‘ለመዝናናት እንዳልተፈጠረ መለስ ያውቃል’ – በረከት ስምዖን

(ስመኝ ግዛው)

«ሁሌም ስለመለስ ሳስብ የተለየ ነገር መስሎ የሚሰማኝ ተማሪነቱ ነው» የሚሉት ከነባር ታጋዮች አንዱ የሆኑትና በኋላም ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር በቅርበት ሲሠሩ የቆዩት የመንግሥት ኮሙኒኬሸን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን ናቸው። ዘመን መጽሔት ላቀረበችላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ ስለ አቶ መለስ ዜናዊ በርካታ ቁምነገሮችን አካፍለዋል።Minister Bereket Simon speaking about PM Meles Zenawi

ዘመን፡- በቅድሚያ ክቡር አቶ በረከት በጠቅላይ ሚኒስትራችን ህልፈት በደረሰብዎ ኀዘን መፅናናትን እመኝልዎታለሁ።

አቶ በረከት፡- አመሰግናለሁ።

ዘመን፡- በቅድሚያ በአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ምን ተሰማዎ?

አቶ በረከት፡- ያደረብኝ ስሜት በጣም መጐዳት ነው-ጉዳት ነው። አቶ መለስን በቅርብ አውቀዋለሁ። ከኢህአፓ ወጥተን ወደ ትግራይ ከሄድንበት ጊዜ ጀምሮ ነው የማውቀው። መጀመሪያ ላይ ያው አዲሶች እንደመሆናችን መጠን እኛም ወደ ወሎ ተጉዘን በፍጥነት በመግባታችን በጣም በቅርበት አውቀው ነበር ልል የምችልበት ጊዜ አልነበረም። ግን ወደ ትግራይ ስንሄድ በየሦስት ወሩ፣ በየስድስት ወሩ ስንገናኝ፤ በብአዴንና ህወሓት አመራሮች መካከል የጋራ ስብሰባ ሲኖር እንገናኝ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም ስልጠና የምንሳተፍባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። እዚያም ስልጠና ላይ ስንሄድ የምናያቸው ነገሮች ነበሩ።

በኋላ ደግሞ ከ1970ዎቹ አጋማሽ በተለይ ደግሞ ከመጨረሻዎቹ ጀምሮ የአቶ መለስን ልዩ ልዩ ጽሑፎች ለማግኘት በመቻላችን ጭምር ይበልጥ እያወቅነው መጣን፡፡ በተለይ ከ77 በኋላ የረጅም ጊዜ የጥናት ውጤቶቹን እያደራጀ በጽሑፍ መልክ ለሁላችንም እንዲደርስ በማድረጉ የአቶ መለስን አስተሳሰብና ፍልስፍና በቅርብ ለመገንዘብ ዕድል አግኝተናል፡፡ ከዚያ ከደርግ ውድቀት በኋላ ደግሞ እዚህ አዲስ አበባ በቅርብ እየተመካከርን ሠርተናል።

እና አቶ መለስ በጣም የተለየ ሰው ነው። በዚህ ምክንያት መሰዋቱን ስሰማ በጣም በጣም ከባድ ጉዳት ነው የተሰማኝ። ነገር ግን ይህ ትግል እንደሆነ የምገነዘብ በመሆኔና የተሻለ ድርጅታዊና መንግሥታዊ ጥንካሬ ላይ በደረስንበት ወቅት ያጋጠመ ጉዳት በመሆኑ እንዲሁም ትቶልን ያለፈው ነገር በጣም መሠረታዊ ትጥቅ በመሆኑ ደግሞ ተፅናንቻለሁ፡፡

ዘመን፡- አቶ መለስ ብዙ ራዕይና ዓላማ የነበራቸው ሰው ናቸው። እንዲህ ባልታሰበ ወቅት በዚህ ሁኔታ ይለዩናል ብለው አስበው ያውቃሉ?

አቶ በረከት፡- ያው ስለማንኛውም ሰው የዕድሜ ቆይታ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። አቶ መለስ ታጋይ ነው። ሁላችንም የምንለው ነገር አለ፤ እኛ በትግል ላይ ያለፍን ሰዎች ትርፍ ሕይወት ነው የምንኖረው እንላለን። ምክንያቱም ከእኛ ጋር የተሰለፉ ታጋዮችም አመራሮችም በተለያየ ደረጃ መስዋዕትነት ከፍለው ቀደም ብለው አልፈዋል።

አቶ መለስም ሌሎች የትግል ጓዶቹም በአጋጣሚ ነው የተረፉት እንጂ በታሰበበት አኳኋን አልተረፉም። በአጋጣሚ የተረፈ ሰው ሁልጊዜ ትርፍ ሕይወት ነው የምኖረው እኔም እንደሌሎች ጓዶቼ ሊደርሰኝ ይችል ነበር ብሎ ያምናል። ስለዚህ አቶ መለስ ከመስዋዕት እንደሚያመልጥ አድርጐ ራሱን ቆጥሮ አያውቁም። ማንም ሰው እንደሚገነዘበውም አንድ ቀን አይቀርልንም የሚል ነገር ነበረው፡፡

ዋናው ነገር ግን መቼም ይሁን መቼ ከማይቀረው ሞት በፊት እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ለአገርና ለሕዝብ ጥሩ ሠርቶ መሞት ይገባል ብሎ ያለእረፍት የሠራ ሰው መሆኑ ነው ትልቅ የሚያደርገው ፤ የተለየ የሚያደርገው በእኔ ግምት ያ ነው። እንጂ በአጭር መቅረትንም ሆነ ረጅም ጊዜ ለመኖር መታደልን ሁላችንም በእጃችን ያለ ነገር አድርገን አንወስደውም። እርሱም በእጁ ያለ ነገር አድርጐ አይወስደውም ነበር። በእጁ ያለውን ነገር በተመለከተ «በሕይወት እስካለሁ ጊዜ ድረስ መስራት አለብኝ፤ ያ ነው በእኔ እጅ ያለው» ብሎ የሚያምንና ይህንን በተግባር የተረጐመ ሰው መሆኑ ነው፡፡

ዘመን፡- ከአቶ መለስ ጋር ተያይዞ ከትግሉ ጀምሮ አብራችሁ እንደመሥራታችሁ ምን ያስታውሳሉ?

አቶ በረከት፡- ብዙ ነገር ማስታወስ ይቻላል። ከአቶ መለስ ጋር በኖርንባቸው፣ አብረን በታገልንባቸው ጊዜዎች፣ በሁሉም መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የነበረውን አስተሳሰብ የነበረውን ተግባር፣ የሚያሳየውን ሥነ ምግባር፣ ሥራውን፣ ስለ ኅብረተሰብ፣ ስለ ቤተሰብ፣ ስለ ዓለም፣ ስለ አገር ያለውን አመለካከት እያነሱ ብዙ ነገር ማስታወስ ይቻላል። ባይሆን የቱን ከየቱ አንስቶ ማማረጡ ነው የሚከብደው።

ለእኔ ግን በጣም በጣም የተለየ ነገር መስሎ የሚሰማኝ የአቶ መለስ ተማሪነት ነው። ሁሌ የሚያስገርመኝ-ሁሌ፤ ሁሌ። በ1993 እና 94 ዓ.ም ቀውስ ውስጥ በገባንበት ጊዜ በድርጅት የመጀመሪያውን 10 ዓመታት እንዴት እንዳሳለፍን ዝም ብለን ቁጭ ብለን እናወራ ነበር። እና ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣና እርሱ የአገር መሪ ሆኖ ሲመደብ የመጀመሪያ ሥራ አድርጐ የወሰደውን ያጫውተን ነበር ። «ይሄን ሕዝብና ይሄን አገር ሳላውቅ ልመራው አልችልም» ብሎ ለራሱ ቃል የገባ ሰው ነበር። ይሄ ለህዝቡ ያለውን አክብሮትና የነበረውን የኃላፊነት መንፈስ ያሳያል።

ስለዚህ የመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት የቅርብ ጓዶቹ እንደምናውቀው ጥልቀት ያላቸውን የምርምር ሥራዎችን ሥራ ላይ ሆኖ ሲሠራ ነበር ያሳለፈው ፣ በጣም ጥልቀት ያላቸው! ጥናት ላይ፣ ንባብ ላይ። በነገራችን ይህ የጥናትና የምርምር ሥራ አዲስ አበባ ከገባን የተጀመረ አይደለም፡፡ ከበረሃ ጀምሮ ያካሄደውና በጣም ጥልቅና ዘመን ተሻጋሪ የሚባሉ ሥራዎችን ያመረተበትም ነው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ እኔ በየጊዜው ስሄድ ቤተመጻሕፍቱን አየው ነበር፤ ቢሮው ውስጥ ያለውን ቤተመጻሕፍት። በየጊዜው እየሞላ እየሞላ ይሄዳል። እየሠራ ያነብባል፣ እያነበበ ይሠራል። እና ደከመኝ አይልም። ራሱን ለማሳደግ፣ ለማስተማር ደከመኝ አይልም፤ እንዲህ ዓይነት ሰው ነበር። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በጥልቀት በተጠኑና በምርምር ላይ በተመሠረቱ ፖሊሲዎች እየተመራች ነው የምንለው።

ይሄ የመጀመሪያው ጉዳይ ነው። ሌላው የአቶ መለስ ልዩ ባህሪ ሆኖ የሚታየኝ የሚቆጥበው ነገር ያልነበረ መሆኑ ነው ። የሚቆጥበው ጉልበት የለም፣ የሚቆጥበው እውቀት የለም፤ «እውቀትን ማካፈል ብርሃንን የማካፈል ያህል በጐ ነገር ነው» ብሎ የሚያምን ሰው ነበር። እና ለማንም የተገለጠ መጽሐፍ ነው የነበረው ። የውጭ ሰዎች መጥተው ያገኙታል፤ ትምህርትና ዕውቀት ገብይተው ይሄዳሉ። እኛም እንሄዳለን። ቢሮው ጥያቄና ምክር ፈልገን፤ ስንሄድ ይዘን ከሄድነው በተጨማሪ ባልጠየቅነው ጉዳይ ተምረን እንመጣለን። እና አቶ መለስ እውቀቱንና ጉልበቱን ማካፈል የማይሰለች ታላቅ ሰው ነበር። መሠረታዊና ጥቃቅን ነገሮችን ለያይቶ የሚያይም ሰው ነበር። ሁሌም ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ማተኮር የሚፈልግ መሪ ነው የነበረው ። አልባሌ ነገር፣ ጊዜን የሚያባክን፣ ጊዜን አለ አግባብ የሚገድል ነገር ላይ ጊዜውን የማያሳልፍ ሰው ነው የነበረው።

ስለዚህ መሪ ብዙ ማለት ይቻላል። በሕይወቱ ስለራሱ ጥቂትም ብዙም አልተናገረም ፤ እኛም ስለእርሱ ብዙ አልተናገርንም። ከአሁን በኋላ የምናውቀውን ያህል እንናገራለን ብለን እናምናለን። በቅርብ የምናውቀው ሰዎች አቶ መለስን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከመብትና ጥቅማቸው በመነሳት በምርጥ ቋንቋና ማሳያ ከሚገልጹበት ደረጃ ጋር ባይመጣጠንም በምናውቀውና በምንችለው ልክ ልንናገር እንሞክራለን። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አቶ መለስን በጣም በጣም በሚያኮራ ደረጃ ሲገልፁት ሰምተናል። ከእኛ በላይ የሚያውቀው ሕዝብ እንዳለ እየገባን አንዳንዴ እኛ በምንገልጸው እናፍራለን፡፡ የአቶ መለስን ማንነት በተመለከተ ምስክርነቱን ከሰጡት ከኢትዮጵያ ሕዝቦች እኛም በፋንታችን ከሕዝቡ እየተማርን ነው፡፡ ለካ እኛ ብቻ አይደለንም የምናውቀው እንላለን። እናም ወደፊት ሁላችንም የምናውቀውን ያህል እንናገራለን ብለን እናምናለን። ይሄን ጉዳይ ወደፊትም በተለያዩ አጋጣሚዎች በዝርዝር የምንመለስበት ነው የሚሆነው።

ዘመን፡- አንዳንዶች አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት እያሉ የማናውቃቸው ልዩ ሰው ነበሩ ሲሉ በሕይወት ሳሉ ስለእርሳቸው በሚገባ ማወቅ ነበረብን ብለው የሚቆጩ ሰዎች አጋጥመውኛል። በአሁኑ ደረጃ ስለእርሳቸው ቀደም ብሎ መግለጹ መልካም አልነበረም ይላሉ?

