በፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፉት 10 ወራት የተመረመሩ የሙስና ጉዳዮች

(ፍሬው አበበ)

[የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የ2005 በጀት ዓመት የአሥር ወራት ሪፖርቱን ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርቧል። ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን ካቀረቡት ሪፖርት ውስጥ የሙስና ወንጀልን መመርመርና መክሰስን በተመለከተ በንባብ ያቀረቡት እንደሚከተለው ተስተናግዷል።]

ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀሎች ወይም ብልሹ አሰራሮች ሲፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን በማጋለጥና በመመርመር ክስ መስርቶ ለፍርድ በማቅረብ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ማድረግና የተመዘበረ ሀብት እንዲመለስ ይሰራል። በዚህ በኩል ባለፉት አሥር ወራት ከተከናወኑት ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

በፀረ-ሙስና ትግሉ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ በመንግሥት አሠራር ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ስለመከሰታቸው ጥርጣሬ /መረጃ ሲኖር መረጃውን ለኮሚሽኑ መጠቆም ነው። ከዚህ አኳያ ባለፉት አሥር ወራት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን ጨምሮ 3001 ጥቆማዎችና አቤቱታዎችን የመቀበል፣ የመመዝገብና ውሳኔ የመስጠት ሥራ ተከናውኗል። ከነዚህ ጥቆማዎች ውስጥ በኮሚሽኑ የሥልጣን ክልል ሥር የሆኑት 1335 (44 በመቶ) ሲሆኑ 1666ዎቹ (56 በመቶ) ከኮሚሽኑ የሥልጣን ክልል ውጭ ናቸው።

በኮሚሽኑ የሥልጣን ክልል ሥር የሚወድቁ ሆነው በባህርያቸው ግን ቀላል በመሆናቸው ምክንያት ስልጣን ባላቸው ሌሎች መርማሪ አካላት እንዲመረመሩ ከተላኩ 231 ጥቆማዎች ውስጥ 179 ምርመራቸው ተጠናቆ ተመልሰዋል።Ali Suleyman, Commissioner of Federal Ethics and Anti-Corruption Commission

ከ2004 በጀት ዓመት የተሸጋገሩትን ጨምሮ ከተመሩ 517 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 443 የምርመራ መዝገቦች ላይ ምርመራ ተካሂዶ ተጠናቋል።

ከ2004 በጀት ዓመት የተሸጋገሩትን ጨምሮ ለውሳኔ ከተመሩ 911 መዝገቦች ውስጥ 694ቱ ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል።

በአሥር ወሩ ውስጥ በፍርድ ቤት ቀጠሮ/አጀንዳ በተያዘላቸው 630 መዝገቦች ላይ ክርክር ለማድረግ ታቅዶ በ606ቱ መዝገቦች ላይ አስፈላጊው ክርክር ተደርጓል።

የፍርድ ቤት ውሳኔ ከተሰጣቸው 164 መዝገቦች መካከል 144 መዝገቦች ለኮሚሽኑ የተወሰኑ ሲሆን ውሳኔ ካገኙ 409 ተከሳሾች መካከል 293ቱ ጥፋተኛ ሲባሉ በንብረት ነክ ክርክሮችም ለ23 ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ የንብረት ይወረስ ውሳኔ ተሰጥቷል። ስለሆነም በዘጠኝ ወሩ ውስጥ የመርታት አቅማችን በመዝገብ 87.8 በመቶ፣ በንብረት ነክ ጉዳዮች መቶ በመቶ ሊደርስ ችሏል።

ሙስናን በመጠቆማቸው እና /ወይም ምስክር በመሆናቸው የሕግ ከለላ እንዲሰጣቸው ከቀረቡ 42 አቤቱታዎች ውስጥ 20ዎቹ ከለላ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፤ 13ቱ ያቀረቡት አቤቱታ ከለላ የሚያሰጣቸው ሆኖ አልተገኘም፤ ቀሪዎቹ 9ኙ በመጣራት ላይ ናቸው።

ምርመራቸው ተጠናቆ ክስ ከተመሰረተባቸውና በምርመራ ላይ ካሉ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፤-

በመሬት አስተዳደር

ሀሰተኛ የማኅበራት ማደራጃ ሠነድ በማዘጋጀት፣ የአቅም ማሳያ ገንዘብ በባንክ ሳይያዝ እንደተያዘ የሚያሳይ ሀሰተኛ ማስረጃ በማቅረብ የመንግሥትን መሬት አለአግባብ መውሰድ ጋር በተያያዘ፡-

* ግምቱ ብር 21.1 ሚሊዮን የሆነ 3‚226 ካሬ ሜትር መሬት አለአግባብ ከመያዝ ጋር በተያያዘ 8 መዝገቦች ተጣርተው ክስ ተመስርቶባቸዋል፣

* ግምቱ ብር 25.1 ሚሊዮን የሆነ 3‚837 ካሬ ሜትር መሬት አለአግባብ ከመያዝ ጋር በተያያዘ 3 የምርመራ መዝገቦች ተጣርተው ለዐቃቤ ሕግ ውሣኔ ቀርበዋል፣

* ግምቱ ብር 842 ሚሊዮን የሆነ 128‚709 ካሬ ሜትር መሬት አለአግባብ ከመያዝ ጋር በተያያዘ በአንድ የምርመራ መዝገብ ምርመራ በመጣራት ላይ ይገኛል፣

በታክስ አስተዳደር

* ከጉምሩክ ሠራተኛ ጋር በመሻረክ ቀረጥ በማጭበርበር፣ ለዋስትና የተያዘ ቦንድ ተከታትሎ ባለማስፈፀምና ሠነዱን በማጥፋት፣ ታክስ በመሰወር፣ በኮንትሮባንድ የተያዘ ንብረት በመውሰድ፣ በተለያዩ ሸቀጦች መከፈል ያለበት ታክስ ሳይከፈልበት በማሳለፍ፣ የስኳር ሽያጭ ታክስ በማስቀረት መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ብር 47.9 ሚሊዮን በማሳጣት 6 የምርመራ መዝገቦች ተጣርተው ለውሣኔ ተዘጋጅተዋል፣

* የቻይና መንገድ ሥራ ድርጅት ለአፋር ክልላዊ መንግሥት መክፈል የነበረበት 10.7 ሚሊዮን ብር የሥራ ግብር አጭበርብረው ሊወስዱ በነበሩ የክልሉ የፋይናንስ ጽ/ቤት ኃላፊ ሠራተኛ ላይ ከአፋር የሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ምርመራው ተጣርቶ ክስ ተመስርቷል፣

በመንግሥት ትላልቅ ግዥና ሽያጭ

* የመንግሥትን የግዥ ሕግና መመሪያ በመተላለፍ፣ የሐራጅ ሽያጭ ሕግን በመጣስ፣ ጥራት በማጓደል፣ በጨረታ መገዛት የሚገባን ግዥ ያለጨረታ በመፈፀምና ከአገልግሎት ሽያጭ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ ብር 164.6 ሚሊዮን እና 2.9 ሚሊዮን ዩ ኤስ ዶላር አለአግባብ ወጭ በመደረጉ በ11 የምርመራ መዝገቦች በመጣራት ላይ ይገኛሉ።

* ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የምንጣሮና የሸንኮራ አገዳ ዘር ተክል ወደ ማሳ ለማመላለስ የገልባጭ መኪኖች ኪራይ ጋር በተያያዘ 75.3 ሚሊዮን ብር አለአግባብ በተከናወነ ግዥ ምርመራው ተጣርቶ አጥፊዎች ተለይተው ክስ ተመስርቷል፣

በፍትህ አስተዳደር

* ጉቦ በመቀበል በተጠረጠሩ ሁለት ዳኞችና ሁለት ጠበቆች እንዲሁም ተባባሪ ግለሰቦች ላይ ምርመራ ተጣርቶ ክስ ተመስርቷል፣

ሌሎች ልዩ ልዩ ወንጀሎች

* የመንግሥት ንብረት በመስረቅ፣ የተሰበሰበ ገቢ ለግል ጥቅም በማዋል፣ ቼክ በማጭበርበር በመንግሥት ላይ ብር 10 ሚሊዮን እና 200 ሺህ ዩ ኤስ ዶላር ጉዳት በማድረስ ወንጀል 8 መዝገቦች ተጣርተው ክስ ተመስርቷል።

* ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ በረራ ጋር በተያያዘ የብር 6.2 ሚሊዮን የሚገመት የመንገደኛ ንብረት ለግል ጥቅም በመውሰድ ወንጀል በአንድ መዝገብ ምርመራው ተጣርቶ ተጠናቋል።

* ብር 7.4 ሚሊዮን የሚሆን ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በመያዝና ይህንኑ ሀብት ሕጋዊ ለማስመሰል ወደ ሌላ ሰው የማዛወር ወንጀል ጋር በተያያዘ አንድ የምርመራ መዝገብ ተጣርቶ ክስ ተመስርቷል።

* ጉቦ በመቀበል ደረጃቸውን ያልተጠበቁ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በመወሰን፣ በሕገወጥ መንገድ ለውጭ አገር ሰዎች መግቢያና መውጫ ፈቃድ በመስጠት እና የካሣ ግምት አለአግባብ በማጋነን ወንጀል በመንግሥት ላይ የብር 3.8 ሚሊዮን ጉዳት ባደረሱ ሕገወጦች ላይ 5 የምርመራ መዝገቦች ተጣርተው ክስ ተመስርቷል።

የንብረት እግድና ማስመለስ ሥራዎችን በተመለከተ

* በሙሰኞች የተመዘበረን ሀብት ለማስመለስ ይቻል ዘንድ ባለፉት አሥር ወራት 128‚709.3 ካሬ ሜትር መሬት፣ 28 መኪኖችና፣ 64 መኖሪያ ቤቶች፣ 11 ድርጅት፣ ጥሬ ገንዘብ ብር 2.8 ሚሊዮን እንዲሁም የአሜሪካን ዶላር 15.1 ሚሊዮን በፍርድ ቤት እንዲታገዱ ተደርገዋል።

* በሙሰኞች ተመዝብረው ከነበሩት መካከል 4 ህንፃዎች፣ 1‚945 ካሬ ሜትር መሬት፣ ብር 21.1 ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ለመንግስት / ለሚመለከታቸው መ/ቤቶች ተመላሽ ተደርገዋል።

**************

Source: Sendek – May 15, 2013.

Daniel Berhane

more recommended stories