Sendek | አረና፣ ሕወሓት በትግራይ የመንግስት ሰራተኞች ላይ የፖለቲካ ሙስና እየፈፀመ ነው አለ

(በዘሪሁን ሙሉጌታ)

የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ በሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ላይ የፖለቲካ ሙስና እየፈፀመ ነው ሲል አረና ትግራይ ለዲሞኪራሲና ለሉአላዊነት (አረና) አማረረ።

የአረና ትግራይ በሉአላዊነት ፓርቲ (አረና) ለሰንደቅ በላከው መረጃ ህወሓት አቶ መለስ ዜናዊ በጠና ታመዋል እየተባለ በሰፊው መወራት ከጀመረበት የ2004 ዓ.ም የክረምት ወቅት ጀምሮ የትግራይ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ህወሓት አባል የሆኑና ያልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ተጠንቶ በአስቸኳይ እንዲቀርብ ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም በተ ፃፈ ሰርኩላር ደብዳቤ ለሁሉም በመቀሌና በክልሉ ለሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች መላኩን አስታውቋል።

ፓርቲው ሰርኩላሩን በማስረጃነት አስደግፎ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ እንዳስታወቀው ገዢው ፓርቲ ህወሓት የመንግስት ሠራተኞች መቶ በመቶ አባል ለማድረግ የያዘው እቅድ ፓርቲውን በእጅጉ እንደሚያሳስበው አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህይወት የመኖር ተስፋ የላቸውም የሚለው አስተያየትና ዜና እያየለ በመጣበት ወቅት የክልሉ መስተዳድር የመንግስት ሠራተኞችን የህወሓት አባል የሆነና ያልሆነ በሚል ቆጠራ መግባቱ የመለስ ራዕይ አራማጆቹ ጭንቀት ውሰጥ እንዲገቡ ያስገደዳቸው መሆኑን ያሳያል ብሏል።

የክልሉ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ በመንግስት ማህተምና የፅሕፈት መሳሪያ ፣ ግብር ከፋዩ በሚከፍለው ገንዘብ በሚተዳደሩ የመንግስት ሠራተኞችን የድርጅት ጉዳይ ሠራተኛ አድርጎ ማሰራት የመለስ ራዕይና አደራ ጠብቆ የፖለቲካ ሙስና መፈፀም ነው ብሏል። የአቶ መለስ ራዕይ የመንግስትን ተቋማት ለገዢው ፓርቲ አገልጋዮች በማድረግ የፖለቲካ ሙስናን ማራመድና የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብን የክልሉ በአፍጢሙ መድፋት ሆኗል ሲልም ከሷል።

የአቶ መለስ ራዕይ አራማጆችም ሥራቸው ይህንኑ የጥፋት መንገድ መጠበቅ ከሆነ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚያፋልስና የህብረ ፓርቲ ስርዓትን የሚንድ ተግባር ስለሆነ የደርግን ስርዓት ደምስሶ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን የከፈሉ እጅግ ውድና ብዙ የትግራይ ወጣት ሰማዕታት መካድ መሆኑን ያረጋግጣል ያለው አረና ለነገሩ አሁን ሁሉም ሰማዕታት ተረስተውና ተክደው ሁሉም ሥራ የመለስ ነው ተብሎ ታውጆልናል ሲል ገልጿል።

የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ በርኧ ድርጊቱ የክልልን ህገ-መንግስት ፣ የሲቪል ሰርቪስ አዋጅና የፓርቲዎች የስነ-ምግባር ደንብን የጣሰ መሆኑንም በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል።

አረና በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ በርካታ አባላት እንዳሉት የገለፁት አቶ ብርሃኑ ድርጊቱ አባሎቻችን እድገት እንዳያገኙና በቁጥጥር ውስጥ እንዲገቡ ያደረገ ነው ብለዋል።

የትግራይ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊዎችን ሁኔታውን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገን አልተሳካልንም። በዚህ ጉዳይ ምላሻቸውን እንዳገኘን ለመዘገብ እንደምንችል እንገልፃለን።

****************
*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 24, 2012. Republished here with the permission to do so, without implying endorsements.

Check the drop down menu for posts on related topics.

Daniel Berhane

more recommended stories