አቶ በረከት፡- አቶ መለስን በሕይወት ዘመኑ የሕይወት ታሪኩን በመናገር እርሱም ሆነ እኛ ጊዜያችንን አሳልፈን ቢሆን ኖሮ ሕዝቡ እንዲህ እንዳሁኑ ሊያውቀውም ሊወደውም አይችልም ነበር። አቶ መለስም ሆነ ድርጅቱ በሕይወት ዘመኑ ጊዜውን ማሳለፍ የነበረባቸው ስለመሪያቸው በማውራት አይደለም። የመሪው መልካም ሃሳብ በተግባር ላይ ስለማዋል ነው መጨነቅ የነበረባቸው። በነገራችን ላይ አቶ መለስ ብዙ ጋዜጠኞች የግል ታሪክህን እንፃፍልህ ብለው ጠይቀውት በሕይወት እያለ ፈፅሞ እንዲሆን ያልፈቀደ ሰው ነው፡፡ ያ ስለሆነ አሁን የአቶ መለስ ሃሳቦች በየጓዳው፣ በየፋብሪካው፣ በየት/ቤቱ ገብተዋል። ምክንያቱም የአቶ መለስ እና የድርጅቱ የኢህአዴግ ሃሳብ ትምህርት ነው፣ ብርሃን ነው፣ ፋብሪካ ነው፣ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋም ነው፣ የተሻሻለ አመራረት ያለው ግብርና ነው፤ ዴሞክራሲ ነው፤ ፓርላማ ነው፤ የፓርላማ ሙግት ነው፤ በብዙ መልኩ ልንገልጸው እንችላለን። እና ስለእርሱ በራሱም በእኛም አለመነገሩ መጥፎ አልነበረም፣ ጥሩ ነው የነበረው። ሁላችንም ተስማምተንበት ያደረግነው ነገር ነው። መጥፎ ነበር ብዬ አላስብም። እዚያ ላይ ጊዜያችንን ማባከን ነበረብን ብዬም አላስብም። ዛሬም የግድ ሆኖ፣ የግድ መናገር ስላለብን ነው የምንናገረው። ሕዝብ አለ። ታሪክ የሚሠራው ሕዝብ ነው። የእዚህ ሕዝብ ታሪክ ነው መነገር ያለበት። የአቶ መለስ መርህና ፍልስፍና ይሄ ነው። ስለዚህ በመሪዎችና በሕዝብ ሚና መካከል እኛ ኢህአዴጐች በጣም በጣም ግልፅ የሆነና የጠራ አቋም ነው ያለን። መሪዎች አስፈላጊና ጠቃሚ ፍጡራን ናቸው። ዞሮ ዞሮ ወሳኙ ኃይል ሕዝብ ነው ብለን የምናምን ሰዎች ነን። አቶ መለስም በእዚህ የኢህአዴግ እምነት ፀንቶ ነው ስለ ራሱ ያልተናገረው። ነገር ግን አይታወቅም ማለት አይደለም። የሚያውቀው ኢትዮጵያዊ፣ የሚያውቀው አፍሪካዊ፣ ዛሬ በአቶ መለስ ማንነት ላይ አስተማማኝ የጥራት ማረጋገጫ ማህተም አስቀምጦበታል። ስለዚህ ስለሚያውቀው ነው ያለቀሰለት። ስለሚያውቃቸው ነው ይህንን ማህተም ያሳረፈለት ማለት ይቻላል። ስለእርሱ ባንናገርም ሥራውና መልካም ምግባሩ ተናግሯልና፡፡

ዘመን፡- ስለ አቶ መለስ የሥራ ስብዕና ሊነግሩኝ ይችላሉ?

አቶ በረከት፡- ስለ ሥራ ያለውን ስብዕና በተመለከተ እኔ በማውቀው ልግለጸው ብል ያስቸግረኛል። ታመምኩ ብሎ ሥራ ያቆመበት ጊዜ መኖሩን አላውቅም። አንዳንዴ ሀይለኛ በጣም ኃይለኛ ጉንፋን ይይዘውና መናገር እስኪያቅተው እንደደረሰ በድምፁ ወይም ከሁኔታው እየታወቀን ሥራ አያቋርጥም፡፡ ያኔ ለመነጋገር ስለማይመች እንግዳ አይቀበል ይሆናል ግን ሥራ አያቆምም። ይሄ ጉንፋን ትንሽ ስለሆነ ነው ሊባል ይችላል። አሁን መጨረሻ ላይ ታሞ በነበረበት ጊዜም ሥራ አላቆመም። እንደሁሌው ስለኢትዮጵያ ያስብ ነበር፤ ስለሕዝቡ ያስብ ነበር፡፡ ስለ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ያስብ ነበር፤ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ስለሚያደርግባቸው ጉዳዮች ያስብ ነበር፣ ስለሁሉም። ስለመከላከያ ያስብ ነበር። ሁላችን የሥራ ባልደረቦች አሁን ስንነጋገር የምንለውና የምንነጋገረው አንዱን እንዲህ ብሎ ጠይቆት እንደነበር፤ ሌላውን ስለሌላው ሥራ ጠይቆት እንደነበር፤ የት ደረሰ? ምን እያደረጋችሁ ነው ብሎ ይከታተል እንደነበር እናውቃለን። ስለዚህ ስለሥራ ባህል እንነጋገር ከተባለ እንግዲህ የመጨረሻዋ ፈታኝ ወቅት መጨረሻ ላይ የታመመበት ጊዜ፤ በዚያ ወቅት እንኳ ሥራ ያላቆመ መሪ ነው። ከዚህ ሰው ሁላችንም የምንማረው ይህን ሕዝብና ይህቺን አገር ለማገልገል፣ ክፍለ ዓለማችንን ለማገልገል ጉንፋን ያዘኝ፣ እንቅፋት መታኝ ብለን ለትንሹም ለትልቁም ከሥራ ላለመቅረትና ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ጥረት ማድረግን ነው፡፡ ለህመም ሳይበገር ለአገር የመስራት ባህል ያሳየን በዚያ ደረጃ የሚታይ የሥራ ባህል የነበረው ታላቅ መሪ ነው።

ዘመን፡- አንዳንዶች አቶ መለስ በሥራ ጫና ውስጥ እንዲቆዩ ያደረጋቸው ድርጅታቸው ነው፤ ድርጅታቸው ጨክኖባቸዋል ሲሉ በመቆርቆር ይወቅሳሉ፤ እረፍት አይገባቸውም ነበር ይላሉ?

