Sendek | የጁነዲን ሳዶ ባለቤትን ጨምሮ 29 ሰዎች በሽበርተኝነት ተከሰሱ

* የጁነዲን ባለቤት በኦሮምያ ክልል አክራሪነት እንዲስፋፋ አድርገዋል – 1.5 ሚሊዮን ብር ከ27ኛ ተከሳሽ ተቀብለዋል

(በዘሪሁን ሙሉጌታ)

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32(1) (ሀ)(ለ)፣ 38(1) እና የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3(1) (2) (4) (6) እና 4 ስር የተመለከተውን ተላልፈዋል ያላቸውን 29 ሰዎችና ሁለት ድርጅቶች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቷል።

ዐቃቤ ሕግ ክሱን የመሠረተው ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ሲሆን፤ ተከሳሾቹም በፍርድ ቤቱ ቀርበው ክሱ እንዲነበብላቸው ተደርጓል።

የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ በክሱ ላይ መቃወሚያ ለማቅረብ የአንድ ወር ጊዜ መጠየቃቸውን ገልፀው፤ ፍ/ቤቱ ግን ለህዳር 13 ቀን 2005 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ገልፀዋል።

የክሱ ዝርዝር:-
——–
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት
ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት
አዲስ አበባ

ከሣሽ …… የፌዴራል ማዕከል ዐቃቤ ሕግ
ተከሳሾች …….
1. አቡበከር አህመድ መሐመድ
ዕድሜ 36 ዓመት
አድ.አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 06 የቤ.ቁ.
2. አህመዲን ጀበል መሐመድ
ዕድሜ 32 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 6 የቤ.ቁ.
3. ያሲን ኑሩ ኢሣአሊ
ዕድሜ 34 ዓመት
አድ. አ/አ ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 9 የቤ.ቁ.
4. ካሚል ሸምሱ ሲራጅ
ዕድሜ 34 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 01 የቤ.ቁ.
5. በድሩ ሁሴን ኑርሁሴን /ኢንጂነር/
ዕድሜ 33 ዓመት
አድ. አ/አ ን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 02 የቤ.ቁ.
6. ሼህ መከተ ሙሄ መኮንን
ዕድሜ 45 ዓመት
አድ. አ/አ ቦሌ /ክ/ከተማ ወረዳ 1 የቤ.ቁ.
7. ሳቢር ይርጉ ማንደፎሮ
ዕድሜ 33 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ቀበሌ 02/03 የቤ.ቁ.
8. መሐመድ አባተ ተሰማ
ዕድሜ 33 ዓመት
አድ. አ/አ አ/ከ/ክ/ከተማ ቀበሌ 14/21 የቤ.ቁ.
9. አህመድ ሙስጠፋ ሀቢብ
ዕድሜ 32 ዓመት
አድ. አ/አ ጉለሌ /ክ/ከተማ ቀበሌ 01/02 የቤ.ቁ.
10. ሙራድ ሽኩር ጀማል
ዕድሜ 40 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 02 የቤ.ቁ. አዲስ
11. አቡበከር አለሙ ሙሄ
ዕድሜ 34 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ቀበሌ 11/12 የቤ.ቁ. አዲስ
12. ኑሩ ቱርኪ ኑሩ
ዕድሜ 36 ዓመት
አድ. አ/አ ጉለሌ ክ/ከተማ ቀበሌ 10/11/12 የቤ.ቁ.084
13. ሼህ ባህሩ ዑመር ሽኩር
ዕድሜ 37 ዓመት
አድ. አ/አ አራዳ ክ/ከተማ ቀበሌ 01/02 የቤ.ቁ. 479/03
14. ሀሰን አሊ ሹራባ
ዕድሜ 46 ዓመት
አድ. አ/አ አ/ከ/ክ/ከተማ ወረዳ 4 የቤ.ቁ. 139
15. ሙኒር ሁሴን ሐሰን
ዕድሜ 31 ዓመት
አድ. አ/አ አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ቀበሌ 19/20 የቤ.ቁ.442
16. ሼህ ሰዒድ ዓሊ ጁሀር
ዕድሜ 30 ዓመት
አድ. አ/አ ን/ላ/ክ/ከተማ ቀበሌ 05/06/07 የቤ.ቁ.
17. ሼህ ሱልጣን ሀጂአማን
ዕድሜ 63 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 02 የቤ.ቁ. አዲስ
18. የሱፍ ጌታቸው
ዕድሜ 36 ዓመት
አድ. አ/አ የካ/ክ/ከተማ ቀበሌ 10 የቤ.ቁ. አዲስ
19. ሼህ ጀማል ያሲን ራጅኡ
ዕድሜ 38 ዓመት
አድ. አ/አ ወረዳ 13
20. ሙባረክ አደም ጌቱ አሊዬ
ዕድሜ 19 ዓመት
አድ. ኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ዞን ቡራዩ ወረዳ ቀበሌ 01
የቤ.ቁ 2531
21. ሼህ ጣሂር አብዱልቃድር አብዱልሀፊዝ
ዕድሜ 63 ዓመት
አድ. አ/አ ን/ላ/ክ/ከተማ ቀበሌ 10/18
22. ካሊድ ኢብራሂም ባልቻ
ዕድሜ 31 ዓመት
አድ. አ/አ ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 10 የቤት ቁ. 856
23. አብዱረዛቅ አክመል ሀሰን
ዕድሜ 26 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ቀበሌ 13/14 የቤት ቁ. 43
24. ሀሰን አቢ ሰኢድ
ዕድሜ 39 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 14 የቤት ቁ. 120/157
25. አሊ መኪ በድሩ
ዕድሜ 40 ዓመት
አድ. አ/አ ኮ/ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 4
26. ሼህ ሀጅ ኢብራሂም ቱሂፋ
ዕድሜ 64 ዓመት
አድ. ኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ዞን ሰበታ ወረዳ ቀበሌ 04
27. ሼህ አብዱራህማን ኡስማን ከሊል
ዕድሜ 58 ዓመት
አድ. አ/አ ከተማ ኮልፌ ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 1 የቤት ቁ. 2825
28. ሀቢባ መሐመድ መሐሙድ (የአቶ ጁነዲን ባለቤት)
ዕድሜ 34 ዓመት
አድ. አ/አ ከተማ ን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 4
29. ዶ/ር ከማል ሀጂ ገለቱ ማሜ
ዕድሜ 62 ዓመት
አድ. አ/አ ኮልፌ ቂ/ክ/ከተማ ቀበሌ 03/02 የቤት ቁ.
30. አልቢር ዴቨሎፕመንት እና ኮኤፕሬሽን አሶሴሽን
አድ. አ/አ ቂ/ክ/ከተማ ወረዳ …… የቤት ቁ. 1059
31. ነማእ የበጎ ድራጎት ማኅበር
አድ. አ/አ ን/ላ/ክ/ከተማ ቀበሌ 06 የቤት ቁ. 062

1ኛ ክስ
(ከ1ኛ እስከ 29ኛ፣ ተከሳሾችን በተመለከተ)

ወንጀሉ:-
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32(1)(ሀ)(ለ)፣ 38(1) እና የፀረ
ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጠር 652/2001 አንቀፅ 3(1)(4)(6) እና 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ።

