ደመወዝተኞች ከነጋዴዎች የተሻለ ታክስ ይከፍላሉ | የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን [Amharic]

በሀገሪቱ የቀረጥና የታክስ ህግ ተገዢነት ባህል ደካማ መሆኑን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስታወቀ። አብዛኛው ገቢ የሚሰበሰበው ዛሬም ከመንግሥት ሠራተኛው መሆኑ ተጠቆመ።

የኢትዮጵያ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ትናንት ሁለተኛ ቀኑን ባስቆጠረው ሁለተኛው አገር አቀፍ የታክስ ጉባዔ ላይ ጥናታዊ ፅሑፋቸውን ሲያቀርቡ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ቀረጥና ታክስ በፍላጐትም ሆነበግዴታ በአግባቡ የመክፈልና ለህጉ ተገዢ የመሆን ባህል ገና አልዳበረም።

ጥናት አቅራቢው አቶ ገብረዋህድ የአዲስ አበባ ከተማን የ2003 በጀት ዓመት የገቢ አሰባሰብ ሁኔታ በመጥቀስ እንዳቀረቡት፤ ከቀጥታ ታክስ ገቢ የተደረገው 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ውስጥ 1 ነጥብ 76 ቢሊዮን ወይም 72 ነጥብ 7 ከመቶ የሚሆነው ከደመወዝተኞች የተሰበሰበ ነው። ከንግድ ትርፍ ግብር 525 ነጥብ 6 ሚሊዮንወይም 21 ነጥብ ከመቶ ብቻ ተሰብስቧል። ይህም የንግዱ ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን ግብርና ታክስ በአግባቡ እየከፈለ አለመሆኑን ያመለክታል።

በተመሳሳይም በዚሁ በጀት ዓመት በከተማዋ በ98 ሺ የንግድ ቤቶች በተካሄደው የቤት ለቤትጉብኝት 11 ሺ ግብር ከፋዮች ለተጨማሪ እሴት ታክስ ያልተመዘገቡ መሆናቸውን ለማወቅ መቻሉን ገልጸው፤ በተጨማሪም 22 ሺ ግብር ከፋዮች ደረጃ « ለ» መሆን ሲገባቸው ደረጃ «ሐ» ነን በሚል መክፈል ከሚገባቸው በታች ያሳወቁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ከስምንት ሺ በላይ ግብር ከፋዮችም በትላልቅ የንግድ ሥራ የተሰማሩ ቢሆንም፤ ንግድ ፈቃድ ያላወጡና በግብር ከፋይነት ያልተመዘገቡ መሆናቸው እንደተረጋገጠ ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ ጥናቱ « የሀገሪቱ የታክስ ህግ ተገዥነት በአነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመላክታል» ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም ሀገሪቱ በተነፃፃሪ መልኩ ውጤታማ ካልሆኑት የታክስ አስተዳደር ካላቸው የዓለም ሀገራት ተርታ እንደሚያሰልፋት ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ በ2003 በጀት ዓመት የችግሩን መጠን ለመቀነስና ህጉን ለማስከበር በርካታ ሥራዎችን ያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለህጉ ተገዢ ያልሆኑ 868 ግለሰቦችን ለህግ የማቅረብ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። እንዲሁም ባለሥልጣኑ በ690 መዝገቦች ላይ ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል። ለ255 መዝገቦች ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን፤ 243ቱ ተከሳሾች ላይ የእስርና የገንዘብ መቀጮ መተላለፉን አመልክተዋል።

« ይህም የባለሥልጣኑ አቃቤ ህግ የመርታት አቅም 95 ነጥብ 29 ከመቶ መድረሱን ይጠቁማል» ብለዋል። ይሁን እንጂ ውሳኔ የተሰጣቸው መዝገቦች መጠን አነስተኛ ከመሆኑም በላይ አወሳሰኑም ችግሮች የተስተዋሉበት እንደነበር ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ ውስጥም በተለይ በርካታ ተከሳሾች የጥፋተኝነት ውሳኔ ቢሰጣቸውም በቅጣት ማቅለያ ምክንያት በገደብና በአነስተኛ ጊዜ እስር የሚቀጡ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ይህም የህጉን በሚገባ ተፈፃሚነት አጠራጣሪ የሚያደርገው መሆኑንና ደንብ በማስከበር ረገድ እንቅፋት እንደሚፈጥር አብራርተዋል። ስለሆነም የቀረጥና የታክስ ህግ ተገዥነት በማጠናከር ረገድ የአስተዳደርና የፍትህ አካላት የሚገባውን ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ የቀረጥና የታክስ ህግ ተገዥነት በማስፈን ረገድም መፍትሔ ይሆናሉ ያሉትን አቶ ገብረዋህድ ጠቁመዋል። ከእነዚህ መካከልም ልማታዊ የታክስ አስተዳደር ሠራዊት መገንባት፣ ገቢን አስልቶ በራስ የማፈላለግን የታክስ ግዴታ የመወጣት ሥርዓት ማጠናከር፣ የተጠናከረ የግብር ከፋዮች ትምህርት ግንኙነት ሥራ መሠራት የሚሉት ይገኙበታል።

Source: Addis Zemen – June 10, 2012 (by Mahlet Abdul)

*******************

Check the drop down menu at the top for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories