Addis Zemen|የጠ/ሚኒስትሩን መታመም ተከትሎ ጎንበስ ቀና መብዛቱ ያስተዛዝባል

(ዳርእስከዳር)

እውነት ነው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ካየናቸው በርካታ ቀናትን አስቆጥረናል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ከፍተኛ ኃላፊነትን ተሸክሞ ጧት ማታ ሲባዝን የኖረን ሰው፣ መታያው ብዙ መገኛውም በርካታ የነበረን መሪ ማየት ማቆም ያስደነግጣል፡፡

የእርሳቸውን ከዓይን ዞር ማለት ተከትሎ ግን የአገር ውስጥም ይሁኑ የውጭ መገናኛ ብዙኃንና የተለያዩ አካላት የሚሉትና እያስባሉት ያለው የወሬ ድሪቶ ያስተዛዝባል፡፡ እነዚህ አካላት ‹‹ደረሰን፣ ደረስንበት፣ እርግጠኛ ነን፣ ይባላል፣ ሲሉ ሰምተናል፣ ታማኝ ምንጮቻችን ያደረሱን ነው…›› ወዘተ ወዘተ የሚሉ ወሬዎቻቸውን ዛሬም ድረስ አለማቆማቸውን ልብ ያላለ ሰው አላማቸው ምን እንደሆነ ግልጽ አይሆንለትም፡፡

በእኔ እምነት ከእዚህ የወሬ ጋጋታ ጠብ የሚለው አንድ ሃቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመም ብቻ ነው፡፡ ሌላውማ እንኳን ለእኛ አንባቢዎችና አድማጮች ይቅርና የወሬው ጸሐፊዎችም ስለሚጽፉት ነገር በቅጡ የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ ብቻ ነጋ ጠባ ይጽፋሉ፤ ያወራሉ፡፡ እኔ ግን እላለሁ ‹‹አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል››፡፡

አሁን አሁንማ የወሬዎቹ አናፋሽ ሚዲያዎች ‹‹እርሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸውና ለምን ታመሙ? ወይንም ለምን ይታመማሉ?›› የሚል አቋም የያዙ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ነጋ ጠባ የሚያወሩትና የሚያስወሩት በዚህ ዙሪያ ያሉ የፈጠራ ወሬዎችን ብቻ ሆኗልና ነው፡፡

በግሌ ግን የአቶ መለስ መታመም ይሄንን ያህል ሊያነጋግር አይገባም ብዬ አምናለሁ ፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ በሥራ ላይ እያሉ የታመሙ የመጀመሪያው መሪ አቶ መለስ ብቻ አይደሉምና፡፡ እንደተባለው ሰው ናቸው ሰው ደግሞ ይታመማል፡፡ በመጨረሻም ተገቢውን ህክምና ያገኘ ወደ ነበረበት ጤናማነት መመለሱ አይቀርም፡፡ እውነታው ይሄ ነው ብለን የምንነሳ ከሆነና በዚህም ከተስማማን ጉዳዩ አቶ መለስ ላይ ሲደርስ ፉርሽ የሚሆንበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡

እርሳቸውም እንደእኔና እንደ እርስዎ ሰው ናቸው፤ ሰው ሁሉ ደግሞ ይታመማል፤ ስለዚህ አቶ መለስም ታምመዋል፡፡ ህክምና ተከታትለው የሐኪም እረፍት ላይ ናቸው፡፡ ይሄንን ተከት ሎም ቢሯቸው መገኘት አልቻሉም- አራት ነጥብ፡፡ እውነታው ይሄ ከሆነ ለምን እንዲህ ቅጥ አንባሩ የጠፋ ወሬ ይናፈሳል?

የእዚህን ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ብዙም ማሰብ አይጠይቅም፡፡ አካባቢያችን ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ልሳኖቻቸው መረዳት እንችላለን፡፡ የከሰረ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ከእዚህ ውጪ ሌላ አጀንዳ ሊቀርጽና ሊንቀሳቀስ ስለማይችል ያጡትን የህዝብ ጆሮ ለማግኘት ገና ብዙ ብዙ ማለታቸው አይቀርም፡፡

እኔ እንደሚገባኝ ግን የአቶ መለስን መታመምን ተከትሎ የሚነሳው ክርክር ሁሉ ወንዝ የሚያሻግር ውሃም የሚቋጥር አይደለም፡፡ እርሳቸው ከሥራ እስከወዲያኛው ከተገለሉ ‹‹ኢትዮጵያ አበቃላት›› እያሉ መናገርና ማስነገርም ጤነኛ አዕምሮ ያፈለቀው አመለካከት ነው ብሎ መቀበል ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም አቶ መለስ እኮ አንድ ግለሰብ እንጂ ብቻቸውን ድርጅት አይደሉም፡፡ እስከማውቀው ድረስ ደግሞ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ኢህአዴግ የተባለ ድርጅት እንጂ አቶ መለስ ዜናዊ የተባሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ አይደሉም፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ከአንድ ሰው (መሪ) ጋር ብቻ አቆራኝቶ መመልከት የከሰረ ፖለቲካና ፖለቲከኛ አካሄድ እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩልን ሲል ይሁንታውን የሰጠው ለ545 የኢሕአዴግ እጩዎች እንጂ ለአንድ አቶ መለስ ብቻ አይደለም፡፡ ይሄ በቅጡ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይሄንን እውነታ አለመቀበል የአስተሳሰብ ደሃ ያሰኛል፡፡

