የህዳሴ ግድብ ግንባታ ‘በሶስት ፈረቃዎች ለ24 ሰዓታት’ እየተከናወነ ነው [Amharic]

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተፋጠነ መልኩ እየተካሄደ ነው። ዋናው ግድብ በሚያርፍበት ስፍራ እየተካሄደ ባለው ቁፋሮም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ልል አፈርና ድንጋይ ተነስቷል።

በሰዓት 8 መቶ ሜትር ኪዩብ አርማታ ማምረት የሚያስችሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች ተከላም ግድቡ በሚያርፍበት የወንዙ ግራና ቀኝ እየተካሄደ እንደሚገኝ የግድቡ ፕሮጄክት ማናጀር ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ታላቁን ግዳጅ ለመወጣት ከሚያስፈልገው የሰው ሃይል 4 ሺው ስፍራው ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ 120ዎቹ ባህር አቋርጠው የታላቁ ታሪክ ተካፋይ ለመሆን የመጡ ባለሙያዎች ናቸው። ስራው በሶስት ፈረቃዎች ያለማቋረጥ ለ24 ሰዓታት እየተከናወነ ይገኛል።

ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው አንድ አመትን በተሻገረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስፍራ ነው። የግድቡ ፕሮጄክት ማናጀር ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እንደነገሩን ግንባታው በተያዘለት እቅድ መሰረት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ከዋናው ግድብ አንጻር ግድቡ የሚያርፍበትን ቦታ ለማመቻቸት እየተካሄደ ባለው ቁፋሮ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ልል አፈርና ድንጋይ ተነስቷል። ግድቡ በሚያርፍበት መሬት ላይ ሲካሄድ የነበረው የከርሰ ምድር ፍተሻ ስራም መቶ በመቶ ተጠናቋል። ግንባታውን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ከ7 መቶ በላይ ግዙፍ ማሽነሪዎችም ግዳጃቸውን ያለማቋረጥ እየተወጡ ይገኛሉ።

በዚህ ግዙፍ የግንባታ ሂደት የሚያስፈልገውን በርካታ መጠን ያለውን ኮንክሪት ለማምረት ግድቡ በሚያርፍበት የወንዙ ግራና ቀኝ የአርማታ ማምረቻ ፋብሪካዎች ተከላም እየተካሄደ ነው።

ለዚህ የአርማታ ምርት የሚያስፈልገው የጠጠር ግብዓት ደረጃውን በጠበቀና በአስተማማኝ ክምችት እዛው በግንባታዉ ስፍራ ተገኝቷል።

ይህንን ክምችት ደግሞ በሚፈለገው መልኩ በሰዓት 2 ሺ ቶን የመሚያመርት የድንጋይ ወፍጮም እየተተከለ ይገኛል።

ለዋናው የግድቡ ግንባታ የወንዙን አቅጣጫ የማስቀየር ስራም ተጀምሯል።

ኢንጂነር ስመኘው እንዳሉት በተለይ መጪውን ክረምት ተከትሎ የሚፈጠረው የወንዙ ሙላት ስራውን እንዳያስተጓጉል ከወዲሁ አስፈላጊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የግድቡ ግንባታው በየቀኑ ልዩነቱ በሚታይ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ያሉት ኢንጂነር ስመኘው የአሁኑ ክረምት ከመድረሱ በፊትም ዙሪያ ጥምጥም የሚያስኬደውን ጉዞ የሚያስቀረው ድልድይ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተፋጠነ መልኩ እየተካሄደ ነው

**************

Source: Fana Broadcasting – June 4, 2012.

Check the Grand Ethiopian Renaissance dam archive for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories