Brief | የፕ/ር መስፍን የ‹አባይ ጦርነት› ግልብ ትንተናና ምክር

(Daniel Berhane)

ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም ባለፈው እሮብ ከአባይ ጉዳይ በተያያዘ የጦርነት ቅስቀሳን ለመገሰጽና የግብጽን የጦር ሀያልነት ‹ለማሳወቅ› አንድ ጽሑፍ አስነብበውናል፡፡

ጽሑፉ በጥድፊያ እና/ወይም እንደተለመደው የኢሕአዴግን ባለስልጣኖች ለማብሸቅ ተብሎ የቀረበ ስለመሰለኝ አላተኮርኩበትም ነበር፡፡mesfin woldemariam

ነገር ግን እሳቸው የጽሑፋቸውን ግልብነት (shallowness) አስተውለው – ጠለቅ ያለ ማብራሪያ በመስጠት ለማጠናከር ወይም ለማስተባበል ይሞክራሉ ብዬ ስጠብቅ፣ ትችት የሰነዘሩባቸውን ሰዎች በመሀይምነት መፈረጅ ነው የመረጡት፡፡

ሰለሆነም እንደው ምናልባት እሳቸውም ሆነ <መስፍን ህፀጽ አይገኝባቸውም> ብለው የሚያምኑ የሚመስሉት ደጋፊዎቻቸው ልብ አላሉት እንደሆን ለማስገንዘብ፤ ስለፕ/ር መስፍን ጽሑፍ አንድ ሁለት ልበል፡፡

የ ጽሁፉ ዋነኛ ጭብጥ በሚከተለው ጥቅስ ይወከላል፡፡

‹‹ጦርነት እንኳን ገና በልቶ ላልጠገበ ሕዝብና ለጥጋበኞቹም አይመጭም፤ የተራበ ሕዝብ በጠገቡ መሪዎች ሲነዳ ግን ጦርነት ለአጉል ጀብደኛነት ዝና የሚጠቅም መስሎ ይታያቸዋል፤……ለፍቅር መተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለጠብም መተዋወቅ ያስፈልጋል፤ የተሟላ መረጃ ቢኖረን የጥንት ታሪክ እየጠቀስን ሰዎችን ለጦርነት እንቀሰቅስም ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ››

የትኛው ‹የጠገበ› ባለስልጣን ነው ለጦርነት የቀሰቀስው?

የመንግስት ባለስልጣኖች አንድ ሁለት ጊዜ – ከ2 ዓመታት በፊት – ‹‹ግብጽ ብትወረንስ›› የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ታሪክ ጠቅሰው እንደማይፈሩ መግለፃቸውን አስታውሳለሁ፡፡ (ግን ሌላ ምን መልስ ሊሰጡስ ይቻላቸዋል?) ከዚያ ባለፈ ግን ግብጽን አስመልክቶ አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ ዘገባ እና ቅስቀሳ በመንግስት ሚዲያ ሰምቼ አላውቅም፡፡

እንዲያውም ከካይሮ ግድም አሉታዊ ወሬ በመጣ ቁጥር የመንግስት ባለስልጣኖች ጦርነትና ግጭት የመከሰት ዕድሉን ስለሚያጣጥሉ፣ አንዳንድ ታዛቢዎች ‹‹እነዚህ ሰዎች አስጠንቁለዋል እንዴ›› ያሉበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ – ከአንድ ወር በፊት የጠ/ሚኒስተሩን ቃል-አቀባይ ጌታቸው ረዳን ሳናግረው ‹‹ግድቡን እንደማናቆም ሲያውቁ ራሳቸውን ከእውነታው ያስታርቃሉ›› ነበር ያለኝ፡፡

እርግጥ መንግስት በይፋ የሚያሳየው መተማመን ስልታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ግብጾችንም ‹‹ማነው ከግድቡ ጀርባ ያለው?›› የሚያሰኛቸውም እሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሌላው የጽሑፉ አንኳር ሀሳብ እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹አንዳንድ አስፈላጊ መረጃዎችን ላቅርብ፤ — የግብጽ የጦር ኃይል በዓለም አሥረኛ ነው፣ በአፍሪካና በመሀከለኛው ምሥራቅ የሚወዳደረው የለም፤ አንድ ሚልዮን ተኩል ያህል የጦር ኃይል አለው፤ በዓየር ኃይልም ከዓለም አሥራ አራተኛ ነው፤ በታንክ ብዛት አራተኛ ነው፤ በባሕር ኃይል ሰባተኛ ነው፤ በጦር በጀት አርባ ሦስተኛ ነው፤››

የመረጃ ምንጩን ባይጠቅሱም ከመጠነኛ አሰሳ በኋላ እንደተገነዘብኩት መረጃውን ያገኙት ከGlobalFirePower.com ነው፡፡ የዌብሳይቱን የደረጃ አሰጣጥ ስልት ከተረዳሁ በኋላ ግን መስፍን ጽሑፋቸውን በችኮላ እንደጻፉት ደመደምኩ፡፡

ከGlobalFirePower.com ደረጃዎች ጥቂቶቹን በምሳሌነት ላቅርብ፡-

* የእያንዳንዱን ሀገር ጠቅላላ የጦር አይሮፕላን (ጀት፣ ሔሊኮፕተር፣ ወዘተ) ብዛት በመቁጠር፡- በአየር ሀይል ለኢራን 5ኛ፣ ለሳውዲ አረቢያ 11ኛ፣ ለግብጽ 14ኛ፤ ለእስራኤል 20ኛ ደረጃ ይሰጣል፡፡

