On PM Meles Zenawi death: ከሚኒስትሮች ም/ቤት የተሰጠ መግለጫ [Official statement]

ከኢፌዴሪ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች

የኢፌዴሪ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አገራችንን ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በከፍተኛ ብስለትና ብቃት ሲመሩ የቆዩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካደረባቸው ህመም ለመፈወስ በውጭ አገር በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ በትላንትናው እለት ከምሽቱ 5፡40 በድንገት ማረፋቸውን ለመላው የአገራችን ህዝቦ በታላቅ ሃዘን ይገልፃል፡፡

ክቡር ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ላለፉት ሁለት ወራት በህክምና ሲረዱና በጤናቸው ላይ መሻሻል ሲታይ ከቆየ በኋላ ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በተከሰተ ድንገተኛ ኢንፌክሽን እንደገና ህመማቸው ተባብሶ ለአስቸኳይ የህክምና ርዳታ ወደ ሆስፒታል ገብተው በህክምና ሙያተኞችም ከፍተኛ እገዛ ቢደረግላቸውም በትላንትናው እለት ከምሽቱ 5፡40 ላይ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት የሚንስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነትና በታማኝነት አገራቸውን አገልግለው ከፍተኛ የለውጥ ተስፋ ያሳዩንን ክቡር ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ እልፈተ ህይወት ሲገለፅ በሀዘን በተሰበረ ልብ ነው፡፡ ጠ/ሚ/ር መለስ ከምንም ነገር በላይ አገራቸውንና ህዝባቸውን የሚወዱ ለዚህች አገርና ህዝብ የላቀ ራዕይ የነበራቸው መሪ ነበሩ፡፡ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ራዕያቸውን እውን ማድረግ የጀመረና አስተማማኝ ውጤት ማምጣት የቻለ ድርጅትና መንግሥት የገነቡ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ መጠራት እንድትጀምር ያደረጉ ታላቅና እጅግ አርቆ አሳቢ መሪ ነበሩ፡፡ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ አገራችን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ እንድትጓዝ ጥራት ያላቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነድፈው በብቁ አመራራቸው በገነቧቸው ድርጅትና መንግሥት አማካይነት ተግባራዊ ማድረግ የቻሉና በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለው ታላቅ አገራዊ የህዳሴ ጉዞ በሰመረ አቅጣጫ እንዲጓዝ ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡

ክቡር ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ በአገራችን ህገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፣ የህዝቦች እኩልነትና የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገ-መንግስታዊ ዋስትና አግኝተው በተግባር ላይ እንዲውሉ በአገራችን  መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና በድህነት የሚማስኑ ወገኖችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ተግባር የፈፀሙ፣ ኢትዮጵያን በአዲስና ፅኑ ዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ ያዋቀሩ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያና አፍሪካ ታላቁን የለውጥ ሃዋሪያ ልጇቸውን አጥተዋል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ትንሳኤ ያበሰረው አዲስ የአመራር ትውልድ አርቆ አሳቢ መሪያቸውን በሞት ተነጥቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አገራችንን በከፍተኛ ደረጃ ለመለወጥ የሚያስችለው የታላቁ የአምስት ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ መሃንዲስ ከመሆናቸውም በላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ካደረባቸው ህመም ጋር እየታገሉ የዕቅዱን ተግባራዊነት የመሩና ባሰቡት መሰረት አገራችን የጀመረችው ተከታታይ ፈጣን እድገት የማስመዝገብ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያደረጉ ታላቅ የህዝብ ልጅ ነበሩ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለአፍሪካ ቀንድና ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ መሪ ናቸው። ኢትዮጵያ ለሶማሊያ፣ ለደቡብና ሰሜን ሱዳን፣ ለሩዋንዳ፣ ለብሩንዲና ለላይቤሪያ ዘላቂ ሰላም ያደረጓቸውን አስተዋፅኦ ታሪክና መላ አፍሪካውያን የማይዘነጉት ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአፍሪካ ህዝቦች ድምፅ እንዲሰማ፣ አፍሪካ በንግድና በልማት፣ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ በሰላምና መረጋጋት አቅጣጫ እንድትጓዝ ታላቁን የኔፓድ ፕሮግራም ከአፍሪካውያን የትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ያመነጩና ይህን የተቀደሰ ሃሳብ በአገራቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን  በርግጥም የተለመደ አህጉራዊ ኃላፊነቷን ከውስጧ በመጀመር እንድትወጣ ያበቁ ታላቅ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ህዳሴ መሪ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በዓለማችን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲዋቀር የታዳጊ አገሮች ድምፅ በመሆን፣ በዓለም አደባባይ የተሟገቱና ተቀባይነት ያተረፉ፣ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡ በዓለማችን የተፈጥሮ ሃብት ሚዛን እንዲጠበቅ፣ በቃላቸው መሰረት ኢትዮጵያ የአረንጓዴው ልማት ሃሳባቸው ተግባራዊ ማሳያ እንድትሆን ያደረጉ ታላቅና በሳል መሪ ነበሩ፡፡  በብስለታቸውና በአርቆ አሳቢነታቸው በአገራችን የበራውን የተስፋ ሻማ የለኮሱ ኢትዮጵያንና መላውን የጥቁር ማህበረሰብ ያኮሩ፣ መላው ዓለም ብቃታቸውን የመሰከረላቸው ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ህልፈተ ህይወት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለማችንም አንድ አርቆ አሳቢ አእምሮና የለውጥ ኃይል እንዳጣች በፅኑ የሃዘን መንፈስ ይገነዘባል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦችና

የኢትዮጵያ ወዳጆች

በክቡር ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ አለጊዜ መሞት የኢፌዴሪ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአገራችን አስተማማኝ ዴሚክራሲያዊና ልማታዊ ህገ መንግስታዊ ስርዓት ገንብተው በማለፋቸው ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ይፅናናል፡፡   የጠ/ሚ/ር መለስ የለውጥ ሃሳቦች ዛሬ የ80 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሃሳቦች ሆነዋል፡፡  የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጅምራቸው በመላ አፍሪካዊያን ዘንድ አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ፣ ለለውጥና ለተሻለ ህይወት መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡

የጠ/ሚ/ር መለስ ፖሊሲና ስትራቴጅዎች መቼም ቢሆን ደከመንም በማያውቁ የትግል አጋሮቻቸውና ድርጅታቸው እንዲሁም በልማታዊ መንግስታችንና በመላ የአገራችን ህዝቦች ንቁ ተሳትፎ በከተማና በገጠርም በተግባር ተተርጉመው አገራችንን በፍጥነት ለመለወጥ የሚያስችሉ ፍቱን አቅጣጫዎች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡  ታላቁ መሪያችን ዛሬ ከጎናችን ቢለዩም ትተውልን የሄዱት ህገ-መንግስታዊ፣ ልማታዊና ዴሞክራዊያዊ ስርዓት ከአለት በፀና መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ በታላቁ መሪያችን ምንጊዜም ቢሆን እንድንኮራ፣ በራሳችን ያለን መተማመን ከፍተኛ እንዲሆንና በሀገራችን በመካሔድ ላይ ያለውን የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን የማድረግ ጉዞ መቼም ቢሆን እንደማይቀለበስ አረጋግጦልናል።

ኢትዮጵያ ታላቋን መሪዋን በማጣቷ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ብትሆንም የ/ጠ/ሚ/ር መለስ ብሩህ አእምሮ ያፈለቃቸው መሰረታዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተጠናክረው ተግባራዊ መሆን ይቀጥላሉ፡፡ በህገ-መንግስታችን የተከበሩ የግልና የቡድን  መብቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰፍተውና ጎልብተው ይቀጥላሉ። በሀገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ በጠ/ሚ/ር መለስ ፈለግና ራዕይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በአፍሪካ በመጫወት ላይ ያለችው ገንቢ፣ ሰላማዊና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥል ከመሆኑም በላይ ሀገራችን ዛሬም እንደትላንቱ የመልካም ጉርብትና አብነት ሆና ትቀጥላለች፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትላንቱ በአፍሪካ ህብረትና በዓለም አደባባይ የምትጫወተው ገንቢ ሚና ጠ/ሚ/ር መለስ ባስቀመጡት ራዕይና ፈለግ በመመራት ተግባራዊነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች

ታላቁ የሀገራችን መሪ ክቡር ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ የመታመማቸው ወሬ ከተሰማ በኋላ  የሀገራችን ህዝቦች ለመሪያችን ልዩ ልባዊ ፍቅር በማሳየትና በየእምነታቸው መሰረት በፀሎት መልካም ምኞታቸውን ሲገልፁ እንደቆዩ በከፍተኛ አድናቆት ተገንዝቧል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መላ የሀገራችን ህዝቦች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ሀገራቸውን በተረጋጋ ሰላማዊና ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስቀጠል ላደረጉት ከፍተኛ ትግል ያለውን አድናቆት እየገለፀ ከእንግዲህም ሀገራችንን ከዚህ አስቸጋሪ ነገር ግን በአስተማማኝ ሁኔታ ከምናልፈው ወቅት ባሻገር ለዘላቂ እድገቷ፣ ሰላሟና የህዝብ ተጠቃሚነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እንድትንቀሳቀስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በርካታ የአፍሪካና የዓለም መሪዎች የታላቁ መሪያችንን ጤንነት ሁኔታ ከሰሙ በኋላ በተለያዮ መንገዶች ለላኩልን የመልካም ምኞትና የድጋፍ መግለጫ የኢፌዴሪ መንግስት የሚንስትሮች ምክር ቤት በከፍተኛ አድናቆት እንደሚመለከተውና በዚህም አጋጣሚ ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገሮች ጋር የፈጠረችውን መልካም ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ለመግለጽ ይወዳል፡፡

ክቡር ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ በህክምና ሲረዱ በቆዩበት ወቅት  ከአጠገባቸው ሳይለዩ የተቻላቸውን ሁሉ ድጋፍ ላደረጉና የመሪያችንን ጤንነት ለመመለስ አቅማቸው የፈቀደውን ትብብር ላደረጉልን የህክምና ሙያተኞች የኢፌዴሪ መንግስት ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀብር ስነ-ስርዓት የሚፈፀምበትን ሒደት በማስመልከት ቀጣይ መግለጫዎችን የሚያቀርብ ሲሆን በህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረት ክቡር ም/ጠ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እየመሩ ይቀጥላሉ፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች

ሀገራችን ታላቁንና አርቆ አሳቢውን መሪዋን በማጣቷ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ከመቼም ጊዜ በላቀ ሁኔታ የጠ/ሚ/ር መለስን የለውጥና የሀገር ግንባታ ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ በከፍተኛ ሀገራዊ  የአንድነት መንፈስ ልንረባረብ የምንገደድበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ የኢፌዴሪ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህ አስቸጋሪ ወቅት በአስተማማኝ ሁኔታ ታልፎ ሀገራችን በእርግጥም የተነደፈላትን የለውጥ ራዕይ ተግባራዊ እንድታደርግ ከመቼም ጊዜ በላቀ አንድነትና የትግል መንፈስ እንድንረባረብ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለመላው የሀገራችን ህዝቦችና ለታላቁ መሪያችን ለአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰቦች መፅናናትን ይመኛል፡፡

 

 

 

Daniel Berhane

more recommended stories