የነዳጅና ወርቅ ፍለጋ ሥራዎች | የማዕድን ሚኒስቴር የፓርላማ ሪፖርት [Amharic]

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። ምክር ቤቱ በዕለቱ በዋናነት የማዕድን ሚኒስቴርን የ2004 በጀት ዓመት የ10 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።Ethiopian Mnister of Mines - Sinkinesh Ejigu

የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ የመሥሪያ ቤታቸውን ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መንግሥት የዘረጋውን መጠነ ሰፊ የአምስት ዓመት ዕቅድ ለማሳካትና ዘርፉ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በሰፊው ይንቀሳቀሳል። የተቋሙን የለውጥ ትግበራ ቀጣይነት ማረጋገጥ፣ የአመለካከት፣ የክህሎትና የአቅርቦት ችግሮችን መፍታት፣ እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነት አሠራሮችን በመለየትና ምንጮቹንም በማድረቅ ጠንካራ የሲቪል ሰርቫንት በተቋሙ መገንባት ትኩረት ተሰጥቷቸው የተከናወኑ ተግባራት ናቸው።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የአብይ ተግባር አፈጻጸምን በተመለከተም ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የጂኦሳይንስ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ደረጃቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ የናሙና ምርመራና ልዩ ልዩ የጂኦሳይንስ ጥራት አገልግሎት ሰጥቷል።

በዚሁ መሠረት ባለፉት አሥር ወራት ለውስጥና ለውጭ ተገልጋዮች በአጠቃላይ 28ሺ 960 ማዕድኖችንና ከማዕድን ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ናሙናዎች ለመመርመር ታቅዶ 28 ሺ 463 ለውጭ ተገልጋይና ስድስት ሺ 026 ለውስጥ ተገልጋይ በድምሩ 34ሺ 489 ወይም የዕቅዱን 119 በመቶ አከናውኗል። አፈጻጸሙን በተመለከተ ከፍ ሊል የቻለበት ምክንያት የናሙና ምርመራ አገልግሎት የሚጠይቁ ደንበኞች ቁጥር መጨመር፤ ከታቀደው ጊዜ ቀድሞ ናሙና በመግባቱ እና በአባይ ሸለቆ የመሬት መንሸራተት ጥናት ፕሮጀክት አማካኝነት በርካታ የናሙና ምርመራ በመጠየቁና ውጤቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመጠየቁ መሆኑ ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አባላትም በሰጡት አስተያየት የዕቅድ መሠረትን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መረጃ ቢኖር መልካም ነው። ምክንያቱም ሪፖርቱ ላይ ዕቅዶቹ አነስተኛ ናቸው። በአንፃሩ አፈጻጸሙ ከፍተኛ ነው። ይህ ለምን ሆነ? ሚኒስትሯ ለዚህ ጉዳይ በሰጡት ምላሽ የመሥሪያ ቤታቸው የዕቅድ መነሻ አቅማቸው መሆኑን ተናግረዋል። «… አገልግሎት እንሰጣለን ብለን ያጠናነው መነሻ አለ። ነገር ግን በዋናነት በእኛ እና በአገልግሎት ጠያቂዎቻችን መካከል የነበረ የፍላጐት አለመመጣጠን ያመጣው ልዩነት ነው» ብለዋል።

የሌሎች ማዕድናትንና የነዳጅ ፈቃድ የመስጠትና የማስተዳደር ሥራዎች አፈጻጸምን በተመለከተም በሀገሪቱ አንድ ወጥ የሆነ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓትን ለማጠናከር ተሰርቷል። የፍሌክሲ ካዳስተር ሶፍትዌር በየዕለቱ ከሚቀርቡ የአመልካቾች ጥያቄ መነሻነት መረጃዎች እየተመዘገቡ ነው። በፍሌክሲ ካዳስተር ሶፍትዌር አጠቃቀም በክልል ማዕድን ቢሮ ለሚገኙ ባለሙያዎች በሥራ ላይ ስልጠናና ልምምድ እንዲያገኙ በቢሮና በመስክ የደቡብ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ እና አማራ ክልሎች እንዲሁም ለድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድሮች ድጋፍ መደረጉ በሪፖርቱ ተገልጿል።

ባለፉት አሥር ወራት በአጠቃላይ አንድ ነጥብ 21 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ በድምሩ 59 የማዕድን ሥራ ፈቃዶች የተሰጡ ሲሆን፤ ግዴታቸውን ያልተወጡ አምስት ፈቃዶች ውላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል። በተጨማሪም በ102 የፍለጋና ምርመራ 40 የማዕድን ማምረት ፈቃዶች ላይ የመስክ የቴክኒክ ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ ታቅዶ በ57 የማዕድን ፍለጋና ምርመራ ላይ ቁጥጥና ክትትል መደረጉንም ወይዘሮ ስንቅነሽ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት 10 ወራት በኢኮኖሚያዊ ማዕድናት ተሳትፎው የጐላ ነበር። በዚህም ሦስት ሺ 675 ኪሎ ግራም ወርቅ፤ 161 ነጥብ 25 ቶን ታንታለም እና 110 ሜትር ኩብ እምነበረድ ወደ ውጪ ተልኳል። በገቢ ረገድም 230 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታቅዶ 159 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 66 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል። አፈጻጸሙም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ16 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አሳይቷል።

ያለፈውን አፈጻጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ በቀረቡ አስተያየቶች፤ የታንታለም ማዕድን ከወርቅ ቀጥሎ ለሀገሪቱ ጥሩ የሚባል ገቢ እያስገኘ ነው። በዘርፉ በባህላዊ አመራረትም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ነገር ግን ሚኒስትሯ በሰጡት አስተያየት የታንታለም ምርት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል። በተለይም ዘርፉ ውስጥ የባህላዊ አምራቾች በሰፊው መግባት ተከትሎ የቅንጅት ሥራ ባለመሠራቱ የታንታለም ምርት ማውጣትን አስቸጋሪ አድርጎታል። ይህም ከታንታለም ባህላዊ አምራቾች ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት ምክክር ላይ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ወይዘሮ ስንቅነሽ አስረድተዋል። በተጨማሪም በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የወርቅ ክምችት መገኘቱ ተገልጿል። በትግራይ ክልል መርሂ በተባለ ሥፍራ 13 ቶን፤ በመተከል ወደ 31 ቶን፤ ቢኒዮታ ከ40 ቶን በላይ በሆኮቴ 80 ቶን ወርቅ መኖሩ ተረጋግጧል።

ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ካካተቱት ውስጥ የነዳጅ ዘይት (የፔትሮሊየም) ሀብት ይገኝበታል። የሀገሪቱን የነዳጅ (የፔትሮሊየም) እምቅ ሀብት፣ በኩባንያ የተያዙና ያልተያዙ ሥፍራዎችን በመለየት የኮንትራት ጉዳዮችንና የነዳጅ አወጣጥ ሕጐችን የማስተዋወቅ ሥራ ተከናውኗል። በነዳጅ ስምምነት መሠረት የፔትሮሊየም ፍለጋና ጥናት እንዲስፋፋ ማድረግ እና የኩባንያ ጥያቄዎችን በመገምገም ለድርድር ማብቃት፤ በኩባንያዎች ፈቃድ ጥያቄ መሠረት የሚፈለግባቸውን ግዴታዎች ማሟላታቸውን የማረጋገጥ ሥራ ሰርቷል።

በዚህ መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ነዳጅ ፍለጋ ላይ ከተሰማሩ የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። ፔትሮትራንስ ኩባንያ በኦጋዴን ቤዚን ካሉብና ሂላላ የተባሉትን የጋዝ ዓይነቶች እንዲሁም ሌሎች አምስት ጨረታዎች አሸናፊ በመሆኑ የኮንትራት ስምምነቶችን ተፈራርሟል።

በጋምቤላ ክልል ለሚሰማራ ለነዳጅ ፈላጊና አልሚ ኩባንያ ፍቃድ ለመስጠት በታቀደው መሠረት አስፈላጊው ድርድር ተደርጓል። የድርድር ሰነዱም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ ኩባንያ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። በተጨማሪም ይኸው ድርጅት በሶማሌ ክልል ቀብሪ በያህ አካባቢ ፍለጋውን በማካሄድ ላይ ይገኛል። በዚህ ሥፍራ ባደረገው ጥነት፤ መደበኛ የሳይዝሚክ መረጃ የመሰብሰብ ሥራ አንድ ሺ ሦስት መቶ ኪሎ ሜትር አከናውኗል።

ሌላው በፍለጋ የተሰማራው ተሎው የነዳጅ ኩባንያ ነው። ኩባንያው በደቡብ ኦሞ የሚያካሂደውን የነዳጅ ፍለጋ ጥናት ቢጂፒ በተባለ የቻይና ኩባንያ ንዑስ ኮንትራክተር አማካኝነት ጥናቱን ያካሂዳል። ድርጅቱ ከኦሞ ወንዝ በስተምሥራቅ ላለው ይዞታው የሳይዝሚክ ጥናት ያጠናቀቀ በመሆኑ ቀጣይ ሥራውን ከኦሞ ወንዝ በስተምዕራብ በሚገኝ ሥፍራ እንደሚቀጥል ሚኒስትሯ አስረድተዋል።

አፍሪካ ኦይል ኩባንያ በኢትዮጵያ በነዳጅ ፍለጋ ከተሰማሩ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው። ድርጅቱ 27ሺ ሁለት መቶ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የኦዲጎላ ብሎክን የመጀመሪያ የሥራ ጊዜ አጠናቅቋል። በአዲሱ ፕሮግራም መሠረት ኩባንያው በኦዲጋላ ብሎክ ይዞታው ለሚያካሂዳቸው ሥራዎች አስፈላጊ ዝግጅቶችን በማድረግ በተጠቀሰው ጊዜ ጥናቱን ማከናወን ችሏል። በተመሳሳይ ፋልኮን ፔትሮሊየም ኩባንያ በወሰደው ፈቃድ መሠረት በዚህ ዓመት በዋድላ ደላንታና በወረይሉ አካባቢ ጥናቱን በማካሄድ ላይ ሲሆን በዚህ ወር ሥራውን ይጀምራል።

ሌላውና ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ያካተቱት ጉዳይ የባህላዊ ማዕድናት ምርትና ግብይት ሥራዎች አፈጻጸምን ይመለከታል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ከ85 በመቶ በላይ ማዕድናት በባህላዊ መንገድ እንደሚመረቱ ይገመታል። በኢትዮጵያ በተለይ በወጪ ንግድ ላይ የላቀ ተሳትፎ ያላቸው እንደ ወርቅ፣ ታንታለምና ፕላቲንየምን ጨምሮ የጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል። በዘርፉ በርካታ ዜጐች ይሳተፋሉ። የባህላዊ ማዕድናት ምርትና ግብይት ሥራ የሚኒስቴሩን ጥናት እና ፍለጋ ሳያሰናክል እንዲሁም የአምራቾቹንም ጥቅም በማይጐዳ መልኩ ለማስኬድ የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል።

በባህላዊ መንገድ ማዕድናትን በማውጣት የተሰማሩትን ዜጐች በኅብረት ሥራ ማኅበራት በማደራጀት በቂ የአመራረት ዘዴዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የሥራ ላይ ደህንነት ሥልጠናዎችን ሚኒስቴሩ ይሰጣል። በተጨማሪም ምርታቸው እንዲያድግ ዘመናዊና የተሻሻሉ የማምረቻ መሣሪያዎችን ድጋፍ ያደርጋል። በዚህም ፍትሐዊ የሆነ የግብይት ሥርዓትን ለመዘርጋት ይጥራል። በሪፖርቱ መሠረትም ሀገራዊ የወርቅ፣ የጌጣጌጥ እና የታንታለም ማዕድናት አቅርቦት ቀደም ሲል ከነበረው ከፍ ብሎ እንዲታቀድ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህም ለ2004 በጀት ዓመት 13ሺ ሁለት መቶ ኪሎ ግራም ወርቅ፣ 18ሺ ኪሎ ግራም የጌጣጌጥና 125 ቶን ታንታለም ለብሔራዊ ባንክና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዕቅድ ተይዟል።

ባለፉት አሥር ወራት በባህላዊ መንገድ የተመረተ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ያቀርባሉ ተብለው በዕቅድ ከተያዙት የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የደቡብ፣ የአማራና የጋምቤላ ክልሎች ይገኙበታል። ክልሎቹ 428 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ 10ሺ 720 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ በዕቅድ ይዘው 368 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ስድስት ሺ 786 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ገቢ አድርገዋል።

የወርቅ አቅርቦትን በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያከናወናቸው ተግባራት አሉ ይላሉ። በተለይም ለወርቅ አቅራቢዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል አዲስ አበባ ላይ ተወስኖ የነበረው የብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግዥ በየክልል ከተሞች እንዲሆን ተደርጓል። መቀሌ፣ ጅማ፣ አሶሳ እና ሀዋሳ ለአቅርቦት የተመረጡት ከተሞች ናቸው። የክልሎችን የማምረቻ መሣሪያዎች ፍላጐት በመለየት የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ አምስት ክልሎች ፍላጐታቸውን አሳውቀዋል።

ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ሪፖርቱ በኦሮሚያ ክልል በጐጂ እና ቦረና ዞን በምርትና ግብይት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች ይጠቀሳሉ። ችግሩን በውይይት ለመፍታት የተዋቀረ ቡድን ወደ ሥፍራው ተጉዟል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየገባ ያለውን የወርቅ ምርት መቀነስ ምክንያት ለማጣራት አንድ ቡድን ተቋቁሟል።

በሪፖርቱን አፈጻጸም ላይ ተመስርተው የምክር ቤት አባላት ያቀረቡትን ጥያቄ ለማዕድን ፍለጋ የሚነሱ ነዋሪዎች የሚደረግላቸው የካሳ ክፍያ ነው ወይ? ለዚህ ጥያቄ ሚኒስትሯ በሰጡት ምላሽ «… ካሳው ያንሳል የሚለው ትክክል ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሁን አሁን ከኩባንያዎች የሚቀርበው ፍላጐት ተነሽዎችን ብር ከፍሎ ብቻ የሚያርቅ ሳይሆን ቀጣይ ሕይወታቸውን መለወጥ ላይ ያተኮረ ነው» ብለዋል። በተጨማሪም በተነሽዎች ቦታ የአካባቢውን ነዋሪዎች ቀጣይ ሥልጠና በመስጠት የልማቱ ተሳታፊ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል። ሚኒስትሯ እንደሚገልጹት የማዕድን ፍለጋው ለተፈናቃዮች ስጋት ሳይሆን ቀጣይ የልማት ተሳታፊነትን የሚያረጋግጥ ይሆናል።

በሪፖርቱ ባይካተተም የምክር ቤት አባላቱ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ካሉብ ጋዝ የማውጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ነበረ። ይህ ጉዳይ ምን ላይ ደረሰ? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ሚኒስትሯ ወይዘሮ ስንቅነሽ በሰጡት ምላሽ የካሉብ ጋዝ ጉዳይ ለመሥሪያ ቤታቸውም ችግር እንደነበር ገለጸዋል። «… ነገር ግን ችግሩ ቢኖርም ወደ ኋላ አንመለስም። ድሮ ጋዝ ዋጋ አልነበረውም። አሁን ግን ወደ ተለያዩ የጋዝ አይነቶች በመቀየር ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል» ብለዋል። ለዚህም በቁርጠኝነት ወደ ትግበራ የሚገባ ኩባንያ መገኘት አለበት። ነገር ግን ሚኒስትሯ እንዳሉት ካሉብ ጋዝ የመሥሪያ ቤታቸው ሌላው ቀጣይ የልማት አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ነዳጅ ፍለጋን በተመለከተም መልካም ጅምሮች እንዳሉ ተናግረዋል። በአጠቃላይ የማዕድን ሚኒስቴር በአሥር ወር አፈጻጸሙ መልካም የሚባሉ ሥራዎችን ቢያከናውንም ማሻሻል ይገባቸዋል የተባሉ ጉዳዮች በምክር ቤት አባላት ተጠቁመዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማዕድናት መገኛ ከሆኑት የሀገሪቱ ክልሎች ጋር ያለውን ትስስር እንዲያጠናክር፤ የመሥሪያ ቤቱ አፈጻጸሞች ከነበረው ዕቅድ ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ እንደ ድክመት ተጠቅሷል። ከባህላዊ ወርቅ አቅራቢዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የማዕድን ምንጩን እንዲያጠናክር ማድረግ አለበት የሚሉት ነጥቦች ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተጠቆሙ ክፍተቶች ናቸው።

* Originally published on Addis Zemen, on June 8, 2012, titled ‘የነዳጅና ወርቅ ፍለጋው ጥረት ብሩህ ነው’, by reporter Beruk Berhe.

*****************

Check the drop dwon menu at the top for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories