13 ቀናት ወስደውበታል፡፡ በወቅቱ ባወጣው መግለጫም ይህንን ታላቅ የአገራችን ህዳሴ መገለጫና የዘመናት የህዝባችን ቁጭት ምላሽ የሆነውን ፕሮጀክት ለማንኳሰስ የግድቡ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት እንዳልተጠና፣ የሚሰራበት ቦታ ደህንነት አስተማማኝ እንዳልሆነ፣ ግድቡ የህዝቡን የፖለቲካ አቅጣጫ ለማስቀየር ተብሎ የተቀየሰ ፕሮጀክት መሆኑን እንዲሁም ከግድብ ግንባታ በፊት በፓርቲዎች መካከል ድርድር መደረግ አለበት የሚሉና ሌሎች ተልካሻ ምክንያቶችን በመደርደር በተጋጋለው የአገራችን ህዝብ ስሜት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ለመቸለስ ሞክሮ ነበር፡፡

የኢህአዴግ መንግስት ፕሮጀክቱ የመላ የአገራችን ህዝቦች ፕሮጀክት መሆኑን በማመን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት አስተባባሪ ምክር ቤት ውስጥ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ጋብዟል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ2 ምክር ቤቱ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር የተካተቱበት መሆኑም ይታወቃል፡፡ ራሱን ከሰለጠነ የፖለቲካ ትግል ያገለለው መድረክ ግን ከዳር ሆኖ የግድቡን ስራ ከጅምሩ ጀምሮ ሲያጣጥል እንደነበረ ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡

ከግንቦት 2ዐ የድል በዓል 22ኛ ዓመት ጋር ተያይዞ የግድቡን ግንባታ ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገው የውሃውን ፍሰት የማስቀየርና ለግድቡ ግንባታ አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እንቅስቃሴን ተከትሎ የግብፅ መንግስትና አንዳንድ ሃይሎች ጫና ለመፍጠር ያደረጉትን ሙከራ መንግስት በትእግስትና መላ የአገራችንን ህዝቦች ባሳመነ መንገድ ሲመክት ሰንብቷል፡፡

የግድቡ ግንባታ የማንንም አገር ጥቅምና ደህንነት እንደማይጐዳ፣ ይልቁንም የሁሉንም የተፋሰሱን አገሮች ጥቅምና ፍላጐት በሚያረጋግጥ አኳኋን ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በሚያስችል መንገድ መካሄዱን ለማንኛውም ንፁህ አእምሮ ላለው ሁሉ አሳማኝ በሆነ መንገድ መንቀሳቀሱን አስረድቷል፡፡ ለዚህም ከተለያዩ ወገኖች ከግብፅም ሳይቀር ሰፊ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን የግብፅ መንግስትም መፍትሄው ውይይት መሆኑን አምኖ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩን በመላክ ወደ ሰለጠነ የችግር አፈታት አቅጣጫ እንዲገባ አድርጓል፡፡

መድረክ ዘንድሮም እንደተለመደው የነገሮችን አወዳደቅ ካየ በኋላ ባወጣው መግለጫ ከዚህ በፊት አላምንበትም ያለውን ግድብ ግንባታ ለማሳካት ከኢህአዴግ ጋር መደራደር አለብኝ፤ ከግብፅ ወገን የሚመጣ ስጋትን ለመመከት ከኔ ጋር መደራደር የግድ ነው ብሎ ተነስቷል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግንባታ ለፖለቲካ ገበያ ድርድር የማይቀርብ የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ቁጭት የወለደው ፕሮጀክት መሆኑን ለመድረክ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ የአገራችን ህዝቦች ግድቡን የማንንም እጅ ሳያዩ ለመገንባት ቆርጠው እንደተነሱ ሁሉ ለግድቡ ግንባታ በኩርፍያ ጥግ ይዘው የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይሁንታ ማግኘትም አያስፈልጋቸውም፡፡ የህዳሴያቸው አሻራ የሆነውን ግድባቸውን ከማንኛውም ጥቃት ለመመከትም የመድረክ አይዞህ ባይነት አያሻቸውም፡፡

ከመድረክ ቀደም ብሎ የዚሁ ስብስብ አባል የሆነው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ግድቡ ከመሰራቱ በፊት ማለቅ የነበረባቸው ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ማለቅ ነበረባቸው በማለት በቅርቡ ለተፈጠረው ውጥረት የኢህአዴግን መንግስት ተጠያቂ ለማድረግ ሞክሯል፡፡

የአባይን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትክክለኛ አቅጣጫ አስቀምጦ ላለፉት 22 ዓመታት የተንቀሳቀሰው የኢህአዴግ መንግስት በተለይ ባለፉት 13 ዓመታት የአባይ ተፋሰስ አገሮችን ያካተተ ተነሳሽነት በመምራት ለዘመናት የዘለቀውን በቅኝ ግዛት ውሎች ላይ የተመሰረተ ኢፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል ለማስቀረት መስራቱን አንድነት/መድረክ ይዘነጋዋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ይህ የኢህአዴግ ጥረት ተሳክቶ በአሁኑ ወቅት ፍትሃዊ የስምምነት ማእቀፍ በአብዛኞቹ የተፋሰሱ አገራት ተፈርሟል፡፡ በሃሣቡ ላይ ከግብፅ በስተቀር ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል፡፡ የግብፅ መንግስታት ለዘመናት አይነኬ አድርገው ይዘውት በነበረው የአባይ ጉዳይ ላይ እንዲህ አይነት ድል ማስመዝገብ የተቻለውና በራሳችን ሃብትና ውሳኔ በአባይ ላይ ታላቅ ግድብ ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ የወሰድነው የኢህአዴግ መንግስት በታላቁ መሪ አማካኝነት በተከተለው ዴሞክራሲያዊ የሰለጠነ የትግል ስልት ነው፡፡

