Nile | ዶ/ር መረራ:- በሳዑዲ መንግሥት የተሰጠው ማስተባበያ «ጨዋታ» ነው

ኢትዮጵያን ወደ ህዳሴ ያሸጋግሯታል በሚል የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ከፍተኛ ተስፋ ከጣሉባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንዱና ዋነኛው ነው። ግድቡ በኢትዮ ጵያውያኖች ሙሉ ተሳትፎና ኅብረት የሚከናወን መሆኑ ልዩ ቢያደርገውም የልዩነቱ መገለጫ ግን ይህ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ግድቡ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁለት ታላላቅ ስንቆችን አኑሯል። የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረታችን መቻል እንደምንችል አረጋግጧል፤ ከድህነት እንደምንወጣም አመላክቷል።

የግድቡ ግንባታ ክንውን ኢትዮጵያውያኖች ከተባበሩ በራሳቸው አቅምና ጉልበት ምንም ነገር መሥራት እንደማይሳናቸው ያመለክታል። ሀገራችን የነበራት ገናና ሥልጣኔ በእዚህኛውም ባለታሪክ ትውልድ በሚቆይ አሻራ ዳግም እንደሚታደስና መጪው ትውልድ የድህነት ታሪክ እንዳይኖረውም ያደርጋል። እነዚህ ተደማምረው የወለዱት ቁጭትም ነው ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ታላቅ ሥራ በቁርጠኝነት በመጨረስ ህያው ታሪካቸውን እንዲያፀኑ ብርታት የሆናቸው።

ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ይህ የታላቅነትና የቁርጠኝነት ተግባር በርካታ ፈተናዎችን እያለፈ ሁለተኛ ዓመቱን ለማክበር ተቃርቧል፤ ሆኖም በእዚህ ሰሞን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ጥቅም በሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ክንውን ላይ ያነጣጠረ ሐሰተኛ ወሬ የሳዑዲ አረቢያ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትርና ልዑል ተሰንዝሯል። ሃሳቡ አደገኛና የጠላትነት ስሜት የተንፀባረቀበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያያዥ የሆነ መልክዓ ምድራዊ ትስስር ከሌላት «ሳዑዲ» መሰማቱ ብዙዎችን አስገርሟል።

ልዑሉ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሡልጣን በግብፅ ካይሮ በተካሄደው የዓረብ ውሃ ካውንስል ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ባገኘችው አጋጣሚ ዓረቦችን ለመጉዳት የማትባዝን መሆኗን ገልጸዋል። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ይልቅ በጠላትነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳለው እንዲሁም ለሱዳንና ግብፅ አደጋ መሆኑን በስብሰባው ተናግረዋል።

የምክትል ሚኒስትሩን ገለጻ ይፋ ያደረገውን የሱዳን ትሪቢዩን ድረ ገፅ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ሳዑዲ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንድትሰጥ ጠይቋል። የሳዑዲ መንግስትም ሃሳቡ የሳዑዲ አለመሆኑን በመግለጽ አስተባብሏል፤ ኢትዮጵያና ሳዑዲ የቆየና የተጠናከረ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን በመግለጽ ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አሳስቧል።

ይሁንና በርካታ ወገኖች የምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ ሃሳብ የሳዑዲ ፈቃድና ይሁንታ ሳይኖርበት አልተገለጸም፤ በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረው አደገኛ ሃሳብና የጠላትነት ማሳያ የግለሰቡ የግል ገለጻ ተደርጎ መታየት የሌለበት ነው፤ የሳዑዲ ማስተባበያም የሚያረካ አይደለም እያሉ ነው።

ይህንኑ መነሻ በማድረግ በተለይ መንግሥት፣ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ዙሪያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የተለያዩ ወገኖች የየራሳቸውን መላምት እየሰጡ ነው። የመላምቶቹ ድምር ሃሳብ መንግሥትና ሕዝብ የኢትዮጵያን ሕዝቦች የጋራ አቋም የበለጠ የሚያጠናክር ተግባር መፈፀም እንዳለባቸው ያመላክታሉ።

በዚህ እትምም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ዶክተር መረራ ጉዲና፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር አብዲሳ ዘርዓይ እንዲሁም በኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሰጡንን አስተያየት ይዘን ቀርበናል።

የፖለቲካ ሣይንስ ምሁሩ ዶክተር መረራ ጉዲና እንደሚገልጹት በሳዑዲ መንግሥት የተሰጠው ማስተባበያ አሳማኝ አይደለም፤ በእርሳቸው አባባል «ጨዋታ» ነው። ዶክተር መረራ «እሳት ሳይኖር ጭስ አይኖርም» ይላሉ፤ የግለሰቡ ገለጻም የሳዑዲ ፈቃድ ያለበት ብቻ ሳይሆን የግብፆች እጅ ያለበት ላለመሆኑ ማስረጃ የለም ብለዋል።

