ኢሕአፓ፡- መንግሥት በህዳሴ ግድብ ሰበብ ‘ግብጽን እየተነኮሰ’ ነው

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ሰኔ 4 ቀን 2005 ዓ.ም.

የወያኔ አገዛዝ ሕዝብን ለጦርነት፤ ሀገርን ለጥቃት እያዘጋጀ ነው

የወያኔ አገዛዝ የሕዝብን ትኩረት መደረግ ካለበት ወሳኝ ትግል ለመነጠል ሲያደርገው የነበረውን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ በተመክሮ የተገነዘበው ነው።

በቅርቡ ደግሞ ህዳሴ ግድብ በሚለው ማታለያ የለመደባቸውን ተላላዎች በዙሪያው እያሰለፈና ሕዝብንም እየዘረፈ ያለው አልበቃ ብሎት ግብጽን እየተነኮስና እየቀሰቀስ በመቀጠሉ የአባይ ውሀ አንድም ጠብታ አይቀነሰብኝም ከምትለው ከስግብግቧ ግብጽ ጋር ጦርነትን እየጋበዘ ነው። ኢትዮጵያና ሌሎች ሀገሮች በነጭና ጥቁር አባይ የመጠቀም መብታቸው የተጠበቀ መሆኑ አያክራክርም። በአለም አቀፍ ህግ መሰረትም ሌሎች ከወንዞቹ ተጠቃሚ ሀገሮች ውሃ እንዳያገኙ ማድረግ የሚፈቀድ አይደለም። አባይን በተመለከተ ተንኮለኛው የእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ሱዳንና ግብጽን ብቻ ይዞ የወሰነው የውሀ ድርሻ/ክፍፍል ትክክለኛ አለመሆኑም አከራካሪ ኣይደለም — ግብጽና ሱዳን አሌ ቢሉም። ግብጽ በረሀዋን ልታለማና ሚሊዮኖችን ልታሰፍር በመፈለግ የአባይን ውሀ በተጨማሪ ደረጃ መፈለጓና የተፋሰስ ሀገሮችን ጥቅም ከቶም አላዳምጥ ማለቷም የሚደገፍ አይደለም።

ወያኔ በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ግድብ በሌለ ገንዘብ እሰራለሁ ብሎ የተነሳው ለኢትዮጵያ አስቦ (ወያኔና የኢትዮጵያ ጥቅም ሆድና ጀርባ ናቸውና) ሳይሆን የሕዝባዊ አመጽ ነፋስ ወደሀገራችንም እንዳይነፍስ በሚል የህዝብን እይታ ለማደናገር የሸረበው ተንኮል መሆኑ ክርክርንአይጠይቅም።

በኢትዮጵያ እስከዛሬ የተሰሩት ግድቦችና ገና ያላለቀው ግልገል ጊቤ ቁጥር ሶስትንምጨምሮ ለሀገሪቷ የመብራት ሀይል ፍጆታ ከበቂ በላይ ሆነው ሳለ ዛሬም በብዙ ከተሞች መብራት በፈረቃ እየተሰጠ እንዳለ ሕዝባችን የሚያውቀው ነው። ግዙፍ ግድብ ለመገንባት መነሳትና ይህንንም ግብጽ እንደምትቃወም እየታወቀ በስልት ጉዳዩን በመያዝ ፈንታ ድንፋታና ፕሮፓጋንዳንማስቀደሙ፤ ቦንድ ብሎ ሕዝብን ማስጨነቁና ማስገደዱ፤ ሀገር ወዳድ መስሎ ለመቅረብ መፍጨርጨሩ ሕዝብን ሊያደናግር የሚችል አይደለም። የለመዳባቸው የወያኔ የገደል ማሚቴዎችና አደናጋሪዎች –በባድሜ ጦርነት እንዳየነው ሁሉ– ሀገር ልትጠቃ ነው ኡኡ በሚል ወያኔንበመታገል ፈንታ ሕዝብ እንዲደግፍና ከጎኑ እንዲሰለፍ ለማድረግ ከወዲሁ የተንኮል ቅስቀሳ፤የማደራጀት ስራና ጫጫታ ጀምረዋል። ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ይህንን በሚገባ ተገንዝቦ ውጉዝከመ አርዮስ መባል አለባቸው።

የግብጽ ሕዝብ ጠላታችን አይደለም። አንዋር ሳዳት የአባይ ወንዝ ከተገደበብን ጦርነት የግድ ይሆናል ያለውንም አንረሳውም–ዛሬም የግብጽ መሪ ተመሳሳይ አቅዋም በመውሰድ እሱም በበኩሉ ልክ እንደ ወያኔ ውስጣዊ ውጥረቱን ዘወር ለማድረግ ይፈልጋል። ተጨባጭ ሁኔታውንና አቅምን ሳያውቁ ሳይመዝኑ ህዳሴ ግድብ ይሰራል ብለው ጫጫታ ላይ ያሉት ክፍሎች ቅዠት ላይ ናቸው ።

ከግብጽ ጋር ጦርነት ቢነሳ ይህ የኢትዮጵያ ሳይሆን የወያኔ ነው – ልክ እንደ ባድሜ። 130 ሺ ዜጋ አልቆ ምን ተገኘ? ወያኔና አጫፋሪዎቹ–አንዳንዶቹ ደግሞ ተቃዋሚ ነን ሊሉም ይጥራሉ–ኢትዮጵያ በአባይ ልትጠቀም ስትነሳ በግብጽ ተጠቃች ወይም ልትጠቃ ነው በሚል ሀገር ወዳድሁሉ ተነሳ ለማለትና ለማደናገር አቅደዋል። የሚሞኝላቸው አይኖርም ማለትም አይቻልም። ለነገሩ ግብጽ ኢትዮጵያን ሊወር አይችልም– አይሮጵላኖች አስነስቶ ግድብ ተብየውን ሊደበድብ ይችላል። የሚያቆመውም አይኖርም ። ዕድሜ ለወያኔ ስንት ሚሊዮን ብር የፈሰሰበትን አየር ሃይል በትኖ በጀሌዎቹ ሞልቶት ይቀልዳል። መካላከያ ተብየው ሆኖ ሕዝብንም ከፋፍሎና አሽመድምዶ ይገኛል።

ኢትዮጵያ መብቷን ለማስከበር አቅም የላትም። ወያኔ የአሜሪካ ሎሌና ተገዢ ነው–አሜሪካ ደግሞ ግጭት ከተነሳ ግብጽን መቃወም ኣንችልም ብላ ለወያኔ አስጠንቅቃለች። የወያኔ አገዛዝ ከድጡ ወደ ማጡ ሊከተን ነው እየጣረ ያለው። ይህን መቃወም ደግሞ ለሀገራችን ደህንነትወሳኝ ነውና ወያኔና ቅጥረኞቹን ወግዱ እረፉ እንበላቸው። ዛሬ ባለንበት ሁኔታ ከግብጽ ጋር ግጭቱ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት የለም። ወያኔ ስልጣን ሲይዝ ከግብጽ ጋር ተፈራርሞ የሀገርን ጥቅም መሽጡንም መርሳት አንችልም። ወያኔ ጫካ ሳለም በግብጽ መረዳቱንና የተከዜ ድልድይን ሊያፈርስ መሞከሩንም የምንረሳው አይደለም። ወያኔ ከስረ መሰረቱ ሀገርን ለባዕድ ሻጭ ጸረ ኢትዮጵያ ሀይል ነበረ–አሁንም ነው። ለዚህም ነው ከባዕድ ጋር የፍጥጫን ጎዳና መርጦ ሀገራችንን ለጥቃት ሊያጋልጥ እየተፍጨረጨረ ያለው። በዚህ ጸረ ኢትዮጵያዊ ጉዞው ሀገር ወዳድ ዜጎች ከቶምመቸም ልናጅበው አይገባም ። በባድሜ የወደቁ ዜጎቻችን አጥንት ያወግዘናል። በአባይ ስም አገርን ለማስጠቃት ወገንን ለማዘናጋት የታቀደውን ወያኔያዊ ሴራ በአንድነት ልናወግዝይገባል።

Source: Ethiopian People´s Revolutionary Party (EPRP)

*********

ማስታወሻ፡- ፓርቲው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 130,000 ኢትዮጲያውያን ወታደሮች ተሰዉተዋል ለማለት መነሻ የሆነውን የመረጃ ምንጭ ማወቅ ባልችልም የInternational Crisis Group (ICG) ግምት ግን ከሁለቱም ወገን በድምሩ 70,000 ሰው እንደሞተ ነው፡፡ የቀድሞው የጦር ሀይሎች ኤታማጆር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሣኤ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ በሚዲያ ተጠይቀው ሲመልሱ 17,000 ገደማ ኢትዮጲያውያን እንደተሰዉ ገልፀዋል፡፡

ስለወያኔና ግብጽ ‹ግንኙነት›ም ፓርቲው ያብራራው ነገር የለም፡፡

(ዳንኤል ብርሀነ)

Daniel Berhane

more recommended stories