የኢህአዴግ መንግስት በአባይ ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ ላደረገው ቁርጠኛ ትግል በተፋሰሱ አገሮች መንግስታትና ህዝቦች ምስጋና ሲቸረውና በሌሎች አካላት አድናቆት ሲጐርፍለት አንድነትና መድረክ ውግዘት ማዥጐድጐዳቸው ሃገራዊ ጥቅምንና ደህንነትን በተመለከተ ያላቸውን ፀረ ህዝብ አሰላለፍ አሁንም በድጋሚ በግላጭ የሚያረጋግጥ አቋምና ተግባር ነው፡፡

አንድነት/መድረክ በመግለጫው ግብፅና ኢትዮጵያ ከፀብ አጫሪነት ተግባር ሊታቀቡ ይገባል በማለት የግብፅን መንግስት ኢፍትሃዊ የጉዳይ አያያዝ በቀጥታ ላለመንቀፍ ተንቀሳቅሷል፡፡ ወትሮውንም ችግሮችን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት ባህል ያለውን የኢህአዴግ መንግስት በፀብ አጫሪነት ተርታ መድቦታል፡፡ ይህን ካለ በኋላ ደግሞ የግብፅ መንግስት የሚሰነዝረውን ዛቻና ማስፈራሪያ አጥብቆ እንደሚቃወም ገል ል፡፡

በመጀመሪያ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት የሌለውንና ለፖለቲካ ጥቅም የዋለ ነው የሚለውን ፕሮጀክት፤ የህዝብ ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅት ንብረት ነው ብሎ የሚያስበውን ፕሮጀክት ከጥቃት ለመከላከል አንድነት/መድረክ ፍላጐቱም ወኔውም እንደሌለው ለሁላችንም ግልፅ ነው፡፡ አንድን አገራዊ አላማ ከጥቃት መከላከል የሚቻለው ከአላማው ላይ የተሟላ እምነት ሲኖር ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ግንባታ እና በየወቅቱ እየታየ ያለው እድገት የሚያንገበግበው መድረክ ግድቡን ከጥቃት ለመከላከል መቼውንም እንደማይነሳ ኢህአዴግም የኢትዮጵያ ህዝቦችም አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያነሱትን ሃሣብ የአገራችን ሰው ‘ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ’ ብሎ እንደሚያልፈው የታመነ ነው፡፡

የአንድነት/መድረክ ሃላፊዎች በአደባባይ ግንቦት 2ዐ ለኛ ምናችንም አይደለም በማለት ሲናገሩ ትንሽም እፍረት የማይሰማቸው ናቸው፡፡ የአገራችን ህዝቦች በከፍተኛ መስዋእትነት አስከፊውን አገዛዝ ጥለው ዛሬ እነሱም በነፃነት ለሚኖሩበት ዘመን አብቅተዋቸዋልና በዚህ ነፃነት እንዳሻቸው ቢፈነጩ ብዙም አይደንቅም፡፡ የግንቦት 2ዐ ድል የህዳሴያችን አንድ ትልቅ ምዕራፍ ነው፡፡ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት የውሃውን ፍሰት የማስቀየሩ ስራ በግንቦት 2ዐ ቀን መካሄዱ የህዝቡን የድል አድራጊነት መንፈስ ከማጠናከር ባለፈ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡

አንድነት/መድረክ ግን ግንቦት 2ዐን ከኢህአዴግ ጋር ብቻ አስተሳስሮ ስለሚያየው በእለቱ በተከናወነው ታላቅ ተግባር ከመደሰት ይልቅ መከፋቱ የቆመበትን ቦታ የሚያሳይ ነው፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የህዝብ ፕሮጀክት ነው፡፡ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቅርስ፣ መንፈስ፣ ክህሎትና ቁጭት የፈሰሰበት በማንኛውም መልኩ የአንዱ ወይም የሌላው ፓርቲ ሃብት ሊሆን የማይችል ታላቅ ሃገራዊ ክንዋኔ ነው፡፡ ይህንን የህዳሴያችን ሃውልት የሆነ ፕሮጀክት መላ የአገራችን ህዝቦች ከዳር እንደሚያደርሱት ደጋግመው ቃላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ መድረክና ሌሎች የአገራችንን ውድቀት የሚሹ ሃይሎች ከዳር ሆነው በሚሰነዝሩት ሟርት የሚዘናጋ ሃይል እንደማይኖር መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ኢህአዴግ ዛሬም አንደትናንትናው መላ የአገራችንን ህዝቦች በማስተባበር እንዲሁም የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ቢኖራቸውም የአገራችንን ህዳሴ በቅንነት የሚመለከቱ የፖለቲካ ሃይሎችን በማሳተፍ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ የፀረ ድህነት ትግሉን ከግብ እንደሚያደረስ ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህ ሂደት የተመኙትን የውድቀት አጋጣሚ አገኘን ባሉ ቁጥር የፖለቲካ ድርድር ገበያ ለመውጣት የሚሹ እንደ መድረክ ያሉ ሃይሎች የበሬ ምናምን ይወድቅልኛል ብላ ስተከተል እንደመሸባት ቀበሮ እንደሚመሽባቸው ኢህአዴግ ሊያስታውሳቸው ይወዳል፡፡

የኢህአዴግ ም/ቤት ፅ/ቤት
ሰኔ 2005 ዓ.ም
***********

Daniel Berhane

more recommended stories