መለስ ‘ለሌሎች ሕይወት ሳስቶ ራሱን ሊያጠፋ ነበር’ – ስዩም መስፍን

(ሰለሞን በቀለ)

ላለፉት 40 ዓመታት አብረው ቆይተዋል፡፡ ከሰኔ 1964 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ወንድምም፣ እንደ ስራ ባልደረባም፣ እንደ ትግል ጓድም ሆነው ብዙ ውጣ ውረዶችን አብረው አሳልፈዋል፤ አቶ መለስና አምባሳደር ስዩም መስፍን፡፡ መለስ እንደ ማለዳ ጀንበር ለአፍታ ቀና ብሎ ሕዝቡ ለእርሱ ያሳየውን ክብርና ፍቅር ባየ እንዴት መልካም ነበር? የሚሉት አምባሳደር ስዩም በትግሉ ዘመን ከአቶ መለስ ጋር ስላሳለፉት መከራና ችግር፤ ስለ አቶ መለስ ባህሪም አጫውተውናል፡፡ አምባሳደር ስዩም በጓዳቸው ህልፈት ክፉኛ ማዘናቸው ያስታውቃል፡፡ ባነጋገርናቸው ጊዜም እንባቸው ለመውረድ ይታገላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ‹እንበርታ እግዚአብሄሔር ያፅናን› ብለዋል፡፡Seyoum Mesfin - Ethiopian Ambassador to China and former Foreign Minister

ዘመን፦ እንደሚታወቀው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም አዝኗል። ይህን ኀዘን እርስዎ እንዴት ይገልፁታል?

አምባሳደር ስዩም፦ ሕዝቡ ከሚገልፀው የተሻለ አንደበት የለኝም። ጥልቅ ኀዘን ውስጥ ነው ያለነው። አገሪቱ በሙሉ፤ በውስጥም በውጭም ያለው ሕዝባችን፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያውቁዋቸው የነበሩና ጓደኞቻቸው በሙሉ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ህልፈት ስለሆነባቸው ሁሉም ጥልቅ ሐዘን ውስጥ ነው ያሉት። እንግዲህ ይሄ የተፈጥሮ ሕግ ነው። የሰው ልጅ በህይወት እንደሚኖር ሁሉ ማለፉ ደግሞ የማይቀር ነው። በእርግጥ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ህልፈት በብዙ መንገድ መቀበል አቅቶናል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ውጥን ነበረው።

እንደሚታወቀው ድርጅቱ(ኢህአዴግ) የአመራር ሽግግር ላይ ነው ያለው። ከኔ የተሻለ ወጣቱ ትውልድ ቦታውን ይረከብ የሚል አቋም ነበረው፡፡ እናም ስልጣኔን እለቃለሁ ማረፍም እፈልጋለሁ ሲል ቆይቷል።የድርጅቱ ውሳኔ ስለሆነበትና እስከ መጪው ምርጫ ድረስ አምስት ዓመታቱን በግድ መቆየት አለብህ ተብሎ ነው በስልጣን ላይ እስካሁን የቆየው፡፡ ይህን ግን እርሱ ባያምንበትም ለድርጅቱ ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ ተገዢ ሆኖ ነው የቀጠለው። በዚህ አምስት አመታት ውስጥም የወጣቱንና የአዲሱን ትውልድ የአገር ተረካቢነት ሚና የማጠናከርና በድርጅቱም፣ በመንግሥትም ውስጥ ተተኪና ጠንካራ አመራርን የመፍጠር እቅድ ነበረው፡፡ ምክንያቱም የድርጅቱንና የመንግሥትን አመራር ሳያጠናክሩ የልማቱን ጉዞ በተያዘው አቅጣጫና በተፈለገው ፍጥነት ለማስኬድ ስለማይቻል ነው፡፡ ይህን እንደ አይነተኛ ጉዳይ አድርጎ ነው ሲንቀሳቀስ የነበረው፡፡ ይህ ውጥን ነበረው። ራዕዩ እውን እንዲሆንና የሕዝቡም ልማት በሚያስተማምን ፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ፍላጎት ነበረው፡፡

እድል አግኝቶ እንደጠለቀችና ተመልሳ በነጋታው የብርሃኗን ድምቀት እንደምትሰጥ ፀሀይ ለአፍታም ቢሆን ቀና ብሎ ቢያየው እንዴት ጥሩ ነበር? እርሱ የቀየሰው ራዕዩ፣ መስመሩ፤ የኢህአዴግ አባልና ደጋፊው ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይ ደግሞ ጭቁኗ ሴት፣ አፍላው ወጣት፣አርሶአደሩ፣ ሰራተኛው፣ ምሁሩ፣ ባለሀብቱ፣ ነጋዴው፣ ሁሉም መፍትሄያችን ነው፣ የሀገራችን ህዳሴ ነው፣ ድህነት ከፈጠረብን ውርደት የምንወጣበት መንገድ ነው እያለ ነው፡፡ ይሄ የሁሉም አስተሳሰብ ሆኖ ሁሉም በአንድ ድምጽ በድህነት ላይ የዘመተበት መሆኑንና በዚህ ደረጃ ለእርሱ እየገለፀ ባለው ፍቅርና ሀዘን ልቡ እየነደደ መሆኑን ለማየት ቢችል ኖሮ ‹የቀረብኝ ነገር የለም፣ መስራት ያለብኝን ሥራ ሰርቻለሁ› በማለት ረክቶ በተመለሰ ነበር። ግና ሳይረካ እሰራለሁ ሲል ነው ያለፈው።

ይህ ነው ለሁላችንም እንደእሳትና እንደረመጥ እያቃጠለን ያለው። ለማንኛውም ይህን ሕዝቡም፣ ወጣቱም እየገለፀው ነው፡፡ ኢህአዴግም የመንግሥት አመራሩም ኀዘን ከዚህ የተለየ አይደለም። ይህንን ሕዝብ ይዞ የመለስን ራዕይ ከዳር ለማድረስ ይቻላል። እናም በቁርጠኝነት ታጥቀን መነሳት አለብን፤ ሕዝባችንን አሰልፈን። መለስን የሚተካ አንድም ሰው ባይኖርም ቢያንስ እንደ ድርጅትና እንደመንግሥት ኃይላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ኢህአዴግ ብዙ ፈተናዎች ደርሰውበት አዝኖ ኀዘኑንም ተቋቁሟል። እንደዚህ አይነት ከባድ ነገር ገጥሞት ባያውቅም የተለያዩ የህልውና የመኖርና ያለመኖር ፈተናዎች ገጥመውታል፡፡ ይህንንም ችግር ከሕዝቡ ጋር ሆነን እንወጣዋለን የሚል እምነት አለን። የእኔም እምነት ይሄ ነው።

ዘመን፦ አቶ መለስ የትግል አጋርዎ ናቸው፡፡ ለእርሳቸው የበለጠ ቀረቤታ ይኖርዎታል ብዬም አስባለሁ። በትግሉ ጊዜ ከነበራችሁ አንዳንድ ትውስታዎች ሊነግሩኝ ይችላሉ?

አምባሳደር ስዩም፦ የመለስ ራዕይ የሕዝብ ፍቅር ነው፡፡ይህም በቁርጠኝነት ተግባር ላይ እንዲውል ድርጅቱንና ሕዝቡን መርቶ ወደ ተግባር የመግባቱን ጉዳይ በስፋት የሚያውቅ ነው። እንዳልከው ቢያንስ ለአርባ አመታት አብረን ነበርን። ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር በወጣትነት እድሜዬ በ 1964 ዓ.ም ክረምት ላይ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው። ያኔ እርሱ የዊንጌት ትምህርቱን ጨርሶ በ1965 ዓ.ም ዩኒቨርስቲ ለመግባት ይጠባበቅ ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው የተማሪ ንቅናቄ ምክንያት ከመጀመሪያው ሴሚስተር በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተዘግቶ ስለነበር የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ሁሉም በተደራጀ መልክ በወቅቱ በየጠቅላይ ግዛቱ ሄዶ ሕዝቡን እንዲያነሳሳና ከሕዝቡ ጋር የሚያገናኙት አንዳንድ ነገሮችን ይዞ ተንቀሳቅሷል፡፡ በእንቅስቃሴው ውስጥም አመራር ነበር፡፡

አድዋ ላይ እንደዚሁ ከትግራይ የተውጣጣ ቡድን በየጠቅላይ ግዛቱ አውራጃዎች ርዕሰ ከተሞች ይንቀሳቀስ ስለነበር የቅርጫትና የእጅ ኳስ ጨዋታ አለን በሚል ከአዲግራትና ከመቀሌ ተወጣጥተን አድዋ ንግሥት ሳባ ድረስ በሄድንበት ጊዜ አቶ መለስም እዛው ከነበሩት የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር አብሮ ስለነበር እዚያ ተገናኝተናል፡፡እና ከእዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው የምንተዋወቀው። በ65 ዓ.ም ነው አቶ መለስ ዩኒቨርሲቲ የገባው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተማሪውን እንቅስቃሴ መሰረት ያደረገ የትግራይ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር ነበር። ይህ የተቋቋመው ማህበር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ማህበር ጋር በተጓዳኝ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ አቶ መለስ ያኔ ከሁላችንም ያነሰ ወጣት ነበር፡፡ ነገር ግን ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብና ውይይቶችን በመምራት በኩል የጎላ ሚና ነበረው።

በተለይ በ1966 ዓ.ም የአገሪቱ አጠቃላይና አብዮታዊ እንቅስቃሴ ከዳር እስከ ዳር እየተቀጣጠለ የመጣበት ሁኔታ ነበር። ያኔም አቶ መለስ ከሳይንስ ፋኩልቲ ተመርጦ የተማሪዎች መማክርት አመራር ውስጥ ተካቶ ነበር። በእንዲህ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው እንግዲህ በቅርብ ልንተዋወቅ የቻልነው፡፡ አቶ መለስ ያን ጊዜ ወጣትና ከሁላችንም ያነሰ ቢሆንም ብልህና አስተዋይ ነበር።በሳልና ብዙ አስተዋፅኦ ያበረከተ ሰው ነው፡፡ እንግዲህ በኋላም ደርግ የሕዝቡን አመፅ አኮላሽቶ ወታደራዊ አገዛዙን አውጆ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የትግራይ ተራማጆች ብሔራዊ ንቅናቄ ህቡዕ ድርጅት ትግሉን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡እርሱም በአመራሩ ውስጥ ባይኖርም ያኔም በንቅናቄው ውስጥ ከታቀፉትና ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ታጋዮች አንዱ ነበር።

የደርግ አካሄድ እጅግ አስከፊና ሁለትና ሶስት ሆኖ በጋራ መምከር የማይቻልበት ሁኔታ ነበር፡፡ በወቅቱም ፋሽስታዊው ደርግ የጭካኔ አዋጅ በማወጁ ሠላማዊ ትግል የሚባል ነገር የሚቻል አልነበረም። በእዚህም የትጥቅ ትግሉን መጀመር አለብን ብሎ የትግራይ ተራማጆች ብሔራዊ ንቅናቄ ውሳኔ ሲያስተላልፍ አቶ መለስም ከዩኒቨርሲቲ ወጥቶ የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ከሚዘጋጁት አንዱ ነበር። እርሱ መጀመሪያ በጥር ወር 1967 ዓ.ም ወደ ኤርትራ ለስልጠና ከተላኩት ጥቂት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ታጋዮች ውስጥ አንዱ ነበር።ወታደራዊ ስልጠናውን ሳይጨርስ እርሱና አቶ አባይ ተመልሰው ወደ ፖለቲካ ስራ እንዲገቡና የትግሉን አቅጣጫ በሰነድና በማኒፌስቶ መልክ እንዲያዘጋጁ የቤት ስራ ስለተሰጣቸው በትግራይ ከተሞች በአክሱምና በአድዋ ተደብቀው ይህንን እንዲያዘጋጁ መመሪያ ተሰጥቷቸው ሲያዘጋጁ ቆይተዋል።

በመጨረሻም በ1967 ዓ.ም ደደቢት ወደነበረውና እዚያ ወደተሰማራው ኃይል ተቀላቅሏል።ስለዚህ በእዚህ ሁሉ የአቶ መለስ ሚና የጎላ ነበር። በተለይ ትግሉን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙ ጊዜ የችግሩን ባህሪ፣ መውጪያና መፍትሄውን አሳማኝ በሆኑ መንገዶች ጥናቶችን አጥንቶ በማቅረብ ድርጅቱንና የድርጅቱን ህልውና በማስጠበቅ ድርጅቱ ሕዝባዊ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የትግራይ ሕዝብን ብሔራዊ ትግል ከኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መደባዊ ትግል ጋር እንዴት ይቀናጃል? የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች እንዴት ይሰባሰቡ? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳትና የጠራ መስመር በማቅረብ የጎላና ተኪ የሌለው ሚና ሲጫወት ቆይቷል።እነዚህን ጉዳዮች ሁሉም የሚያውቃቸው ናቸው፡፡ ምናልባት ጠቃሚ መስሎ የሚታየኝ ባህሪያቸው ምን አይነት ነበር የሚለው ነው፡፡

ዘመን፦ አዎ! ስብዕናቸው ምን ይመስል ነበር?

