የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ጉባዔ ውሎ | ጋዜጦች እንደዘገቡት

 ሰምሓል መለስ ዜናዊ፡- “አሰራሩ እኔ አልገባኝም።….ፋውንዴሽኑ የአስተሳሰብ ምንጭ ይሆናል ብለን ነው ያሰብነው።… በፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተወከለው መለስ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ሁኔታ በበቂ ደረጃ የሚወከል ስላልሆነ በጥሩ መንፈስ እንድንሄድ የመንግስት ተወካዮች ለሌሎች ግለሰቦች ቦታቸውን ቢለቁ ጥሩ ይመስለኛል”፡፡

ሚያዝያ 2-2005 የተካሄደውን የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን መሥራች ጉባዔን ሂደት ሪፖርተር እና ሰንደቅ ጋዜጦች እንደሚከተለው ዘግበውታል፡፡

*************

የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን መሥራች ጉባዔ በተደበላለቀ ስሜት ተካሄደ
(ሪፖርተር ጋዜጣ – በታምሩ ጽጌ)

– ፋውንዴሽኑ የሚገነባበት ቦታ ቢለይም ዲዛይኑ አልተጠናቀቀም
– ፋውንዴሽኑ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ስጦታ አግኝቷል
– ለቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ቤት ለመገንባት ዲዛይኑ እስከሚፀድቅ እየተጠበቀ ነው

ከሰባት ወራት በፊት በሞት የተለዩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታሰቢያ “መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን” መሥራች ጉባዔ መጋቢት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደበላለቀ ስሜት ተካሄደ፡፡

ፋውንዴሽኑ የአቶ መለስ ዜናዊ እሴቶችና መርሆዎች፣ በቀጣይነት ከትውልድ ትውልድ ይሰርፁ ዘንድና ቀጣይነት እንዲኖራቸው፣ ሐሳቦችና ፕሮግራሞች የሚፈልቁበት ህያው ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል “መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን” በሚል ስያሜ፣ በተወካዮች ምክር ቤት ጥር 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዋጅ እንዲቋቋም መደረጉ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም ፋውንዴሽኑን በአዋጅ ለማቋቋም ላለፉት ሰባት ወራት ሒደቱን የሚመራና የሚያስተባብር የሌጋሲ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጎ፣ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት፣ አዋጁ ከፀደቀ በኋላ መሥራች ጉባዔውን ለማካሄድ መቻሉን የገለጹት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የሌጋሲው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ካሣ ተክለብርሃን ናቸው፡፡

በአጭር ጊዜና ዝግጅት፣ በአገር ውስጥ ከአርሶ አደር እስከ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም ከአፍሪካ እስከ ዓለም ድረስ ላሉ የአቶ መለስ ወዳጆችና አድናቂዎች፣ የተደረገላቸውን ጥሪ አክብረው በፋውንዴሽኑ መሥራች ጉባዔ ላይ በመገኘታቸው ምሥጋናቸውን የገለጹት አቶ ካሣ፣ አቶ መለስ በሥራቸው በአኅጉር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታወሱ እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡ በእሳቸው የሕይወት ዘመን በአመራር ቦታ ላይ ለመድረስ የቻሉ ሰዎች ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር እሳቸው በዘፈቀደ የደረሱበት ሳይሆን፣ በጥልቅ ጥናትና በማይቆም ከፍተኛ ምርምርና በየዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን ወደ ተግባር በመመንዘር መሆኑን የገለጹት፣ በፋውንዴሽኑ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲሆኑ፣ “የመለስን ራዕይ ጠንቅቆ መረዳት አሁን ላለነው የኢሕአዴግ አመራሮች ዝም ብሎ የተሰጠን ውርስ እንዳልሆነ ላሳስብ እፈልጋለሁ፤” ብለዋል፡፡