ይልቁንም የምክትል ሚኒስትሩ ሃሳብ ግብፅም ውስጥ፣ ሳዑዲም ውስጥ አንድ ጭንቀት እንዳለ ያሳያል፤ ግብፆች በቀጥታ ሊገልጹ ያልፈለጉትን«ሰውየው» ገልጸውታል የሚል እምነት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል። «ሚኒስትሩ መንገደኛ አይደሉም፤ የንጉሡ ቤተሰብም ጭምር ናቸው። ስለሆነም የሳዑዲ መንግሥት ማስተባበያ ብዙ አያሳምንም» የሚሉት ዶክተር መረራ በግለሰቡ ሃሳብ ላይ ጊዜ ከመፍጀት፣ የሳዑዲ መንግሥት የሰጠው ማስተባበያ ከልብ ነው አይደለም የሚለውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል። መንግሥት በሳዑዲ በኩል የተሰጠው ሃሳብ ምን ያህል ስፋት እንዳለው በመመርመርና በምክትል ሚኒስትሩ ሃሳብ ውስጥ ግብፆች እጃቸው እንዳለበት በማጣራት ጥንቃቄ ሊወስድ ይገባል ሲሉም መክረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር አብዲሳ ዘርዓይ በበኩላቸው የብሔራዊ ጥቅማችንን ጉዳይ ለይተንና ሕጋዊ አካሄድ ተከትለን አቋማችንን ማሳወቅ ይገባናል ይላሉ። በየትኛውም ሀገር ያለ ሚዲያ በማህበረሰቡ ውስጥ የበቀለ በመሆኑ የሀገሩ ደህንነትና ብልጽግና ለራሱ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን መረዳት እንዳለበትም ይናገራሉ። ዶክተር አብዲሳ፣ መገናኛ ብዙሃን በሀገር ውስጥ ስላሉ ችግሮች የሚዘግቡበት መንገድ አለ፤ ነገር ግን በሀገራዊና ሕዝባዊ ጥቅም ዙሪያ የጋራ መግባባት ሊኖራቸው ይገባል በማለትም ያስረዳሉ።

በተለይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በሚመለከት ዋነኛ የመገናኛ ብዙሃኖች፣ የሀገሪቱ መንግሥትና የፖለቲካ ምሁራኖች የጋራ መግባባት ላይ በሚደርሱባቸው ሁኔታዎች ሊዘግቡ ይገባል ይላሉ። መገናኛ ብዙሃን የማህበረሰቡ አካል በመሆናቸው ፖሊሲን ለመጠበቅና በመደገፍ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ገልጸው፤ ይኸው የተሻለ ዴሞክራሲ አላቸው በሚባሉ አገሮች ጭምር እንደሚታይ ያስረዳሉ።

የአረብ ሀገሮች የውሃ ካውንስል ስብሰባ ላይ ሳዑዲን ወክለው የተገኙት ሚኒስትር ንግግር የታቀደ ነው የሚሉት ምሁሩ፣ የግለሰቡ ሃሳብ የግላቸው ነው የሚል እምነት የለኝም ብለዋል። የሳዑዲ መንግሥት ማስተባበያም አደጋውን ለመቆጣጠር የተደረገ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ መንግሥት የሳዑዲን አምባሳደር ጠርቶ ማብራሪያ የጠየቀው ሚኒስትሩን እንደ ግለሰብ ባለማየቱ መሆኑን ያብራራሉ።

«ሰውየው ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ስለሆኑ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ስላሉና እርሳቸው ያሉትን እንደ ግለሰብ መውሰዱ አስቸጋሪ ስለሚሆን ማብራሪያ ጠይቀናል» የሚሉት ቃል አቀባዩ፣ የምክትል ሚኒስትሩ ገለጻ የጠላትነትን ስሜት ያንፀባረቀና ከሳዑዲ ጋር ያለንን ግንኙነት የማይገልጽ ነው ብለዋል። የሳዑዲ መንግሥት በውሃ ካውንስሉ ላይ በመከላከያ ምክትል ሚኒስትሩ የተሰጠው ሃሳብ የሰውየው የግል አቋም መሆኑን የሚገልጽበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ጥቅም ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊታችን ሁልጊዜም ዝግጁ ናቸው ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ጥንቃቄው እገሌ ይህን ተናገረ በሚል ሳይሆን ሁልጊዜም ያለ ነው ብለዋል፤ አሁንም የተለየ ነገር አለመኖሩን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ከዓረቡ ዓለምም ሆነ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ሰላማዊ መሆኑን ገልፀዋል።…