የወንጀሉ ዝርዝር:-

ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን እና የወንጀል አድማ ስምምነት በማድረግ በመላ ሀሳባቸው እና
አድራጎታቸው የወንጀል ድርጊቱን እና ወንጀሉ የሚሰጠውን ውጤት ሙሉ በሙሉ በመቀበል እና የራሳቸው በማድረግ
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግስት ከተረጋገጠው የእምነት ነፃነት በመቃረን ከራሳቸው አክራሪ አስተሳሰብና አስተምሮት ውጪ
በሀገሪቱ (ኢትዮጵያ) ውስጥ ሌላ እምነት እና አስተሳሰብ እና አስተምህሮት መኖር የለበትም የሚል ሃይማኖታዊ አላማ እና በሀገሪቱ ሃይማኖታዊ መንግስት ማቋቋም /መመስረት/ የሚል የፖለቲካዊ ግብ በማስቀመጥ፤ ቀኑና ወሩ በውል ተለይቶ ካልታወቀበት ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የሀይማኖት አስተማሪዎች ቡድን በማለት በህቡዕ ባቋቋሙት ቡድን
የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ እቅድ በማውጣት እና እስትራቴጂዎችን በመንደፍ፤

በተለይም የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማቋቋም እና በነዚሁ ድርጅቶች አማካኝነት የሽብር አላማቸውን ለማስፈፀም አክራሪነትን በማስፋፋት፤ ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ምንጮች በማሰባሰብና በማሰራጨት፤ ከመጅሊሱ እውቅና ውጪ አክራሪነትን ለማስፋፋት የሚረዱ ተቋማትን በማቋቋም፤ ይህንኑ አክራሪነት የሚሰብኩ መገናኛ ብዙሃንን በመመስረትና በመጠቀም፤ በሃይማኖታዊ ፅንፈኝነትና በአክራሪነት ዙሪያ በውጭ ሀገር ስልጠና በመውሰድና የተፃፉ መፅሐፍቶተን ከተለያዩ ሀገራት በማስመጣትና መፅሐፍቶቹ ላይ ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት ስለሚቻልበት ሁኔታ ውይይት በማድረግ የዝግጅት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ በታህሳስ ወር 2004 ዓ.ም በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ክልል ውስጥ በሚገኘው በአወሊያ ኮሌጅ የኮሌጁ ተማሪዎች ካነሱት አስተዳዳራዊ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተነሳውን አለመግባባት የሽብር አላማቸውን ለማስፈፀም እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር የተማሪዎቹን ጥያቄ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ መፍትሄ የሚያፈላልግ ኮሚቴ በሚል የሽብር ቡድኑን ዓላማ የሚያስፈጽም ኮሚቴ እርስ በርስ በመመራረጥ አቋቁመው ወደ አወሊያ በመሄድ፣ በህዝብ የተመረጡ ለማስመሰል
አስቀድመው ባቀዱት መሠረት የተማሪውን ጥያቄ ሃይማኖታዊ አስተማሪዎች ሊመሩት ይገባል በማለት መድረኩን በመቆጣጠር ባካሄዱት ምርጫ ሕዝቡ ከመረጣቸው 20 ተወካዮች 14ቱን በተለያየ ምክንያት በማስወጣት ከሽበር ቡድኑ ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያራምዱ 11 ሰዎችን በመጨመር “የሙስሊሙ ኅብረተሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” በማለት ሰይመው በሕዝቡ የተወከሉ ለማስመሰልና ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ፊርማ በማሰባሰብ፤ የተማሪዎቹን ጥያቄ ለሽብር አላማቸው በሚመች መንገድ በመቀልበስ ሂደቱን በመቆጣጠርና በመምራት፤ የሽበር አላማቸውን ለማስፈፀም ከጥር 5 ቀን 2004 ጀምሮ በየሳምንቱ አርብ ለፀሎት በአወሊያ መስጊድ ለሚሰበሰበው ሕዝብ፣ የሽብር አላማቸውን ለማራመድ በአዲስ አበባ እና በክልሎች ባዘጋጁት የሰደቃ እና የአንድነት ዝግጅቶች በማለት ለሚጠሩት ሕዝብ፣ በማኅበራዊ ድህረ ገጾች፣ ለዚሁ ተግባር በተቋቋሙት የተለያዩ ሃይማኖታዊ መገናኛ ብዙሃኖች፣ በመፃህፍት፣ በበራሪ ጽሁፎችና ዘጋቢ ፊልሞች አማካኝነት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የእምነት ነፃነቱ ያልተከበረ ሃይማኖታዊ ነፃነቱን የተነፈገ እንደሆነ መንግሰት እንደ ቀድሞ ሥርዓቶች እስልምናን በተቀነባበረ መንገድ እያጠቃና እየጨቆነ እንደሆነ፣ ሃይማኖቱን በግድ እንዲቀይር እያደረገውና ሆነ ተብሎ በከፍተኛ ትምህርት እንዳይማር እየተደረገ እንደሆነ በማስመሰል ህዝበ ሙስሊሙ ጅሃድ በመውጣት ሃይማኖትህን ነፃ ልታወጣ ይገባል!!፤ ገዢው መንግስት አያስተዳድረንም! አክራሪ አስተምህሮት ውጭ የሚያስተምሩ ኢማሞችን መግደል ጅሃድ ነው! ሌላው አስተምህሮት ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ እስካልወጣ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል፣ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት አለብን በማለት ሕዝቡን ለሸብር አላማቸው የቀሰቀሱና ያነሳሱ ሲሆን በተለይም፤

1ኛ ተከሳሽ አቡበከር አህመድ፡ ከላይ በተገለፀውና ለሸብር ዓላማ በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አባልና ራሱን የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ብሎ በሚጠራው ሕገወጥ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን የካቲት 6 ቀን 2004 በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው አወሊያ መስጊድ ውስጥ ለሃይማኖት ስርዓት ለተሰበሰበው ሕዝብ ቢላል የሞተው ለሃይማኖቱ ነው፣
ለሃይማኖታችን መስዋዕትነት መክፈል አለብን፣ መጅሊስ የሚያካሂደውን ስብሰባ እና ሌሎች ዝግጅቶች በረብሻ ማቋረጥ አለብን፣ ሌሎች ከእኛ አስተሳሰብ ውጪ ያሉ አስተምህሮቶች ተጠራርገው እስካልወጡ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል
ማለታቸውን፤
ቀኑ በውል ባልታወቀ በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም ከላይ በተገለፀው ቦታና ተመሳሳይ ሰዓት መስጊድ ውስጥ
ለተሰበሰበው ህዝብ መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ እየገባ በመሆኑ አንፈራም ጅሃድ አውጀናል፤ ሰኔ 17 ቀን
2004 ዓ.ም በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ሀምዛ መስጊድ በተዘጋጀ የሰደቃና አንድነት ፕሮግራም ላይ ለተሰበሰበው
ሕዝብ ለሃይማኖት መሞት ፀጋ ነው መንግስት ሌላ አስተምህሮት ስላመጣብን ለጅሀድ መዘጋጀት አለብን፤
ሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ ተደበደብን፣ ተገረፍን የሚመጣብንን
እንከላከላለን ካልሆነ ግን ህዝባችንን ይዘን ጅሀድ እንወጣለን ሃይማኖታዊ መንግስት እንመሠርታለን በማለት
የተሰበሰበውን ህዝብ የሽብር ድርጊት እንዲፈጽም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፤

2ኛ ተከሳሽ አህመዲን ጀበለ፡ ከላይ በተገለፀው በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አባልና ራሱን የሙስሊሙ መፍትሄ
አፈላላጊ በማለት በሚጠራው ሕገወጥ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ በመሆን፤
በመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ሀምዛ መስጊድ ለተሰበሰበው ሕዝብ እኛ ሙስሊሞች
ሃይማኖታችንን አሳልፈን አንሰጥም፣ ለሃየማኖታችን መስዋዕትነት መክፈል ጅሃድ ነው ብንሞትም ገነት ነው የምንገባው እስልምና ሠላም ስለሆነ ነው እንጂ ዝም ያልናቸውን ሙስሊሙ 80 በመቶ ስለሆነ በአንድ ድምፅ ነው የምናጠፋቸው፤
ቀኑ እና ወሩ በውል ተለይቶ ባልታወቀበት በ2004 ዓ.ም በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው በአወሊያ መስጊድ አዲስ
መጅሊስ እንመርጣለን ይህንን መንግስት ካልተቀበለው እስከ ህይወት መስዋዕትነት እንከፍላለን። አባቶቻችን መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩልን ስለሆነ ይህንን መንግስት አውርደን ሃይማኖታዊ መንግስት ማቋቋም አለብን በማለት፤
ሐምሌ 7 ቀን 2004 ዓ.ም በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ወረዳ 3 ክልል በሚገኘው ሀምዛ መስጊድ ለተሰበሰበው ህዝብ ተጋግዘን ሌሎች አስተምህሮቶችን ማጥፋት አለብን ለእምነታችሁ ስትሉ መሞት አለባችሁ ወደኋላ ማለት የለባችሁም በማለት የሽብር ድርጊት እንዲፈፅሙ በማነሳሳትና በመቀስቀስ፤

3ኛ ተከሳሽ ያሲን ኑሩ፡ ከላይ በተገለፀው በህቡዕ በተደራጀው ቡድንና ራሱን የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ብሎ
በሚጠራው ሕገወጥ ኮሚቴ አባል በመሆን፤
በመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም በአወሊያ መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ስለገባ
ጅሀድ አውጀናል፣ የህይወት መስዋዕትነት እንከፍላለን፣ እስልምናን ለማጥፋት ለሚመጣ አካል አንድ ሆነን እንመልሰው፤ እኛ አንድ ነን መንግስት ሊከፋፍለን ስላሰበ ሁሉም ሙስሊም ለጅሀድ መዘጋጀት አለበት፤
በሰኔ ወር 2004 ዓ.ም በተመሳሳይ ቦታ የሌላ አስተምህሮት ኢማም የሚያስተመራችሁን አስተምህሮ እንዳትቀበሉ እሱ
እምነቱን ክዷል ብትገድሉትም ጅሀድ ነው በማለት
ሐምሌ 7 ቀን 2004 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጊድ ለተሰበሰበው ህዝብ መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ስለገባ
ሙስሊም ሆይ በጋራ ልትነሳ እና ልትወጣ ይገባል፤ የሌሎች አይደግፉንም የሚላቸውን አስተምህሮቶችን በስም እየጠራ
እንኳን ደስ አላችሁ ሙስሊም ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ ተገደሉላችሁ፤
በሐምሌ 08 ቀን 2004 ዓ.ም ከላይ በተጠቀሰው ተመሳሳይ ቦታ ለተሰበሰበው ሕዝብ መንግስት አያስተዳድረንም
አይመራንም፤ ሃይማኖታዊ መንግስት እንመሰርታለን፤ አክራሪ ያልሆነ አስተምህሮ አንቀበልም እስከመጨረሻው በኃይልና በጉልበት የሚጠበቅብንን እንወጣለን ፖሊስ ሙስሊሞችን ገድሏል እናንተ ምን ትጠብቃላችሁ በማለት የተሰበሰበውን ህዝብ የሽበር ድርጊት እንዲፈጽም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፤

4ኛ ተከሳሽ ካሚል ሸምሱ፡ ከላይ በተገለፀው በህቡዕ በተደራጀው የኡሰታዞች /የዳኢወች ቡድን አባልና ራሱን የሙስሊሙ ኅብረተሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ብሎ በሚጠራው ሕገወጥ ኮሚቴ የሕግ ጉዳዮች ተጠሪ በመሆን፤
በመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም በአወሊያ መሰጊድ ለተሰበሰበው ሕዝብ ለሃይማኖታችሁ መስዋዕትነት ክፈሉ መንግስት
ሊከፋፍለን ስለሞከረ ለጅሃድ መዘጋጀት አለብን፤
ሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዘበ መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ
እየገባብን ነው፤ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከ65 በመቶ በላይ ስለሆነ ሃይማኖታዊ መንግሰት እናቋቁማለን
/እንመሠርታለን/፤ ፖሊስ ሙስሊሞችን ገድሏል ስለዚህ ምን ትጠብቃላችሁ በማለት የተሰበሰበውን ህዘብ የሽብር
ድርጊት እንዲፈጽም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፤

5ኛ ተከሳሽ በድሩ ሁሴን፡ ከላይ በተገለፀው በህቡዕ በተደራጀው የኡስታዞች /የዳኢዎች ቡድን አባልና ራሱን
የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ብሎ በሚጠራው ሕገወጥ ቡድን ተባባሪ በመሆን የቡድኑን የሽብር ዓላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም
ሐምሌ 7 እና 8 2004 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ ከእኛ ከአክራሪዎች ውጪ ያላችሁ
ሰው ሞተላችሁ ፖሊስ በአወሊያ ሙስሊሙን ገድሏል እናንተ ምን ትጠብቃላችሁ እኛ ብንታሰር እናንተ ወደቤታችሁ
መግባት የለባችሁም በማለት የተሰበሰበውን ህዝብ የሽብር ድርጊት እንዲፈጽም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፤

6ኛ ተከሳሽ ሼህ መከተ ሙሄ፡ ራሱን የሙስሊሙ ኅብረተሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ብሎ በሚጠራው ሕገወጥ ኮሚቴ አባል በመሆን፤
ሚያዚያ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 6፡00 ሰዓት ሲሆን በአወሊያ መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ
ከእኛ ሌላ ሌሎች አስተምህሮቶች ማስተማር ካላቆሙ እስከመጨረሻው ትግላችንን አናቋርጥም፤
ቀኑ እና ወሩ በውል ተለይቶ ባልታወቀበት በ2004 ዓ.ም በተመሳሳይ ቦታ ለተሰበሰበው ህዝብ መንግስት ከኢትዮጵያ
የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት /መጅሊስ/ ጋር በመሆን ከውጪ መንግስታት በተመደበ 60‚000‚000 (ስልሳ
ሚሊዮን) ዶላር ሌላ አስተምህሮትን ለማስፋፋት እየሰራ ነው፣ ለሃይማኖታችን አንገታችንን እንሰጣለን፣
በዩኒቨርስቲዎች ሰላት መስገድ ተከለከለ፣ መንግሰት ሃየማኖታችንን መርገጥ ጀመረ፣ በማለት የተሰበሰበውን ህዝብ
የሽብር ድርጊት እንዲፈጽም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፤

