የትራንስፖርት ሚኒስቴር የምሽት ጉዞዎችን ሊከለክል ነው

የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል የምሽት ጉዞዎችን እንደሚከለክል የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ላይ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ለመከላከል የአጭር ጊዜ የቁጥጥርና ክትትል ስራን ለመስራት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቅቋል፡፡

ለመንገድ የትራፊክ ደህንነት አደጋ መንስኤዎች ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ ህገወጥ የሌሊት ጉዞ ፣ ከተፈቀደ የሰው ቁጥር በላይ መጫን የመንገድ ህግና ስርአትን አለማክበር ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በተለይ በህገወጥ የሌሊት ጉዞ ተሳታፊ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር በትራንስፖርት ሚኒስቴር የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሃይለማርያም ህግና ስርአትን ተላልፈው የሚገኙ አሽከርካሪዎችን ከጥፋታቸው ለማረም የተለያዩ መንገዶችን እንጠቀማለን ብለዋል፡፡

ከክልል ከተሞች ጋር በመቀናጀት በክልል የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስና ለመከላከል የፌዴራል ፖሊሲና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባሉ ከተሞች አዲስ የቁጥጥር ሰርአት እንደሚጀመር የገለፁት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ናቸው ፡፡

ኮሚሽነሩ ሞጆ ፣ አዳማ፣ ዝዋይ፣ ሻሸመኔ ፣ ጎሀጽዮን ፣ ወሊሶ ፣ወልቂጤ፣ ደብረብርሃን፣ ደብረሲና ፣ አምቦና ነቀምቴ በዚህ ወር ቁጥጥር የሚጀመርባቸው ከተሞች እነደሆኑም ገልፀዋል፡፡

ቁጥጥርና ክትትሉ በሌሊት የትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በቀንም በሚደረጉ የትራፊክ አገልግሎት ላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡

የቁጥጥርና ክትትል ስራውን ለማጠናከር የተለያዩ አጋዥ ተሽከርካሪዎችና መሳሪያዎችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑም ኮሚሽነር ደምላሽ ገብረሚካኤል ተናግረዋል፡፡

በአለም ላይ በየአመቱ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን እንደሚያጡ የአለም የጤና ደርጅት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

90 ከመቶ የሚሆነው አደጋ የሚከሰተው ደግሞ በታዳጊ ሀገሮች ነው፡፡

(ሪፖርተር የልቤ ማዘንጊያ)

*************

Source: ERTA – March 11, 2013

Daniel Berhane