የመስኖ ግድቦች ግንባታ ክፉኛ ተጓትቷል

* በ2007 ዓ.ም የትልልቅ መስኖ ሽፋን ወደ683ሺ340 ሄክታር ለማድረስ ግብ ተጥሏል።
* እስከአሁን በተከናወኑ ሥራዎች 220ሺ ሄክታር ለማልማት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል።

(የማነ ገብረስላሴ)

የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተጀመረበት 2003 ዓ.ም የአገሪቱ የትልልቅ መስኖ ሽፋን ሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ ነበር። በእቅዱ ዘመን መጨረሻ ማለትም በ2007 ዓ.ም ሽፋኑን ወደ 15ነጥብ4 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው። ይህ ማለት በወቅቱ ይለማ የነበረውን 127ሺ ሄክታር መሬት ወደ683ሺ340 ሄክታር ለማድረስ ግብ ተጥሏል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደሚያስረዱት፤ በመስኖ ልማት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት እንዲሁም ባለሀብቶች የየራሳቸው ድርሻ አላቸው።Kessem dam Intake Tower.

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመሩ 11የመስኖ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ብዙነህ፤ የሌሎች ሁለት ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው የሚገልጹት። የከሰም፣ የተንዳሆና የቆጋ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ የራያ፣ የዝዋይና የቆቦ ፕሮጀክቶች ደግሞ በጅምር ላይ የሚገኙ ናቸው። የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ 230ሺ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንደሚኖራቸውም ነው የሚታመነው።

እንደ አቶ ብዙነህ ገለጻ የፕሮጀክቶቹን ግንባታ ለማከናወን አሁን ባለው የገበያ ዋጋ መሰረትሲሰላ 18 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። በተያዘው የበጀት ዓመት ብቻ ለፕሮጀክቶቹ ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ተይዞ ነው ወደ ሥራ የተገባው። እስከአሁን በአገር አቀፍ ደረጃ በተከናወኑ ሥራዎች 220ሺ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል።

በተያዘው የበጀት ዓመት በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶች ሥራ በመፋጠን ላይ መሆኑን ዳይሬከተሩ ገልጸው፤ «በዓመቱ ሊሰሩ ከታቀዱት ፕሮጀክቶች የከሰም 86 በመቶ፣ የተንዳሆ 97 በመቶ ተከናውኗል፤ የቆጋ፣ የራያና ቆቦ ግንባታዎችም በመፋጠን ላይ ናቸው» ብለዋል።

በተቃራኒው የርብ ግድብ የ 24 በመቶ፣ ጊዳቦ 47 በመቶ አፈጻጸም ያስመዘገቡና የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም። ለፕሮጀክቶቹ መጓተት በዋናነት የተቋራጮች የማስፈጸም አቅም ውስንነት ተጠቃሽ ችግር መሆኑንም ይናገራሉ። የተቋራጮችን የአቅም ውስንነት ለመፍታት በጋራ እየተሰራ መሆኑን ያመለክታሉ። የማሽነሪ እጥረት ዋነኛው ችግር እንደሆነም ነው የሚገልጹት።

በፌዴራል የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጥራት ቁጥጥር ንዑስ የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ዘውዱ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት አስር የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በማከናወን ላይ መሆኑን ያመለክታሉ።

የተንዳሆና ከስም ግድብ ግንባታ ስራዎች ዘግይተውም ቢሆን መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት የመስኖ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። የተንዳሆ የመስኖ ፕሮጀክት 60 ሺ ሄክታር መሬት የሚያለማ ሲሆን፤ከዚህ ውስጥ ድርጅቱ 30ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት የሚያስችል ሥራ በማከናውን ላይ ይገኛል። በአሁኑም ወቅት 21 ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል።

በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ክንውን ላይ የመዘግየት ችግር ታይቷል። ለዚህ ደግሞ የማሽነሪ እጥረት ዋነኛው ችግር መሆኑን ነው አቶ ዘውዱ የገለጹት። በቂ ማሽነሪዎች ባለመኖራቸው በኪራይ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ። የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች እጥረት ቢፈታ የመስኖ ፕሮጀክቶቹን ግንባታ ይበልጥ ማፋጠን እንደሚቻ ልም ያምናሉ።

እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ፤ በአገሪቱ የኮንስ ትራክሽን ዘርፍ እያደገ ቢሆንም የግንባታ መሳሪያዎች ፍላጎትና አቅርቦት ያለመጣጣም ችግር ጎልቶ ይታያል። የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ችግሩን ለመፍታት የተወሰኑ መሳሪያዎች ገጣጥሞ በማቅረብ ላይ ነው። የተንዳሆ፣ የከሰም፣ የጊዳቦና የርብ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

************

Source: Addis Zemen – April 29, 2013. Originally titled “በማሽነሪ እጥረት የመስኖ ግድቦች ግንባታ ተጓትቷል”

Daniel Berhane

more recommended stories