7ኛ ተከሳሽ ሳቢር ይርጉ፡ የኮሚቴው ተባባሪ እና አጋዥ በመሆን የቡድኑን የሽብር ዓላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም፤
በመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም በአወሊያ መስጊድ ውሰጥ ለተሰበሰበው ህዝብ ትግላችን እስከሞት ይቀጥላል መስዋዕትነት እንከፍላለን፤
በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም በአወሊያ መስጊድ ለተሰበሰበው ህዝብ፤ መንግስት እና መጅሊስ ከአክራሪ አስተሳሰብ
ሌላ ከውጪ መንግስታት 60‚000‚000 ዶላር በመቀበል እየሰሩ ነው ለሃይማኖታችን አንገታችንን እንሰጣለን፤
በሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጊድ ለተሰበሰበው ህዝብ ፖሊስ በአወሊያ መስጊድ ሙስሊሞችን
ገድሏል እናንተ ምን ትጠብቃላችሁ በማለት የተሰበሰበው ህዝብ የሽብር ድርጊት እንዲፈጽም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፤

8ኛ ተከሳሽ መሐመድ አባተ፡ ራሱን የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ብሎ በሚጠራው ኮሚቴ የቅርብ ረዳት እና ተባባሪ በመሆን የቡድኑን የሽብር ዓላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም፤
ሰኔ 21 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ልዩ ቦታው ፈቲህ መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ መጅሊስ
እና መንግስት ሃይማኖታችንን እየከፋፈለብን ነው፤
በሐምሌ 07 ቀን 2004 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መሰጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ ፖሊስ በ6/11/2004 ዓ.ም
በአወሊያ መስጊድ ውስጥ ሙሰሊሞችን ገድሏል ለተገደሉት ፀሎትና ሰላት እናድርግ በማለት በሀሰት ህዝቡን ለሽብር
ድርጊት በማነሳሳት እና የተለያዩ መድረኮችን በመምራት በመንቀሳቀሱ፤

9ኛ፣ 10ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ፣ 13ኛ እና 14ኛ ተከሳሾች ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ከላይ በተገለፀው በህቡዕ በተደራጀው የኡስታዞች /የዳኢዎች ቡድን አባልና እራሱን የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ብሎ በሚጠራው ኮሚቴ ፀሐፊ፣ የቅርብ ረዳት፣ ተባባሪና የሽበር ቡድኑን ጽሁፎች አዘጋጅ በመሆን፤

9ኛ ተከሳሽ አህመድ ሙስጠፋ፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አባል በመሆን ይህንን የቡድኑን
ዓላማ ለማስፈፀም የሚያስችለውን ስልጠና ውጪ ሀገር በመሄድ ስልጠና በመውሰድ ከተመለሰ በኋላ፤ ይህንኑ ስልጠና
ለቡድኑ አባላት በመስጠት ለዓላማው አፈፃፀም ስትራቴጂ በማውጣት ሲንቀሳቀስ ከቆየ በኋላ “የሙስሊሙ ኅብረተሰብ
መፍትሄ አፈላላጊ” በማለት ራሱን የሰየመው ኮሚቴ ፀሐፊ በመሆን በተለያዩ የሰደቃ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍና
በመንቀሳቀስ፤

10ኛ ተከሳሽ ሙራድ ሽኩር፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አባል በመሆን ይህንን የቡድኑን
ዓላማ ለማስፈፀም በሚቻልባቸው ስትራቴጂዎች ላይ በመወያየት እና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ የሽብር
ቡድኑ በኮሚቴ ስም ከተደራጀ በኋላ የቡድኑን የሽብር ዓላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም፤ ከሐምሌ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በሕግ አግባብ በፖሊስ የተያዙትን የቡድኑን አባላት ሕገወጥ በሆነ መንገድ ለማስፈታት በውጭና በሀገር ውስጥ ከሚኖሩ የቡድኑ አባላት ብር 80‚000 በማሰባሰብ፣ በራሪ ወረቀቶችን በማባዛት የሽበር ቡድኑን ዓላማ ለማስፈፀም በመንቀሳቀስ

11ኛ ተከሳሽ አቡበከር ዓለሙ፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አባል በመሆን ይህንን የቡድኑን
ዓላማ ለማስፈፀም በሚቻልባቸው ስትራቴጂዎች ላይ በመወያየት እና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሲንቀሳቀስ ከቆየ በኋላ
የቡድኑን የሽብር ዓላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም ሐምሌ 7 ቀን 2004 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጊድ ግቢ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ መንግስት አወሊያ መስጊድ ውስጥ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ የሃይል እርምጃዎችን በመውሰድ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል በማለት የተሰበሰበው ህዝብ የሽብር ድርጊት እንዲፈፅም በማነሳሳትና በመቀስቀስና የሽብር ቡድኑ ከሚያራምዳቸው ዓላማዎች ጋር ተያያዥት ያላቸው ፅሁፎች በማዘጋጀት፡-

12ኛ ተከሳሽ ኑር ቱርኪ፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አባል በመሆን ይህንን የቡድኑን ዓላማ
ለማስፈፀም በሚቻልባቸው ስትራቴጂዎች ላይ በመወያየት እና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሲንቀሳቀስ ከቆየ በኋላ
በሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም በአራዳ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ቤኒን መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ ከአክራሪዎች
ውጪ ያሉ አስተሳሰቦችን እንቃወማለን፣ መንግስት ከውጪ መንግስታት ገንዘብ ተቀብሎ ነው ወደ ኢትዮጵያ ያስገባው፣ አክራሪነት ውጪ ማስተማር ካላቆመትግላችን ይቀጥላል በማለት የተሰበሰበውን ህዝብ የሽብር ድርጊት እንዲፈፅም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፡

13ኛ ተከሳሽ ሼህ ባህሩ ዑመር፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አባል በመሆን ይህንን የቡድኑን
ዓላማ ለማስፈፀም በሚቻልባቸው ስትራቴጂዎች ላይ በመወያየት እና ውሳኔዎችን በማሳፍ ሲንቀሳቀስ ከቆየ በኋላ፣
የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ.ም በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው አወሊያ መስጊድ ለጸሎት ለተሰበሰበው ህዝብ መከራ
ቢመጣም ወደ ኋላ መመለስ የለብንም፣ ብንመታም ሆን ብንታሰር ወደ ኋላ መመለስ የለባችሁም እስከ ህይወት
መስዋዕትነት መክፈል አለብን በማለት የሰበሰበውን ህዝብ የሽብር ድርጊት እንዲፈፅም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፣

