ቴዲ ኣፍሮ፣ እምዬ ሚኒሊክ፣ ባልቻ ኣባነፍሶ እና ኣድናቂዎቹ

ቴዲ ኣፍሮ ታላቅ ጥበበኛ ነው፡፡ ሙዚቃዎቹ በሃሳብ ብስለትም በዜማ ጥኡምነትም ሁሌም ቢሆን ተደምጠው የማይሰለቹ ምርጦች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ኣርቲስቱ በርካታ ኣፍቃሪዎችን ማፍራት ችሏል፡፡ ታዲያ የቴዲ ኣፍቃሪዎች ሁሉም ኣንድ ኣይነት ኣይደሉም፡፡ የፍቅራቸው ምክንያትም ይለያያል፡፡ ቢዚህም ምክንያት ደረጃ 1 እና ደረጃ 2 ኣድናቂዎች ልንላቸው እንችላለን፡፡ ደረጃ 1 ኣድናቂዎች ስለ ኑሮ፣ ስለፍቅር፣ ስለመተሳሰብ፣ ስለጥበብ ዘፍኖ ልባቸውን ያሸፈተባቸው ሲሆኑ በቁጥርም ብዙሃን ናቸው (እኔ ራሴ እዚሁ ምድብ ውስጥ ነኝ ብዬ ኣስባለሁ)፡፡ የነዚህ ሰዎች ፍቅርና ኣድናቆት  ልባዊና ከምንም ጋር ያልተያያዘ (unconditional) ነው፡፡ በሌላ በኩል ደረጃ 2 ኣድናቂዎች በቁጥር ብዙ ባይባሉም የሱን ታዋቂነትና በህዝብ ዘንድ ያለው ተሰሚነት በፖለቲካዊ ስራዎቻቸው ላይ ለመጠቀም የሚፈልጉ ጮሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህም በብዛት በተቃዋሚነት ጎራ ያሉ ሲሆን መሰረታቸዉም ዲያስፖራ ነው፡፡

“ያስተሰርያል” ዘፈን በተለቀቀበት ወቅት ኣዲስ ኣበባ ነበርኩኝ፡፡ ያ ዘፈን በወቅቱ ከነበረው የምርጫ ትኩሳት ጋር ተገጣጥሞ (ተገጣጥሞ የሚለውን ቃል በየዋህነት ተጠቀምኩኝ እንጂ ታስቦበት ጊዜውን ጠብቆ የተለቀቀ ዘፈን ነበር) በብዙዎቹ ኣእምሮ ውስጥ ተቀርፆ ይገኛል፡፡ በወቅቱ ኣሁን ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት የሚቃወሙ ሰዎች ቴዲ ኣፍሮን ከሰውነት በላይ ኣግዝፈው ማየት የጀመሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ቴዲ ብፁእ ነው ኣሉ፡፡ በደረጃ 2 ኣፍቃሪነት የሚመደቡና የፖለቲካ ድርጅትን እንመራለን የሚሉ ኣንዳንድ ሰዎችም የቴዲን ኣእምሮ እንደሚያደንቁና የሱን ያህል ጭንቅላት ቢኖራቸው እንደሚመኙ ለኛ ለህዝቦች ነግረውን ነበር (ይሄን ውለታ መመለሳችን ግን ኣላውቅም)፡:

ኣንድ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃንን በመኪና ገጭተህ ኣምልጠሃል ተብሎ በታሰረበት ወቅትም “ቴዲ በፍፁሞ ሰው ኣልገደለም” ብለው በታቦት ስም የሚምሉ በርካቶች ነበሩ፡፡ እኔ በበኩሌ ገድሎታል ኣልገደለዉም የሚለዉን ነገር ከቀረቡት ማስረጃዎች በመነሳት የራሴ የሆነ መላምት ቢኖረኝም በዛ ጉዳይ ላይ እርግጠኛ መሆን ኣልችልም፡፡ እርግጠኛውን ነገር የሚያውቁት ቴዲ ኣፍሮና እግዚኣብሄር ብቻ ናቸው፡፡ ለነገሩ ቴዲ ራሱ የጭፍን ኣፍቃሪዎቹን ያህል ኣልማለም፡፡ ከኣንድ ሁለት ወራት በፊት Bosaso, Puntland  ውስጥ የሞት ቅጣት ተበይኖበት ሞቱን በመጠባበቅ ላይ የነበረ አስመሮም ሃይለስላሴን 700,000 ብር ከፍሎ ሲያስለቅቀው የተሰማኝ ስሜት ግን ኣልደብቅም፡፡ እንዲህ ነበር ያልኩት-  “እውነት ቴዲ የጎዳና ተዳዳሪውን ህፃን ገድሎ ከሆነ እውነት ይሄ ልጅ እግዚኣብሄር ይወደዋል፣ ይቅርታ ሊያደርግለት ፈልጎ ሰበብ የላከለት ይመስላል፡ ውስጡ ይሰማው የነበረውን ፀፀት ኣስመሮም ላይ በሰራው ስራ ይፈውስለታል”፡፡

ቴዲ ክእስር ቤት ከተፈታ በኋላ ደረጃ 2 ኣፍቃሪዎቹ  የፈለጉት ኣልሆነላቸውም፡፡ በመጀመርያ መፈታቱን ያልወደዱ ብዙ ሰዎች ነበሩ – ኣሁን ኖርወይ ኣገር የሚገኝ ጓደኛዬን ጨምሮ፡፡ እሱ እንደነገረኝ ከሆነ “ቴዲ ኣፍሮ ይፈታ”  በሚል በርካታ ሰላማዊ ሰልፎች ኦስሎ ጎዳናዎች ላይ ተካሂደዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በመሳተፍ  የኢትዮጵያን ባንዲራ በመያዝና መንግስትን የሚያወግዙ መፎክሮችን በማንገብ የተነሳቸው ፎቶዎች በኖርዌይ ጥገኝነት ለማግኘት ላስገባው ማመልከቻ ማጠናከሪያ እንደሆኑለት ይናገራል፡፡

ቴዲ እንደተፈታ እነዚህ ደረጃ 2 ኣድናቂዎች የመከሩት ኣገሩን ጥሎ እንዲወጣ ነበር፡፡ ኣላደረገዉም፡፡ ከዛም ኣልፎ በልመና ለሚተዳደሩ ወገኖች ማቋቋሚያ በተዘጋጀ ኮንሰርት ላይ በመሳተፍ በርካታ ገንዘብ እንዲሰበሰብ ሲያደርግ ይበልጥ ኣበሳጫቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የነበረ የቴዲና የነዚህ ሰዎች ግንኙነት ጥሩ ኣልነበረም፡፡ ኣብዛኞቹ እሱን ትተው ሌላ ርእስ ላይ ሲጠመዱ ሌሎቹ ደግሞ ቴዲን ማጣጣል ጀመሩ፡፡ ወያኔ፣ ተንበርካኪ ወዘተ የሚሉ ቅፅል ስሞች ተሰጥተውት ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚፈልጉት ጥበቡን ሳይሆን ታዋቂነቱንና እነሱ ያምንበታል ብለው የሚያስቡት የፖለቲካ ኣቋም ነበርና፡፡  ለማንኛዉም ነቄው ቴዲ እነዚህ ወዳጆቹን ለማስደሰት በሚመስል መልኩ ኣንድ ዘፈን ይዞላቸው ብቅ ብሏል – ምን ወይም የማንን ስም ኣንስቶ ቢዘፍን የኮረኮራቸውን ያህል እንደሚደሰቱ ያውቃልና፡፡ ተሳክቶለታልም፡፡

ቴዲ ኣፍሮ ስለ ኣፄ ሃይለስላሴ፣ ኣትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ልጅ ኣለማየሁ፣ ቦብ ማርሌ ኣቀንቅኗል፡፡ ኣሁን ደግሞ ጥቁር ሰው በሚለው ኣልበሙ ኣፄ ሚኒሊክን ኣሞካሽቶ ዘፍኗል፡፡ ስለ እቴጌ ጣይቱና ዋናዎቹ የጦር ጄኔራሎቻቸዉም ነካክቷል፡፡ ጥሬ ሃቁን ብቻ ለሚያይ ሰው ዘፈኑ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ የኣድዋ ጦርነት ላይ ኣፄ ሚኒሊክ ስለነበራቸው ሚና፤ የእቴጌ ጣይቱ ኣሰተዋፅኦ፣ ከጎናቸው የነበሩ የጦር መሪዎች ሚናና ማንነት በቃ!!! ታዲያ ችግሩ ያለው ሰዎች የሚሰጡት ትርጓሜ ላይ ነው፡፡

1/ ኣፄ ሚኒሊክ ኣድዋ ላይ ድል ቢያደርጉም ህዝባቸው ውስጥ ገዳይና ጨፍጫፊ ነበሩ፣ ብዙ ሰዎችን ከቀያቸው ኣፈናቅለው መሬታቸውን ነጥቀው ለወታደሮቻቸውና ኣገልጋዮቻቸው ሰጥተዋል፣ ይህን የተቃወሙትም ተገድለዋል፣ በማንነታቸው ተሰድበዋል፣ እናቶች ጡቶቻቸው እንዲቆረጥ ሆኗል፣ ኣንዱን ብሄረሰብ የበላይ ሌላዉን እንደ እንስሳ ቆጥረው ኣሰቃይተዋል፣ የባርያ ንግድ ኣስፋፍተዋል፣ ኢትዮጵያን ከጣልያን ጋር በመፈራረም ወደብ ኣልባ እድርገዋታል፣ ….. ወዘተ ወዘተ የሚሉ ክስ ለሚደረድሩት ወገኖቼ ዘፈኑ ኣልተዋጠላቸዉም፡፡ ለጨፍጫፊ፣ ለገዳይ ሰብኣዊነት በጎደለው ኣያያዝ ህዙቡን ላሰቃየ መሪ ሊዘፈንለት ኣይገባም ይላሉ፡፡ በየፌስቡኮቻቸዉም ስሜታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ ኣንዳንዶቹም ለምን ስላለፈ ታሪክ ብቻ እያወራን እንኖራለን ብለው ይጠይቃሉ፡፡

2/ በስሜት ይሁን በድክመት ባላውቅም “እምዬ ሚኒሊክ”  የሚሏቸዉም ኣሉ፡፡ ለነዚህ ሰዎች ኣፄ ሚኒሊክ የኢትዮጵያ ፈጣሪ ናቸው፡፡ እሳቸው ባይኖሩ ኖሮ ኢትዮጵያውያን ኣይኖሩም ነበር፡፡ እነዚሀ ሰዎች በሁለት ምድብ ይከፈላሉ፡፡ ኣንደኛው ምድብ እምዬ ሚኒሊክ  ቅንጣት ያህል ስህተት ኣልፈፀሙም፣ ብፁእና ብርቅዬ ሰው ናቸው ሲል ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ማሰር፣ ማፈናቀል፣ መግደል፣ የናቶችን ጡት መቁረጥ የመሳሰሉ ነገሮች መፈፀማቸውን ያምናል ነገር ግን እንደዛ ማድረጋቸው በወቅቱ ኣስፈላጊ ስለነበረ እንደ ስህተት ኣይቆጠርም ባይ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ለነዚህ ሰዎች ሚኒሊክን መውደድና የኣገር ፍቅር ኣንድ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ከሆንክ እምዬ ሚኒሊክን ማደናነቅ ኣለብህ ኣለበለዚያ ኢትዮጵያዊነትህን ኣይቀበሉትም፡፡ ኣፄ ሚኒሊክን መተቸት ከኣገር ክህደት ጋር ያያይዙታል፡፡ በመሆኑም ለነዚህ ሰዎች የቴዲ ኣፍሮ “ጥቁር ሰው” ዘፈን  ልክ ሌላ የኣድዋ ድል ያስመዘገቡ ያህል ኣስደስቷቸዋል፡፡ ጉዳዩን እንደተለመደው ወደ ፖለቲካ መሳሪያነት ለመጠቀምም እየሞካከሩ ነው፡፡ ከነዚህ ኣይነቶቹ ሰዎች መካከል ኣንዱ በሽሙጥ ስራ የሚተዳደረው ወዳጃችን ኣቤ ቶኪቻው (በጣም ኣድናቂው ነኝ) እንዲህ ብሎ ፅፏል –  “ይሄ የሙዚቃ ሲዲ ህውሃት ከማይደርሱበት ቦታ ይቀመጥ ተብሎ ይፃፍበት”

ስለ ፖለቲካ ካነሳን ኣይቀር ይህንን እንይ፡፡ በዲያስፖራ ኣካባቢ ያሉ የወቅቱ መጠነኛ የፖለቲካ ስብሰባዋችና በተለያዩ ከተሞች የሚደረጉ ቱሮች ኣላማቸውና ርእሶቻቸው ስለ ኦሮሞዎች ትግል ሆኗል፡፡ በ”ኣንድነት” ስም ጆሯችንን ሲያደነቁሩን የከረሙ ሃይሎች በስተመጨረሻው የኦሮሞ ተቆርቋሪ ሆነው ብቅ ብለዋል፡፡ በነዚህ “የኣንድነት ሃይሎች” ሚድያዎች የሚነበቡ ዜናዎችና የሚቀርቡ ትንታኔዎችም ወጋቸው ያ ነው – ለምሳሌ “ኦሮሞዎች ከኛ (“ከኣንድነት ሃይሎች”) ጋር ሆነው ለመታገል ወሰኑ፣ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያዊነታቸውን ኣምነው ለመቀጠል ተስማሙ (ድሮስ ምን ነበሩና?)፣ የቀድሞዎቹ ስርኣቶች የኣማራ ቢባሉም ኦሮሞ ባለስልጣናት ነበሩ (የተወሰኑ ግለሰቦች ስም ይጠቀሳሉ)፣ ዶክተር ብርሃኑ ኦሮምኛ ዘፈን ላይ ደነሱ” … ወዘተረፈ፡፡

የቴዲ “ጥቁር ሰው” ዘፈን ስለ ኣፄ ሚኒሊክ ቢሆንም እግረ መንገዱ የእነ ባልቻ ኣባ ነፍሶና ዲነግዲሬ ተራ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ የኦሮምኛ ቶንም ተጨምሮበታል፡፡ ኣንዳንድ ሃሜተኞች ይህ የቴዲ ኣዲስ ዘፈን ወቅቱን ያገናዘበ ዘፈን ነው ይሉታል – ኣገልግሎቱ ረዥም ጉዞ የሚያስጉዝ ባይሆንም፡፡ ስለዚህ የ1997 “ያስተሰርያል” ዘፈን ይዘት፣ የወቅቱ የፖለቲካ ኣጀንዳዎችና ኣልበሙ የተለቀቀበት ጊዜ በማስታወስና የኣሁኑን ዘፈን ጭብጥና ጊዜ በማሰላሰል ‘እውነትም ቴዲ ኣፍሮ ወቅትን እያገናዘበ የሚዘፍን ባለሙያ ነው’ ብንል ጥሬ ሃሜት ይሆንብን ይሆን? እንጃ፡፡

**************

Jossy Romanat

more recommended stories