አቶ በረከት፡- እኔ አቶ መለስ መቼም ቢሆን የሚያርፍ አይመስለኝም-መቼም ቢሆን! ማለት ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ሥራውም እየተነባበረ ሲሄድ መድከም የሰብዓዊ ፍጥረታት ግዴታ ነው። ስለዚህ ከዕድሜ ጋር፣ ከሥራ ጫናና ብዛት ጋር መድከም የማይቀር ነው ብለን ልንወስድ እንችላለን። በመድከም ብዛት ማረፍ የሚባል ነገር ግን የለውም። በግልፅኮ ነው የነገርን። ስድስት ክንድ ጉድጓድ ውስጥ እስክቀበር ድረስ አላርፍም-ይሄን ሕዝብ ሳላገለግል አልቀርም ነበር የሚለው ። ይሄ የመጀመሪያው ጉዳይ ነው።

ኢህአዴግ የትግል ድርጅት ነው። ኢህአዴግ የትግል ድርጅት ስለሆነ እንኳን የአቶ መለስን ያህል ትልቅ አቅም ያለው ሰውና ከአቶ መለስ ያነሰ አቅም ያለውን ሰውም በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቀምበት ይገባል እንጂ ሊያባክነው አይገባም። ስለዚህ አቶ መለስን በተመለከተ በኢህአዴግ በኩል እረፍት አልተፈቀደለት ከሆነ ኢህአዴግ መፀፀት የለበትም። ማለት መስራት አለብህ ብሎ ሥራልን ምራን ብሎ ቢለምነው፣ ቢያግባባው ቢመርጠው ነውር የለውም። መለስ በዚህ ደረጃ ከሥራና ከትግል ራሱን ነፃ የማድረግ ሃሳብም ተግባርም ያልነበረው ሰው ነው፡፡ በዚያ ላይ መለስን ያህል ሰውስ ማነው ሥራ አትስራ ሊለው የሚችል? የራሱ ትልልቅ ራዕይ የነበረውና በአርአያነት የሚንቀሳቀስ ሰው ነውና የነበረው፡፡ ሁላችንም ፈለጉን እንድንከተል እረፍትን ያላስተማረን መሪ ነበር፡፡ ኢህአዴግም ይህን ያደረገው ሥራውን የሚያውቅ፣ ኃላፊነቱንና ተልዕኮውን የሚያውቅ ድርጅት ስለሆነ ነው።

ለመዝናናት እንዳልተፈጠረ አቶ መለስ ያውቃል። ይህን አገር ከችግር ለማውጣት ነው የተፈጠርነው ብሎ ነው ያስተማረን -ኢህአዴግንም ። እርሱም በዚያ ደረጃ ነው ራሱን የቃኘው ። ስለዚህ የእርሱን ፈለግ ተከትሎ የሚያስብ ሰው ሁሉ የማርፍበት ጊዜ አነሰኝ እንዳይል አድርጎ ነው የተንቀሳቀሰው ። እና እንግዲህ ኢህአዴግም አሠርቶት ከሆነ በራሱ በመለስ ፈለግ ብቻ ነው። ይሄ ጥያቄ የሚነሳበት ምክንያት ይገባናል። ሕዝቡ አንድ ትልቅ መሪ አጥቷል። ቁጭት አለው። ቢቆይለት ይወድ ነበር። ሕዝቡ እረፍት ብንሰጠው ይቆይ ነበር ወይ? ያርፍ ነበር ወይ? የሚለውን ጥያቄ አንስቶ መመለስ ይፈልጋል። እረፍት ብንሰጠው አያርፍም ነበር። እረፍት የሚጠይቁ ሰዎች ሲኖሩ በስንት ዓመት አንድ ጊዜ ‘እስቲ ሞክሩት-እስኪ ሞክረው እንደማታርፍ እናውቃለን’ ብሎ ነው የሚልከው። ለዚህ ነው እረፍት ወጥቶ የሚያውቅ ሰው ኢህአዴግ ውስጥ የሌለው።

እና አቶ መለስን ባይጠቀምበት ፣ የአቶ መለስን አቅም ሥራ ላይ ባያውል ኖሮ ነው ኢህአዴግ ደካማ ድርጅት የሚሆነው። ኢህአዴግ የአዲሱን ሆነ የነባሩን ትውልድ አመራር ከአሁን በኋላ አቶ መለስ ባስለመደንና ባስቀመጠው ፈለግ ነው ሊጠቀምበት የሚገባው። «ሰው ተጋግዞ መሥራት አለበት፤ ሰው ደከመኝ ማለት የለበትም» ይሄ ነው የአቶ መለስ መርህ። እንደኛ በመሰለ አገር ሁሉም ታጋይ ሰው ስድስት ክንድ ጉድጓድ ውስጥ እስኪገባ ይሄን ፈለግ መከተል እንዳለበት ነው በተግባር ያስተማረው።

ዘመን፡- አቶ መለስ አንባቢ መሆናቸው ይታወቃል። እስኪ ስለዚህ ጉዳይ ያጫውቱኝ?

አቶ በረከት፡- እንግዲህ አቶ መለስ እኔ ሳውቅ ገና ትግራይ ስንሄድ የነገረኝን ነገር ከራሱ የሰማሁትን ነገር ነው የምነግርሽ። አንዳንድ ጊዜ ንባብን በተመለከተ በተለይ ትላልቅ ምርምር ባደረገበት ጊዜ ለተከታታይ ሁለት ሦስት ቀናት ሳይተኛ የሚያነብበት ጊዜ ነበር። ቀን ይጀምራል፣ እያነበበ ያመሻል። አድሮበት እንደገና ያነጋል። ሲደክመው ደግሞ እንደዚሁ በተከታታይ ይተኛል። እንዲህ አድርጌ አነብ ነበር ብሎ አጫውቶኛል።

ይሄን ከእርሱ ነው የሰማሁት። እና በዚህ ወቅት ያደረገውን ምርምር በኋላ በተለይ በ1977 እና 78 ዓ.ም ህወሓት ይዟቸው በወጣው የምርምር ሥራው ሳየው በርግጥም አቶ መለስ ቀን ከሌት ያነበበ ሰው መሆኑን ለመገንዘብ የቻልኩበት ሁኔታ አለ። ይሄን በቃል የነገረኝን ይዤ ነው የማነሳው። በኋላ በሥራዎቹ በጽሑፎቹ አገር ያነቃነቀ፣ ደርግን ለመጣል እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነውን የአስተሳሰብ ግልፅነት የፈጠረበት ሁኔታ እንደነበር አውቃለሁ። እና ከመጽሐፍ እውቀት ይገኛል። ይሄ ብቻ ሳይሆን ትኩረት ሰጥቶ መጻሕፍትን ማንበብ፣ ለቀናት ሳይተኙ ማንበብ የሚችልና በተግባር ይህን ያደረገ ሰው ነበር።

አዲስ አበባ ከገባን በኋላም ያንን የንባብ ባህል አላጠፋውም፤ አላጠፋውም ብቻ ሳይሆን በጣም በጣም አጐልብቶታል። በተለይ በመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት ቀደም ሲል እንዳልኩሽ ቢሮው እንሄዳለን ጠረጴዛው ላይ መጻሕፍት ነው ያለው። ሦስት አራት ትልልቅ መጻሕፍት ያነባል። ቢሮ ስንሄድም ወይ እያነበበ እናገኛዋለን ወይ እየፃፈ እናገኛዋለን ከሁለት አንዱ ነው። ሰው ከሚያነጋግርበት፣ ስብሰባ ከሚመራበት ውጪ ጊዜው ወይ በመፃፍ ወይ በማንበብ ነው የሚጠፋው፡፡ የካቢኔ ስብሰባ ስንገባ ለዚህ ካቢኔ ለውይይት የሚቀርበው ዶክመንት በጣም ትልቅ ነው። በሚገርመን ሁኔታ በሁሉም ዶክመንቶች ላይ አንዳንድ ጊዜ ከየቢሮው የተላከ 400 ወይ 500 ገጽ ሊሆን ይችላል አንብቦ ተዘጋጅቶ ሃሳብ ይዞ ትችቱን አደራጅቶ ነው የሚመጣው።

እና የሥራም ጉዳይ ያነባል፣ የዕውቀት መጻሕፍትንም ያነባል። አሁን መጨረሻ ላይ ሥራ እየበዛበት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ማለትም በትራንስፎርሜሽን ፕላኑ ላይ የተቀመጡ የህዳሴ ግድብ፣ የባቡር፣ የቴሌ የመሳሰሉት ሥራዎች ላይ ነው ትኩረቱን ያደረገው። በዚህ የሥራ መደራረብ ወቅት ስለንባብ ስናወራ ሥራው እንዴት እንደበዛ፣ ጫና እንዳሳደረ ግን በቃ ባለችው ትርፍ ጊዜ ሁሉ ማንበብ ይገባል ይላል ሁላችንን ሲመክረን፡፡ መፅሃፍ ቸግሮት እንደማያውቅ አውቃለሁ፡፡ ለብዙ ሰው የአዳዲስ መጻሕፍት ዋነኛ ምንጭ እርሱ ነበር፡፡ የንባብ ባህልን በተመለከተ መጽሐፍ ዘግቶ ከመቀመጥ በእጅህ የገባውን ማንኛውንም መጽሐፍ ማንበብ አለብህ ይል ነበር። የሚጠቅመውን ትወስዳለህ የማይጠቅመውን ትተዋለህ ይላል። እና ራሱን ያስተማረ ሰው በመሆኑ በእኔ ግምት ከትምህርትና ከንባብ አኳያ በጣም ብዙ ብዙ ልንማርበት የሚገባ የሕይወት ልምድ የነበረው ሰው ነው። ሌሎቻችን ያዝ ለቀቅ እያደረግን ነው የመጣነው የንባብ ባህልን። ሥራ በዛብን ብለን እናስተጓጉላለን፣ እንደገና እንጀምራለን፣ እንደገና ይቋረጣል። እናም በአቶ መለስ ደረጃ የሚታይ ባህል ያለው ሰው አለ ማለት የሚቻል አይመስለኝም።

ዘመን፡- እንደው አቶ መለስ ምን ያህል መጻሕፍት እንዳሏቸው መገመት ይችላሉ?

አቶ በረከት፡- እንግዲህ መገመት ያስቸግራል! እኔ ሳውቀው የመጀመሪያ 10 ዓመታት ቢሮው የነበረውን መደርደሪያ አውቀው ነበር። መደርደሪያው ትንሽ መጻሕፍትን ይዞ ነው የጀመረው። እየሞላ እየሞላ እየሞላ በሦስት አራት ዓመታት አንድ መደርደሪያ ሲሞላ፤ ሞልቶ አይቆምም ወደ ቤቱ የሚወስድበት ሁኔታ አለ። ይሄ ብቻ አይደለም ብዙ ሰው ደግሞ ይዋሳል። ተውሶም የማይመለሱ መጻሕፍት ብዙ ናቸውና ወደፊት መቁጠር የሚቻል ይመስለኛል፤ ከአቶ መለስ የተዋሳችሁ ሁሉ እስቲ ንገሩን ብለን እናጠናለን። ግን በእጁ በጥቂት ሺዎች ያህል መጻሕፍት ይኖራሉ። በግል ቤተመጻሕፍት ደረጃ ምናልባት ትልቁ ቤተመጻሕፍት የእርሱ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ።

ዘመን፡- አቶ መለስ ምን ዓይነት ባህሪ ያላቸው ሰው ናቸው? አንዳንዶች ጨዋታ አዋቂ ናቸው፣ ፈገግታ የሚታይባቸው ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ፤ ሌሎች ደግሞ ኮስታራ ናቸው ይላሉ፤

አቶ በረከት፡- ለእኔ ጨዋታ አዋቂ ነው። ከአቶ መለስ አጠገብ ቁጭ ብለሽ ዘና ባለ ጊዜ ለመጫወት ከቻልሽ በጣም ጨዋታ አዋቂ ነው። አንዳንዴ ዘና ብለን የምንጫወትባቸው አጋጣሚዎች የሚፈጠሩባቸው ሁኔታዎች ነበሩ።

እንዲሁ እንደቀልድ እርስ በእርሳችን ስንቀላለድ የት/ቤቱን፣ የአገርን፣ ከመጻሕፍት ያገኛቸውን አስቂኝ ነገሮች፤ በሕይወት ልምዱ ያጋጠመውን ነገሮች ክፉውንም ደጉንም አንስቶ በጣም የሚያዝናና ወሬ ማውራት የሚችል፣ ጨዋታ የሚያውቅ ሰው ነው። በዚህ ዓይነቱ ጊዜ ሲቆጣ አይቼው አላውቅም። በቤተሰብ ደረጃም በጣም ትልቅ የቤተሰብ ሰው ነበር። ከልጆቹ ጋር ከሕፃንነታቸው ጀምሮ እንደትልቅ ሰው ነው የሚወያየው። ከልጆቹ ጋር አብሮ ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀስ ጊዜ ሲመካከር፤ ሲወያይ፤ ሲነጋገር እናያለን። ብዙ ሰው ቤተሰቡን ልጆቹን በቁም ነገር የሚያመካከርበት ሁኔታ ጐልቶ አይታይም። ይሄን ስትመለከቺ ጥሩ አባት፣ ጥሩ የቤተሰብ ሰው እንደሆነ የሚያሳይሽ ነገር አለ።

አቶ መለስ የሚቆጣበት ጊዜም አለ። የሚገርምሽ ነገር መቼም ቢሆን በግሉ በመጣ ጉዳይ ሲቆጣ አይቼው አላውቅም መቼም። ግን በሁለት ሦስት ምክንያቶች ሲቆጣ አይቼዋለሁ። አንደኛ ሥራ ሲወድቅ አይወድም፤ ይናደዳል በጣም! ሁሉ ሰው መሥራት አለበት፤ ተልዕኮውን መፈጸም አለበት ብሎ የሚያምን ሰው ነበር። እና ሥራ ላይ የደከመ ሰው የተሰጠውን ተልዕኮ አውገርግሮ በደንብ ሳይፈጽም የመጣ ሰው ሲኖር ይናደዳል። ይሄ በግሉ የመጣ አይደለም። በአገሩና በሕዝቡ የመጣ ጉዳይ ስለሆነ ነው የሚያናድደው። ሁለተኛ ሕዝብን የሚጐዳ ነገር የሚፈፅም ሰው ሲያይ ይቆጣል። ይሄ ሲያናድደው አይቻለሁ። አንዳንድ ጊዜ ‘በመቃብራችን ላይ!’ ሲል እንሰማዋለን። ‘መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም በመቃብራችን ላይ! ይላል በቁጣ! በኃይለ ቃል ሲናገር እንሰማዋለን። የአባቱ መሬት ኖሮ ያንን ሊወስድ የመጣ ሰው ቢኖር በዚያ መልክ የሚከራከር አይመስለኝም። በሕግ አግባብ ጨርሱት ይል ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ የኢትዮጵያን ገበሬዎች ከመሬት ለማፈናቀል የሚሞክር ማንኛውም ኃይል ካጋጠመው ግን ለምን የፈለገው የዓለም ልዕለ ኃያል አይሆንም የምታደርጉትን እናያለን፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመጣችሁ ወይ አጥፍታችሁን ነው የምትሰሩት እንጂ እኛ እያለን አይሆንም በሚል ቁጣውን የሚገልፅበት ጊዜ አለ። ስለዚህ በሕዝብ ጥቅም የመጣ ጉዳይ ላይ ሲቆጣ ትሰሚዋለሽ።

አቶ መለስ ውሸታም አይወድም፤ እየገባው እያወቀው የሚያጭበረብር ሰው አይወድም። በቃ ግልፅነትና ታማኝነት ቅንነት እንዲኖር ይፈልጋል። አጠገቡ እንዳይደርስ የሚፈልገው አጭበርባሪን ነው። አጭበርባሪ የተባለን ሰው እንዲጠጋውም አይፈልግም። እና ሁሉንም ነው የያዘው። ለሕዝብ በጣም ጥሩ ሰው ነው። ደግሞ ሕዝብን ለሚበድል ሰው ቁጡ ነበር ማለት ይቻላል።

ዘመን፡- አቶ መለስ ራሳቸው ከእሑድ በቀር እረፍት የለኝም ሲሉ የተናገሩበት ሁኔታ አለ። በዚህች እሑድ ምን እየሠሩ ነው የሚያሳልፉት? ለምሳሌ በቤታቸው ቡና ይጠጣሉ?

አቶ በረከት፡- ቡና ሲጠጣ አይቼው አላውቅም። ግን እሑድ ያርፋል በርግጥ ጉዞና የእሁድ ሥራ ከሌለበት። በፊት ቴኒስ ይጫወት ነበር ገና በ30ዎቹ መጨረሻና በ40ዎቹ የዕድሜ መጀመሪያ በነበረበት ጊዜ። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ምሽት ሥራ ላይ ነው። አሁን እሁድ ለማረፍ ይሞክር ነበር፡፡ እንደነገረኝ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም እንደዚያ እንድናደርግም ይመክረን ነበር። ‘አንዳንዴ ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁ ወጣ በሉ እስኪ ሥራ ይበዛባችኋል’ ይለናል፡፡ ትንሽ ደከምከም ስንል ከተመለከተ ይሄ ነገር እንዳይጐዳችሁ ይላል። ለራሱ እረፍት እንደሌለው እያወቅን ማለት ነው። እና ‘ለምን ከአዲስ አበባ ወጣ ብላችሁ፤ ደብረ ብርሃንም ቢሆን ወጣ በሉና ዘና ብላችሁ ኑ’ ይላል። ሌላ ነገር እንድናደርግ አይደለም የሚመክረን። ለእኔ ለራሴ ደከምከም ያለኝ ጊዜ ‘ለምን እንዲህ አታደርግም?’ የሚልበት ሁኔታዎች ነበሩ። እና አሁን አሁን እሑድን ቤቱ በፀጥታ ማሳለፍ የሚመርጥበት ጊዜ እንደነበር ነግሮኛል። ከልጆቹና ከባለቤቱ ጋር ቀኑን የቤተሰብ አድርጐ ማለፍ የሚፈልግበት ጊዜ እንደነበር አውቃለሁ።

ዘመን፡- የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጠንሳሽ ናቸው አቶ መለስ። ሕዝቡም ኀዘኑን በሚገልጽ ጊዜ በተለይ ይህንን ራዕያቸውን አብሮ ሲያነሳው ተደምጧል። ከግድቡ ጋር ሕልማቸው ምን ነበር?

አቶ በረከት፡- አቶ መለስ ቢሮውን ወደፊት ለሕዝብ እናሳየዋለን ብዬ አስባለሁ። ስለ ህዳሴው ግድብ ብቻ አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ በአባይ ላይ የሚሠሩ ግድቦች ካርታን ይዞ ያሳየናል። ሙያተኞች ሠርተው ያቀረቡለትን ካርታ ማለት ነው። እንግዲህ አባይ ላይ ሦስት አራት ግድብ የመሥራት ሕልም ነው የነበረው። የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ነው እንጂ የመጨረሻው አልነበረም። እና የባቡሩም እንደዚሁ ነው። የባቡር ዝርጋታ ዲዛይኑ ቢሮው ውስጥ አንድ ኮርነር ላይ ሲወጣ ሲገባ በሚታይ ቦታ ላይ ተለጥፏል፡፡ አንዳንዴ ቢሮው ገብተን ስለ ባቡር ሲያወራንም በእጁ ካርታውን እያመላከተ ወይ ተነስቶ ከዚህ እስከዚህ የሚደርሰው፤ ከዚያ እስከ እዚያ የሚደርሰው እያለ የሚያወራበት ሁኔታ ነበር። የቅርብ ርቀት ትልቁ ራዕዩ እነዚህን ሜጋ ፕሮጀክቶች አሳክቶ ዳር አድርሶ ማየት ነበር የነበረው። ያው በጊዜ የመቀደም ሁኔታ መጥቷል እንጂ።

ግን አቶ መለስ እነዚህን ራዕዮች መልክ አስይዞ ቦታ ቦታ አስይዞ ለተተኪዎቹ ትቶ ነው የሄደው። ሁላችንም ድርጅቱ፣ መንግሥታችን፣ ሕዝቡ፣ ይህን ራዕይ ማሳካት የሚችሉበት ብቃት አለ። ያንን ብቃት ፈጥሮ ነው የሄደው። በዚህ ደረጃ ብዙ የሚያጠራጥር ነገር አለ ብለን አናምንም። በጣም ትልቅ ትልቅ ራዕይ የነበረውና ያንንም በተግባር ለማዋል የተዘጋጀ ሰው ነበር። ቢሮው ውስጥ ካለው ካርታ አቀማመጥ ስትመለከቺ እነዚህን አስፈፅሞ ዳር አድርሶ የማየት ሕልም እንደነበረው ማየት ይቻላል።

ዘመን፡- የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ ከተናገሯቸው ነገሮች ስናይ አቶ መለስ ብዙ ቁጭት ያላቸው ይመስላል፤ ጠንከር ያሉ ነገሮችን ሲናገሩ ነው እናደምጥ የነበረው። የተለየ ቁጭት ያሳደረባቸው ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ በረከት፡- አዎ ቁጭት ያሳደረበት ብዙ ነገር አለ። አንዱ የሐፍረታችን ምንጭ የውርደታችን ምንጭ የሚለው ነገር ነው የሚያስቆጨው ሁሌ። ሁላችንም እንደምናውቀው በግልፅም ተናግሮታል። ለኢትዮጵያ የንቀት አመለካከት የነበራቸው አንዳንድ ሰዎች ድህነታችንን እያነሱ ሲሳለቁ አቶ መለስ ይህንን እንደ ትልቅ የእልህና የወኔ ምንጭ አድርጎ ነበር የሚወስደው፡፡ ግድየለም እንዲህ ተብለን አንቀርም ብሎ በቁጭት ይናገር ነበር፡፡ አንዳንዶቻችን እንዲህ ዓይነት ነገር ስንሰማ ለመቀበል እንቸገራለን። የእዚህ ዓይነት እውነት ሲነገር መስማትና መቋቋምም ያቅተናል፡፡ የታባታቸው እንላለን። እርሱ ግን «ግዴለም ይበሉን ይሄ የእልህና የቁጭት ምንጫችን ነው» የሚለው ነገር ነበረው።

«ረሃብተኞች ቢሉን ከዚህ እልህ እንገዛለን፤ ከዚህ ቁጭት እንገዛለንና እስክንለውጠው ድረስ አናፍርም፤ ከለወጥነው በኋላ እንደሚተውት እናምናለን» የሚል አመለካከት ነው የነበረው። እና ድህነታችን ኋላ ቀርነታችን ነው ያስቆጨው የነበረው። ለእዚህ ነው የኢትዮጵያን ድህነትና ኋላ ቀርነት ለማስወገድ ሌት ተቀን የሠራው። እልህና ቁጭት ስለነበረው፣ ይሄ ሕዝብ በድህነት መኖር አይገባውም ብሎ የሚያምን በኋላቀርነት መኖር የለበትም ብሎ የሚያምን መሪ ስለነበር ነው ወደ ትልቁ ነገር ያመራው።

ዘመን፡- በመጨረሻም ክቡር አቶ በረከት የአቶ መለስን ህልፈት አስመልክተው በተለይ በውጭ አገር ያሉ አንዳንድ ፖለቲከኞች ብሔራዊ እርቅ ይምጣ፤ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም በሚል የሚያነሱት ሃሳብ አለ እዚህ ላይ አስተያየት ሊሰጡኝ ይችላሉ?

አቶ በረከት፡- ከአቶ መለስ መስዋዕት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የወደፊት ጉዳይ ምን ይሆናል በሚል የሚነሳ ሃሳብ እንዳለ እንሰማለን ግን ይሄ ተመልሶ ያደረ ጉዳይ መሆኑን ማስታወስ ይቻላል፣ ይገባልም ። በኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት አለ። ይሄ መንግሥት አምስት ዓመታት ሊያገለግል ተመርጧል። አምስት ዓመታት ሲያገለግል ደግሞ የጀመራቸው ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች አሉ። የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አለ፤ ይሄን ለማስፈፀም ነው የሚሠራው። የሕዝብ አመኔታ አትርፎ የተመረጠ ፓርቲም አለ። ይሄ ፓርቲ ዓላማውን ለሕዝብ አቅርቦ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተወዳድሮ አሸንፎ በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ የመምራት ኃላፊነትን የተረከበ ፓርቲ ነው። ስለዚህ ይሄ ፓርቲ ከአቶ መለስ በኋላ ምንድን ነው የሚያደርገው የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ቀጣይነት ነው የሚኖረው። የሚለወጥ ነገር አይኖርም ነው መልሳችን፡፡ ሕዝብም በእልህና በቁጭት የነገረን ይህንኑ ነው፡፡

የሕዝብ ድምፅ አግኝተን ስንመረጥ የገባናቸው ቃሎች አሉ። ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ ጥሩ ፕሮግራም ነው። እርሱ ተቀርፆ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። ሁለት ዓመት ተሠርቶም ጥሩ ውጤት ተገኝቶበታል። በቀሩት ሦስት ዓመታት ከመንግሥት አኳያ ይህን ፕሮግራም ማስፈፀም ነው ሥራችን። ውክልና ያለው መንግሥት ነው፤ ሌላ ውክልና ጥየቃ አይሄድም። አምስት ዓመታትን ነው ሕገ መንግሥቱ የሰጠው። ፓርቲውም ለእነዚህ አምስት ዓመታት ተመርጧል። ከዚያ በኋላ አዲስ ምርጫ ይካሄዳል። ያኔ ፓርቲው እንደ አዲስ ይወዳደራል፤ ተቃዋሚዎችም ይወዳደራሉ። ሕዝቡ አመኔታ አሳድሮበት የመረጠው ፓርቲ ደግሞ በኃላፊነት ላይ ይቀጥላል። ከዚያ በፊት አቋራጭ መንገድ የለም። አንድም ዓይነት አቋራጭ መንገድ አይኖርም። ይሄ ትናንት አልነበረም፣ ዛሬ የለም፤ ነገም የሚኖር አይሆንም። ከሕዝብ ድምፅ ውጪ የሕዝብ ስልጣን መያዣ ሽግግር የሚደርግበት ሁኔታ የለም። ቀጣይነት ነው የሚኖረው። እንደገለፅኩት ከሦስት ዓመት በኋላ አዲስ ምርጫ ይካሄዳል ያኔ እናንተን አንፈልግም ካለ ኢህአዴግን ያስወግደዋል፤ የለም ኢህአዴግ ነው የሚሻለኝ ካለ ኢህአዴግ ይቀጥላል። በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መች ነው ስልጣን የሚለቁት ሲባል «እንግዲህ ተመርጠናልና ጥቂት ዓመታት መጠበቅ ሊኖርብን ነው» ብሎ መልስ ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ፈለግ ሦስት ዓመት መጠበቅ አይቀርልንም ማለት ነው።

ዘመን፡- እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመሪው ያለውን ፍቅርና አክብሮት ባየነው መንገድ ገልጿል፤ በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖር ይሆን ለሕዝቡ?

አቶ በረከት፡- እኔ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንገር የምችል አይመስለኝም። ይሄ ሕዝብ በጣም ትልቅ ሕዝብ ነው። በጣም ኩሩ ሕዝብ ነው። ራሱን ያከበረም ሕዝብ ነው። በአቶ መለስ ህልፈት የጎደለበትን የሚያውቅ፣ ነገር ግን ትተውለት የሄዱለትን ትልቅ አቅም ደግሞ የሚገነዘብ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሕዝብ ብዙም ነጋሪ ሳያስፈልገው የአቶ መለስ የድርጅቱን ራዕይ እውን ያደርጋል ብዬ አስባለሁ።

አቶ መለስ ጠንካራ ድርጅትና መንግሥት መስርቶ ነው የሄደው። ከጓዶቹ ጋር ሆኖ ባካሄደው ያላሰለሰ ትግል ፓርቲውን በጣም ትልቅ ደረጃ ላይ አድርሶታል። መንግሥትም ጠንካራ ነው። ነገር ግን መንግሥትና ፓርቲው ምንም ጉድለት የላቸውም ማለት አይደለም። ጉድለት ይኖራቸዋል። ይህም ሆኖ መንግሥትም ፓርቲውም ጉድለቶቻቸውን እያረሙ ያላቸውን ጥንካሬና ትልቅ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀሙ ሕዝብን ለማገልገል የተዘጋጁ ፓርቲና መንግሥት ናቸው። ስለዚህ ፓርቲውና መንግሥቱ የአቶ መለስ እና የኢህአዴግን ራዕይ ለማሳካት ከሕዝብ፣ ከዚህ በጣም ኃይለኛ ማዕበል ሆኖ ከተነሳው ሕዝብ ጋር ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ ይኖራል ብለን እናስባለን።

በእኔ ግምት አሁን ሁላችንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ መሪ ድርጅቱ ኢህአዴግ፣ መንግሥቱ ማድረግ የሚገባን የሚመስለኝ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ጥርሳችንን ነክሰን ነገር ግን አቶ መለስ ያስበው ከነበረው በላቀ ቁርጠኝነትና ውጤታማነት መፈፀም ነው፤ ለእርሱና ለሰማዕታት ባለን ክብር፣ ለእርሱና ለሕዝቡ ራዕይ ስንል ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ጋር ሲፋለም መስዋዕትነትን ለከፈለው መሪያችን ስንልም ይሄን እናደርጋለን። ሕዝቡ ይሄን እንደሚያደርግ ቃል ገብቶልናል። እኛ እንደ ኢህአዴግ እየተመካከርን ያለነው ይህን የሕዝብ ድምፅ ይህን የሕዝብ ቃል የላቀ ውጤት ለማግኘት ልንጠቀምበት የምንችልበት ቁርጠኛነትና ዲሲፕሊን ይዘን ሕዝቡን የማገልገልን ጉዳይ ነው እየተነጋገርንበት ያለነው። በዚህ ደረጃ ወደተሻለ ነገር እናመራለን ብዬ አስባለሁ።

***********

Source: Zemen Megazine – December 2012.

Daniel Berhane

more recommended stories