14ኛ ሐሰን አሊ፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በህቡዕ በተደራጀው ቡድን አባል በመሆን ስሀይማኖታዊመንግስት ምስረታ
በተደረገ ውይይት በመሳተፍ እና ይህንን ዓላማ ለማስፈፀም የሚያስችል በ1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች አማካኝነት ስልጠና
በመውሰድና በቤቱም ተመሳሳይ ስልጠና እንዲሰጥ በማመቻቸት ሲንቀሳቀስ ከቆየ በኋላ የቡድኑን የሽብር ዓላማ
በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም ከታህሳስ ወር 2004 ጀምሮ ቡድኑ የጀመረውን ህዝበ ሙስሊሙን ለሽብር ዓላማው
የማነሳሳት እንቅስቃሴ ከጀመረ በኋላ ለኮሚቴው እንቅስቃሴ የሚረዱ በራሪ ወረቀቶችን እና መፃህፍትን በማሳተም
እንዲሁም የሰደቃ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የተሰበሰበውን ህዝብ የሽብር ድርጊት እንዲፈፅም በማነሳሳትና በመቀስቀስ

15ኛ ሙኒር ሁሴን፡ “የሙስሉሙ ህብረተሰብ መፍትሔ አፈላላጊ” በማለት ራሱን የሚጠራው ህገ ወጥ ኮሚቴ የቅርብ
አጋዥና ተባባሪ በመሆን የቡድኑን የሽብር አላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም፡-
ከጥር ወር 2004 ጀምሮ እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው አወሊያ መስጊድ ዘወትር አርብ
በመገኘት “አዎ አሸበሪ ነኝ” “ቢባል የሞተው ለእምነቱ ነው” የሚል ርእስና ይዘት ያላቸው አመፅ ቀስቃሽ ግጥሞች በማቅረብ እንዲሁም ይህ ቡድን ህዝቡን ለአመፅ ለመቀስቀስ ከሚጠቀምበት ስትራቴጂ መካከል ዋነኛው በሆነው በአንድነትና ሰደቃ ፕሮግራሞች ላይ በመገኘት በተለይም መጋቢት ወር 2004 ዓ.ም አየር ጤና በሚገኘው አንሳር መስጊድ፣ በሚያዚያ ወር 2004 ዓ.ም በሸጎሌ አካባቢ በሚገኘው ሰለፊ ሳላህ መስጊድ፣ በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም በካራ ቆሬ አካባቢ በሚገኝ መስጊድ ውስጥ በተዘጋጀ ሰደቃ ላይ የተሰበሰበውን ህዝብ የሽብር ድርጊት እንዲፈፅም በማነሳሳትና በመቀስቀስ፤

16ኛ ተከሳሽ ሼህ ሰዒድ አሊ፡ ራሱን “የሙስሊሙ ህብረተሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” በማለት የሚጠራው የሽብር
ኮሚቴ አጋዥና ተባባሪ በመሆን የቡድኑን የሽብር አላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም፡-
በሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት ሲሆን በቂርቆስ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ቄራ መስጊድ ሰዎችን ሰብስቦ ወደ መስጊድ ውስጥ ይዞ በመግባት እረብሻ በማስነሳት፣ በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ረብሻውን የመራ በመሆኑ እንዲሁም ከላይ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ በጁምአ ስግደት በኋላ በ6/11/2004 በአወሊያ እንዲገኙ ጥሪ በማቅረብ፡-

17ኛ ተከሳሽ ሼህ ኡስማን ሀጂ አማን፡ ራሱን “የሙስሊሙ ህብረተሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” በማለት የሚጠራው
የሽብር ኮሚቴ አባል በመሆን እና ይህንኑ ለማስፈፀም በማሰብ፡- ቀኑና ወሩ በውል ተለይቶ ባልታወቀበት በ2004 ዓ.ም ለኮሚቴው ሰብሳቢ ለሆነው ለ1ኛ ተከሳሽ ብር 200.00 (ሁለት መቶ ሺ) በመስጠት በመንቀሳቀስ

18ኛ ተከሳሽ የሱፍ ጌታቸው፡ “የሙስሊሙ ህብረተሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” በማለት የቅርብ አጋዥና ተባባሪ
በመሆን እና ይህንኑ ለማስፈፀም ቀንና ወሩ በውል ተለይቶ ባልታወቀበት ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ቡድኑ ዓላማውን
ለማስፈፀም ካስቀመጣቸው ስትራቴጂዎች አንዱ የሆነውን አክራሪ እስላማዊ የመገናኛ ብዙሃን በማቋቋም አላማውን
የማራመድና የማሰራጨት ሃላፊነት ወስዶ አመጽ ቀስቃሽ የሆኑና የተዛቡ ዘገባዎችን እና ጽሁፎችን በማውጣት ሕዝቡን ለሽብር አላማው በመቀስቀስ፣

19ኛ ተከሳሽ ጀማል ያሲን፡ ራሱን የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ብሎ በሚጠራው ህገ ወጥና አሸባሪ
ቡድን የኮሚቴ አባል በመሆን የተንቀሳቀሰና ከጥር ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው አወሊያ መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰቡ ወጣቶች ለአመጽ እንዲነሱ ከአክራሪነት ውጪ ያለ አስተምሮ ስለመጣብን ለጅሐድ ተዘጋጁ፣ ንቁ በማለት በመቀስቀስ፣

20ኛ ተከሣሽ ሙባረክ አደም፡ የሽብር ቡድኑን የሽብር አጀንዳ እና ዓላማ በመቀበል እና ይህንኑ ለማስፈፀም፡-
ከጥር ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው አወሊያ መስጊድ ውስጥ ለሚሰበሰበው ህዝብ መንግስት
ከኛ ውጪ ያሉ አስተሳሰቦችን እየደገፈ ነው የሚል የሀሰት ንግግር በማድረግ ሙስሊሞች ሆይ መንቃት አለባችሁ
በማለት የተፈጠረውን ረብሻ ለማረጋጋት የተላኩ የመጅሊስ አመራሮችን ማይክ በመቀማት መኪናቸው ላይ ጉዳት በማድረስ እንዲሁም ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን አመፅ ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመበተንና እረብሻውን በማስተባበር፣

21ኛ ተከሣሽ ሼህ ጣሂር አብዱልቃድር፡ የህዝብ ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ህገ ወጥና አሸባሪ ቡድን ኮሚቴ
እና አባል በመሆን ይህ ቡድን በተለያዩ ጊዜያት የሚያደርጋቸውን ስብሰባዎች በቢሮ ውስጥ በማስተናገድ እና
ለስብሰባው አስፈላጊውን ወጪ በመሸፈን እንዲሁም በ17/8/2008 ዓ.ም ለተለያዩ ግብረ አበሮቹ ስልክ በመደወል
መንግስት መጅሊሱን በራሱ አምሳል መቅረፅ እንደሚፈልግና ሌሎች አስተምህሮቶች የተቆጣጠሯቸውን መስጊዶች ለማፍረስ ወኔ እንደሚያስፈልግና ሕዝቡ ግን ወኔ እንደሌለው በመግለፅ መልእክት በማስተላለፍ ፡- በታህሳስ ወር 2004 ዓ.ም ከኦሮሚያ ክልል ባሌና ምዕራብ አርሲ ዞን የተለያዩ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችን በመጥራት በአከባቢያቸው ሌሎች አስተምህሮቶችን የማጥፋትና የማጥላላት ስራ እንዲሰሩ ትዕዛዝ በመስጠት፡-

22ኛ ተከሳሽ ካሊድ ኢብራሂም፡ የቡድኑን የሽብር ዓላማ በመቀበል ይህንኑ ለማስፈፀም በተለያዩ መስጊዶች በተለይም
በኮ/ቀ/ከቀ/ከተማ ልዩ ቦታው አወሊያ መስጊድ ውስጥ ቀስቃሽ ጽሁፎችን የበተነ በመሆኑና ሐምሌ 6 ቀን 2004
ዓ.ም ከላይ በተገለፀው መስጊድ ውስጥ የሽብር ቡድኑ በ8/11/2004 ለማዘጋት አቅዶት በነበረው የሰደቃ
ፕሮግራም ቅድመ ዝግጅት ሂደት ላይ የተሳተፈ በመሆኑ፡-
ከጥር 7 ቀን 2004 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ለጊዜው በስም ባልታወቁት ግብረአበሮቹ
ስልክ በመደወል መልስ በኮሚቴያችን ብቻ ይሰጠን መጅሊስ የለም ከኛ ውጪ ሌላ አስተምህሮት የለም፤ የተናቀው ህዝብ ታሪክ ይሰራል፤ ከዚህ በኋላ አንከፋፈልም መጅሊስና የሌላ አስተሳሰብ የአይሁድ ስራ ወያላ ስለሆነ እናወግዛለን
አመጽ ቀስቃሽ ወረቀቶችን ሲዲዎች አዘጋጁ፣ ከኛ ውጪ ያለ አስተምህሮት ተቃወሙ፣ ረብሻው መቀጠል እንዳበትና
ለሐይማኖታችን ጠላት የሆኑ ሰዎችን ለይተው መግደል እንዳለባቸው እና ሌሎች አመጽ ቀስቃሽ መልእክቶችን በስልክ
በማስተላለፍ፤

23ኛ ተከሳሽ አብዱረዛቅ አክመል፡ የተባው የኮሚቴውን የሽብር ዓላማ እና አጀንዳ በመቀበል ይህንኑ አጀንዳ
ለማስፈጸም ከሐምሌ 14 እስከ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ለጊዜው ማንነቱ ባታወቀ ግብረ አበሩ ስልክ በመደወል
የኦሮሞ ህዝብንና ክርስትያኖችን ለአመጽ /ሁከት/ ማነሳሳት አለብን በማለቱ የሽብር ቡድኑ አባላት ባስነሱት አመጽ
ምክንያት የታሰሩ የረብሻ ተሳታፊዎች መፈታት አለባቸው በማለት መልእክት ማስተላለፍ፡

24ኛ ተከሳሽ ሀሰን አቢ፡ የኮሚቴውን የሽብር አላማ እና አጀንዳ በመቀበል ይህንኑ አጀንዳ ለማስፈፀም በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው አወሊያ መስጊድ ለተሰበሰበውህዝብ ቀስቃሽ ይዘት ያላቸው ግጥሞችን ወደ መድረክ እንዲቀርቡ በማድረግ እንዲሁም መስጊዱን በመቆጣጠር እና ሰዎችን በመፈተሽ የተሳተፈ በመሆኑ እንዲሁም ከ28/08/04 ዓ.ም ድረስ ላልታወቁ ግብረ አበሮቹ አወሊያ በሚቀጥለው ሳምንት የጁምአ ትግላችን ይቀጥላል፣ እኛ የመቱ ሙስሊሞች ስማችን በደህና ይጠራ ነበር በአሁኑ ሰዓት ግን እስልምናችን እየተረገጠ ይገኛል፤ ሙስሊሞች ለመሆኑ በህይወት እያለን ሃይማኖታችን የማንም አይሁድ እና የማንም ለሆዳቸው ባደሩ መናፍቅ ካድሬዎች መጫወቻ መሆን የለበትም ወይም እንዴት ይሆናል፣ የመቱ ሙስሊሞች ፀጥ ብለው አክራሪ ያልሆኑ ስልጠና መከታተላቸው ትክልል አይደለም፤ ወኔ ይጎድላቸዋል በአንዋር መስጊድ ለሚደረገው ተቃውሞ አፋቸውን የሚለጥፉበት ፕላስተር ማዘጋጀቱንና የሚበተን ወረቀት እንዲያዘጋጅ መመሪያ በመስጠት በተለይም ሚያዝያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም ለ4ኛ ተከሳሽ ለሆነው ካሚል ሸምሱ ስልክ በመደወል ለህገ ወጥ ሰልፍ እንዲዘጋጁ የድምፅና ፅሁፍ መልዕክት በማስተላለፍ፤

25ኛ ተከሳሽ አሊ መኪ፡ የሽብር ቡድኑን አላማ እና አጀንዳ በመቀበልና በመደገፍ ይህን ለማስፈፀም ቀኑና ወሩ
ባልታወቀበት በ2004 ዓ.ም አመፅ ቀስቃሽ በራሪ ወረቀቶችን ፒያሳና አየር ጤና አካባቢ በሚገኙ ኮፒ ቤቶች
በማባዛት ልዩ ቦታው አብዱራህማን መስጊድ ውስጥ ለተሰበሰበው ህዝብ በመበተን ህገ-ወጥና የሽብር ቡድኑ ባቀደው
መሰረት በ1ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ ራሳቸውን ለማቋቋም ባሰቡት የመጅሊስ ምርጫ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም በማድረግ፤
እንዲሁም የሰደቃና የአንድነት ፕሮግራሞችን በቁጥር 7 የሚሆኑ መስጊዶች ላይ እንዲዘጋጁ በማስተባበር፤ ከግንቦት
23 ቀን 2004 እስከ ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ለጊዜው ማንነታቸው ላልታወቀ ግብረአበሮቹ ስልክ
በመደወል እና መልእክት በማስተላለፍ የሽብር ቡድኑ አባላት ማለትም 1ኛ 2ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ስለታሰሩ
ተቃውሟችን ይቀጥላል የሚል መልዕክት በማስተላለፍ፤

26ኛ ተከሳሽ ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፡ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ከሳውዲ ኤምባሲ የሃይማኖት ክፍል በወር 7 ሺህ ሪያል
እየተቀበለ ሃይማኖትን እንደሽፋን በመጠቀም የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ቡድኖችን ጋር በመሆን
በ2004 ዓ.ም የቡድኑ አመራሮችን ተከሳሹ ቀደም ብሎ ባቋቋመው የኦሮሚያ እስላማዊ ጥሪ ማህበር በሚባል
መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በሚስጥር ስብሰባ እንዲያደርጉ በማመቻቸት፣ ከአክራሪ ውጪ ያሉ አስተምሮቶች
በግድ እየተጫነብን ነው በሚል በማነሳሳት፤
በተለይም በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም ከየት እንደሚመጣ የማይታወቅ በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ በተቃውሞ ሰበብ
ለተነሳው የአመጽ ተግባር እንዲውል በማሰብ ለተለያዩ ግለሰቦች በማከፋፈል በመጨረሻም “እስካሁን ለሰዎች
ያደልኩትን ገንዘብ ደህንነት አውቆብናል መረጃ ሰምቻለሁ” በሚል የተረፈውን 500000 (አምስት መቶ ሺህ) ብር
በመሰወር፣ በወንጀል ተፈላጊ ሸህ መሀመድ ሁሴን የተባለ የቡድኑ አባል የነበረና በአሁኑ ሰዓት ሣውዲ አረቢያ
የሚገኝ በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም በእስር ላይ ለሚገኙ የቡድኑ አባል የሆኑ ቤቶሰቦቻቸው መርጃ በሚል ከተላከለት
ብር ለ22 የእስረኛ ቤተሰቦች 88000 (ሰማኒያ ስምንት ሺህ ብር) በማከፋፈል የተከሳሾችን ድርጊት በመደገፍና
ተሣታፊ በመሆን፡-

