ኢትዮጵያ | በስምጥ ሸለቆ ተጨማሪ የነዳጅ ጉድጓዶች ይቆፈራሉ

በኢትዮጵያ ደቡባዊ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ከሚካሄደው አንድ የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት የነዳጅ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩ ታሎው የተባለው ኩባንያ አስታወቀ፡፡

የኩባንያው ቃል አቀባይ አቶ ሲሳይ ዘሪሁን እንደገለጹት፣ በደቡባዊ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚካሄደው አንድ የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ በጥቂት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡

ሌሎቹ ሁለቱ የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓዶች ቁፋሮ የሚካሄዱት በዳሰነች እና በሐመር ወረዳ ኤርቦሬ ከተማ አቅራቢያ ጨው ባሕር በተባለው አካባቢ ነው፡፡

የነዳጅ ጉድጓዶቹን ለመቆፈር በአውሮፕላን «የኤይር ቦርን ግራቪቲ» እና በመሬት ላይ ደግሞ «የሴስሚክ» ጥናት ሥራ መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡

በተለይም በጨው ባሕር አካባቢ ለሚካሄደው የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ ከ1 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ቦታ የሚሸፍን «የሴስሚክ» ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያው የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ማስቆጠሩንና ሰባት ያህል ዓለም አቀፍ የሥራ ተቋራጮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያው ቁፋሮ ነዳጅ ከተገኘ በአካባቢው ሌሎች ተጨማሪ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩም አስረድተዋል፡፡

የመጀመሪያው የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ የሚካሄድበት አካባቢ ኬንያና ኡጋንዳ የነዳጅ ምርት ካገኙበት አካባቢ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውም አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ የታሎው ኩባንያ እያካሄደ ላለው የመጀመሪያው የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ እስካሁን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል፡፡

ኩባንያው ለአካባቢው ሕዝብ የትምህርት፣ የውሃና የጤና አገልግሎት ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው እያካሄደ ላለው የነዳጅ ፍለጋ ሥራ መንግሥት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብና በተለይም የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ከ550 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ከ83 በመቶው በላይ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

በኩባንያው የሥራ ዕድል ካገኙት የአካባቢው ማኀበረሰብ አባላት መካከል ሎቡዋ ካኩታ እና ኮግና ጅኔሬሜጃ በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት፣ ኩባንያው በአካባቢው የነዳጅ ፍለጋ ቁፋሮ በመጀመሩ በርካታ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያው በትምህርት፣ በውሃና በጤና አገልግሎት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስድስት ዓለም አቀፍ ትልልቅ ኩባንያዎች የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡

በመላ አገሪቱ አሥር ያህል ፈቃዶችን በመውሰድ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ በማካሄድ ላይ የሚገኙት ታሎው፣ አፍሪካ ኦይል፣ ፔክሲኮ፣ ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ፣ አፋር ኤክስፕሎሬሽንና ኒው ኤጅ የተባሉ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

*********

Source: Addis Zemen – April 14, 2013. Originally titled “ተጨማሪ የነዳጅ ጉድጓዶች ይቆፈራሉ”

Daniel Berhane

more recommended stories