የሳዑዲ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር በካይሮ በተካሄደው የአረብ ሀገሮች የውሃ ካውንስል ያደረጉት ገለጻ በእርግጥም ያልተጠበቀና አደገኛ ነው። የግለሰቡ ንግግር ጣልቃ ገብነት የተስተዋለበትም ነው። የልዑሉ ሃሳብ ኢትዮጵያውያን ልማታቸውን ለማፋጠንና ድህነትን ለማሸነፍ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉበት ባለው የታላቅነታቸው መሠረት ላይ የተቃጣ በመሆኑም ከሀገራችን ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ከምሁራንም አዳዲስና ጠንካራ ሃሳቦች ይጠበቃሉ። በእዚህ ረገድ ምሁራኖቻችን እንደ ሌሎች ሀገራት ምሁራን ጎልተው መውጣትና መከራከር ያልቻሉት ለምንድን ነው ብለን ላቀረብነው ጥያቄ አስተያየት ሰጪዎቹ ምላሽ ሰጥተውናል።

ዶክተር መረራ «እኔ ባለሁበት ዩኒቨርሲቲ ያለው ምሁር መንግሥትን እያገለገለ አይደለም። ወደ መንግሥት ሲጠጋ ከሕዝብ ጋር ይቀያየማል፤ ወደ ሕዝብ ሲጠጋ ደግሞ የኢህአዴግን ዱላ ይፈራል» ብለዋል።

ዶክተር መረራ እንደገለጹት የምሁሩ ችግር ሁለት ዓለም ከመፍራት ይመነጫል፤ ምሁሩ እንዲህ ካልኩ ሕዝብ ወደ መንግሥት ተጠጋ፣ ለሆዱ አደረ ይለኛል ብሎ ይፈራል። ከእዚህ አጥር ለመውጣትም መንግሥት በቂ ስፍራ አልሰጠም በማለት ተናግረዋል።

መንግሥት ብሔራዊ መግባባት በተወሰነ ነገር ላይ መፍጠር ካልቻለ የሁለት ዓለም ሰዎች ሆነን እንኖራለን የሚሉት ዶክተር መረራ ምሁሩ ሀገሩን በሚጎዳና በሚጠቅም ሃሳብ ዙሪያ መናገር እንዲችል ምህዳሩ መስፋት አለበት ብለዋል።

መንግሥት ከግብፆች ምክንያታዊ ሃሳብ መጠበቅ የለበትም፤ ይልቁንም ነገሮችን ደጋግሞ በማሰብና በአካባቢው ያለውን የኃይል አሰላለፍ በመረዳት እንዲሁም ወዳጅን በማስፋት የበለጠ ሊሠራ ይገባል በማለትም ተናግረዋል። ከስምምነትና ፊርማ ባሻገር ሁለት እርምጃ ወደፊት የሄደ ጠለቅ ያለ ጥናት ያስፈልጋልም ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር አብዲሳ ዘርዓይ በበኩላቸው የሀገራችን ምሁራን ምሁራዊ ጉዳዮችን አንስተው ብዙ እንዲገልጹ የሚያስችል ዕድል አለመኖሩን ይናገራሉ። በምሁራኑና በመንግሥት አካባቢ ያለው ሁኔታ የተቀናጀ ነገር እንደማይታይበትም ያስረዳሉ።

«ምሁራን ምሁራዊ ሃሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ የለም፤ የፖለቲካ ትስስር ያላቸው ካልሆኑ በስተቀር ገለልተኛ ምሁር ነኝ ለሚል ሰው አስቸጋሪ ሁኔታ አለ» በማለትም ይናገራሉ። «ምሁራኑ ለምን አይመጡም ማለት ብቻ ሳይሆን መድረክ ፈጥረናል ወይ? በጋራ ተቀራርበን እየሠራን ነው ወይ?የሚለው መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ነው» ሲሉም ይጠይቃሉ።

ምሁራን በአንድ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰጡ ሚዲያዎቹ ከራሳቸው ጥቅም አኳያ የተወሰነውን ሲጠቀሙ ይታያሉ የሚሉት ዶክተር አብዲሳ በእዚህ ምክንያት ምሁራኑ ለመሳተፍ ፍላጎት የሚያጡበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል። የፖለቲካ ሰዎች ከምሁራኑ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጤን እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል። ማንኛውም ዜጋ ለሀገሩ መልካም ነገር እንደሚያስብ በመረዳት በሃሳብ፣ በንግግርና በተለያዩ ክርክሮች የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በሳዑዲው ጉዳይ በምሁራኑ ብዙ ክርክር ሲደረግ አልታየም የሚሉት ዶክተር አብዲሳ እንዲህ ዓይነት የተለየ ነገር ሲያጋጥም ማብራሪያ መስጠት ያለባቸው ምሁራኑ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ከምሁራኑ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል ብሎ መመርመር እንደሚያስፈልግም ነው ምሁሩ የገለጹት።

ዶክተር አብዲሳ፣ የሳዑዲው ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ሃሳብ አስደንጋጭ ነው። አደገኛ ንግግሮችን ነው የተናገሩት። የተናገሩት የሱዳን መከላከያ ሚኒስትርና የግብፅ መከላከያ ሚኒስትር ቢሆኑ አይገርምም። የሳዑዲ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ኢትዮጵያ አረቦችን ለመጉዳት ሁልጊዜ ታስባለች፤ እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን አግኝታ ችግር ለመፍጠር ታስባለች በሚል ወደ ኋላ ጭምር ተመልሰው ተገቢ ያልሆነ ሃሳብ በመሰንዘራቸው ወቅሰዋል።

ምሁሩ ሉዓላዊ በሆነች ሀገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የተሳሳተ ሃሳብ መስጠት ተገቢነት እንደሌለውም ነው ያብራሩት። የሀገራችን ምሁራን በእዚህ ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን ሃሳብ መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመው መንግሥት ሚዲያውና ምሁራኑ ያላቸው ግንኙነት ምንድን ነው ብሎ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል።

ምሁራን ሃሳባቸውን በመግለጽና እውቀታቸውን በማካፈል ከመንግሥት ጋር በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ አብሮ በመሥራት የሀገርን ጥቅም የሚያስከብሩበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት በማለትም አስረድተዋል። ዳያስፖራውና በውጭ ያለው ምሁር የሃሳብ ልዩነት ቢኖረውም በሀገሩና ብሔራዊ ጥቅሙ ጉዳይ ተመሳሳይ ነገር እያንፀባረቀ ነው። የሳዑዲን አስተሳሰብ ተቃውሞ እየጻፈ ነው በማለትም ነው የተናገሩት።

የሀገራችንና የመጪው ትውልድ የወደፊት ሕይወት የተሻለ ለማድረግ ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው መንግሥት ልበ ሰፊ እንዲሆንና ምሁራንም ብብሔራዊ ጉዳዮች ድርሻ እንዳላቸው ተገንዝበው በጋራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሀገር ጥቅም፣ ሉዓላዊነት፣ ነፃነትና የሀገር ደህንነት የጋራ ጉዳይ ነው፤ ኢትዮጵያውያን በእዚህ ጉዳይ ልንለያይ አንችልም ሲሉ ይናገራሉ። የሚያለያዩ ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳ በሀገራዊና ሕዝባዊ ጥቅም ጉዳይ መለያየት አይኖርብንም። ምሁራኖች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ዕድገትና ሰላም በሚመለከት የሚኖራቸው ሚና እንደማንኛውም ዜጋ የጎላ ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የልማታችን አንዱና ዋና አካል ብቻ ሳይሆን የአብሮነታችንና የብልጽግናችን ማሰሪያ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በአባይ ላይ ልማት ማሰብ ፈፅሞ የማንችል መስሎን የቆየንበት የጨለማ ዘመንን አሁን በተጨባጭ ገፍፈነዋል። ባለራዕዩ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ የግድቡን መሠረት ባኖሩበት ወቅት የህዳሴው ግድብ ግንበኞች እኛው ተጠቃሚዎችም እኛው መሆናችንን አበክረው ነግረውናል። የኢትዮጵያ የህዳሴ ዘመን ላይደናቀፍ መጀመሩንም አብስረውናል። ያ የአደራ ቃል መፈፀሙ የትውልድ የቤት ሥራን መወጣት ነው። ትውልዱ ከእዚህ በኋላ ድሃና ተረጂ ሆኖ እንደማይኖር ቃል መግባትም ጭምር ነው። የህዳሴው ግድብ እውን እንዲሆን የጀመርነው ልማትና ሩጫ በውስጣችን በሚፈጠሩ ችግሮች ፈፅሞ እንደማይሰናከል ምሁራኑ አስረጂዎች ናቸው። ሃሳባችንን እያዋጣን፣ የውስጥ ችግሮቻችንን እየፈታን ወደ ብልጽግና ማምራታችን አይቀሬ ስለመሆኑም እነርሱው ምስክሮች ናቸው።

******************

* Originally published on Addis Zemen on March 10, 2013, titled “የህዳሴው ግድብ-የሳዑዲ ወይስ የኢትዮጵያ ጉዳይ?”, authored by Seife Derbe.

Check the archives for related posts.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories