የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የግብጽን አምባሳደር ጠርቶ ማብራሪያ ጠየቀ

ኢትዮጵያ በመከባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንደምታራምድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት እና ከሌሎችም አገሮች ጋር በመከባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ በጽናት ስታራምድ መቆየቷ ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በመሆኑም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በግብጽ ዘንድ ሰፍኖ የቆየውን ጥርጣሬ ለማስወገድ ግድቡ ግብጽንም ሆነ ማንኛውንም የታችኛውን ተፋሰስ አገር እንዳይጎዳ የሚያረጋግጥ የግብጽ፣ የሱዳን፣ የኢትዮጵያ እና አለም አቀፍ ባለሙያዎች የሚገኙበት አጣሪ ቡድን እንዲቋቋምና ሪፖርት እንዲያቀርብ ሃሳብ አቅርባ ስራው ሲሰራ ቆይቷል፡፡

የአጣሪ ቡድኑ ስራውን ሰርቶ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ የሚፈጥረው ችግር እንደሌለ ባረጋገጠበት ማግስት አንዳንድ የግብጽ ባለስልጣናትና የፖለቲካ ድርጅቶች ተቀባይነት የሌለውና በሁለቱ አገሮች መካከል ተጀምሮ የነበረውን መልካም ግንኙነት የሚያሻክር ፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ማድረጋቸው የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ኣሳዝኗል፡፡

ባለፉት ጥቂት ቀናት የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩ ወደተባባሰ ሁኔታ እንዳይገባ በትእግስት ለማለፍ ቢሞክርም ይህ ገንቢ ያልሆነ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አሁንም ቀጥሏል፡፡ በመሆኑም በትላንትናው ግንቦት 27 / 2005 ዓ.ም የግብጽ አምባሳደር ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠርተው ስለዚህ ሁኔታ በአስቸኳይ የመንግስታቸውን አቋም ጠይቀው እንዲሰጡ ተነግሯቸው ምላሽ በመጠበቅ ላይ ነው፡፡

አገራችን አሁንም ዋነኛ ትኩረቷ ድህነትን ማሸነፍ እና ለዚሁ አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር ከሩቅና ቅርብ አገሮች የወዳጅነት ግንኙነት መፍጠር በመሆኑ ከግብጽ ጋር የተጀመረውን የትብብር ግንኙነት በዚሁ መርህ መሰረት አጠናክራ መቀጠል ትሻለች፡፡ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ለአገራችን እድገት መፋጠን ከሚያደርገው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ግብጽንም ጨምሮ ለሌሎች ጎረቤት አገሮች ያለውን ጠቀሜታ አሁንም በድጋሚ ማስታወስ ትፈልጋለች፡፡

ምንጭ፡- ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

Daniel Berhane

more recommended stories