27ኛ ተከሳሽ ሼህ አብዱራህማን ኡስማን፡ ለረዥም ጊዜ ወደ ሳውዲ አረቢያ በመሄድ የአክራሪነትን ትምህርት ወስዶ
በ1991 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመግባት አዲስ አበባ በሚገኘው የሣውዲ አረቢያ ኤምባሲ የሃይማኖት ክፍል (ሙልቅ
ሰቃፊ) በወር 14000 አስራ አራት ሺህ ብር በደመወዝ መልክ እየተከፈለው የአክራሪነትን ትምህርት የሚያስፋፋ፡-
• በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ከመጅሊስ ዕውቅና ውጭ አክራሪነት የሚስፋፋባቸው 71
የሚደርሱ መስጊዶችን በማስገንባት በሚቀጥራቸው ሰዎች አማካኝነት አክራሪነት እያስፋፋ የሚገኝና ከአክራሪ
አስተሳሰብ ውጪ ያሉትን እናስወግዳለን በሚል ለሚንቀሳቀሰው ቡድን በተለያዩ ዘዴዎች ድጋፍ ሲያደርግ የነበረ
በመሆኑ፡-
• ቀደም ሲል የነበረው እስልምና ሀራም ነው፤ እድር የሚባል ነገር መኖር የለበትም፤ ከመንግስት የመሬት ማዳበሪያ ወስዶ መጠቀም ሀራም ነው፤ ሱሪ ያላሳጠረ ሙስሊም አይደለም፤ ሌሎች የእስልምና አስተማሪዎች ሃይማኖት የሌላቸው
ስለሆኑ ጀሀድ ሊደረግ ይገባል በማለት ህዝቡን በመከፋፈልና ለግጭት በማነሳሳቱ፤
• ይህንኑ የአክራሪነት አላማውን ለማስፋፋት በሚል ለ28ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሀቢባ መሀመድ በተለያየ ጊዜ 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ በመስጠት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አክራሪነትን በማስፋፋትና ይህንኑ ለማድረግ የሚያስችል ቦታ
እንዲሰራ በማድረግ፡-

28ኛ ተከሳሽ ሀቢባ መሀመድ፡ ከ27ኛ ተከሳሽ አብዱራህማን ኡስማን ጋር በመገናኘትና 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ
በመቀበል ከመጅሊሱ እውቅና ውጭ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አክራሪነትን በማስፋፋት፣ ቦታውን በማስገንባትና በአ/አበባ ከሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ የሃይማኖት ክፍል ግንኙነት በመፍጠር ለአክራሪነት ማስፋፊያ የሚሆን በቀን 09/11/2—4 ዓ.ም 50.000 (ሀምሳ ሺህ ብር) በመቀበል እንዲሁም ለህገ ወጥ አላማ እየተጠሩ የነበሩትን
የሰደቃ ፕሮግራም ለመደገፍ የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይዛ ስትንቀሳቀስ እጅ ከፍንጅ በመያዟ፡-

29ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ከማል ሀጂ ገለቱ፡ ወደ ውጪ ሀገር በመሄድ የአክራሪነትን ትምህርት ተከታትሎ ወደ ኢትዮጵያ
በመግባት አዲስ አበባ በሚገኘው የሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ የሀይማት ክፍል (ሙልቅ ሰቃፊ) በወር 20.000 ሺህ
ብር በደመወዝ መልክ እየተከፈለው የአክራሪነትን ትምህርት የሚያስፋፋ፡-
• በዚሁም የአክራሪነት ተግባር በየጊዜው ለሃይማት ክፍሉ ሪፖርት በማቅረብ እና የሽብር ተግባር ለመፈፀም
የተንቀሳቀሰውን ቡድን በህቡዕ በመሰብሰብና የምክር ድጋፍ በመስጠት በመሳተፉ፡-

በአጠቃላይ ተከሳሾች ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አላማቸውን ለማራመድ በማሰብ ይህንኑ ለማስፈፀም ከላይበተገለፀው መልኩ በመደራጀትና የህዝብ ሙስሊሙን ጥያቄ ለመፍታትና ለሚመለከተው አካል እናቀርባለን በሚል ሽፋን ባቋቋሙት ሕገ ወጥ ኮሚቴ ሰዎችን በማደራጀትና በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራትና የሀገሪቱን መሰረታዊ ፖለቲካዊና ህገ መንግስታዊ ተቋማትን ለማናጋት የጅሐድ እና የአመጽ ጥሪ አድርገው በማነሳሳት በተለይ ከላይ በተገለፀው ኮሚቴ የህዝብ ሙስሊሙን ጥያቄ ለመንግስት ለማቅረብ ተወክያለሁ በማለት ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር እንደ ሽፋን የሚጠቀሙባቸውን ጥያቄዎች አቅርበው፤ የካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም መልስ ቢሰጣቸውም ለጥያቄያችን መልስ አልተሰጠንም በሚል የሽብር ተግባሩ
እንዲቀጥል በማድረግ በአ/አበባ በተለያዩ ቦታዎች ረብሻ በማስነሳት በተለይም

ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ታላቁ አንዋር መስጊድ እና አወሊያ መስጊድ
በተነሣ ረብሻ 1ኛ /ኮ/ር ግርማይ ገ/ሚካኤል በተባሉት የግል ተበዳይ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰ በመሆኑ
እንዲሁም
1ኛ/ በአወሊያ መስጊድና ት/ቤት ላይ ግምቱ 55000 (ሀምሣ አምስት ሺህ ብር) የሚሆን የንብረት ጉዳት የደረሰ በመሆኑ
2ኛ/ ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ በነበሩት የሠሌዳ ቁጥራቸው ኮድ3-75189፣
ኮድ3-73962፣ ኮድ3-005534፣ ኮድ3-76592 እና ኮድ3-19067 የአንበሳ አውቶብሶች ላይ የብር
61944 (ስልሣ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ አርባ አራት) የሚገመት የንብረት ጉዳት፣
3ኛ/ ንብረትነቱ የበድር ህንፃ ነጋዴዎች ኃ.የተ.የግ.ማህበር በሆነው ህንፃ ላይ የብር 27347 (ሃያ ሰባት
ሺህ ሶስት መቶ አርባ ሰባት ብር) የሚገመት የንብረት ጉዳት እንዲደርስ በማድረጋቸው
4ኛ/ ንብረትነታቸው የግል ተበዳይ አቶ ተሻለ ዳኜ የሆነ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-69292 አ.አ እና ሱፍያን
በያን የሆነ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2-82203 ተሽከርካሪዎች ላይ ግምቱ 7500 (ሰባት ሺህ አምስት መቶ ብር)
የሚሆን የንብረት ጉዳት የደረሰ በመሆኑ በአጠቃላይ በድምሩ 151791(አንድ መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ ሰባት መቶ
ዘጠና አንድ) ብር የሚገመት የንብረት ጉዳት በማድረሳቸው በፈፀሙት የሽብር ድርጊቶችን መፈፀም ወንጀል ተከሰዋል።

2ኛ ክስ (ከ1-29ኛ ባሉ ተከሳሾች ላይ ብቻ)

ወንጀሉ:-
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27/1/32/1/ሀ/፣ለ እና 38/1/፣
238/1/ሀ/እና/2/ በመተላለፍ

የወንጀሉ ዝርዝር:-
ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን እና በወንጀል አድማ ስምምነት፣ ህገ መንግስቱንና
ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ በማሰብ ቀንና ወሩ ባልታወቀበት ከ2001ዓ.ም ጀምሮ የሃይማኖት አስተማሪዎች
ቡድን በማለት በህቡዕ ባቋቋሙት ቡድን በሀገሪቱ ሃይማኖታዊ መንግስት ማቋቋም /መመስረት/ የሚል ፖለቲካዊ ግብ በማስቀመጥ የረጅም፣ የመካከለኛ እና አጭር ጊዜ ዕቅድ በማውጣት እና እስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ ከላይ በ1ኛ ክስ በተዘረዘሩት የወንጀል አፈፃፀም አማካኝነት፤
* በሕገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን የሃይማኖት እኩልነትን ለማፍረስ በማሰብ ከአክራሪ እምነት ውጪ ሌላ እምነት
መወገድ እንዳለበት በምትኩ አክራሪነት እንዲስፋፋና ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች እንዲፈርሱ የተለያዩ የአመፅና
ሽብር ቅስቀሳዎች በመፈፀም
* ሐምሌ 7 ቀን 2004 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጊድ በተሰበሰበው ህዝብ መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ስለገባ
ሙስሊም በጋራ ልትነሳና ልትወጣ ይገባል
* ፖሊስ ሙስሊሞችን ገድሏል እናንተ ምን ትጠብቃችሁ
* መንግሥት ከኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት /መጅሊስ/ ጋር በመሆን ከውጭ መንግስታት በተመደበ 60
ሚሊዮን ዶላር ከኛ ውጪ ያሉትን አስተሳሰቦችን ለማስፋፋት እየሰራ ነው። ለሃይማኖታችን አንገታችንን እንሰጣለን፣
በዩኒቨርስቲዎች ሶላት መስገድ ተከለከለ፣ መንግስት ሃይማኖታችንን መርገጥ ጀመረ፣ ለሃይማኖታችን አንገታችንን
እንሰጣለን
* የኦሮሞ ህዝብንና ክርስቲያኖችን ለአመፅ /ሁከት/ ማነሳሳት አለብን
* ሙስሊሙ ህብረተሰብ የእምነት ነፃነቱ ያልተከበረ እና ሃይማኖታዊ ነፃነቱን የተነፈገ ሆኗል። ገዢው መንግስት አያስተዳድረንም፤
* መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ እየገባ በመሆኑ አንፈራም ጅሀድ አውጀናል ይህንን መንግስት አውርደን ሃይማኖታዊ
መንግስት ማቋቋም አለብን።
የሚሉና የመሳሰሉትን የሚያሳሱና በህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ አመኔታን የሚያሳጡ ንግግሮች፣ ፅሁፎችና
የመሳሳሉትን በመጠቀም ለአመፅና ለሽብር ተግባር በማዘጋጀትና አመፅ በማስነሳት በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት
በማድረስና ንብረት በማውደም በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ሆነው በፈፀሙት ህገ-መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ
ስርዓቱን የማፍረስ ሙከራ ወንጀል ተከሰዋል።

3ኛ ክስ (በ30ኛ ተከሳሽ ላይ)

ወንጀሉ:-
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 34(1) እና የፀረ ሽብርተንነት አዋጅ ቁጥር
652/2001 አንቀጽ 5(1) መ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ፤

የወንጀሉ ዝርዝር:-
ተከሳሽ በ17ኛ እና በ10ኛ ተከሳሾች ሥራ አስኪያጅነትና ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ሲተዳደር የተቋቋመለትን የበጎ
አድራጎት አላማና ህጋዊ ግዴታ በመጣስ ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ የተጠቀሰው የሽብር ቡድኑን አላማና እቅድ ለማራመድና
ለማሳካት
1ኛ ቀኑ በትክልል ካልታወቀበት ጥር ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ጎፋ ተብሎ
በሚጠራው አካባቢ ህቡዕ የሽብር አጀንዳ የያዘውን የሽብር ቡድን ያደርግ የነበረውን ስብሰባ ቦታ በማዘጋጀትና
የመስተንግዶ አገልግሎት በመስጠቱ፡-
2ኛ ሚያዚያ 4 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ሲሆን ን/ላ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ሳር ቤት ካርል
አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የማህበሩ ንብረት በሆነው ኮድ ዕድ 35-3574 ተሽከርካሪ የሽብር ቡድኑ
ለአመጽና ረብሻ መቀስቀሻነት ይጠቀምበት የነበረውን በራሪ ወረቀት ለመበተን በ10ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ በማህበሩ
ሾፌር አሽከርካሪነት ጭኖ ሲንቀሳቀስ የተያዘ በመሆኑ በፈፀመው ለሽብርተኝነት ድጋፍ በመስጠት ወንጀል ተከሷል።

4ኛ ክስ (በ31ኛ ተከሳሽ ላይ)

ወንጀሉ:-
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 34(1) እና የፀረ ሽብርተንነት አዋጅ ቁጥር
652/2001 አንቀጽ 5(1)መ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ።

የወንጀሉ ዝርዝር:-
ተከሳሽ በ21ኛ ሥራ አስኪያጅነት ሲተዳደር የተቋቋመለትን የበጎ አድራጎት አላማና ህጋዊ ግዴታ በመጣስ ከላይ
በ1ኛ ክስ ላይ የተጠቀሰው የሽብር ቡድኑን አላማና እቅድ ለማራመድና ለማሳካት ቀኑ በትክክል ካልታወቀበት ጥር
ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ ን/ላ/ክ/ከተማ ልዩ ቦታው መካሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 21ኛ ተከሳሽን በአባልነት
የያዘው የሽብር ቡድን ያደርግ ለነበረው ስብሰባ ቦታ በማዘጋጀትና የመስተንግዶ አገልግሎት በመስጠቱ በፈፀመው
ለሽብርተኝነት ድጋፍ መስጠት ወንጀል ተከሷል፡

በክሱ ላይ ከሰነድ ማስረጃ በተጨማሪ
የሰው ምስክሮች ብዛት 192 (አንድ መቶ ዘጠና ሰባት) ሲሆን ለምስክሮች ደህንነት ሲባል በአዋጅ
ቁ.652/2009 አንቀጽ 32 መሰረት ለተከሳሾች የማይደርስ፤ መሆኑን ክሱ አመልክቷል።
****************
*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 31, 2012.
Republished here with the permission to do so, without implying
endorsements.

Check the drop down menu for posts on related topics.

Daniel Berhane

more recommended stories