ሌላው መታወቅ ያለበት እውነታ ብዬ የማስበው ዛሬ አቶ መለስ በህመም ከቢሯቸው ራቁ እንጂ በቀጣዩ አምስት ዓመት እኮ በሥራቸው እንደማይቀጥሉ ካስታወቁን ከራርመዋል፡፡ ይህንን ማለታቸው እርሳቸው የዘላለም መሪ አይደሉም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ታምመው ከሥራ ገበታቸው አልተገኙም፤ በ2008 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ደግሞ በፓርቲ ያቸው የመተካካት መርህ መሰረት ከቢሯቸው አይገኙም፡፡

ለእኔ ሁለቱም ክስተቶች አንድ ናቸው፡፡ ልዩነቱ ያለው አቶ መለስ አሁን ከጤና ጋር በተያያዘ ከቢሮቸው አለመገኘታቸው ብቻ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እንዳልኩዎት የሰው ልጅ በምድር ላይ እስካለ ድረስ ከማይቀርለት እጣ ፋንታው መካከል አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ማለት የምንችለው ፈጣሪ ለአቶ መለስ ጤንነቱን እስከወዲያኛው ይመልስላቸው፤ ምህረቱንም ይላክላቸው ብቻ ነው፡፡ ከእዚህ ውጪ ያለው የፈጣሪ እንጂ የእኛ የሰዎች ጉዳይ አይደለም፡፡

‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይገለጣል›› እንዲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጤንነት ሁኔታ አቶ በረከት እንዳሉት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደመገኘቱ ወደ ሥራቸው የተመለሱ እለት የምንታዘባቸው ግለሰቦችና ሚዲያዎች ቁጥር ቀላል አይሆንም፡፡ እስከዛሬ ድረስም ያልተጨ በጠ መረጃን ሲያቀብሉን እንደኖሩ ጥሩ ማሳያ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ሚዲያዎች መጀመሪያ ያወጡት ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርፈዋል›› የሚለውን ዘገባቸውን ሐሰትነት ካሁኑ በመረዳታቸው ይመስላል ተዓማኒነታቸውን ከጥያቄ ውስጥ ለማውጣት ደፋ ቀና ማለት ጀምረዋል፡፡

ለእዚህ ማሳያው ኢሳት ነው፡፡ ኢሳት ‹‹አቶ መለስ አርፈዋል›› ሲል መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ የእዚህ ዜና
ነጭ ውሸትነት ሲገለጥበት ጊዜ እንዲህ የሚል ዘገባ ይዞ ወጥቷል፡፡ ‹‹…በሌላ በኩል ግን አቶ መለስ እንደምንም ብለው ለህዝብ በቴሌቪዥን ቢታዩ ኢሳት ላለፉት ሁለት ዓመታት የገነባውን ተአማኒነት ያጣ ይሆናል በማለት የሚጨነቁ ወገኖች መኖራቸውንም ዘጋቢዎቻችን ገልጠዋል›› የሚል ነው፡፡

ጥሩ መመጻደቂያ ናት፡፡ ሲጀመር ኢሳት መቼና የት የገነባው ተአማኒነት እንዳለው ግልጽ አይደለም፡፡ ግድ የለም እንስማማለት ቢያንስ ለራሱ ተዓማኒ ነኝ ብሎ ይመን፡፡ ችግሩ ያለው ግን ካሰራጨው ዘገባ ላይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርፈዋል ሲል የጻፈው የመንደር ወሬ ፍጹም ውሸት መሆኑ ሲታወቅበት መልሶ ‹‹ተዓማኒነቱን›› በተመለከተ ‹‹የሚጨነቁ ወገኖች›› ሲል በሳላቸው ገጸ ባህሪያቱ የራሱን ስጋትና ቀጣፊነት ነግሮናል፡፡ ‹‹አፍ ሲከፈት…›› ይሏልም እንዲህ ነው፡፡