አምባሳደር ስዩም፦ ከመጠን በላይ ሩህሩህ ነው። ወገን፣ደም አይለይም፡፡ የተጨነቀ፣ የተቸገረ ሲያይ እንባው ነው የሚቀድመው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ አይደለም፣ የሁሉንም ህዝብ ታሪክ ያነባል፡፡ የታጋይና የጭቁን ሕዝቦችን ታሪክ ያነባል። ችግራቸውን እንዴት እንዳለፉት ያጤናል።ሁሉም ሕዝብ ፍጡር ነው፣ ሰው ነው ብሎ ያምናል።ሰውን በጣም ያከብራል። ሰው ሁሉ እኩል ነው የሚል የፀና አቋም አለው። እያንዳንዱ ሰው ሚና አለው ብሎም ያምናል። ሁሉም የራሱ ሚና አለውና ያን ሚና ይዞ ሲመጣ ውጤት ይመጣል ይላል። ያበረታታል። ሚናውን ይበልጥ የሚያጎለብትበትን መንገድ ያሳያል፡፡

መለስ የጎላ የሰው ፍቅር አለው። መለስን ቀርቦ ለሚያየው ከእርሱ ብዙ እንደሚማር ያውቃል። ሰብአዊ ርህራሄ የነበረው ሰው ነው። ሲያዝንም ያለቅሳል፣ ሲደሰትም፣ ሲቀልድም እንባውን ያፈሳል፤ ከልቡ። ለይምሰል ብሎ ሳቅ አይስቅም። የመለስ ንግግሮች ከሕዝቡ ኑሮና ከሕዝቡ ትግል የተለዩ አይደሉም። መለስ ሲስቅ ጥርሱን ገልጦና ከልቡ ነው፡፡ ሰው ምን ይለኛል አይልም፡፡ይቀልዳል፣ ይጫወታል፣ ሰውን ይቀርባል፡፡ይህ የአቶ መለስ ባህሪ ነው። መለስ ከትምህርት፣ ከጥናት፣ ከንባብ ተለይቶ አያውቅም።

በአጠቃላይ ለእውቀት ብቻ ብሎ አያነብም፡፡ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡ ለጥያቄዎች መፍትሄ ፍለጋም ነው የሚያነበው። የሕዝብ ጥያቄዎች ሲሆኑ አንብቤ መልስ አገኝበታለሁ ይላል። ጽሑፎቹ ወታደራዊ ጥበብና ሳይንስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሁሉም ዘርፎች ፈጣን ጥያቄዎች ሲነሱ መልስ አገኝበታለሁ ብሎ ይንቀሳቀሳል። ከተግባር ይማራል፣ ከመጽሐፍት ይማራል።ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም፡፡ ሌሎችንም ያስተምራል።ያወቀውን ሁሉ ያካፍላል፤ያጋራል።ይሄ የእኔ ነውና አንብቡ ብሎ አያውቅም፡፡ የሰራውን ስራ እዩልኝ፣ ይሄ የእኔ ውጤት ነው፣ይህን ሰርቻለሁ ብሎ አይኩራራም፡፡መታወቅን አይፈልግም። ይሄ ጎድሎኛ፤ ይህን ስጡኝ፣ ይሄ ያስፈልገኛልና ይሄን አድርጉልኝም ብሎ አያውቅም።

አባቱ አቶ ዜናዊ የነገሩኝን ታሪክ ልንገርህ፡፡ ጀነራል ዊንጌት ፈተና አልፈሃል ተብሎ አባቱ ከአድዋ በአውቶቡስ ይዘውት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ወልዲያ ያድራሉ። ምሽት ወልድያ እራት እየበሉ« ምን ትጠጣለህ?» ይሉታል፡፡ «ውሃ» ይላል። ልብ በል ያኔ ገና ወጣት ነው። ስምንተኛ ክፍልን ጨርሶ ወደ ዘጠነኛ ክፍል አልፎ ነው ጀነራል ዊንጌት ይሄድ የነበረው። ያን ዕለት ታዲያ አባቱ አቶ ዜናዊ «ኮካኮላ ጠጣ» ይሉታል፡፡ «የለም ውሃ ነው የምጠጣው» ይላል፡፡ አባትየውም «ለምን? ገንዘብ የለውም ብለህ ነው? ችግርኮ የለም መጠጣት ትችላለህ» ይሉታል፡፡ በኋላ «አይ ከሆነስ እሺ» ብሎ ጠጣ ብለውኛል፡፡ አየህ አባቱንም፣ ቤተሰቡንም ማስቸገር አይፈልግም። ርቦኛል፣ ያስፈልገኛል፣ ይህን አድርጉልኝ፣ ይህን ግዙልኝ አይልም። ኮካኮላ በወቅቱ 25 ሳንቲም ነበር ግን ሊያስቸግር አልፈለገም።

ሌላ ከማስታውሰው ምን ያህል ለሰው ያስባል? ለቆመለት ዓላማስ ምን ያህል የፀና ነው? የሚለውን አንድ ነገር ላንሳልህ። የትጥቅ ትግሉ በ1967 ዓ.ም በተጀመረበት ወቅት ክረምት ሐምሌና ነሐሴ ላይ ዝናቡ ከፍተኛ ነበር፡፡ያኔ እንግዲህ ቤት ወይም መንደር ገብተህ አታድርም፡፡ ራስህን ደብቀህ በረሃ ነው የምትንቀሳቀሰው፡፡ ድርጅቱም ጥቂት የነበሩት ታጋዮችም ራሳቸውን ደብቀውና ሰው ካለበት ርቀው ራሳቸውን በማደራጀት ላይ ነበሩ፡፡ እና ጠላት ታጋዮቹም ገና ሳይበራከቱና ወደሌላ ሳይሻገሩ፣ትግሉን በእንጭጩ መቅጨት አለብን በሚል ነጭለባሾችንና ሰላዮቹን ያሰማራበት ጊዜ ስለነበር በጣም ፈታኝ ወቅት ነበር፡፡ ይሄ የመጀመሪያው የትግሉ ዓመት ነበር። በዚህ ፈታኝ ወቅት አቶ መለስ የታይፎይድ በሽታ ይታመማል። ታይፎይድ መሆኑን ያወቅነው በኋላ ላይ ነው። በጣም ከፍተኛ አደጋ ላይ ደርሶ ነበር። ሕይወቱንም እስከ ማጣት የደረሰበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው፡፡ያኔ እንግዲህ በዋልክበት አታድርም፣ እራት በበላህበት አታመሽም፣አታድርም፡፡ ቀንም ሌሊትም ጉዞ ላይ ነህ። በጊዜው እንደ መለስ ሁሉ በወባም፣ በተስቦም የታመሙ ሌሎች ታጋዮች ነበሩና እንቅስቃሴያችን ተገድቦ ነበር፡፡ የማስታውሰው አንድ በቅሎ ነበረን፤ ስንቅ ምናምን የሚያመላልስ፡፡

ከሁሉም በጠና ታሞ የነበረው አቶ መለስ ስለነበረ በዛ በቅሎ ላይ ብቻውን ተቀምጦ መጓዝ ስለማይችል ሰው ደግፎት ጉዞ ጀመርን፡፡ ጉዞው ደግሞ በጨለማ ነው፡፡ በወቅቱ እንቅስቃሴያችን ድብቅና የተገደበ ነው፡፡ ምክንያቱም ታጋዮች ገና የሚረባ ትጥቅ እንኳ ያልታጠቁበትና ያልተጠናከሩበት ጊዜ ነውና ‹እኔን ሲጎትቱ እዚህ አካባቢ ነው ያሉት የሚል ወሬ ለጠላት ከደረሰ አደጋ ላይ እጥላቸዋለሁ፤ የእነርሱንም ሕይወት ለአደጋ እዳርጋለሁ። እነርሱ ደግሞ አደጋ ላይ ከወደቁ ትግሉ በእንጭጩ ይቆማል› የሚል ስጋት አድሮበት ታጋዮቹ ባረፉበት ምዕራብ ትግራይ ቆላማ፣ተራራማና ገደላማ አካባቢ ነበር ‹ሕይወቴን ባጠፋ የእነርሱን ሕይወት አድናለሁ› ብሎ ያሰበው። ‹የእኔ ሕይወት ቶሎ ቢያልፍ ይሻላል፣ እኔን ሲጎትቱና እኔን ሲሉ አደጋ ላይ ይወድቃሉ፣ ለእኔ ሲሉ ያልሆነ ቦታ እያደሩና እየዋሉ ነው፣ እኔ ከሞትኩ ግን እንደልባቸው መንቀሳቀስ ይችላሉ› ብሎ አስቦ ኖሮ ታጋዮቹ ካረፉበት ቦታ ተንፏቆ ገደል አፋፍ ሊደርስ ሲል አዩት። ገደል ገብቶ ራሱን ሊያጠፋ ነበር ግን ያዙት። በእዚህ ጊዜ እርሱም ያለቅሳል፣ ታጋዮቹም ተላቅሰው ደግፈውት ጉዞው ቀጠለ፡፡

በኋላ ግን ነገሩ ጥሩ ሆነ፡፡ ከከተማና ከድርጅት መድሃኒት ተላኩልንና ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ዳነ። መጨረሻ ላይ የነበረውን ሁኔታ ሲያጫውተን ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ለሌሎች ታጋዮች ሕይወት ሳስቶ የራሱን ሕይወት ለማጥፋት ወስኖ እንደነበር ነገረን፡፡ የእነርሱ ህይወት ከጠፋ የትግሉ ጉዞ ይሰናከላል፣ በእንጭጩ ይቀጫል ብሎ ስላሰበ ነው። እንዲህ አይነት ሰው ነው መለስ። እና እነዚህ ባህሪዎቹ ብዙም የሚታወቁ አይደሉም። አቶ መለስ ሰው አይለይም፡፡ በጣም በጣም አሳቢ ነው፡፡ አዛኝ ነው። ስስ ነው፤ ለሰው። ለሕዝቡና ለአገሩ የላቀ ስሜት አለው፡፡ አገር ሲባል ሕዝብ ነው፡፡ ከሕዝብ ውጪ የሚታይ ነገር የለም ብሎ የሚያስብ ሰው ነው መለስ።

ዘመን፦ ከእርስዎ ጋር በነበራችሁ ቀረቤታ ሌላሰ የሚያስታውሱት የተለየ ነገር ይኖራል?

አምባሳደር ስዩም፦ በሥራ፣ በትግል፣ በመንግሥት ኃላፊነትም አብረን ቆይተናል። ሳንገናኝ የቀረንበትን ቀን መቁጠሩ ይሻላል። አብረን ሰርተናል። የሚያየውን ጉድለት አይደብቅም።ጉድለትህን እንድትማርበት ነው የሚያነሳው፡፡ እርሱንም ጉድለት አለብህ ካልከውና በትክክል ጉድለቱን ከጠቆምከው ከመቀበል ወደኋላ አይልም። ጉድለቱን አይቶ ይቀበላል፣ ይማራል፣ ሰውንም ያስተምራል። ጉድለትህን ይነግርሃል፣ ያስተምርሃል። ይህን የሚያደርገው እንድትታነፅበት ነው። ኢህአዴግ መለስን አንጿል፣ መለስም ኢህአዴግን አንጿል። ገንብቷል። እኛ የምናየው በመለስ እይታና በመለስ ራዕይ፣ በመለስ መስመር፣ በመለስ ፖሊሲ የታነፁ ግድቦችን፣ መንገዶችን፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን፣ የኢኮኖሚ ልማትንና እነዚህን ነው፡፡ ጎልተው በተጨባጭ የሚታዩት እነዚህ ናቸው።መለስ ያነፀውና የማይጠፋው ነገር ካለ የሕዝቡ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሀብትም የሚፈጥረው፣ ትራንስፎርሜሽን የሚያመጣውና የመጪውንም ትውልድ የሚወስነው ይሄ ነው። በሕዝቡ ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ምን አንጿል? የሚለውን ነው መለስ የሚያየው፡፡ ድህነትን እናሸንፋለን። ሥራ ክቡር ነው። ሳይሰሩ መብላት ሀጢያት ነው። ሙስናን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚያወግዝና ይህም የልማት፣ የትውልድ፣ የትንሳኤያችንና የሕዳሴያችን ነቀርሳ መሆኑን በወጣቱም ሆነ በሁሉም ዘንድ እንዲሰርጽ አድርጓል። በድርጅቱ ቁርጠኝነትን፣ የሕዝብ አገልጋይ መሆንን፣ የራስን ጥቅም ከሕዝብ ጥቅም፣ ልማትና እድገት ጋር የማስተሳሰርን አስተሳሰብ በታጋዩ፣ በደጋፊው፣በሕዝቡ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ ማድረግ ችሏል፡፡ ዋስትናችን ይሄ ነው በእዚህ አስተሳሰብ እንቀጥላለን ብሎ ሕዝቡ ይሄንን ስላመነበት ነው የተቀበለው። ለምንድን ነው ሕዝቡ በመለስ ህልፈት እንደዚህ አንጀቱ ያረረውና የተቃጠለው?

ዘመን፦ አዎ እርሱን ላነሳልዎት ነበር፡፡ አሁን ሕዝቡ በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ ነው ኀዘኑን እየገለፀ ያለው፡፡ ይሄ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?

አምባሳደር ስዩም፦ ይሄ ምንን ያሳያል? ይሄን ሀሳብና ራዕይ ያመነጨ፣ወደ ተግባር ያሸጋገረው መሪ ጠፋብኝ፤ ይሄን ያስታጠቀኝን መሪዬን አጣሁት፡፡ አከብርሃለሁ፡፡ ምክንያቱም አንተ የሰጠኸኝን ይዤ ተጠቃሚ ሆኛለሁ ነው ሕዝቡ የሚለው።ወጣቱም ሥራ አልባ ነበርኩ፣ ጨልሞብኝ ነበር፣ የብርሃን መንገድ አግኝቼ መንቀሳቀስ ጀምሬያለሁ። ዳር ላይ ሳታደርሰኝ ሄድክብኝ እያለ ነው። ይሄን መገንባቱ ነው ዋስትናችን የሚሆነው። ትልቁ ያገኘነው ሀብትም ይሄ ነው። የተገነቡት ተገንብተዋል፡፡ የሚገነቡትን እንገነባለን፡፡ የመሰረተ ልማት አውታሮችን እንቀጥልባቸዋለን፣ ወደ ኋላ የሚመለሱ አይደሉም፡፡ ግን ከእዚህም በላይ አማትረው የሚሄዱና ብዙ ራዕይን መሰረት ያደረጉ የሰነቅናቸው አመለካከቶች አሉ። መለስ ሁል ጊዜ እነዚህ አመለካከቶች፣እነዚህ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊና የእኩልነት መብቶች በሕዝቡ አስተሳሰብ ውስጥ ከነገሱ ኢህአዴግ ቢኖርም ባይኖርም ችግር የለውም ይል ነበር፡፡ አሁን ሕዝቡ እነዚህን አስተሳሰቦች የእኔ ናቸው ብሎ አቅፎ ይዟቸዋል። ይህንን ነው መለስ ያነፀው፡፡ይሄም አይመክንም፡፡

ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገራል። መለስ ሁል ጊዜ የእኛ ትግል የማራቶን እሩጫ አይደለም ይል ነበር። አንድ ሰው ብቻውን ሮጦ የሚጨርሰው የማራቶን ሩጫ አይደለም። የዱላ ቅብብሎሽ ነው፡፡ ትውልዶች የሚቀባበሉት ነው። አንድ ትውልድ አንድ ቦታ ላይ ያደርሳል። በአንድ ወቅት የተጀመረ የሕዝብ ትግል ስለማያቋርጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ነው የሚሄደው፡፡ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ነው ይዘነው የምንጓዘው ይል ነበር።መለስ ይህን ዱላ ተቀባይ ወጣት ፈጥሯል። ሴቱን፣ ወንዱን፣ ወጣቱን፣ አዛውንቱን፣ሁሉንም በእዚህ አስተሳሰብ አንፀነዋልና ዋስትናችን ይሄ ነው። ይሄ ደግሞ የመለስ ራዕይ ነው።ይሄ የመለስ አስተዋጽኦ ነው።ተኪ የሌለው አስተዋፅኦ ነው።ውጤት ነው። ለዚህ ነው መለስ በስጋ ቢለየንም በስራውና በያዝነው አመለካከት ሁልጊዜም አብሮን ይኖራል፡፡ መጪው ትውልድም አብሮት ይኖራል የምንለው። ሕዝቡም ይህን ጥልቅ ግንዛቤ በሚገባ ተረድቶታል ብዬ አምናለሁ።

ዘመን፦ቀጣዩ የኢትዮጵያ አመራር፣ ሕዝቡም ኀዘኑን ረስቶ ጠንክሮ ወደ ሥራ በመግባቱ ረገድ ምንድን ነው የሚጠበቅበት፤ በተለይ አመራሩ?

አምባሳደር ስዩም፦ በታሪክ አንዳንዴ የሚወሳ ነገር አለ። አዲሲቷ የቻይና ሕዝባዊት ሪፐብሊክ በፈረንጆች አቆጣጠር በ1949 ዓ.ም ነው የተመሰረተችው። በቻይና አብዮት የሕዝብ ትግል ከሚታወቁት መሪዎች አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቹ ዬን ላ ናቸው። በ1976 ዓ.ም በፈረንጆች አቆጣጠር ነው ድንገት ያረፉት።በድንገተኛ አደጋ ነው የሞቱት። የእዚች አገር ታሪክ አሁን ያለውን የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያሳይ ነገር ነው ተፅፎ የምታገኘው። አሁን በሕይወት ያሉ ታሪኩን የሚያውቁት ሲናገሩ በወቅቱ አገሪቷን በሙሉ ሽባ ያደረገ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር ነው የሚሉት፤ በእርሳቸው ሞት። ከእርሳቸው ሞት በኋላ ሕዝቡ በጣም ደንግጧል። አሁን የምታየው የኢትዮጵያ አይነት ሕዝቡ መንገድ ወጥቶ በማልቀስና በማዘን ወደ ሥራ መንቀሳቀስ የተሳነው ጊዜ እንደነበረ ነው የሚነገረው፡፡ ከሐዘኑ ለማገገም የወራት ያህል ጊዜ ወስዶባቸዋል። በሐዘን ምክንያት ሁኔታው የጨለመበት ነበር። በኋላም የማኦ ዘይቱንግ ሞት ተከተለ፡፡ እና በወቅቱ በአገሪቱ ያልተረጋጋ ሁኔታ ነበር ተፈጥሮ የነበረው።

እኛ ዛሬ ከእዚህ መማር አለብን እላለሁ። እያዘንን ወደ ሥራ መግባት ነው ያለብን። ሀዘናችንን በሥራ ነው መግለፅ ያለብን። እየሰራን ነው መለስን ህያው አድርገን እርሱነቱ እንዲቀጥል የምናደርገው። እያዘንን ወደ ሥራ በመግባት ሀዘናችንን በሥራ ነው መግለጽ የሚገባን፡፡በእዚህ አይነት ሁኔታ ነው መለስን ህያው የምናደርገው፡፡ እርሱ የፈጠረልንን ሥራ፣ እርሱ የሰጠንን ራዕይ ይዘን የእርሱ ፍላጎት የነበረውንና የእኛንም ጥቅም የምናረጋግጥበትን ይህን ራዕይ አጠናክረን መቀጠል አለብን።

ኀዘናችን ከልባችን እስኪወጣ ድረስ ጊዜ ሊወስድብን ይችላል። ሀዘናችን ጥልቅ ነው፡፡ ግን ይህን ተሸክመን በሥራ ነው መግለፅ ያለብን፡፡ መለስን በሥራ ህያው እናድርገው የሚለው ነገር አሁን የወጣቱና የአዛውንቱ ቋንቋና አስተሳሰብ ሆኗል። ቀና ደፋ እያሉና አካፋና ዶማ ይዘው እየቆፈሩ ግድቡን እየገደቡ ነው ሐዘናቸውን እየገለፁ ያሉት፡፡ ሥራ አቁመን አይደለም ማዘን ያለብን፡፡የእኛ ትልቁ መልዕክት ይህን አገሪቱ የጀመረቻቸውን ጅምሮች በዚሁ አጠናክሮ መቀጠል ነው የሚያስፈልገው፡፡ እኛ የሞት ሞት የምንሞተው ሀዘናችን ከስራ ውጪ ካደረገን ነው።

በቃ መለስ አልፏል።ሁልጊዜ እናከብረዋለን፣ እንወደዋለን፡፡ ግን የእኛ ክብርና ፍቅር የሚገለፀው በስራ መሆን አለበት የሚለውን በትክክል መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ዘመን፦አመራሩ በቀጣይ የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ እንዴት ነው በጥንካሬና በብስለት መጓዝ ያለበት?

አምባሳደር ሰዩም፦ እንግዲህ ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ሌሎች አማራጮች፣ አማራጮች አይደሉም፡፡ ህዝቡን በበሳል መስመር መምራት የተቀመጠለት መስመር ነው፡፡ አዲስ መስመር ፍለጋ ላይ አይገባም፡፡ ይህን መስመር እንዴት ተግባራዊ ላድርግ ብሎና በቁርጠኝነት ለእዚህ የሚያበቃውን አደረጃጀት አጠናክሮ እንዲሁም የተፈጠረውን የህዝብ ማዕበል ይዞ መቀጠል አለበት። ህገ መንግስታችንን በመጠበቅ የድርጅቱን መመሪያዎችና ህጎች መሰረት ያደረጉ ተቋማትን ነው መገንባት ያለብን።መለስን አንድም ሰው ባይተካውም የመንግስትና የድርጅቱ አመራርና የህዝቡ እንቅስቃሴ እንዴት ተቀጣጥሎ ይሂድ የሚለውን ማየት አለበት፡፡

ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ወደ ኋላ፣ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ የሚባልበት መንገድ የለም። የአገራችንና የህዝባችን መፃኢ እድል ብሩህ ነው። በጣም ብሩህ ነው።እንዲህ አይነት ለለውጥ፣ ለትራንስፎርሜሽን፣ ለስራ የተነሳሳ የህዝብ ማዕበል ከሁሉም የሚበልጥ ሀብትና ፀጋ ነው። በዴሞክራሲ፣ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የህዝቡን ይሁንታ ያገኘ አገር በታሪክ አጋጣሚ ጥቂት ነው። ይህን እድል አግኝተናል።ሁሉንም ሀብትና ጥበብ የሚያስጨብጠንና የሚፈጥርልን ይሄው ነው፡፡ በዚህ ይሁንታ እንዴት አድርገን ነው ህዝቡም አመራሩም በጋራ ተሳስሮ የሚሄደው የሚለውን ያያል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም።

ዘመን፦ በዚህ ሁኔታ በቀጣይ የአቶ መለስ ራዕይ ይሳካል፣ ኢትዮጵያም ታላቅ አገርና ህዝብ ትሆናለች ብለው ያምናሉ?

አምባሳደር ስዩም፦ አልጠራጠርም። ወደ ኋላ የምንመለስበት ምንም ምክንያት የለም። ሁሉም ዕድል አለን፡፡ እንኳን አሁን ይሔን የፈነጠቀውን ብርሀንና ውጤት እያየ ይቅርና ህዝቡ በተስፋ ድርጅቱንና አመራሩን አምኖ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።አሁን የራሱም አድርጎ ይዞታል፡፡ ወደኋላ የሚመለስበት ምክንያት የለም።

ዘመን፦ ይህን ያነሳሁብዎት አንዳንድ ወገኖች ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ የፖሊሲ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፤ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ የሚሉ ሃሳቦችን እያነሱ ስለሚገኙ ነው፤

አምባሳደር ስዩም፦ የጥፋት መንገድ ዕድል የለውም። ህዝባችን ተገቢ ጥርጣሬዎች ሊኖሩት ይችላሉ። መነሳት ያለባቸውን ጥያቄዎች ቢያነሳ ተገቢ ነው። መለስን የሚተካ ሰው ይገኛል? አይገኝም። የዘመናችን ትውልድ የሚያፈራቸው በጣም ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ በዓለም ነበሩ የሚባሉ ካሉ አንዱ መለስ ነው። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ ጥቂቶች ናቸው፤ ባለንበት ዘመን፡፡ እነዚህ ሁሉም መሬት ላይ ያሉ ትውልዶች ያፈሩት የዘመናችን ብልህና አዋቂ፣ ለህዝብ አመራር የሰጠ ታላቅ መሪ ነው መለስ። እርሱ የአፍሪካም መሪ ነው፡፡ በዓለም አመራር ሲሰጡ ከነበሩት ጥቂት ከሚከበሩና አንቱ ከሚባሉ መሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የዚህ ባለቤት በመሆኗ ትኮራበታለች፤ ከህይወት ህልፈቱም በኋላ። እንደነዚህ አይነት ሰዎች በፈለግህበት ደረጃ የሚገኙ አይደሉም። አቶ መለስ ግን እንዲህ አይነት ሰው ቢሆንም ከድርጅቱ ውጪ ማናቸውንም ሚና መጫወት የቻለበት ሁኔታ የለም፡፡ በእርግጥ እርሱ ድርጅቱን፣ መንግስትንና ህዝቡን አንጿል። ህዝቡ፣ መንግስትና ድርጅቱም አቶ መለስን አንፀዋል። ይሔ ተሳስሮ ነው የሚሄደው።እና አመራሩና ህዝቡ አንድ ላይ በዚህ በተፈጠረው ሁኔታ አብሮ በሚሄድበት ጊዜ የሚጎድለውን እየተካ መጓዝ አለበት።ብዙ መለሶች ወደ ፊት ይወጣሉ ብለን በዚህ አስተሳሰብ ነው መሄድ ያለብን ብዬ አምናለሁ።

ዘመን፦ እንዳው በእርሶዎ ዕይታ አቶ መለስን ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ይኖራል?

አምባሳደር ስዩም፦ እኔ ይሄንን በአንድ ቋንቋ ብገልፀው ይሻላል። አቶ መለስን መለስ ያደረገው ባለራዕይና ራዕዩን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት የሚንቀሳቀስ መሆኑ ነው።ይህን ራዕይ ደግሞ ራዕይ ብሎ የሚያየው ህዝቡን እስከጠቀመና የህዝብ ነው ብሎ እስካመነ ድረስ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጥልቅ የሆነ ህዝባዊ ፍቅር ይዞ ራዕዩን በፈለገው መንገድ ለመተግበር የሚያቅተው ሰው አለ። አቶ መለስ ብቻ ነው ጥልቅ የህዝብ ፍቅር ያለው ማለትም አይደለም፡፡ ግን ጥልቅ የህዝብ ፍቅር ኖሮት፣ የአመራር ብቃትንና የህዝብን ፍቅር መሰረት አድርጎ ህዝቡን በልማት፣ በዴሞክራሲ፣ በፍትህና በመልካም አስተዳደር መርቶ መሄድ ላይ አቅሙ የማይኖረው ብዙ ሰው ነው ያለው፡፡ ጥልቅ የህዝብ ፍቅርን መነሻ በማድረግ ግን መለስ ባለ ራዕይ ነው፡፡ ራዕዩንም ወደ ተግባር የማሸጋገርና ሌሎችንም አደራጅቶ የመምራት ብቃት ነበረው፡፡ ይሔ የመለስ ባህሪ ነው፡፡

ዘመን፦ በህይወት ዘመናቸው ይመኙትና ይፈልጉት የነበረው ምን ነበር?

አምባሳደር ስዩም፦ አስታውሳለሁ በመጀመሪያ ጊዜ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝደንት በነበረበት ወቅት አብረን ዋሽንግተንን ጐብኝተን ነበር። በዚያን ወቅት አንዲት ኢትዮጵያዊት በሚቀጥለው አስር አመት ለኢትዮጵያ ያልዎት ራዕይ ምንድን ነው? ብላ ጠየቀችው፡፡ የምመኘው በሚቀጥሉት አስር አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሦስት ጊዜ እንዲበላ ነው ብሏል፡፡ የመለስ ራዕይ ድህነትን ማሸነፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገባበት ውርደትና አንገቱን ካሰበረው ችግር እንዲላቀቅ ማድረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እፁብ ድንቅ የሚባል ባህልና ስልጣኔ ባለቤቶች ናቸው፡፡ በሃይማኖትም ተባብሮና ተቻችሎ፣ አገር ገንብቶ የኖረ ሕዝብ ነው፤ ለብዙ ትውልዶችና ዘመናት፡፡ ነገር ግን የእነዚህ እሴት ባለቤት ሆኖም ግን አንገቱን ሰብሮና ሀፍረት ተከናንቦ የድህነት፣ የጦርነት፣ የልመናና የረሀብ ተምሳሌት ሆኖ ነው የኖረው፡፡ አገር ለቆ ወይንም ለቃ ስደት ሄዶ ወይንም ሄዳ አሜሪካ የገባ ልጅ ወይንም የገባች ልጅ ያለው ቤተሰብ እንደ ትልቅ ፀጋ የሚያይበት፡፡ልጄ ተለየኝ ወይንም ተለየችኝ ብሎ ሳይሆን ልጄ አሜሪካ ገባ ወይንም ገባች የሚል፡፡የክረምት ጐርፍና ወንዝ ሞልቶ ለያይቶት ሲከርም መቼ ነው የሚያባራልኝ ብሎ ናፍቆቱን መወጣት አቅቶት የሚጨነቅ ሕዝብ፡፡ ባህር ማዶ ተለይተውት የሄዱ ልጆቹን የሀብትና የኑሮ ምንጭ አድርጎ የሚያይበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው። ህፃናት ተወልደው ምን ትፈልጋለህ ? ሲባሉ አሜሪካ መሔድ እፈልጋለሁ ነው የሚሉት፡፡ አገሬን አስከብሬ እኖራለሁ አይደለም መልሳቸው። ከእዚህ የባሰ ውርደት የለም፡፡ ስደትን እንደክብር የሚያይ ሕዝብ ነበር፡፡

መለስ ታዲያ ለዚህ ውርደት የዳረገን ድህነት ነው። የሰላም፣ የመልካም አስተዳደር፣ የዲሞክራሲ እጦት ነው። ድህነትን አሸንፈን ልማትን እውን ካደረግን የመልካም አስተዳደሩንም ሥራ ከአጠናከርንና የሕዝቡን መብት ካረጋገጥን ሕዝባችን ብድግ ይላል፡፡ ለዚህ ማብቃት አለብን ይል ነበር፡፡ የመለስ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ራዕይ ይሔ ነው።

ዘመን፦ እርስዎ ከትግሉ መስራቾች አንዱ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ያኔ ለዚህ ለአሁኑ ጊዜ እንበቃለን ብላችሁ ታስቡ ነበር?

አምባሳደር ስዩም፦ መለስ ያለው ነው፡፡ የቅብብሎሹ ታሪክ ነው።ሰው መቼ እንደሚሞት አይታወቅም፡፡ እንኳን ለዚህ እድል ልንበቃ ቀርቶ ነገን እንውላለን፣ አንውልም ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ እንጀምረውና ወጣቱ ትውልድ ይቀጥልበታል። ሕዝቡ ትግሉን የእኔ ነው ብሎ ይሂድበት፡፡ ሕዝቡን ባለቤት እናድርገው ነው ምኞታችን። ህወሀትም ኢህአዴግም ልዩ የሚያደርጋቸውና የትግል ሂደታቸውም ሆነ ራዕያቸው የነበረው የዚህ ትግል ባለቤት ህዝቡ ነው የሚለው ነው፡፡

የኢህአዴግና የደርግ ወታደር ተብሎ በሁለት ወታደሮች መካከል የሚካሄድ ጦርነት የህዝብ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነቱ የሕዝቡን መብትና ክብር የአገሪቱንም ህዳሴ እውን ለማድረግ የተካሄደ ነው እና ትግሉ የህዝቡ የራሱ ስለሆነ ህዝቡ ባለቤት ሆኖ ይህን ትግል መምራት አለበት። የሚፈለገውን መስዋዕትነትም በሁሉም መስክ መክፈል አለበት። እኛ ይህችን ለማስጨበጥ እድል ካገኘን ከዛ በኋላ ሚናችንን ተወጥተናል የሚል ነበር፡፡ እና ለዚህም ነው እነመለስ ለእኔ ፣ ለራሴ ክብር ሳይሆን ዛሬ ይህቺን ሰርቼና መስዋዕትነት ከፍዬ ልለፍ ይሉ የነበረው፡፡ የእዚህ ትግል ታሪክ ብዙ ነው፡፡ ተነግሮለት የሚያልቅ አይደለም፡፡ ገና አልተፃፈም። ጀግኖች ጠላት ምሽግ ገብተው ያፈራረሱበትና እንደ ቢራቢሮ የእሳት እራት የሆኑበት፡፡ ፈንጂውን በህይወት እየጠረጉና እየረገፉ የሕዝቡን ትግል ለድል ያበቁበት፡፡መስዕዋትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ፍጡር የታየበት ትግል ነበር፡፡ ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኮራበታል።

ዘመን፦ አምባሳደር ዛሬ ላይ ሆነው የእርስዎ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የመሰል ጓዶቻችሁ የትግልና የመከራ ጊዜ አልፎ ሲያዩት ምን ይሰማዎታል?

አምባሳደር ስዩም፦ እኛና መለስ ያየነውን፣ መለስ የፈጠረውን ሳያዩ ያለፉት የትግል ጓዶች ይታዩኛል። እኛ በጣም እድለኞች ነን እንላለን፡፡ ይህን አይተናል፡፡ መለስ ሁልጊዜ የሰጣችሁኝን አደራ ዳር ሳላደርስ አልቆምም ይል ነበር። ህይወቴ ከመሬት በላይ እስካለች ድረስ ከዚህ ድርጅት አልለይም፤ የሰጣችሁኝን አደራ ተግባራዊ አደርጋለሁ ሲል ነበር።የእርሱን ቃል፣ ራዕይና አመራር እውን ለማድረግ ሲታገሉ አልፈው ለቀበራቸውና መስዕዋትነት ለከፈሉ ብዙ ሺዎች ሲገባላቸው የነበረውን ቃል አክብሮና ፍላጐቱን አድርሶ ሔዷል። የቀረነው እንግዲህ መለስ ያላየው እኛ ያየነው አለ። የመለስና የኢህአዴግን መስመር፣ የሕዝቡንም ፍላጐትና ራዕይ አይተናል፡፡

እኔ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ ከታደሉት ውስጥ ነኝ፡፡ እንኳን አርባ አመት በዚህ ሁኔታ እቆያለሁ ቀርቶ በትግሉ ወቅት አርባ ቀንም እንኳ እኖራለሁ የሚለውን ሀሳብ አልሜውም አላውቅም፡፡ ለማንኛውም ከዚህ ሕዝብ አብራክ መውጣት ሁል ጊዜ እየኮራህበት የምትሔደው ጉዳይ ነው፡፡ የሚያስተምርህና የምትኮራበት ሕዝብ ነው፡፡ለእዚህ ሕዝብ ደግሞ ብትወድቅ የክብር ክብር ነው፡፡

ዘመን፦ እግዚአብሔር ይስጥልኝ አምባሳደር በዘመን መጽሔታችን ስም እግዚአብሔር ያፅናዎት እላለሁ፣ ሁላችንንም እግዚአብሔር ያፅናን፡፡

አምባሳደር ስዩም፦ አሜን ሁላችንንም ያፅናን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቶሎ ከዚህ ሐዘን ወጥቶና ፀንቶ የያዘውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልበት አደራ እላለሁ። እየሰጠን ያለውን ኃላፊነትና አደራም እንሸከማለን ብዬ ላረጋግጥለት እፈልጋለሁ። አመሰግናለሁ።

**********

Source: Zemen Magazine – December 2012.

Daniel Berhane

more recommended stories