* በባሕር ኃይል (ሁሉንም የባህር ላይ የጦር ተሸከርካሪዎች በመቁጠር) በሰጠው ደረጃ ግብጽ ሰባተኛ ደረጃን በመያዝ ከቱርክ ከፈረንሳይ ከጣልያን ከሕንድና ከእንግሊዝ ትበልጣለች፡፡

* በታንክ ብዛትም የግብጽ ደረጃ ከህንድ ከሩሲያና ከፈረንሳይ በላይ ነው፡፡

* የግብጽ ወታደር ብዛትም (ግማሽ ሚሊዮን ቋሚና 1 ሚሊዮን ተጠባባቂ ወታደር በመያዝ) ከፈረንሳይ ከእንግሊዝና ከእስራኤል ይበልጣል፡፡

ይህን የደረጃ  አሰጣጥ መሠረት አድርጎ የወታደራዊ ሀያልነትን መመዘን አሳሳች መሆኑ ለማንም ግልጽ ስለሆነ ብዙ አልልም፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን የኢትዮጲያ ጦር ሀይል የወታደር ቁጥር እና የበጀት መጠን ውስን እንዲሆን የተደረገበት ሳይንሳዊ መነሻ ሲኖረው፤ ግብጽ ደግሞ የጦር ሀይል ብዛትና ወጪ ማብዛት የፈለገችበት የፖለቲካ ምክንያት ለግማሽ ክፍለ-ዘመን ከቆየው ከፊል-ወታደራዊ ስርአቷ ባህርይ ጋር ይያያዛል፡፡

ይልቁንስ ፕሮፌሰሩ ሊያነሱ ይገባ የነበረው ጥያቄዎች፡-

* በዚህ ዘመን የጦርነት መነሳት ሆነ ውጤት በጥይት ብዛት ነው እንዴ የሚመሠረተው? (የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የinternational public opinion ወዘተ ወሳኝ ሚናስ)

* እኛ እና ግብጽ የጋራ ድንበር ስለሌለን፤ ግብጽ ሺህ ኪሎሜትሮች ተጉዞ ለሚደረግ ጦርነት በቂ ክህሎት፣ ልምድ፣ ድርጅት እና ሎጂስቲክ አላት ወይ?

* ሱዳን ወይም ኤርትራ በሺዎች የሚቆጠር የግብጽን ሠራዊት ለማስፈርና ለማሳለፍ ይፈቅዳሉ ወይ?

አንዳንድ ሰዎች፣- ውስን የዓየር ወይም የኮማንዶ ጥቃት(surgical attack) ሀሳብ በማንሳት የመስፍንን ጽሑፍ ለማሻሻል ይሞክራሉ፡፡ እዚህ ላይም የቴክኖሎጂ ጥያቄ አለ፡፡ ከካይሮ ተነስቶ ኢትዮጲያ ደርሶ የሚመለስ አይሮፕላን ግብጽ አላት? (ስለሌላትም) የሱዳንን ዓየር ክልል ጥሶ መብረር ብቻ ሳይሆን ማረፊያም ማግኘት ትሻለች፡፡ እናስ ሱዳን ትፈቅዳለች?

አንድ ነገር ልብ በሉ፡- ግድቡ ሲያልቅ ለማፍረስ ጥቂት ከባድ ቦንቦች ወይም ፈንጂዎች ሊበቁ ይችላሉ፡፡ ዛሬ ላይ ግን ማጥቃት የሚያስፈልገው እንዳለ የፕሮጀክት ሳይቱን ይሆናል፡፡ (ገና በጅምር ላይ ያለን ቤት ማጥቃት እና ተሠርቶ ያለቀን ቤት ማጥቃት አድርጋችሁ እዩት)

እነዚህንና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎች ሳይመልሱ ታንክ መቁጠር ግልብ ትንተና ይሆናል፡፡

ለማንኛውም ከሀይማኖት ወይም ፈሪሀ-እግዚያብሔር በመነሳት በድፍኑ ‹ጥጋብ ውርደት ያስከትላል› ብሎ መናገር ቢቻልም፤ የፕ/ር መስፍን ጽሑፍ ግን የመንግስት ሀላፊዎች ‹ጠግበው› ለጦርነት መቀስቀሳቸውን ሆነ ‹ጥጋባቸው› ‹ውርደት› እንደሚያስከትል በበቂ አላስረዳም፡፡

እርግጥ የግብጹ Al-Jamaa al Islamiya መሪ ኢትዮጲያ በአባይ ላይ የምትሠራው ሥራ የጦርነት አዋጅ ነው በማለት አፀፋውን ለመመለስ ዛቻ ብጤ አሰምቷል፡፡

ፕ/ር መስፍን የ‹ጠገቡ መሪዎች ለአጉል ጀብደኛነት ዝና› እየነዱን እንዳሉ አድርገው የቆጠሩት የሕዳሴ ግድብ ሥራን ይሆን እንዴ?

**************

Related:
Ethiopia-Egypt | A War on Nile Improbable, for now
Military expenditure at a historic low | Ethiopia

Daniel Berhane

more recommended stories