አቶ መለስ የንድፈ ሐሳብ ቀማሪና ቀያሽ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሐሳቦችን በድርጅታቸው በተግባር ማዋል የቻሉ የምጡቅ ሐሳብ ባለቤት መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ከትጥቅ ዘመን አንስቶ በፓርቲውና በመንግሥት ውስጥ ያከናወኗቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው አኩሪ ተግባራት መሆናቸውንና አስተምህሮዎቻቸውን ዘርዝሮ ማስቀመጥ አስቸጋሪ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ከለጋ ዕድሜ አንስቶ ሕይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ ምንም ዕረፍት የማያውቁት አቶ መለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ በሚችሉበት ዘመናቸው ላይ ሕይወታቸው ማለፉ አይደለም ኢትዮጵያውያንንም ሆነ የዓለምን ሕዝብ ያሳዘነ በማለት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በርካታ አኩሪ ተግባራትን መፈጸማቸውን፣ ታግለው ማታገላቸውን፣ መምራታቸውን፣ አገርና ሕዝብን ከዴሞክራሲ ዕጦትና ድህነት የሚወጡበትን መንገድ ቀይሰው ያለፉ መሪ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

አቶ መለስ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም የቆሙ በመሆናቸው፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን አምርረው የታገሉና በድርጅትም ሆነ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘታቸውም በላይ በዕውቀት፣ በጥበብና ፍፁም በሆነ ዴሞክራሲያዊነት በመመሥረት በሰጡት አመራር እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርከተው ያለፉ መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተዝቆ የማያልቀውን ዕምቅ ዕውቀት ለቀጣይ ታሪክ ምርምር ለማዋል ፋውንዴሽኑን መመሥረት አስፈላጊ በመሆኑ ተግባራዊ መደረጉንም አቶ ኃይለ ማርያም አክለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመክፈቻ ንግግራቸውን አድርገው ሲያበቁ፣ በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የተዘጋጀ የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሕይወት ዘመን ትውስታ ከሕፃንነት እስከ ግባተ መሬት ድረስ የነበረውን ዘጋቢ ፊልም ሲታይ በታዳሚዎች ላይ የተደበላለቀ ስሜት ሲፈጠር ተስተውሏል፡፡ በተለይ በዘጋቢ ፊልሙ የአቶ መለስ አስከሬን ከቤልጂየም ብራሰልስ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስና ቤተሰቦቻቸው ከአውሮፕላኑ ሲወርዱ፣ አስከሬኑ ከቦሌ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ቤተ መንግሥት ሲጓዝ፣ የቀብራቸው ዕለት በመስቀል አደባባይ አስከሬናቸውን የያዘው ሳጥን ሲቀመጥና ከፍተኛ ዝናብ እየጣለ አስከሬኑ በሰረገላ ሆኖ ወደ ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሲያመራ የሚያሳየውን ፊልም የተመለከቱ በአፍሪካ ኅብረት የታደሙ ሰዎች፣ ከንፈራቸውን ከመምጠጥ እስከ እንባ ማፍሰስ ድረስ በሐዘን ስሜት ውስጥ ገብተው ተስተውሏል፡፡ ሌላው አዳራሹን ለተወሰኑ ደቂቃዎች የሐዘን ድባብ ውስጥ የከተተ ክስተትም ተፈጥሮ ነበር፡፡ ዘጋቢ ፊልሙን ከሚመለከቱ ታዳሚዎች መካከል የነበሩት የአቶ መለስ እህቶች ድምፅ አውጥተው ለቅሶ በመጀመራቸው፣ ከሰባት ወራት በፊት የነበረውን የሐዘን ሁኔታ ያስታወሰና የሁሉንም ታዳሚዎች ቀልብ የሳበ ሆኖ ነበር፡፡

ታዳሚዎች ድንገት በተቀሰቀሰው የሐዘን ድባብ ውስጥ ባሉበት ሁኔታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ የጂቡቲው ፕሬዚዳንት፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት፣ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የናይጄሪያ የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጌታቸው በትሩ፣ እ.ኤ.አ. ከ1992 እስከ 1998 በኢትዮጵያ የነበሩት የዓለም ባንክ ዳይሬክተርና ሌሎች የተለያዩ አገሮች ተወካዮች፣ ስለ አቶ መለስ የሰላም አባትነት፣ የልማት ጀግናነት፣ አስተዋይነት፣ ብልህነት፣ አርቆ አሳቢነትና ስለማይተካው የአፍሪካና ዓለም አቀፍ መሪነታቸው በየተራ ንግግር አድርገዋል፡፡ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ስለ አቶ መለስ ንግግር ያደረጉት ዘግይተው ጉባዔውን የተቀላቀሉት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ ለፋውንዴሽኑ 300 ሺሕ ዶላር መለገሳቸውን አስታውቀዋል፡፡ እሳቸውን ተከትለው የጂቡቲው 500 ሺሕ ዶላር፣ የደቡብ ሱዳን አንድ ሚሊዮን ዶላር፣ የሱዳን ሁለት ሚሊዮን ዶላር ለግሰዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ በድምሩ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘቱም ታውቋል፡፡

የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን አልፋና ኦሜጋ ዕውቀትን፣ ሕዝባዊ ታማኝነትንና ፅናትን፣ በሌሎች ሳይሆን በራስ አቅምና እጅ የተወለደ የዴሞክራሲና የልማት ሥርዓትን ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ አለመሆን የተናገሩ የአቶ መለስ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ሲሆኑ፣ የመለስ ፋውንዴሽን መገለጫ ግዑዝ ከሆነው ድንጋይና እምነበረድ ድርድር በላይ አስተሳሰቡና ራዕዩ ትውልድ ተሻጋሪ ኃያልነትን እንዲጎናጸፍ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ የመለስን ፅኑ እምነትን የሚያንፀባርቅ፣ ኢትዮጵያን ከድህነት በማውጣት ሁሉም የሚኮራበትና ኢትዮጵያን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ቋሚ ሐሳብና ፕሮግራም ማፍለቂያ ማዕከል እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

ነፍስ ካላወቁ ሕፃናት በስተቀር መላው ኢትዮጵያውያን በአንድ እግር፣ በአንድ ግብ፣ በአንድ ዓይን ያለ እስከሚመስሉ ድረስ፣ በአንድ ላይ እምባቸውን ለመሪያቸው ፍቅር ያሳዩበትን ዕለት ተመልሰው እንዲያስታውሱ የጉባዔውን ታዳሚ የጠየቁት ወይዘሮ አዜብ፣ “የመለስ ሞት ከተነገረበት ዕለት አንስቶ እስከ ግባተ መሬቱ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየው የማይነጥፍ ልዩ ድጋፍና ፍቅር ልቤን ነክቶታል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለን ክብርና ምሥጋና ከቃላት በላይ ነው፡፡ ምንም ማለት አልችልም፡፡ ማለት የምችለው ምሥጋናችን ይድረሳችሁ ብቻ ነው፤” ብለዋል፡፡ ከሞትና ከተፈጥሮ የተሟገተ፣ የሕዝብ ቃላት አልበቃ ያሉት የሐዘን ቀን፣ ከመለስ ራዕይ የተጠቀሙም፣ ያልተጠቀሙም፣ ከጎጆ ቤት እስከ ቤተ መንግሥት፣ ከማጀት እስከ አደባባይ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን የምሽት ጭፈራ ቤቶች ሳይቀሩ የሁሉንም ጓዳ ያንኳኳ የሐዘን ጊዜ እንደነበር ያስተወሱት ወይዘሮ አዜብ፣ ለሁሉም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ለሙሉ ቀን የዋለው የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን መሥራች ጉባዔ ከሰዓት በኋላ በነበረው ውሎው በአቶ አዲሱ ለገሰ የሌጋሲ ኮሚቴ ሪፖርትን በማቅረብ የተጀመረ ሲሆን፣ አቶ አዲሱ ባቀረቡት ባለ 19 ገጽ ሪፖርት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ አዲሱ ማብራሪያ አቶ መለስ በድንገትና ባልታሰበ ሁኔታ በመሞታቸው፣ ቤተሰቦቻቸው ለ21 ዓመታት ይኖሩበት ከነበረው ቤተ መንግሥት፣ በፍጥነት ለመልቀቅ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ቤት ማፈላለጉ ጊዜ በመውሰዱ ነው፡፡ ሆኖም የተገኘው ቤት እንዲታደስ ተደርጎ በጊዜያዊነት እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ለአቶ መለስ ቤተሰቦች ቋሚ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ቦታ መገኘቱን፣ ሥራውን የሚመራ መመደቡንና ግንባታ ለመጀመር የቤቱን የመጨረሻ ዲዛይን እየተጠባበቁ መሆኑን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡ ሌላው አቶ አዲሱ በሪፖርቱ የገለጹት፣ የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን የሚገነባበት ሥፍራ ሰፋ ያለና ብዙ ነዋሪዎችን በማያፈናቅል ሁኔታ ሆኖ አመቺ ቦታ መመረጡን ነው፡፡ በፈቃደኝነት ዲዛይን ያቀረቡና ሌሎች ዲዛይኖችም ቀርበው በመታየት ላይ መሆናቸውንና የትኛው እንደተመረጠ ገና አለመወሰኑን አስረድተዋል፡፡

በጉባዔው ማጠናቀቂያና የጉባዔው የመጨረሻ መርሐ ግብር የነበረው የፋውንዴሽኑን ቦርድ መሰየም ነበረ፡፡ በመሆኑም ከመከላከያ ሚኒስቴር ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር አቶ ሱፍያን አህመድ፣ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅት አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ አቶ ሙክታር ከድር (በኋላ በወይዘሮ አስቴር ማሞ ተተክተዋል) አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ ካሣ ተክለብርሃን፣ አቶ አብዱ አህመድ፣ አቶ አህመድ ናስርና አራት ሰዎች ደግሞ ከአቶ መለስ ቤተሰቦች በዕጩነት ቀርበዋል፡፡ የቀረቡት ዕጩዎች ሁሉም የፓርቲ አባላት ብቻ መሆናቸውን በመቃወም ከንግዱ፣ ከኪነ ጥበብና ከሌሎቹም የኅብረተሰቡ ክፍሎች መካተት እንዳለባቸው የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በተለይ የመከላከያ ውክልናን በሚመለከት “ለምን?” የሚል ጥያቄ ከመቅረቡም በተጨማሪ፣ ሁሉም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውክልና ቀርቶ ሲቪል ማኅበረሰቡ እንዲካተት የአቶ መለስ ቤተሰቦች ጭምር ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡

የተነሱት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተገቢ ቢሆኑም ቦርዱ መቋቋም ያለበት በአዋጁ መሠረት በመሆኑና ከአዋጁ ውጪ ምንም ማድረግ ስለማይቻል፣ የሚሰየመው ቦርድ በቀጣይ አዋጁ የሚስተካከልበትንና የቦርድ አባላት በስፋት የሚካተቱበት ሁኔታ እንደሚኖር በመግለጽ የቀረበው ጥቆማ እንዲፀድቅ አቶ አዲሱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የጉባዔው ታዳሚዎች ያነሱትን ጥያቄና አስተያየት ተከትሎ፣ አቶ ካሣ ተክለብርሃን በራሳቸው ላይ ተቃውሞ በማቅረብ በእሳቸው ምትክ ሌላ ሰው እንዲተካ ቢጠይቁም ድጋፍ በማጣታቸው ተቀባይነት አላገኙም፡፡ በመሆኑም አቶ አዲሱ የሰጡትን አስተያየት አቶ በረከት ስምኦንና ወይዘሮ አዜብ በመደገፋቸው የቀረበው አስተያየት ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በመጨረሻም ወይዘሮ አዜብ መስፍን የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ አቶ ካሣ ተክለብርሃን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

*****************

የመለስ ፋውንዴሽን ምሥረታ አወዛጋቢ መልኮች
(ሰንደቅ ጋዜጣ)

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም ፋውንዴሽን ተቋቁሟል። ፋውንዴሽኑ የተቋቋመው ባለፈው ጥር ወር በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በወጣ አዋጅ ቁጥር 781/ 2005 ዓ.ም መሠረት ባለፈው ቅዳሜ (መጋቢት 28 ቀን 2005 ዓ.ም) በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል።

በዕለቱ ከ70 ያላነሱ በድምፅ የሚሳተፉ የፋውንዴሽኑ ጉባኤተኞችን ጨምሮ የሱዳን፣ የጅቡቲ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሩዋንዳና የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናትና ሌሎች ልዩ ልዩ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚሁ የመለስ ፋውንዴሽን ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን እና ሌሎች የአቶ መለስ ወዳጆችም ሰፊ ንግግር አድርገዋል።

በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የተሰራውና ትኩረቱን በአቶ መለስ የስኬት ትርክቶች ላይ ያደረገው ዘጋቢ ፊልምም ታዳሚውን በድጋሚ ወደ ሐዘን ከመክተቱም በላይ አንዳንዶች ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው በአዳራሹ ውስጥ ሲያለቅሱ ታይተዋል።

በዕለቱ በከሰዓቱ ፕሮግራም ላይ የፋውንዴሽኑን የሚመሩ የቦርድ አመራር አባላትንና ቦርዱን የሚመሩ ፕሬዝዳንቶች ምርጫም ተካሂዷል። ፋውንዴሽኑን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሠረት የፋውንዴሽኑ የቦርድ አባላት የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር 13 ሲሆን ከነዚሁ ውስጥ አራቱ ከቤተሰብ የሚመለመሉ ናቸው።

በእለቱም ድርጅታዊ በመሰለው “ምርጫ” ከመከላከያ ሚኒስቴር ጀነራል ሳሞራ የኑስ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር አቶ ሶፊያን አህመድ፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ከፌዴሬሽን ም/ቤት አቶ ካሳ ተ/ብርሃን እንዲሁም ከአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ከደኢህዴን አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ከኦህዴድ በመጀመሪያ አቶ ሙክታር ከድር የነበሩ ሲሆን፤ በኋላ እራሳቸውን በወ/ሮ አስቴር ማሞ ተክተዋል፣ ከህወሓት አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ ከሶማሌ ክልል አቶ አብዱ ዑመር መሐመድ እንዲሁም ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልል አቶ አህመድ ናስር ተመርጠዋል። በዕለቱ ከአቶ መለስ ቤተሰቦች በአዋጁ መሠረት አራት ሰዎች እንደሚወከሉ ቢገልፅ በመድረኩ ላይ ተወካዮቹ (ከወ/ሮ አዜብ መስፍን በስተቀር) እነማን እንደሆኑ የተገለፀ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ አዋጁን ያልተገነዘቡ ሰዎች በፋውንዴሽኑ ውስጥ አስገቡን ሲሉ ጥያቄ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። ከግለሰቦቹ ባለፈ በአምባሳደር መሐመድ ድሪር አማካኝነት የኋላቀር ክልሎች ተወካዮች በፋውንዴሽኑ እንዲወከሉ ጠይቀዋል። በተጨማሪም በአርቲስት ደበሽ ተመስገን በኩልም አርቲስቶች በፋውንዴሽኑ ካልገቡ ብሏል። በተያያዘ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህብረት ፕሬዝዳንት ነኝ ያለ ወጣትም በፋውንዴሽኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች እንዲወከሉ የሚሉ የአሳትፉን ጥያቄ በአዳራሹ ሲዥጎደጎድ ተስተውሏል።

“የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሌጋሴ ኮሚቴ” ሰብሳቢ አቶ አዲሱ ለገሰ አዋጁ የሚፈቅደው 13 ሰዎች በመሆኑ ለጊዜው አዋጁን ማስተካከል ስለማይቻል ወደፊት ሊታይ እንደሚችል ነው የገለፁት።

ፋውንዴሽኑን የሚመሩ የቦርድ አባላት ከተመረጡ በኋላ አንዳንድ አወዛጋቢ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። ጥያቄ ካነሱት መካከል ሌፍተናንት ጄኔራል ሳአረ መኮንን “የጄነራል ሳሞራን የቦርድ አባል መሆን በምን አያችሁት?” ሲሉ ነበር የጠየቁት። መድረኩን ሲመሩ የነበሩት የትግራይ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳደር “ከመከላከያ ሚኒስትር አንድ ሰው መኖር አለበት በሚል መነሻ የቀረበ ነው” ሲሉ ከመለሱ በኋላ የተለየ ኀሳብ ካለ እንዲያቀርቡ ቢጋብዙም ጄኔራሉ ኀሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ወዲያውኑ ሌላ ያልተጠበቀ አስተያየት የተሰነዘረው በፌዴሬሽን ም/ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተ/ብርሃን በኩል ነበር። አፈ ጉባኤ ካሳ “የተባለው ኀሳብ ሁሉ ጥሩ ነው። ነገር ግን በእኔ ቦታ ሌላ ሰው ቢወከል ብዬ በራሴ ላይ ተቃውሞ ለማቅረብ ነበር” ሲሉ ከፋውንዴሽኑ የቦርድ አባልነት መውጣት እንደሚፈልጉ ገለፁ። እንደሚታወሰው አፈ ጉባኤ ካሳ የአቶ መለስ ህልፈተ-ሕይወት እንደተሰማ ብሔራዊ የቀብር ኮሚቴ በመምራትና በማስተባበር እንዲሁም “የመለስ ሌጋሴ ኮሚቴ” ውስጥ በአባልነት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው አይዘነጋም። ነገር ግን መነሻው ለጊዜው ባልታወቀ ሁኔታ ከፋውንዴሽኑ የቦርድ አባልነት እራሳቸውን ማግለል መፈለጋቸው የአዳራሹን ታዳሚ እንዲያልጎመጉም አድርገውታል።

ይሁን እንጂ አቶ አዲሱ የአፈጉባኤውን ኀሳብ ካዳመጡ በኋላ ስራው በየዕለቱ የሚሰራ ባለመሆኑና በቦርድ ደረጃ ውሳኔ ለመስጠት ብቻ ስለሆነ እንዲቀጥሉ አሳሰቡ። አቶ አባይም አቶ አዲሱ ለገሰ በሰጡት ኀሳብ ላይ በድርጅት እንደሚደረገው ድምፅ ይሰጥበት አሉ። በፋውንዴሽኑ በድምፅ የሚሳተፉ አባላት የአቶ አዲሱን ኅሳብ በመደገፍ አፈጉባኤ ካሳ በቦርዱ እንዲቀጥሉ አስገድደዋል።

ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ ያልተጠበቀ ነገር የተሰማው ከአቶ መለስ የበኩር ልጅ ሰማሀል መለስ የተነሳው ጥያቄና አስተያየት ነበር። ሰማሀል በአስተያየቷ ቀደም ሲል በጀነራል ሳሞራ የኑስ የፋውንዴሽኑ የቦርድ አባልነት ለምን ተካተቱ የሚለውን መነሻ በማድረግ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥታለች።

“አሰራሩ እኔ አልገባኝም። ከዚህ በፊትም ችግሩን ቤተሰብ አንስቶ ነበር። በወጣው አዋጅ ላይ ጥያቄ አንስቶ ነበር። በአዋጁ ላይ የመንግስት ሚና ማጉላቱ ስህተት ነው ብለናል። ፋውንዴሽኑ የአስተሳሰብ ምንጭ ይሆናል ብለን ነው ያሰብነው። ለዚህ ደግሞ ፋውንዴሽኑ ከመንግስት ያለውን ነፃነት ይቀንሳል ብዬ እገምታለሁ። ስለዚህ የመከላከያ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ መንግስት ፋውንዴሽኑ ላይ ያለው ሚና ትክክል አይደለም ባይ ነኝ። በፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተወከለው መለስ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ሁኔታ በበቂ ደረጃ የሚወከል ስላልሆነ በጥሩ መንፈስ እንድንሄድ የመንግስት ተወካዮች ለሌሎች ግለሰቦች ቦታቸውን ቢለቁ ጥሩ ይመስለኛል” በማለት በፋውንዴሽኑ ላይ የመንግስት ሚና እንዲቀርብ ግልፅ የተቃውሞ ጥያቄ አቅርባለች።

ከሰማሀል ጥያቄ በኋላ አዳራሹ እንደገና በሌላ ስሜት የተሞላ መሰለ። የመድረኩ መሪ አቶ አባይ ወልዱ በልጅቷ ኀሳብ ላይ ሌላ ኀሳብ እንዲሰጥ ጠየቁ። አንድ ተሳታፊ በአዋጁ መሠረት የቦርድ አባላት ቁጥር በጠባቡ የተወሰነ በመሆኑ ቦርድ ለወደፊቱ አንቀፅ የሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲያመቻች ሲሉ ኀሳብ አቀረቡ።

በመቀጠል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን በበኩላቸው፤ በፋውንዴሽኑ ዙሪያ በድምፅ የሚሳተፉም ሆነ በማይሳተፉ አካላት የተነሳው አስተያየት ጠቃሚ መሆኑን ካስረዱ በኋላ፤ አዋጁ ሲወጣ በጉባኤ ላይ የሚጨመሩ አካላት እንዳሉ በግልፅ ስለሚጠቁም የመስራች ጉባኤው ተጨማሪ አባላትን ወደፊት መመልመል እንደሚቻል አስረዱ።

ወ/ሮ አዜብ መስፍን በበኩላቸው፤ ፋውንዴሽኑ የመጀመሪያ ጉባኤ በመሆኑ ገና ሕፃን ስለሆነ ብዙ ክፍተቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ ታሳቢ መደረጉን፣ ነገር ግን በሂደት ወደስራ ሲገባ ክፍተቶቹ እየተስተካከሉ ይሄዳሉ የሚል ኀሳብ አንስተዋል።

“ከአዋጁ አንፃር ስንነሳ አዋጁ በፓርላማ የፀደቀ ነው። አሳማኝና ብቃት ያለው ምክንያት እስከተገኘ ፓርላማውን የማሻሻል ስልጣን አለው” ካሉ በኋላ “አዋጁን አክብረን እንውጣ” ብለዋል። አያይዘውም “ለወደፊቱ በፋውንዴሽኑ መሳተፍ የሚፈልጉ ኃይሎች በተደራጀ ሁኔታ እንዲሳተፉ ይደረጋል” ብለዋል።

ወ/ሮ አዜብን ጨምሮ ሁሉም የመንግስት ባለስልጣናት በመለስ ፋውንዴሽን ውስጥ የመንግስት ሚና መቅረት አለበት ያለችውን የሰማሀል ኀሳብ ሳይቀበሉት ቀርተዋል። በአንፃሩ ወ/ሮ አዜብ በፋውንዴሽኑ ውስጥ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር እና ክልሎች የተሳተፉት ትርጉም ስላለው ነው በሚል ትርጉሙ ምን እንደሆነ ሳይገልፁ አልፈውታል።

በመጨረሻ የፋውንዴሽኑን ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ምርጫ ተከናውኖ ወ/ሮ አዜብ የፋውንዴሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ ከቦርድ አባል አስወጡኝ ብለው የነበሩት አፈ ጉባኤ ካሳ ተ/ብርሃን ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። ወ/ሮ አዜብ የፋውንዴሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ “መለስ እንደተሰዋ ሁሉ እኛም እስከምንሰዋ ድረስ ለመስራት ቃል እንገባለን” ሲሉ ተናግረዋል።

በዕለቱ ማምሻውን በሸራተን ሆቴል በተከናወነ የእራት ግብዣ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮምያ ክልሎች እያንዳንዳቸው ለፋውንዴሽኑ ማቋቋሚያ 10 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። የሶማሌ ክልል 8 ሚሊዮን፣ የአፋር ክልል 5 ሚሊዮን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር 11 ሚሊዮን ለግሰዋል። ጥረት ኢንዶውመንት አንድ ሚሊዮን፣ የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ማኅበር 5መቶ ሺህ ብር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ሲሆን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 4 ሚሊዮን፣ የጋምቤላ ክልል 4 ሚሊዮን፣ ሜድሮክ ኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን፣ የሐረሪ ክልል 5 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የሩዋንዳ፣ የሱዳን፣ የጅቡቲ፣ የኡጋንዳ፣ የደቡብ ሱዳን አገራት በጠቅላላው ወደ 4 ሚሊዮን ዶላር ገደማ (80 ሚሊዮን ብር አካባቢ ለግሰዋል)።

***************

ማስታወሻ፡- እኔ እንደገባኝ የሰምሓል መለስ ዜናዊ ጥያቄ፤ መንግስት በፋውንዴሽኑ ምንም ሚና አይኑረው የሚል ሳይሆን፤ የተቋሙን የሀሳብ አመንጪ የመሆን ዕድል በሚያጣብብ ደረጃ በመንግስት ሀላፊዎች እንዳይሞላ፤ ይልቁንም ሌሎች አፍሪካዊና ዓለምአቀፋዊ ባለሙያዎች/ተቋማት ይካተቱ የሚል ነው፡፡ ይህም አግባብነት ያለው ጥያቄ እና – በፋውንዴሽኑ ሥር በሚቋቋም ቲንክ ታንክ (think thank) ካልተካካሰ በቀር – የፋውንዴሽኑን ዓዋጅ ማሻሻል ግድ የሚል ነው፡፡ (ዳንኤል ብርሀነ)

Daniel Berhane

more recommended stories