ሌሎችም ሚዲያዎች ቢሆኑ እንደእዚያው ናቸው፡፡ እስከእዚያው ድረስ ግን ማድረግ የምንችለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት ዙሪያ የሚወጡ ውሸትን መሰረት ያደረጉ ዘገባዎችን ለታሪክ ያህል መከታተል ይሆናል፡፡ ያውም ለታሪክ የሚበቃ ዘገባ ካገኘንባቸው ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዝንብ ማርን ማግኘት ስለማይቻል ነው፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምኦን ‹‹አቶ መለስ ታመዋል፤ ህመማቸው ግን ለክፉ አይሰጥም፡፡ በቅርቡም ወደ ቢሯቸው ይመለሳሉ›› ሲሉ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በእዚህ ሀቅ አልስማማም ብሎ የራስን አቋም መያዝ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ ነገር ግን አቋም ሲያዝ በቂ ማስረጃና መረጃ መያዝ የግድ ይላል፡፡ ማስረጃዎ የኢሳትን አይነት ዘገባ ከሆነ ‹‹በሬ ሆይ በሬ ሆይ…›› እንደሚተረትብዎት ልብ ይበሉ፡፡

የአቶ በረከትን መግለጫ ተከትሎም አንዳንድ ወገኖች ‹‹በቅርቡ ሲባል ምን ያህል ጊዜ ነው? ሳምንት፣ ወር፣ ወይንስ… ስንት?›› የሚል ወሬን ሲያናፍሱ ታዝበናል ፡፡ በእነዚህ አካላት ‹‹…አቶ በረከት በቅርቡ ይበሉ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስራ እስካሁን ሊመለሱ አልቻሉም›› በማለት ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ንግግሮችንና ዘገባዎችን እያደመጥን ነው፡፡

የእኔ ጥያቄ ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ሐኪም ሐኪም እንጂ ፈጣሪ ወይንም ነብይ አይደለም፡፡ የህክምና ባለሙያ አንድ የታመመ ሰው ይሄንን ያህል ቀን ቢያርፍ ይሻለዋል በሚል በግምት ላይ የተንተራሰ እረፍት ይሰጣል እንጂ ፍጹም ትክክል የሆነ ትንበያን ሊያደርግ እንደማይችል እየታወቀ አቶ መለስ በተባለው ቀን ወደ ሥራ አልተመለሱምና የመንግሥት መግለጫ ትክክል አይደለም ማለት ተገቢ ነውን? የታመመ ሰው መቼ እንደሚሻለው በትክክል ሊያውቅ የሚችለው እኮ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ አቶ መለስ ሐኪሞች ከገመቱላቸው ቀን በላይ እረፍት አስፈልጓቸዋል የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡ አቶ በረከትም ቢሆኑ ሐኪሞቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጧቸውን የእረፍት ቀን ተንተርሰው ያሉትን ብለዋል፡፡ ‹‹ወደ ሥራ ይመለሳሉ ባሉበት ቀን አልተመለሱምና መረጃው ስህተት ነው›› ማለት ግን አላዋቂ ያሰኛል፡፡ ምክንያቱም ሐኪም ግምት እንጂ ቁርጥ ያለ ቀን የመስጠት አቅሙም ሆነ መለኮታዊ ስልጣን የለውም ብዬዎታለሁ፡፡

ከእዚህ ውጪ ግን መንግሥት የሰጠው መግለጫ የተሳሳተ ብለው በተቃራኒው ሟርት የሚያወጡት ሚዲያዎች ደግሞ ትክክል ናቸው ማለት እውነታው የወጣ እለት ያስተዛዝባል፡፡ እኔ ግን ለወቀሳም ለምስጋናም እንዲያመች በማለት በእዚህ ዙሪያ የሚወጡ ‹‹ዘገባዎችን›› እየታዘብኩ አለሁ፡፡ ምክንያቱም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ወደቢሮ የመመለስ ቀን ሲመጣ የሚዲያዎች ማንነት መገለጡ አይቀርምና ነው፡፡

አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ደግሞ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን ወደ ህዝቡ ለማስረፅ ብቃትና አቅም ስለሌለው ተፈጥሯዊ የሆነውን የሰው ልጅ መታመንን እንደ ትልቅ ፖለቲካዊ አጋጣሚ ለመጠቀም ሲራኮቱ መታየታቸው ያስተዛዝባል፡፡ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓላማቸውን በፖለቲካዊ ትግል ማሸነፍ እንደማይችሉ በራሳቸው መንገድ ገሃድ አውጥተውታል፡፡ የሀገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት በግለሰብ ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን ህገመንግሥታዊ መሰረት ያለው መሆኑን መረዳት ያልቻሉ ናቸው፡፡

ስለዚህ እላለሁ ጉንጭ አልፋ ክርክራችንንና ፊታችንን ብሎም ትኩረታችንን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት ላይ አንስተን መላ ትኩረታችንን በሥራችን ላይ ብናደርግ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ባልተጨበጠ መረጃ ላይ ተንተርሰን ጎንበስ ቀና ማብዛታችን ምን ለማንሳት ነው ስለሚያስብለን ከወዲሁ አደብ ብንገዛ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ሃሳቤን የማበቃው በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አቶ መለስን ‹‹እግዚአብሔር ምህረትን ይላክልዎት›› በማለት ነው፡፡

Source: Addis Zemen – Aug. 8, 2012.

*****************

Check the Meles Zenawi archive for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories