Sendek | ብሔራዊ መታወቂያ

(በኪዳኔ መካሻ)

– በሁለት ዓመታት ውስጥ ለአካለ መጠን የደረሱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ አይነት መታወቂያ ይኖራቸዋል። – ብሔራዊ መታወቂያው እንደ ቀበሌ መታወቂያችን ብሔራችንን አይገልፅም።
– ብሔራዊ የመለያ ቁጥርም ለእያንዳንዳችን ይሰጠናል።

እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ እንደምናውቀው መታወቂያ ወረቀት ሲሰጡን የነበሩት የመጨረሻው ዝቅተኛ የመንግስት አስተደደር እርከን የሆኑት ቀበሌዎች ነበሩ። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ በቀበሌ ደረጃ የሚሰጥ ሳይሆን በፌዴራል መንግስቱ የሚሰጥ ብሔራዊ የመታወቂያ ወረቀት ይኖረናል።

በአዋጅ ቁጥር 760/04 ስለ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና ስለ ብሔራዊ መታወቂያ የሚደነግግ ነው። አዋጁ የወጣበትን ዓላማ ስንመለከት ዜጐች ከመንግስት ሊያገኙአቸው የሚገቡአቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ፣ ብሔራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ በመግቢያው ላይ ተጠቅሷል። ስለ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ወደ ኋላ ላይ የምንመለስበት ሲሆን፤ አሁን የብሔራዊ መታወቂያ በተመለከተ አዋጁ ያካተታቸውን ነገሮች እንመልከት።

ይህ አዋጅ ከወጣበት ቀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ አዋጁ ላይ ለጊዜው በስም ተለይቶ ባይጠቀስም በአንቀጽ 55 መሠረት ብሔራዊ መታወቂያ የመስጠት ሥልጣን ያለው አካል ይቋቋማል። ይህ አካል ስሙ “የብሔራዊ የመታወቂያ መረጃ ኤጀንሲ” የሚባል ይመስለኛል። ይህን አካል የማቋቋም ስልጣኑ የተሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው።

ይህ ብሔራዊ የመታወቂያ ወረቀት የሚሰጠን አካል ተቋቁሞ ተደራጅቶ የቀበሌ መታወቂያችንን በብሔራዊ መታወቂያ እስከሚተካልን ድረስ በነበሯ የቀበሌ መታወቂያችን አየተገለገልን እንቆያለን ማለት ነው። ይህ የብሔራዊ መታወቂያ ሰጪ አካል ዝግጅቴን ጨርሻለሁ ብሎ በሚገልፅልን ጊዜ ግን በኢትዮጵያዊነታችን ያለንን ብሔራዊ ስሜት ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ መታወቂያ የመያዝ ግዴታም ይጣልብናል።

በሔራዊ መታወቂያ የማውጣት ግዴታ :-
ማንኛውም ለአካለ መጠን የደረሰ ኢትዮጵያዊ (18 ዓመት የሞላው) ብሔራዊ መታወቂያ የማውጣት ግዴታ በአዋጁ አንቀፅ 56(1) ላይ ተጥሎበታል።
አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ደግሞ መታወቂያ እንዲያወጡ ባይገደዱም፤ ወዳጆቻቸው ወይም አሳዳሪዎቻቸው ግን ልጆቻቸው ለአቅመ መታወቂያ እስከደረሱ ድረስ በቤተሰብ መዝገብ ውስጥ የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለባቸው በንዑስ አንቀፅ ሁለት ስር ተደንግጓል።

ምግዘገባ :-
ብሔራዊ መታወቂያ ለማውጣት አስቀድሞ ግዴታው ያለበት ሰው መመዝገብ አለበት። ምዝገባውን ለማከናወን መታወቂያውን እንዲሰጥ ወደፊት የሚቋቋመው የፌዴራል አካል ምዝገባው የሚከናወንበትን ጊዜ እና ቦታ የሚገልፅ ማስታወቂያ ያወጣል። በዚህ ማስታወቂያ መሠረት ተመዝጋቢው ቀርቦ መመዝገብ አለበት። የሚመዘገበው ግለሰቡን የሚመለከት መረጃ የሚከተሉትን መያዝ እንዳለበት በአዋጁ አንቀፅ 57(2) ላይ ተደንግጓል።

1. የግለሰቡ መረጃዎች፡- እነኚህ የግለሰቡን ማንነት ለመለየት የሚያስችሉ መረጃዎች ሲሆኑ፤ ሙሉ ስም ከነአያት፣ የወላጆች ሙሉ ስም እና ዜግነት፣ የትውለድ ቀንና ቦታ፣ ጾታ እና የጋብቻ ሁኔታ እና ፎቶግራፍና የጣት አሻራን እንዲሁም መደበኛ የመኖሪያ ቦታ እና ስራ ናቸው።

2. ሌሎች መረጃዎች፡- ሕጉ ሳይሆን እኔ በዚህ ጐራ ስር የሰበሰብኳቸው በምዝገባው የሚካተቱ መረጃዎች ደግሞ ብዙ ጊዜ አስቀድሞ በነበረው የመታወቂያ አሰራር ላይ መታወቂያችንን የሚመለከት ሌላ አካል በመለያነት ይጠቀምባቸው ያልነበሩ መረጃዎች ናቸው።
– ልዩ ምልክት ካለ ተገልጾ ይመዘገባል
– ብሔርና ሃይማኖት
– ሌሎች አግባብ ባለው የፌዴራል አካል የሚወሰኑ መረጃዎችን ተመዝጋቢው መግለፅ፤ መዝጋቢውም አጣርቶ መመዝገብ አለበት።

የእጣት አሻራን በተመለከተ በአካል ጉዳት የተነሳ የጣት አሻራ መስጠት የማይችል ሰው የሚመለከተው ፀሐፊ ፊት ቀርቦ በሌላ ማንነትን የማጣሪያ ዘዴ በመጠቀም ምዝገባውን ያካሂዳል።
ምዝገባው በሚከናወንበት ጊዜ አስመዝጋቢው የተመዝጋቢውን ማንነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ ጥያቄዎችን የመጠየቅና ሊሟሉ የሚገባቸውን ማስረጃዎች የማስቀረብ ስልጣን አለው።
ተመዝጋቢው ደግሞ የሰጠው መረጃ ትክክለኛ መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት። ይህን ግዴታውን ተላልፎ የሀሰት መረጃ የሰጠ ወይም እውነተኛውን መረጃ የደበቀ ሰው በወንጀል የሚጠየቅ ሲሆን፤ ለጥፋቱም ከአንድ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል አስራት ይቀጣል።
ከላይ የተዘረዘሩትን መረጃዎች አሟልቶ ያቀረበ እና በሚወጣው ደንብ መሠረት የሚወሰነውን የአገልግሎት ክፍያ የፈፀመ ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ መታወቂያ ይሰጠዋል። የሚሰጠን ብሔራዊ መታወቂያ የተመዘገበውን መረጃ ሁሉ የሚያካትት አይደለም። በአዋጁ አንቀፅ 58(2) መሠረት ማካተት ያለበት የተወሰኑ መረጃዎችን ብቻ ነው።

3. የብሔር ጉዳይ፡- ቀድሞ የነበረን መታወቂያ በብዙዎች ዘንድ የሚታማበት እኛነታችንን ለመለየት በቂና አስፈላጊ ከሆኑ መረጃዎች በተጨማሪ ብሔርን የሚጠቅስ ስለሆነ ነበር። ይህ ብሔርን በመታወቂያ ወረቀት ላይ የመጥቀሱ አስፈላጊነት ብዙም ጐልቶ የሚታይ ካለመሆኑ በተጨማሪ ምናልባት ለዘር መድልዎ የሚያግልጥና ዘረኛ የሆነ አመለካከት ላለባቸው ሰዎች የነሱ ዘር ያልሆነ ሰው ላይ የዘር ልዩነት እንዲያደርጉ ሊያመቻች የሚችል ሊሆን ይችላል። ብሔራዊ መታወቂያ ለማውጣት ለመዝጋቢው አካል በምንሰጠው መረጃ ላይ ብሔርና ሃይማኖትን እንድንገልፅ (ለመዝጋቢው አካል ብቻ) የምንገደድ ቢሆንም፤ በብሔራዊ መታወቂያችን ላይ ግን ብሔራችንም ሆነ ሃይማኖታችን አይጠቀስም።

ብሔራዊ የመታወቂያ ካርድ በአዋጁ አንቀፅ 58(2) መሠረት የሚከተሉትን ማካተት አለበት፤
1. የባለመታወቂያውን ሙሉ ስም ከነአያት፣ ጾታ፣ የትውልድ ቀንና ቦታ፣ መደበኛ መኖሪያ ቦታ፣ ፎቶግራፍ፣ የጣት አሻራና ፊርማ የግድ መያዝ አለበት።
2. ብሔራዊ መለያ ቁጥርና የመታወቂያ ካርድ ቁጥርም እንዲኖረው ተደንግጓል። ብሔራዊ የመለያ ቁጥር የሚባለው በአዋጅ አንቀፅ 2(9) መሠረት አንድን ኢትዮጵያዊ ከሌሎች ግለሰቦች ለመለየት የሚያስችል ቁጥር ሲሆን፤ በዚህ ትርጓሜ መሠረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለውና እድሜው ለአካለ መጠን የደረሰ ማንኛውም ሰው ተለይቶ የሚታወቅበት ቁጥር ይኖረዋል። ይህ ቁጥርም በብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ላይ ከሚጠቀሱ የግለሰቡ መረጃዎች አንዱ ነው። በነገራችን ላይ ብሔራዊ መታወቂያ የሚሰጠው አካል ካሉበት ግዴታዎች አንዱ ብሔራዊ የመለያ ቁጥር መስጠት ሲሆን ይህ የመለያ ቁጥር አስቀድሞ ለሌላ ዜጋ ያልተሰጠ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
3. የአገልግሎት ጊዜ፡- በብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ላይ መጠቀስ ያለበት ሌላኛው መረጃ ደግሞ መታወቂያው የተሰጠበት ቀንና የሚያበቃበት ቀን ነው። አሁን ያለን የቀበሌ መታወቂያ በአብዛኛው ከተሰጠበት ቀን አንስቶ ለሁለት ዓመት የሚያገለግል ነው። በአዋጁ አንቀፅ 59 መሠረት ብሔራዊ መታወቂያ ከተሰጠበቅ ቀን ጀምሮ ለአስር ዓመት ፀንቶ የሚቆይ ሲሆን፤ ባለመታወቂያው የማሳደስ ግዴታ የተጣለበት የ10 ዓመት የአገልግሎት ጊዜው እንዳበቃ ነው።
4. ሚስጥራዊ መለያ፤ ሌላው ብሔራዊ መታወቂያችን የሚያሟላው ነገር ቢኖር ለ10 ዓመት ፀንቶ የሚቆይ በመሆኑ እንደአሁኖቹ የቀበሌ መታወቂያዎቻችን ሳይሆን ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግል ሆኖ መዘጋጀት እንዳለበት በአንቀፅ 58(2) ላይ ተገልጿል። በተጨማሪ አሁን አሁን እየተዘወተረ ያለውን ሀሰተኛ መታወቂያ ለመከላከል የሚያስችሉ ሚስጥራዊ መለያዎችንም ያካትታል።

በዚህ ሚስጥራዊ መለያ ሳይገደብ ሀሰተኛ ብሔራዊ መታወቂያ አስመስሎ የሰራ ወይም መታወቂያውን ወደ ሐሰት የለወጠ ሰው ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ሲሆን፤ ወንጀሉን የፈፀመው ብሔራዊ መታወቂያ የመስጠት ስልጣን በተሰጠው የመንግሰት ባለስልጣን ዋይም ሠራተኛ ከሆነ ቅጣቱን እስከ 25 ዓመት እስራት ይደርሳል።
በሀሰተኛ መታወቂያ ሲጠቀም የተገኘ ሰውም ቢሆን ቅጣቱ አይቀርለትም። ከአምስት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።

4. የባለመታወቂያው ግዴታዎች፡- በአዋጁ መሠረት ብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ተግባራዊ ሆኖ መታወቂያውን ያወጣ ማንኛውም ግለሰብ የሚከተሉት ግዴታዎችን እንዲወጣ በአዋጁ አንቀጽ 60 መሠረት ተጥሎበታል።
ሀ. መታወቂያውን በጥንቃቄ መያዝና ሁልጊዜ ይዞ መንቀሳቀስ፣
ለ. በሚመለከተው አካል ሲጠየቅ መታወቂያውን ማሳየት (እዚህ ጋር መታወቂያ ሊጠይቅ የሚችል የሚመለከተው የተባለው አካል ቢገለፅ መልካም ነበር ነገር ግን አልተገለፀም)፣
ሐ. መታወቂያው ላይ የተጠቀሰው መረጀ ላይ ለውጥ ካጋጠመ ለውጡን አግባብ ላለው አካል በ15 ቀናት ውስጥ ማሳወቅ፤ ይህ በዋነኝነት አድራሻን ወይም መደበኛ የመኖሪያ ቦታን የሚመለከት ነው፣
መ. የመታወቂያው ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ እንዳበቃ አግባብ ባለው የፌዴራል አካል ቀርቦ ማሳደስ፣
ሠ. ዜግነቱን የቀየረ ኢትዮጵያዊ ወዲያውኑ መታወቂያውን አግባብ ላለው የፌዴራል አካል የመመለስ ግዴታ አለበት፣ ረ. ብሔራዊ መታወቂያው በምዝገባው ወቅት በተሰጠ የተጭበረበረ ወይም የተሳሳተ መረጃ የተሰጠ ከሆነ በወንጀል ማስጠየቅ ብቻ ሳይሆን መታወቂያው ይሰረዛል። መታወቂያው የተሰረዘበት ሰው ወዲያውኑ ለሰጠው አካል መመለስ እንዲሁም ድጋሚ ተመዝግቦ አዲስ ማውጣት አለበት፣

5. መታወቂያ የጠፋበት ወይም የተበላሸበት፡- የጠፋበት ሰው ለፖሊስ ማመልከቱን ማስረጃ በመያዝ የተበላሸበት ደግሞ የተበላሸውን መታወቂያ በማያያዝ አግባብ ላለው የፌዴራል አካል በማመልከት ተገቢውን ክፍያ በመፈፀም ምትክ ያገኛል። ለፌዴራል ፖሊስ የጠፋ መታወቂያ ያገኘ ሰውም እንዲያስረክብ ግዴታ ተጥሎበታል።

****************
*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 31, 2012. Republished here with the permission to do so, without implying endorsements.

Check the drop down menu for posts on related topics.

Daniel Berhane

more recommended stories